Monday, 05 March 2012 14:19

እናቴና አክስቶቼ

Written by  ከአንድነት ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

ከስድስት ኪሎ ካምፓስ ስወጣ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ይላል፡፡ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ነጠላ ከለበሱ እና ለእስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማለዳ ከነቁ ጥቂት ተማሪዎች በቀር ጊቢው ለማለዳ ወፎች ተለቋል፡፡ ታክሲ ይዤ ለ5 ደቂቃ ያህል ከተጓዝኩ በኋላ ከታክሲ ወርጄ አንድ “ጥቃቅን” የመንግስት ቤቶች የሞሉበት ግቢ ደረስኩ፡፡ የግቢውን በር አልፌ ሶስት መአዘን ሠርተው ከተገጠገጡት ቤቶች የአንዱን በር አንኳኳሁ፡፡ ከውስጥ ለረጅም ሰአት የቆየ የመሰለኝ ምልልስ ይሰማል፡፡ ከእንቅልፍ ይልቅ ጨዋታ መርጠዋል ማለት ነው፡፡

የአክስቴ ልጅ ናት የከፈተችልኝ፡፡ ከተነሳችበት ፍራሽ ተመልሳ ተኛች፡፡ ክፍሏ ስድስት ኗሪዎች ላሉት ቤተሰብ እጅግ በጣም ጠባብ ልትባል የምትችል አይነት ናት፡፡ የታመቀ፣ ወፍራምና የሚሞቅ አየር ይዛለች፡፡ በአየር ታምቃ ልትፈነዳ የደረሰችው ይህች ክፍል፤ እኔ እስከማውቀው አገልግሎቷ ፈርጅ ብዙ ነው፡፡ ጠረጴዛና ትናንሽ ወንበሮች ሞልተዋት ስትታይ እንግዳ እንኳን ቢመጣ ሣሎን እንደምትሆን ይረዳል፡፡ ማታ ማታ በአልጋ ልብስ አምሮ ከሚታየው አልጋ በተጨማሪ አንድ ፍራሽ ተዘርግቶ ወንበሩና ሌሎች ቁሳቁሶች ጠረጴዛው ላይ ሲቆለሎ መኝታ ቤት ትሆናለች፡፡ ቡታ ጋዝ ተለኩሶ፣ ሽሮ፣ በርበሬ፣ መክተፊያ፣ የዘይት እቃ …ወዘተ ሲደረደሩ ደግሞ ኩሽና ትሆናለች፡፡ ኧረ እሷ የማትሆነው የለም፡፡ አገልግሎቷን ለመዘርዘር መሞከር ጥቅሟን ከማጉላት ይልቅ ሊያኮስሰው ይችላል፡፡ ለመሆኑ የታጠቡ ልብሶች እዚህም እዛም ተሰጥቶባት ስትታይ ምን ልትባል ነው?

“አልተነሳሽም እንዴ?” … አልኳት እናቴን፡፡ በጠዋት እንድመጣና ለቅሶ ቤቱን እንዳሳያት ነግራኝ ነበር፡፡ የእህቷ ባል ሞቶ ለቅሶ ለመድረስ ነው የመጣችው፡፡ ወደ 500 ኪሎሜትር ተጉዛለች - አዲስ አበባ ለመምጣት፡፡ እኔ ከተኙት የአክስቴ ልጆች አንዳቸው ቢያሳዩዋት ብዬ ነበር - ፈተና ስለቀረበብኝ፡፡ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ምናልባት ድህነታቸው ሸምቅቋቸው ነው መሰል የሟቹ ባለቤት ከሆነችው አክስታችን ጋር እንደልባቸው አይቀራረቡም፡፡

“ከነቃንስ ቆይቷል የሀገር ቤት ጫወታ ይዘን ነው ያልተነሳነው፡፡” አለች ደጋግማ የምታቃስተው አክስቴ፡፡ በየንግግሯ መሃል ቁስሉን የነኩበት ሰው ያህል ታቃስታለች፡፡ ህመሟ ሰሞኑን እንደበረታባት ትላንት ሰምቼያለሁ፡፡

“ይኸውልህ ሌሊቱን እንዲሁ አነጋሁ … እናትህንም አላስተኛሁዋትም፡፡” ከአልጋዋ ለመውረድ ልብሷን እየለባበሰች፡፡

በስተምስራቅ የወጣችው ጸሃይ በቤቱ የሁዋላ ግድግዳና በጣራው መካከል ባለ ክፍተት ጨረሯን እየለቀቀች ክፍሉ መብራት የበራበት መስሏል፡፡

“ምነው አትተኝም እንዴ… በዚህ ጠዋት?” አለች እናቴ - ማቃሰቷ ጋብ ብሎላት ልብሷን ለባብሳ ከአልጋዋ ልትወርድ እየተዘጋጀች ያለች እህቷን፡፡

“ቁርስ ሳትበሉማ አትሄዱም!”

