Saturday, 25 February 2012 13:23

“ካርዮን”

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

“የማስታውሰው በልጅነቴ መሳል እወድ ነበር” አለ አይኑን ከእኛ ላይ እና ከአሁን አንስቶ ወደ ልጅነቱ አማትሮ እየተመለከተ፡፡

“ሶስተኛ ክፍል በሳልኩት ስዕል ወላጅ ጥራ ተባልኩ” ብሎ አቋረጠ፡፡ አርቆ ልጅነቱ ላይ የሚያየውን ምስል በቀጥታ እየነገረን ይሁን ወይንም ለሱ የሚታየውን በጊዜ ርቀት እየተጭበረበረበት እውነትነቱን ትቶ ለኛ የሚገባንን እና ጨዋ የሚመስለውን ብቻ (ባይመስልም እያስመሰለ) እያወራልን ስለመሆኑ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ይቅርታ፤ እነሱ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ እኔ ለካ የማውቀው ነገር አለ፡፡ ከዚህ ቀደም አውርቶልኛል፡፡ አሁን ለእነሱ እየተረከ ያለውን ታሪክ፡፡

“አውርተህልኛል” አልኩኝ በልቤ፡፡ ሁለቴ አውርቶልኛል፡፡ ሁለትን ጽፌ አንድ አለኝ፡፡ ወይንም ሁለቴ ታሪኩን እንደሰማሁት በመርሳት እንደመጀመሪያዬ ለማዳመጥ፡፡ ከዚህ በፊት ከዚህ ከኋላ የሚናገረውን ታሪክ ሲተርክ ሁለቱንም ጊዜ ታሪኩ የተለያየ አጨራረስ ስለነበረው፤ ልጅነቱን ሳይሆን ድርሰቱን እንደሚነግረን አስቤ ማዳመጥ ቀጠልኩ፡፡

“ሶስተኛ ክፍል ልጆች አበባ እና ቤተክርስቲያን…በር እና መስኮት ያለው ትንሽ ቤት በሚስሉበት ዘመን፤ እኔ አይናለምን መሳል ጀምሬ ነበር…”

አይናለም ከሰባት አመቱ ጀምሮ በአደራ ታሳድገው የነበረች ሴት ናት፡፡ ;;;; አባቱን አያውቀውም፡፡ አባቱ ለሱ ከሱ ስም ጐን የሚፃፍ ሶስት ፊደሎች ተደርድረው የሚፈጥሩት አንድ ድምጽ ነው፡፡ ሦስቱም ፊደሎች ከመሰል የፊደል ተከታዮቻቸው  የቀደሙ የመጀመሪያዎች ናቸው፡፡ ከ”በ” ቤት “በ” ፣ ከ “ቀ” ቤት “ቀ”፣ ከ “ለ” ቤት “ለ”፡፡ በቀለ፡፡ እስክንድር በቀለ፡፡ እስክንድር … አሌክሳንደር … አሌክስ፡፡ እስክንድር ለመንጃ ፍቃድ፤ አሌክሳንደር ለመጀመሪያ ትውውቅ፡፡ (ከጥሩ ጠንካራ እጅ ጭበጣ ጋር) አሌክስ፤ ትውውቁ ከጠነከረ፤ ገንዘብ ከተበዳደረ…ቢራ ከተገባበዘ በኋላ፡፡

ሴቶች በሙሉ “አሌክስ” ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ ከባልቴት እስከ ደናግል፡፡ ሴቶች በሙሉ ይወዱታል፡፡ የሚጠሉት እንኳን እሱን ሊጠይቁት ይሄዳሉ “ለምንድነው የምንጠላህ?” ሊሉት፡፡ “አሌክሳንደር እባላለሁ እንተዋወቅ” ብሎ ይተዋወቃቸዋል፡፡ ለምን እንደሚጠሉት አስረድቶ ይነግራቸዋል፡፡ ከአልቤርጐው ሲወጡ ጥላቻቸው ተቀይሮ ወደውት ቁጭ ይላሉ፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መነኩሲት ሲያስኮበልል አስራ አምስት አመቱ ነበር፤ ይባላል፡፡ እሱ ግን ስለሚባለው ስለሚወራበት በመስማማትም ሆነ በመቃወም ምንም ትንፍሽ ብሎ አያውቅም፡፡ አሌክስም አሁን ሰላሳ አምስት አመቴ ነው ብሎ እንደሚናገረው (እድሜውን አለመዋሸቱ እንዲታወቅለት የመፈለግ በሚመስል ድግግሞሽ) መነኩሲቷም አግብታ ወልዳ እየኖረች ነው፤ ብሎ ሰው ያወራል፡፡ አሌክስ ስለ እድሜው እንጂ ስለመነኩሲቷ አያወራም፡፡ ምናልባት ቢያወራ ደግሞ ወሬው እንደ እድሜው ውሸት ሊሆን ይችላል፡፡

