Print this page
Saturday, 18 February 2012 10:11

የሀውልቱ ምርቃት

Written by  ከዳግማዊ አዱኛ gagano17@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

እሁድ

ዛሬ ሰንበት ነው፡፡ ጠዋት ሶስት ሰዓት አካባቢ፡፡ በአዘቦት ቀን በዚህ ሰዓት ጐዳናው ላይ ፈሰው ከፀሐይ ንዳድ በማያስጥል እጃቸው ግንባራቸውን ከልለው ወደ ታክሲ መምጫ በጉጉት የሚመለከቱ ሰዎች፣ ተገፈታትረው ተረጋግጠው የሚሳፈሩ ሰዎች፣ ቢሳፈሩ ቢሳፈሩ የማያልቁ ሰዎች…ዛሬ የሉም፡፡ ነጭ ነጠላ የለበሱ ከቤተ ክርስቲያን ተመላሾች በመንገዱ ላይ ተሰባጥረው ከመታየታቸው በስተቀር ጐዳናው ጭር ብሏል፡፡ ስራ የለም፣ ትምህርት የለም፡፡ የተለመደው የህይወት ግርግር፣ ከባዱ የኑሮ ትግል ዛሬ የለም፡፡ አብዛኛው ህብረተሰብ ዛሬ ተኝቶ አርፍዷል…ወይም የትናንቱ ስካር አልጋው ላይ ሰፍቶታል ወይም አረፋፍደው ተነስተው ቁምጣ በሸበጥ አድርገው የቤታቸው ደጃፍ ላይ ፀሐይ ይሞቃሉ፡፡ ሁሉ ነገር ጭር ብሏል፡፡ ሀውልቱ ከሚመረቅበት አደባባይ በስተቀር፡፡

የአደባባዩ አጥር አረንጓዴ ቀለም ተቀብቶ፣ በባንዲራ አሸብርቋል፡፡ ውስጡ ሰፊና በቀይ አፈር የተደለደለ ነው፡፡ ባለቀለም ቁርጥራጭ ወረቀት ተጐዝጉዞበት፣ ለእንግዶች መቀመጫ የሚሆኑ ነጭ ጨርቅ የለበሱ ወንበሮች ተደርድረዋል፡፡ በአደባባዩ መሀል ላይ በመጋረጃ መሰል ጨርቅ ተሸፍኖ ሐውልቱ ይገኛል፡፡ ከወደወገቡ በታች ሰፋ ከማለቱ በስተቀር፣ ቀጭን ሃውልት ነው፡፡ ቁመቱም በግርድፉ ሲታይ ከአማካይ ሰው አጠር ይላል፡፡ ዙሪያውን የከበበው ሳር አለቅጥ አድጓል፡፡ ምናልባት ሣሩ አለመከርከሙ የቀራፂው አርቲስት ፍላጐት ሊሆን ይችላል፡፡ ለተሰበሰበው እንግዳ ግን፣ የሣሩ ሁኔታ ተረስቶ የከረመ አይነት ስሜት አሳድሮበታል፡፡ ለማንኛውም ዛሬ በክብር እንድግነት የተጠሩት የሃውልቱ መራቂ ክቡር ሚኒስትር በፈገግታ ታጅበው ሃውልቱን ሲመርቁ…እየሳቁ አቡጀዴውን ሲገፉት…ያን ጊዜ እናየዋለን፡፡ ቀራፂው አርቲስት አቶ ዘመንም ስለሃውልቱ አጭር ማብራሪያ ሳይጨምሩልን አይቀሩም፡፡

ሃውልቱ በክቡር ሚኒስትር የሚመረቀው፣ ቀራፂ አቶ ዘመንም ስለሃውልቱ ምስጢር የሚነግሩን፣ ማለትም ንግግር የሚያደርጉት ዛሬ እሁድ ነው፤ ሶስት ሰዓት ላይ…አሁን ግን ሶስት ከሩብ ሆኗል…፡፡

ታዋቂ ቀራፂያን፣ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ባለስልጣኖች፣ አምባሳደሮች፣ አትሌቶች፣ የተጋበዙ እንግዶች…ቦታ ቦታቸውን ይዘው ይጠባበቃሉ፡፡ የባህል ተወዛዋዦችም ነበሩ፣ ባለካሜራዎችና ባለ ቪዲዮዎችም ጭምር…፡፡ የተጠሩት ሁሉም ተገኝተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ክቡር ሚኒስትር በሞተረኞች በታጀበ ጥቁር ማርቼዲስ ወደ አደባባዩ እንደደረሱ ታወቀ፡፡ እንግዶች ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ ተቀበሏቸው፡፡ ሁሉም ሙሉ ነበር፣ የፕሮቶኮል ሰዎቹና የፕሮግራም መሪው ፊት ላይ የሚታየው ጭንቀት ግን አንዳች አስፈላጊ ነገር እንደጐደለ ሊደብቅ አልቻለም፡፡