“አይነጋም እንዴ? የምን ጥድፊያ ነው …. እዚያ መድረሳችን መች ይቀራል?”

መልስ አልሰጠችም አክስቴ፡፡ አንድ ጥግ አሲዛ ቡታጋዝ ለኮሰች፡፡ በእርግጥ እኔ እስከማውቀው ድረስ እሷ ቤት ታድሮ ቁርስ ሳይበሉ መውጣት ዘበት ነው፡፡ እስካሁንም የቆየችው ምናልባትም ህመሟ ስለበረታባትና ከልጆቹዋም ማልዶ የሚነሳ ስላላገኘች ይሆናል፡፡ እንግዳ ታከብራለች፡፡ በተለይ ለዘመድ ትሳሳለች፡፡ ክርክሩን ትታ ጉድ ጉድ ይዛለች፡፡ እኔም ትላንት እናቴን ከአውቶቢስ ተራ ተቀብዬ ቀጥታ ወዲህ ያመጣሁዋት የሌሎች ዘመዶች ቤት ጠፍቶኝ ወይም ቀጥታ ለቅሶ የመጣችበት የአክስቴ ቤት መውሰድ አቅቶኝ አይደለም (ትንሽ መሽቶ የነበረ ቢሆንም)፡፡ ወይም እዚህ የተሻለ አልጋና እራት ስላለም አይደለም፡፡ ይሄው መልካምነቷ ስቦኝ ነው፡፡

“ማታ ትመለሳላችሁ አይደል?” አለች ልትሸኘን ወጥታ፡፡ ብንመጣ ደስ እንደሚላት ከአጠያየቋ ያስታውቃል፡፡

“አንቺ ደግሞ የመጣሁት ለቅሶ መሆኑን እረሳሽው እንዴ?” … መለሰች እናቴ ታክሲ ውስጥ ከመግባቷ በፊት፡፡

“ደስ እንዳለሽ፡፡ ከመሸ ስለገባሽ አልተጫወትንም ብዬ ነው፡፡” ብላ ሳትጨርስ ታክሲው ተንቀሳቀሰ፡፡

ከመጣሁ ዓመት ያለፈኝ ቢሆንም ባለአንድ ፎቁ የአክስቴ መኖሪያ ቤት አልጠፋኝም፡፡ ሰፈሩ ቦሌ ነው፡፡ በሩ ላይ ጆሮውን ተክሎ ሲጠብቅ የቆየ የሚመስለው ዘበኛ የግቢውን በር ገና ስናንኳኳ ከፈተው፡፡ የመጥሪያ ደወሉን ባለመጫናችን ይሆን በሌላ ምክንያት ፊቱ ቅጭም ብሎ ነበር - ልክ በጠባቡ እንደከፈተው በር፡፡

“ምን ፈለጋችሁ?” ብቻ ለብቻ ለአይን አንሞላ ያልነው ይመስል ሁለታችንንም በአንዴ ለመመልከት እየሞከረ፡፡ “ምንም ልትፈልጉ አትችሉም” የሚልም ይመስላል፡፡

የእናቴ ምላሽ ግን እኔም ያልጠበኩት ነበር፡፡ “ወይኔ ወንድሜ! ወይኔ ወንድሜ! እኔ አፈር ልብላ …”

“እኮ ምን ፈለጋችሁ?” ፊቱንም በሩንም የበለጠ እያጠበበ፡፡ እሷ በሩን ለመክፈት እጆቹዋን ዘርግታ ነው የምታለቅሰው፡፡

“ዘመድ ነን … ለቅሶ ለመድረስ ነው፡፡” አልኩት፤ እልህ እየተናነቀኝ፡፡ በእኔ አልተደሰተም፡፡ እሷ ግን እንባዋ ዝርግፍግፍ ሲል በደመነፍስ በሩን ለቀቀው፡፡

“ወይኔ ወንድምዬ … ወንድምዬ … ወይኔ! ወይኔ! … ውይ …” እያንዳንዱን ፊደል ከላንቃዋ ሳይሆን ከአንጀቷ የምትስበው ነው የሚመስለው፡፡