አሁን አሌክስ ለሌሎቹ (አብረውን ላሉት ሁለቱ) ማውራቱን ቀጥሏል፡፡ ስለ ስዕል አለም እና ስለ አይናለም አለም፡፡ እስካሁን ድረስ ታሪኩ በፊት የሰማሁት ስለነበር ትረካው እስኪቀየር ተራኪውን እና አዳማጮቹን እየመላለስኩ በማየት እያጠናኋቸው ቆየሁ፡፡

አዳማጮቹ ሁለቱም የጥበብ አለም ሰዎች ናቸው፡፡ አንደኛው፤ ሰአሊ፣ ሌላኛው፤ የልብ ወለድ ፀሐፊ ናቸው፡፡ እኔ ፈላጊ እና ተፈላጊን አገናኝ ነኝ፡፡ እኔ ለራሴ ግን ከፈላጊውና ከተፈላጊው ምን እንደምፈልግ አላውቅም፡፡ ልጁ የጠፋበትን አባትና አባቱ የጠፋበትን ልጅ በማገናኘቱ ምን ደስታ እንዳገኘ ለራሱ እርግጠኛ እንማይሆነው ሰው፡፡ የሚፈላለጉ ነገሮችን የማገናኘት ደስታ ነው የኔ፡፡

የተገናኙት ሰዎች ደስታ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ለኔ ገንዘብ መስጠት ይሆናል፤ የመጨረሻ ውጤቱ፡፡ ልክ እሳት ሲነድ ሙቀት መስጠቱ እንደማይቀረው፡፡ እሳትን በግድ ሙቀት ስጥ ማለት አይቻልም፡፡

በቃ ይሰጣል፡፡ የሚፈላለጉ በመገናኘታቸው በደስታ እሳት ውስጥ ተቃጥለው አመድ እስኪሆኑ እኔ የሙቀት “ብሬን” እወስዳለሁ፡፡

አለም በረዶ ናት፡፡ እሳት ያለበት እጄን ዘርግቼ መሞቅ እፈልጋለሁ፡፡ ደግሞም በተደጋጋሚ ለብዙ ዘመናት አሙቄአለሁ፡፡ እጄም በሙቀት ብዛት ጠንክሯል፡፡

አንዳንዴ ግን ይፈላለጉ የነበሩት አባት እና ልጅ ሲገናኙ እና ሲተቃቀፉ፤ የትኛው አባት የትኛው ደግሞ ልጅ እንደሆኑ መለየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ፈላጊው አባት፡፡ ተፈላጊው ልጁ ሳይሆን ይቀራል፡፡ አሁን እንደዛ አይነት ሁኔታ የተከሰተ መሰለኝ፡፡

ደራሲው አሌክስን የፈለገው ለድርሰቱ ነው፡፡ ሰአሊው ደግሞ ለስዕሉ፡፡ አሌክስ የራሱን የህይወት ታሪክ ወደ ልጅነቱ በሩቁ የሚያይ መስሎ ግን በአፉ እየፈጠረ ለደራሲው እየነገረ ነው፡፡ የሚናገረው ደግሞ በልጅነቱ ከሳለው ስዕል ተነስቶ ነው፡፡ ተነባቢው አንባቢ፡፡ አንባቢው ደግሞ ተነባቢ ሆኗል፡፡ እኔ የተቀጣጠለውን እሳት ለመሞቅ እጄን አዘጋጅቻለሁ፡፡ እሳቱ ጠፍቶ ወሬው አመድ ከሆነ በኋላ ነው የምሞቀው፡፡