ፕሮግራሙ ተጀመረ፡፡ ጭንቀት ያደረበትና ራሱን ለማረጋጋት ሲል የተጨነቀው የፕሮግራም መሪ በተቆራረጠ፣ በተሰባበረ፣ በሚንቀጠቀጥ ድምጽ እንደሚከተለው ተናገረ፡፡

“ክቡራትና ክቡራን እንግዶቻችን…ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለመጣችሁ…” ወዘተ ካለ በኋላ “አንዲት ማሳሰቢያ አለኝ…የሀውልቱ ቀራጺ አቶ ዘመን በዛሬው እለት በደረሰባቸው ኧ… ኧ… የቤተሰብ ሃዘን ምክንያት ከመካከላችን ሊገኙ አልቻሉም፣ በዚህ አጋጣሚ ለአርቲስት ዘመን በእናንተ በእንግዶችና ኧ… ኧ… በክቡር ሚኒስትር ስም  ኧ… ኧ… ለደረሰባቸው ጥልቅ ሀዘን መጽናናትን እንመኝላቸዋለን፡፡” ቀጥሎ ክቡር ሚኒስትር የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉና ሃውልቱን እንዲመርቁ ጋብዞ መድረኩን ለቀቀ፡፡

ክቡር ሚኒስትር በቅልጥፍና ወደ መድረክ ከወጡ በኋላ ስለ ሃውልቱ፣ ስለ ታሪካዊ ፋይዳውና ስለሃገሪቱ ስነጥበብ ማበብ በጥቂት በጥቂቱ ገልፀው ሲያበቁ፣ በጭብጨባና በቲፎዞ ታጅበው፣ በካሜራዎች ብልጭታ ደምቀው፣ በፈገግታ ታጅበው በዝግታ ጨርቁን መግፈፍ ጀመሩ፡፡

…ብዙዎቹን እንግዶች ያወያየው የሃውልቱ ቅርጽ እንደሚከተለው ነበር፡፡ ሃውልቱ በአንድ ሰው የቁም ቅርጽ የተሰራ ሲሆን፣ እግሮቹን ግራና ቀኝ በሰፊው ከፍቶ ከጉልበቱ ሸብረክ በማለቱ ቁመቱ ከመራቂው ሚኒስትር ሊያጥር ችሏል፡፡ ሚዛን ለመጠበቅ በሚመስል ሁኔታ ግራና ቀኝ የተዘረጉት ክንዶቹ መዳፎች ተጨብጠዋል፡፡ ወገቡ ላይ ያሰረው ብጣሽ ጨርቅ ሃፍረቱን ከመሸፈኑ በቀር፣ ሃውልቱ በመረቁት ማኒስትርና በተጋባዦቹ እንግዶች ፊት እርቃኑን ነው፡፡ በቅርበት ሲመለከቱት ግንባሩ ተኮሳትሮ፣ ጥርሱን ነክሶ፣ የአንገቱ ስሮች ተገታትረው፣ ክንዶቹና ሰውነቱ ጠቅላላ ክርር ብሎ እርቃኑን የቆመ ኮሳሳ ሃውልት…፡፡ የቀለም ቅቡ ከመደብዘዙም በላይ ዙሪያውን የከበበው ሣር ስር ያሉት እግሮቹ ባዶአቸውን ነበሩ፡፡ “የድል ሃውልት” የሚል ፊደል የተቀረፀበት ቁራጭ ድንጋይ እግሩ ላይ መደገፉን ማንም አላስተዋለም ነበር፡፡

ሚኒስትሩና እንግዶቹ ይህን አስደናቂ ሃውልት በከፍተኛ አድናቆትና ተመስጦ እየተዟዟሩ ይመለከቱ ጀመር፡፡ በድንገት ሚኒስትሩ ለሁሉም በሚሰማ ጉልህ ድምጽ እየጮኹ መናገር ጀመሩ፡፡ “እስኪ ተመልከቱት፤ ለጭቆናዎችና ለጨቋኞች ሁሉ እጅ ሳይሰጥ ላለመንበርከክ የሚታገል ነፍስ በዚህ ሃውልት ተቀርፆአል፡፡ በትክክል ድል እንደሚነሳ የተመለከተው ይረዳል፡፡ የ”ድል ሃውልት” ተብሎም ተሰይሟል፡፡” ንግግሩን ተከትሎ ከፍተኛ ጭብጨባ አስተጋባ፡፡