እጆቼን የኋሊት አጣምሬ አንገቴን አንደደፋሁ ከእሷ ኋላ ኋላ ተከተልኩ፡፡ በየት በኩል መግባት እንዳለባት መወሰን አቅቷት ለአፍታ ወደ ጉዋሮ በር በሚወስደውና ወደ ቤቱ ዋና በር በሚያወጣው ደረጃ መሃል ቆመች፡፡

በጓሮ በኩል አንዲት ልጅ ብቅ አለች፡፡ የቤት ሰራተኛ ናት፡፡ የዛሬ አመት ገደማም ስመጣ ነበረች፡፡ ከሁኔታዋ እሷም የለየችኝ ይመስላል፡፡ ግን ምንም ሳትል በመጣችበት ተመለሰች፡፡ እናቴ ተከተለቻት፡፡

“ወንድሜን … ወንድሜን … እኔ አፈር ልብላ … እኔ አፈር ልብላ …” እጆቹዋን እንደ አሞራ ክንፎች ዘርግታ፡፡

እኔም ግን ማልቀስ እምቢ አለኝ፡፡ ደግነቱ ለቅሶው ሰንበትበት ያለ ነው፡፡ በዛ ላይ እሷ እናቴ መሆኑዋን ያወቀ ማንም ሰው በአረመኔነት አይጠረጥረኝም፡፡

በጓሮ በር ወደ ቤት ገባን፡፡ ወደ ሳሎን ዘለቅን፡፡ የተከተልናት ልጅ የለችም፡፡ እናቴ ለቅሶዋን ገፋችበት፡፡ እኔ ቢጨንቀኝ ሶፋ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ እሷ እያለቀሰች እኔ ቤቱን እያማተርኩ እና በሷ ለቅሶ እየተጨነቅሁ ቆየሁ፡፡ ከአሰልቺ ቆይታ በኋላ ከፎቁ ወደ ምድር ቤት በሚያወርደው ደረጃ ሰራተኛዋ ቁልቁል መጣች፡፡ እሷን ተከትለው ሁለት የሚያሳሱ ህጻናት የደረጃው የላይኛው ጫፍ ላይ ሆነው ወደ ታች ይመለከቱናል፡፡

ሰራተኛዋ፤ የቤቱ ባለቤት (አክስቴ) አለችምም የለችምም አላለችም፡፡ በእናቴ አለቃቀስ ግን የተነካች ትመስላለች፡፡ ምናልባት ለቅሶው ትኩስ እያለ እንኳ በዚህ መልኩ ሲያለቅስ ማንንም አላየች ይሆናል፡፡

“ይብቃዎ እንግዲህ እትዬ ”አለች አንድ ሁለቴ የምታደርገውን በማጣት በገባንበት በጓሮ በር ወጣ ገባ ካለች በኋላ፡፡ እናቴ ለቅሶዋ ትንሽ በረድ አለ፡፡ ዓይኖቹዋንና አፍንጫዋን እየጠራረገች ከአጠገቤ ተቀመጠች፡፡ ሆኖም ትንሽ ተረጋግታ ቤቱን መቃኘት ስትጀምር ደረጃው ጫፍ ላይ ያሉትን ህፃናት አየችና እንደገና መነፍረቅ ጀመረች፡፡ “አበዛሽው እንግዲህ!” ንዴቴ አመለጠኝ፡፡ አልሰማችኝም፡፡

“ለማን ተውካቸው … ለማን ተውካቸው …” እንደ አዲስ ጀመረች፡፡ ትቻት በጓሮ በር ወጣሁ፡፡ ልጅቷ የለችም፡፡ ወደፊት ለፊት አለፍኩ፡፡ ዘበኛው ቁጭ ብሏል፡፡

“ምን ትጠብቃላችሁ? … እትዬ የሉም” እኔን ሲያይ ከተቀመጠበት እየተነሳ፤ ከቅድሙ ሁለት እጥፍ ፊቱን አስቆጥቶ፡

“ልጅቷ የት ሄደች?” … አልኩት በመሰላቸት ቅላጼ፡፡ “እሷስ ብትሆን ምን ታደርግልሀለች?” ተውኩት፡፡ ከዘበኛው ርቄ ግን ወደ ቤት ሳልገባ ቆየሁ፡፡ ከረዥም ቆይታ በኋላ የግቢው በር ተንኳኳ፡፡ ሰራተኛዋ ነች፡፡ እስካሁን ይሄዳሉ ብላ እንዳሰበች ከሁኔታዋ ተረዳሁ፡፡