“እናቴ ወደ ካናዳ ስትሄድ” ብሎ እስክንድር የልጅነቱን ታሪክ ጀምሯል “እናቴ ወደ ካናዳ ስትሄድ የሦስት አመት ልጅ ነበርኩ፡፡

“ከዛ እድሜዬ አንስቶ በተለያዩ ዘመዶች፣ በተለያዩ ባለ አደራዎች እጅ ነው ያደኩት፡፡ እናቴ፤ ከካናዳ የምትልክልኝን ብር ያባከኑ ወይንም እንክብካቤ ያጓደሉብኝ ሲመስላት ሌላ ባለ አደራ ትፈለግልኛለች፡፡ እናም የበፊቶቹን ተሰነባብቼ ሻንጣዬን ጠቅልዬ አዲሶቹ ጋር መኖር እጀምራለሁ፡፡

እናቴ ቶሎ ቶሎ ስልክ ትደውላለች፡፡ ደህንነቴን ታረጋግጣለች፡፡ “በጣም ደህና ነኝ” እላታለሁ፡፡ ደግሞም እውነቴን ነው፡፡ አንዲትም ነገር ጐድሎብኝ አያውቅም፡፡ በአደራ ተረክበው የሚያሳድጉኝ ሰዎች በአካለ ስጋ ባሉበት ለልጆቻቸው ማድረግ አቅማቸው የማይፈቅደውን ነገር፤ እናቴ በሌለችበት ለኔ ታደርግልኛለች፡፡

ሰባት አመት ሲሆነኝ አይናለም ተረከበችኝ፡፡ አይናለም የመጨረሻዋ አሳዳጊዬ ሆነች፡፡ ከሷ በኋላ እድገት ቢጐድለኝ የምሞላው ራሴ ሆንኩኝ፡፡ ከሷ በኋላ ራሴን በራሴ ነው ያሳደግኩት፡፡

አይናለም የእናቴ ጓደኛ ነበረች፡፡ እናቴ ከመሄዷ በፊት እድገታቸውም አንድ ላይ ነው፡፡ እኔ አባቴ ከወለደኝ በኋላ ጥሎኝ እንደሄደው፤ አይናለምን ደግሞ ባሏ ጥሏት ወደ ውጭ ሄዷል፡፡ ልጅ ስለሌላት እንደ ልጇ ታየኝ ጀመር፡፡ እኔም እናት ስለጐደለኝ እሷን እንደእናቴ፡፡ እሷን ባሏ ይናፍቃታል፤ እኔን ደግሞ እናቴ፡፡

እናቴ የምትልክልኝን ብር ማንኛዎቹም አሳዳጊዎቼ በእጄ ሰጥተውኝ አያውቁም፡፡ ለፈተና ቀን እንኳን መዝናኛ ስጠይቅ ከሀምሳ ሳንቲም በላይ አይፈቅዱልኝም፡፡ እሱንም ምን እንደገዛሁበት፣ እንዴት እንዳጠፋሁት ይጠይቁኝ ነበር፡፡ አይናለም ብሩን በሙሉ ትሰጠኝና ለኔ የምትገዛው ነገር ሲኖር መልሳ ትጠይቀኛለች፡፡

“ገንዘብ መያዝ በዚህ እድሜህ ከለመድክ ወደፊት አትቸገርም” ትለኛለች፡፡ እናቴ ስልክ ስትደውል አይናለም እኔን ወደ ስልኩ አቅርባኝ በነፃነት እንዳወራ ትታኝ ትሄዳለች፡፡ እኔ ከእናቴ ጋር አውርቼ ከጨረስኩ በኋላ አይናለም ስልኩን ተቀብላኝ ከጓደኛዋ ጋር ብዙ … ይሳሳቃሉ፡፡

ማታ ልንተኛ ስንል ፒጃማችንን እንለብሳለን፤ ጥርሳችንን እንፍቃለን፡፡ “ተረት አውሪልኝ” እልና እጄን ጡት ፍለጋ እከታለሁ፡፡ ለእናቴ በስልክ ስለ ሁሉ ነገር ስነግራት ጡት መጥባት መውደዴን ግን ጠቅሼላት አላውቅም፡፡ የእናቴን ጡት አልጠገብኩም፡፡

ከጡት ባሻገር አይንዬን ሰውነቷን ስነካካት እረፍ አትለኝም፡፡ በፊት የነበርኩበት ቤት ሰራተኛዋ ጡቷን በግድ እንድጠባ ታደርገኝ ነበር እንጂ ሰውነቷን እንድነካ ግን አትፈቅድልኝም፡፡ የአይናለም ገላ ገደብ የለውም፡፡

ገደብ ያለበት ቦታ ስደርስ፤ ሰውነቷ እንደመኮማተር ይላል፡፡ ያኔ አፈገፍጋለሁ፡፡ መኮማተር የሚፈጥሩትን ቦታዎች አውቃቸዋለሁ፡፡ ከጭኖቿ በላይ አንዱ ነው፤ ከእንብርቷ በታች ደግሞ ሌላው፡፡ አንዳንዴ፤ ተረቱን እያወራች፤ ለኔ እጅ የተከለከለው ቦታ አካባቢ የራሷ እጅ ወርዶ አገኘዋለሁ፡፡

“…ስኖዋይትና ሰባቱ ድንክዬዎች…እ…ሲሄዱ…ሲሄዱ ሲሄዱ ከዛ ምን ልበልህ…” ብላ አይኗ ገርበብ ይላል፡፡

እኔ የጡቷን ጫፍ እየመጠመጥኩ ጉያዋ ተሸጉጫለሁ፡፡

“እና…ልዑሉ…ሳንድሬላን ሲያያት…ይወዳታል…እና”

“ስለ ስኖዋይት ነው እያወራሽልኝ ያለሽው” ብዬ የተምታታውን ተረት ወደ ቅድሙ እመልሳለሁ፡፡ አርማታለሁ፡፡

“አዎ…ስኖዋይት በጣም ታምራለች…ልዑሉም በጣም ያምራል …ይዞ ሲስማት…ሲስማት…እሷም ትስመዋለች…ከዛ እቅፍ ያደርጋታል፡፡ …ላግባሽ ሲላት…እሺ ትለዋለች…ከዛ ፍቀጅልኝ ላፍቅርሽ…ላፍቅርሽ”

ከዛ አይናለም በእግሮቿ መሀል ድንገት ጥብቅ አድርጋ ትይዘኝና መላ ሰውነቷ እየተሰበቀ መንቀጥቀጥ ትጀምራለች፡፡ በጣም ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ከዛ ትራሷ ላይ ጋለል ትልና አይኗን ትጨፍናለች፡፡

“ከዛስ…ላፍቅርሽ ካላት በኋላስ” እላለሁ “ሰባቱ ድንክዬዎችስ?”

ደክሟታል “በቃ አሁን እንተኛ ነገ እቀጥልልሃለሁ… ነገ ጠዋት መነሳት አለብህ አይደል ተኛ”

ጡቷን ትነጥቀኝና ወደ ፒጃማዋ ታስገባለች፡፡ ጀርባዋን ለኔ ትሰጣለች፤ መብራቱን ታጠፋለች፡፡ እንተኛለን፡፡ እኔ ከኋላዋ ተጠግቼ አቅፋታለሁ፡፡

…ብሎ ድንገት ዝም አለ፡፡ እየጠበቅነው እንደሆነ ሲያውቅ በሽታው ይነሳበታል፡፡ አውቀዋለሁ፡፡ “ሳለ አይሰጥ” አይነት ነው ባህሪው

“ሽንቴን ሸንቼ ልምጣ” ብሎን ተነስቶ ወጣ፡፡

ሰአሊውና ደራሲው በመቋመጥ ብዛት የምግብ ደወል እንደሰማ “የፓብሎቭ” ውሻ ሆነዋል፡፡ ጥሩ ድርሰት እና ስዕል በአሌክስ አንደበት ወጥቶ ሊቀርብላቸው ነው፡፡ የጥሩ ምግብን ደወል ከታሪኩ ድምጽ ያውቁታል፡፡