“እትዬ ለምሳ ይመጣሉ?” ጠየኳት፡፡

“አይመጡም፡፡” አለችኝ በሙሉ እርግጠኝነት፡፡ ቀድሜያት ወደ ቤት ገባሁ፡፡ “ለምን አንሄድም?” አልኳት የአገጯን መሀል መዳፏ ላይ ተክላ የምትተክዝ እናቴን፡፡

“እንጠብቃት ትመጣለች፡፡ እነዚህን ህጻናት ሳታይ አትውል መቼም”

“ነገረችኝ እኮ ልጅቷ! ብትመጣም ማታ ነው፡፡”

መጨረሻ ላይ በእኔ ውሳኔ ለመሄድ ተነሳን፡፡ እሺ ብላኝ ስትነሳ ቀለል አለኝ፡፡ እስካሁን ልብ ያላልኩት ባለጥቁር መስታወት መኪና ወደ አንድ ጥግ ገባ ብሎ ግቢው ውስጥ ቆሟል፡፡ እናቴ የግቢውን በር ቀድማኝ ወጣች፡፡ መኪናውን እና አጠገቡ ያለውን አረንጓዴ ሳር ሲያማትሩ የነበሩ አይኖቼ ድንገት በዛው መስመር ሽቅብ ተሳቡ፡፡ የተመለከትኩትን ማመን አልቻልኩም፡፡

ፎቁ ላይ ካለው ክፍል መጋረጃ ገልጣ በመስኮት ስትመለከተን አየኋት፡፡ አክስቴ ናት፡፡ የእናቴ እህት፡በዚያው ቅፅበት መጋረጃውን ሰፋችው፡፡ ማመን አልቻልኩም፡፡ ቀስ እያለ ይሄ ነው የማልለው ሃዘን አጥለቀለቀኝ፡፡ አሁን ምን ይወስዱብኛል ብላ ነው መደበቋ! ለእናቴ ብነግራት ሰው እንደማትሆን አውቃለሁ፡፡ ገንዘብ ልንለምናት አልመጣን፡፡ ቢበዛ ቢበዛ እናቴ ከሩቅ ሀገር እንደመጣ ለቅሶኛ አንድ ቀን ብታድር ነው፡፡ እሱም የግድ አይደለም፡፡

እናቴ ደግሞ ለሰው ባትተርፍም ለራሷ የምታንስ አይደለችም፡፡ እራሷን ችላ ነው የምትኖረው፤ ሁሉም ነገር አንገበገበኝ፤ አቅለሸለሸኝ፡፡ ከግቢው ወጥቼ ቆም አልኩ፡፡ ስቆምባት እናቴ ዞር አለች ወደኋላ፡፡ አስተውዬ ተመለከትኳት፡፡ ያነባችበት አይኗ ፊቷ ላይ ያስታውቃል፡፡ አሳዘነችኝ፡፡ ለካስ የንዋይ ጥንካሬ በደምና ስጋ ከተቋጠረ ዝምድና ይበልጣል፡፡ ስለቱም ዝምድናን ይከታትፋል፡፡ የዝምድናን አጥንት ይሰብራል፡፡ ማዘኔን እንድታውቅ ግን አልፈለግሁም፡፡ ብቻዬን ሆኜ ነው ቢወጣልኝ የሚሻለው፡፡ እናቴ ወደመጣችበት ሃገሯ የምትመለስ ቢሆንም ለዛሬው ወደ አደረችበት ልመልሳት ነው፡፡

“ምን አሰብሽ አልኳት?” ዝምታውን ለማሳሳት ያህል፡፡

“ምኑን?” ያኮረፈች ትመስላለች በኔ፡፡

“በቃ እሷ የለችም! የምታገኛት አይመስለኝም”

“ዝም ብለህ ነው የምታስቸኩለኝ” ቆጣ ብላ፡፡

“እንዴት?” … አልኳት፡፡ ግን ምንም አይነት ማብራሪያም ሆነ ሌላ ነገር ለመቀበል አልፈለኩም፡፡

“በቃ እስከማታም ቢሆን ብጠብቃት ይሻላል፡፡ አሁንም ብቻዬንም ቢሆን እመለሳለሁ እንጂ ያቺ … ስታቃስትብኝ አታድርም”

 

 

Read 3550 times Last modified on Monday, 05 March 2012 15:35