“ከዛስ ቀጥልልኝ በፈጠረህ … የአንተና የአይናለም መጨረሻ ምን ሆነ?” አሉት እንደተቀመጠ፡፡

“አይናለም ሞተች” አለና ፊቱ ግድግዳ ሆነ ድንገት፡፡

በግድግዳ ፊቱ ላይ የተናገረው ነገር ቀልድ መሆኑን የሚገልፁ ምልክቶች እየፈለጉ ነው ሁለቱ ጥበበኞች፡፡ ድንገት ስሜታዊ በሆነ የወሬ ተራክቦ መሀል ወደ እርካታ እየጋለበ ባለ ጆሮ ላይ ፈስ የተፈሳበት የሚመስል ፊት ሁለቱ ጥበበኞች ላይ ታየ፡፡ የቋመጠው ጆሮአቸው ላይ ውሃ ድንገት ተደፍቶበታል፡፡

“ስለ አሳዳጊህ እኮ ነው ስታወራልን የነበረው ጨርስላቸው እንጂ” አልኩት፡፡

“አሳዳጊዬን አይናለም ነው ያልኳችሁ … ተሳስቼ ነው እሷ መአዛ ነው ስሟ…በቃ ሞተች፡፡ እንደሞተች እናቴ ከካናዳ ሆና ስትሰማ …ሌላ አሳዳጊ ፈለገችልኝ፡፡ ግን ሌላ አሳዳጊ አያስፈልገኝም ነበር……. ምክንያቱም በዛ ጊዜ እኔ ራሴ አድጌያለሁ፡፡ ዩኒቨርስቲ ገብቻለሁ፡፡ ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ስገባ እናቴ ለእኔው ለራሴ ብር መላክ ጀመረች፡፡ … ፍሬሽ ማን እያለሁ ከአይናለም ጋር ተዋወቅን፡፡

“ምንድነው የምትዘላብደው … ጥሩ ታሪክ የሚያውቅ ሰው አመጣላችሁኋለሁ ብለኸን አይደለም ያመጣኸን … ጊዜ ታስጠፋናለህ እንዴ” እኔ ላይ ተበሰጫጩ፡፡፡ ርብሽብሽ አሉ፡፡ ተነሱ፡፡ ተቀመጡ፡፡ እጃቸውን አወናጨፉ፤ አጣመሩ፡፡

አለማየሁ፣ አሌክስ አይኑን እሩቅ ተክሏል፡፡ የግራ አይኑ ብቻውን አንድ የእንባ ዘለላ አቆረዘዘ፡፡ የሁለቱን ፈጠራ ሰዎች ቁጣ ቦታ ሳይሰጠው …

“ፍሬሽ ማን እያለሁ ነው ከአይናለም ጋር የተዋወቅኩት አልኳችሁ! አይናለምን የማውቃት እኔ ነኝ እናንተ? እናንተ ምን ታውቃላችሁ ለመሆኑ? ምን አግኝታችሁስ አጥታችሁስ ታውቃላችሁ? እናንተ የሰው ስሜትን እንደ ጥንብ አንሳ እየነጠቃችሁ .. በቀለም እየለቀለቃችሁ …. የምትሸጡ የግማት ነጋዴዎች ናችሁ … እናንተ እኮ የእኔን የእግር ጠፈር መፍታት የማይገባችሁ ርካሽ ናችሁ፡፡

“አይናለምን የማውቃት እኔ ነኝ፡፡ እምወዳት እኔ ነኝ፡፡ እምሞትላት እኔ ነኝ፡፡ እኔን ነው ያፈቀረችው እኔ ብቻ ነኝ ደግሞ የማፈቅራት፡፡ ስለ አይናለም ከእኔ የምትሰሙት የፈጠራ ታሪክ አይደለም፡፡ ፈጠራ ልታደርጉት አትችሉም፡፡ የእኔና የአይናለም ታሪክ ህያው እውነት ነው፤ ጥንብ ስላይደለ ጥንባንሳ ሊቀራመተው አይችልም፡፡ ሞቶም አይበሰብስም … በስዕልም እንደ ልኳንዳ ተሰቅሎ አይሸጥም፡፡ …”

የድምፁ ቅላፄ ከዚህ በፊት ሰምቼው የማውቀው አይደለም፡፡ ድንገት አስፈራኝ፡፡ ሁለቱ ጥበበኞችም ሎሚ አክለው ተድበልብለው መቀመጫቸው ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በአይናቸው አይኑን ለማየት አልደፈሩም፡፡

“ከአይናለም ጋር የተዋወቅነው ኮሌጅ ነው አልኳችሁ፡፡ ፍሬሽማን እያለን ከህንፃ ቁ.4 ጀርባ ካለው ቀጭን መንገድ ላይ፡፡ ማንም አላስተዋወቀንም፡፡ እኛው ራሳችን ተዋወቅን፡፡ ማንም አላፈቀረንም፤ እኛው ራሳችን ተፋቀርን፡፡ ማንም አለያየንም … ግን እኛ ራሳችንም አልተለያየንም፡፡ እኔም እሷም መለያየት በፍፁም አንፈልግም፡፡ እግዜር ምስክሬ ነው፡፡

አንድ በአሜሪካን ሀገር ብዙ አመታት የኖረ ሰውዬ … ከእለታት አንድ ቀን ወደ ባህር ዳር መጣ፡፡ ከሚንያፖሊስ፡፡ … ሚስቱን በካንሰር በሽታ አጥቷል፡፡ … ምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ ሁለት ሁለት ነው፡፡ ሁሉም ነጠላ ሰው … እሱን የሚመስል አንድ ኮፒ አለው፡፡ በሆነ የምድር ገፅ ላይ፡፡ ተራርቀው ነው የሚፈጠሩት፡፡ ግን ማንም ሰው እሱን በመልክ የሚመስል አንድ ሌላ ሰው ምድር ላይ አለው፡፡ “የዚህ ዲያስፖራ ሰውዬ ሚስትን በመልክ የምትመስላት ድጋሚዋ የምትገኘው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ስሟም አይናለም ይባላል፡፡ የሱ ሚስት የመልክ ድጋሚዋ የእኔ ፍቅረኛ ናት፡፡ ጠማማ እጣ ፈንታ ነው፡፡

“ሰውየው ደግም ከሞተችዋ ሚስቱ በስተቀር ድጋሚ ማንንም ሊፈልግ፣ ሊያፈቅር፣ ሊተኛ፣ አብሮ ሊኖር … የማይችል አይነቱ ነው፡፡ እጥፍ ድርብ ጠማማ እጣ ፈንታዬ፡፡ እጣ ፈንታዬና እጣ ፈንታዋ፡፡ … ሰውየው መጣና አገኛት፡፡ በአንድ ትልቅ ባንክ ውስጥ የሚከማች ገንዘብን በአንድ ቦርሳ ይዞ የሚዞር የሀብታም ቁንጮ ነው፤ በሀገሩ፡፡ “አይንዬን ካላገባሁ ሞቼ እገኛለሁ አለ፡፡ ሙት እንጂ አታገባኝም አለችው፡፡ ከእኔ ጋር መሆንዋን ነገረችው፤ ትምህርት እንደጨረስን እንደምንጋባ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ግን ለእኔ አልተነገረኝም፡፡ ሰውየውንም ሆነ ከሰውዬው ጋር ያደረጉትን ንግግር እሷ እኔን በጊዜው ደበቀችኝ፡፡ ባትደብቀኝ ለነገሩ ሰውዬውን እገድለው ነበር፡፡ … ግን ብትነግረኝ ይሻል ነበር፡፡ ምናልባት እሷንም እኔንም ከቀጣዩ ስቃይ ማዳን በቻልኩ ነበር፡፡

“በስተመጨረሻ ሰውዬው አንድ አማራጭ ያቀርብላታል፤ ለአይናለም፡፡ ለመሐፀን ኪራይ አስር ሚሊዮር ብር እንደሚሰጣት፣ አንድ አመት በሚኒያፖሊስ ከእሱ ጋር ተቀምጣ ልጅ እንድትወልድለት … ከወለደች በኋላ ልጁን ጥላለት እንደምትሄድ … ለእኔ ሳይነግሩ ይስማማሉ፤ ሁለቱ፡፡ በእኔ ላይ ሁለቱ ተስማሙብኝ፡፡ በእኔ ቀጣይ ህይወት ላይ፡፡“አንድ አመት የሚያቆይ የትምህርት እድል በአሜሪካ እንዳገኘች እና ከአንድ አመት በኋላ ስትመለስ እንደምንጋባ ነገረችኝ፡፡ ለትምህርት ነው ያለችኝ፡፡ ዋሽታኛለች፡፡ ሴቶች ከመቶ ዘጠና ፐርሰንት ውሸታም ናቸው፡፡ አይኗን በጨው አጥባ ነው የዋሸችኝ፡፡”

ሁለቱ ጥበበኞች አፋቸውን ከፍተው እየሰሙት ነበር፡፡ እኔም እንደ ሁለቱ፤ ሁለት አይኔ ፈጥጧል፡፡ ከዚህ በፊት ሰምቼ የማላውቀው ታሪክ ነው፤ ከአሌክስ አንደበት እየወጣ ያለው፡፡ ታሪኩ የእውነት እንደሆነ አንዳችም ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ በጉንጩ ላይ እንባ እየወረደ ነው፡፡ አይን ደግም አይዋሽም፡፡ ከአይን የሚወጣው ብርሐንም ሆነ እንባ … የእውነት ማህተም … የሰሙ ቅላጭ ነው፡፡ “መጠነኛ ድግስ አዘጋጀን፤ እኔና ጓደኞቼ … መሄጃዋ ሰዓት ደረሰ፡፡ ሸኘናት፡፡ ሻንጣዋን ጠቅልላ ሄደች፡፡ ወደ ምድረ አሜሪካ፡፡ ሚኒያፖሊስ፡፡ ወደ ትምህርት ሳይሆን ወደ እናትነት፡፡ ብቻዋን መስሎኝ ደግሞ መጨነቄ! … ከሰውዬው ጋር እንደሄደች አልነገረችኝም፡፡ … ብዙ ብር ነው ሰጥታኝ የሄደችው፡፡ … ብቸኝነቴን አጠበብኩበት፡፡ አንድ አመት አለፈ፡፡ እንፃፃፍ ነበር፡፡ ድንገት የመመለሻዋ ሰአት ሲደርስ ደብዳቤውን አቋረጠች፡፡ ስልኳንም አጠፋችብኝ …፡፡ ከአመት በኋላ ሳትመለስ ቀረች፡፡ ይህ ታሪክ ከተከሰተ አሁን አስራ አምስት አመት አልፎታል …፡፡” ብሎ ታሪኩን ድንገት አቋረጠ፡፡ እኛም የከፈትነውን አፋችንን ዘጋን፡፡

***

ረጅም ሰአት ዝም አልን፡፡ ደራሲው እና ሰአሊው የሚፈልጉትን አግኝተዋል፡፡ የሰው ታሪክ ለሚለቅሙ እና ለሚሸጡ አይነቶቹ በአሌክስ አንደበት የቀረበው … ከበቂ በላይ ነው፡፡ ድንገት ብድግ ብለው ተከታትለው ወጡ፡፡ እኔን ጨበጡኝ፡፡ ሲጨብጡኝ አስጨበጡኝ፡፡ አሌክስን ከአንገታቸው ዝቅ ብለው የአክብሮት እና የፍርሐት ሰላምታ ሰጥተውት ድንገት ወጥተው ተፈተለኩ፡፡ እንደ ጥንብ አንሳ የቦጨቁትን ይዘው በረሩ፡፡

***

እነሱ ከሄዱ በኋላም ቢሆን የአሌክስ ፊት አልተረጋጋም፡፡

“መች ጨረስኩልህ?” አለኝ ድንገት ተቆጥቶ፡፡

“ምኑን?” አልኩት፡፡ ፈርቼዋለሁ፡፡

***

“ወሬ አይደበቅም የአይናለንም ነገር ደረስኩበት፡፡ ያያት፤ ያገኛት ሰው እኔንም አግኝቶ ነገረኝ፡፡ … ከቱጃሩ ጋር አንድ ልጅ ወልደው አብረው እየኖሩ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ … ወልዳለት የተወለደውን ልጅ ጥላለት ልትመጣ አልቻለችም፡፡ የእናት አንጀቷ አልቻለም፡፡ የወለደችው በሄደችበት የመጀመሪያ አመት ነው፡፡ የልጁ ስም ዳግማዊ ነው ብሎኛል፡፡ ወሬውን ይዞልኝ የመጣው ሰው፡፡ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡”

***

አሌክስን ከዛ በኋላ ለብዙ ወራት አላገኘሁትም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የሱን ወሬ የሰማም ሰው መጥፋት ጀመረ፡፡ ብጠይቅም ባስጠይቅም ልደርስበት ሳልችል ቀረሁ፡፡ ግማሹ ሞቷል ይላል፡፡ ግማሹ ገዳም ገብቷል ይላል፡፡ የተቀረው ዘብጥያ ወርዷል …፡፡ እኔ ግን ባህር ተሻግሮ ሚኒያፖሊስ ገብቷል፤ በሚል አቋሜ ፀናሁ፡፡ አሌክስ፤ በገድለኛነቱ ዘመን የሚለኝ አንድ አባባል ነበረው፡፡ ሁሌ ልንለያይ ስንል አባባሉን ስለሚደግመው፤ እንደ ስንብት ቄንጥ ነበር ሲናገር የማደምጠው፡፡

“አንድ ቀን ከሩቅ … ሩቅ ሀገር ደብዳቤ ፅፌ እልክልሐለሁ”

አንድ ቀን ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ ቴምብርም ሆነ ስም የሌለው አድራሻ፡፡ ክው አልኩኝ፡፡ ለመክፈት ረጅም ጊዜ ወሰደብኝ፡፡ ከፈትኩት፡፡ ዘርግቼ አነበብኩት፡፡

“ታሪኩን አልጨረስኩልህም!” ይላል የመጀመሪያው አረፍተ ነገር፤ እና ይቀጥላል፡፡

“አይናለም አሜሪካ ሄዳ ለቱጃሩ የወለደችለት ልጅ የተፀነሰው ሳትሄድ በፊት ነበር፡፡ ፅንሱ ከእኔ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ልጁን ጥላለት ወደኔ ልትመለስ ያልቻለችው፡፡ ስትመለስም፣ ለእኔ ስለነገሩ ሁሉ ልትገልፅልኝ ያልቻለችው፡፡ አሜሪካ አብራው የምትኖረው ሰውዬው በቅርቡ ሞተ፡፡ እሷም በሰው፣ በአማላጅ እኔን አግኝታ ወደ ሚኒያፖሊስ ጠራችኝ፡፡ … የምሄድ ይመስልሀል? … ነግሬሀለሁ! ሴቶቹ ዘጠና በመቶ የተሰሩት ከውሸት መሆኑን …፡፡ … አልሄድም፡፡ ከአስራ አምስት አመት በኋላ ወደ ከአስራ አምስት አመት በፊቱ መመለስ አልችልም፡፡

ቸር ይግጠምህ ጓዴ!

ከሩቅ - ሩቅ - ሀገር

… ድንገት ነገሩ ሁሉ የተገለፀልኝ መሰለኝ፡፡ … ወዲያው ደግሞ ተመልሶ ጨለመብኝ፡፡ … ይሄ ሁሉ ታሪክ በአሌክስ የተፈጠረ ድርሰት ቢሆንስ ብዬ አሰብኩ፡፡ እውነት እና ውሸቱን መነጠል አቃተኝ፡፡ ህይወትንና ድርሰትን፡፡ “… ሁለቱም ጥንብ ናቸው፣ የበሰበሰ ስጋ” አልኩኝ ለራሴ በአሌክስ ቋንቋ፡፡ … እውነት እና ውሸቱ ሳይነጣጠሉ ከነገባው አመንኳቸው፡፡

 

 

Read 6191 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:32