ከየአቅጣጫው አስተያየቶች መጉረፍ ጀመሩ፡ ጋዜጠኛው እየተዘዋወረ አስተያየቶችን መሰብሰብ ጀመረ፡፡ “እንደሮማውና እንደ ቶኪዮው ጀግና አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ በአልበገር ባይነት ወኔ ድል ማድረግ እንደሚቻል ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ታሪካዊ ሃውልት ነው፡፡” ሲል አንድ ታዋቂ አትሌት ተናገረ፡፡ “መንገዱን በቅንነት የሚጓዝ የሃያሉ የቅኖች አምላክ መንፈስና ኃይል ያድርበታል…በዙሪያው ቄጤማዎች ለምለም ናቸው…በአምላኩ ታምኗልና ፍሬው ይባረካል …በረከት በዙሪያው ነው፣ ለሰው ዘር ሁሉ ይተርፋልና…” የሃይማኖት አባት ተናገሩ፡፡ “ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው፣ ድግዝግዝታም በብርሃን እንደሚተካ፣ እንደ አውራ ዶሮ ጩኸት ንጋትን እንደሚያበስር፣ ይህም ሃውልት እንደዚሁ በፈታኟ ህይወት ላይ ጭቁኖችና በጨለማ የተጣሉ ድል እንደሚያደርጉ ሹክ የሚል ተስፋን ያዘለ ሥራ ነው፡፡” አለ አንድ የታወቀ የኪነጥበብ ሰው፡፡ “ለረጅም ጊዜ ሲጨንቀን የነበረው የልጆቻችን ምን አቆያችሁልን ጥያቄ…በኛ ትከሻ ወድቆ የነበረው የመጪውን ትውልድ መንገድ የመቅረፁ ነገር …ሙሉ ምላሽ የሰጠ፣ በመጪው ዘመናት የዚህ ትውልድ መታሰቢያ የሚሆን ድንቅ ኢትዮጵያዊ ቅርስ ነው፡፡” የሃገር ሽማግሌዎች፡፡

“በአፍሪካ፣ በኤስያ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ ክፍላተ አለማት ከአርባ በላይ በሚሆኑ ሀገራት ጉብኝት አድርጌአለሁ…ኧ…ኧ…ይህን አይነት እጅግ አስደሳች ሃውልት ግን ማየቴን እጠራጠራለሁ፡፡” ክቡር አምባሳደር፡፡

“ይህን መመልከት በራሱ በታሪክ ትምህርት ከመመረቅ ለይቼ አላየውም፡፡” አንድ የታሪክ ምሁር፡ “በዚህ የጥበብ ዘመን በመፈጠሬ…ራሴን እንደ እድለኛ ነው የምቆጥረው፡፡” አንዲት ወጣት ሴት፡፡ “ከየት እንደመጣንና ወደ የት እንደምንሄድ በትክክል ይናገራል…፡፡” “የድላችን ብስራት ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ ከዳር እስከ ዳር ተስተጋባ…” ….ወዘተ….ወዘተ…. ብዙ መፈክር መሰል አስተያየቶች ከዚህም ከዚያም ተደመጡ፣ ብዙ ጭብጨባዎች ተጨበጨቡ፡፡

አስተያየቶቹን በማጀብ ያጨበጨቡ እጆች፣ በድንገት በደስታ የሰከሩ ጐረምሶችን ዜማ በአዲስ ጉልበትና ወኔ ያጅቡ ጀመር፡፡ “አለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ…ኦሆሆ…ኢትዮጵያ ሃገሬ…” በጋራ ተዘመረ፡፡ “ድሌ ዛሬ ነው ድሌ…ድሌ…ድሌ” ተጨፈረ፡፡

ጋዜጠኞች ዘገቡ፣ ካሜራዎችና ቪዲዮዎች ቀረፁ፣ በቲቪና በራዲዮ በቀጥታ ፕሮግራሙ ተሰራጨ፡፡ እጅግ አስደናቂና የተሳካ ፕሮግራም ነበር፡፡ በሃውልቱ ላይ አስተያየቱን ያልሰነዘረ፣ በፕሮግራሙ ያልተደሰተና ያልረካ ሰው ነበረ ማለት ይከብዳል፡፡ …ም…ና…ል…ባ…ት…ቀራፂው…አቶ ዘመን፡፡

ዋዜማ

ዛሬ ቅዳሜ ነው፡፡ ምሽት፡፡ የበላው ምሣ እንደ አንዳች ጉድ ሳይፈጭ በሆዱ ተቀምጦ በጭንቀቱ ላይ ሌላ ጭንቀት ሆኖበታል፡፡ የጋዜጠኛው ጓደኛው ግብዣ ነበረ፣ ምግቡም ውይይቱም አልተስማማውም፡በነገው ምርቃት ላይ ቃለ መጠይቅ እንዲሰጠው ቃል አስገብቶታል፡፡ የሚለብሰው ሙሉ ልብስ ደግሞ አልጋው ላይ ተዘርሯል፡፡ የእህቱ ምርጫ ነበር፡፡ ግን ስለአንዳቸውም ግድ አልነበረውም፡፡ ይልቅ አሁን መርፈድ የለበትም፡፡ ሰዓቱን አየ፡፡ ወዲያው ከጠረጴዛው ላይ አንድ ወረቀት አንስቶ ከፃፈ በኋላ፣ መልሶ አነበበውና ፈረመበት፡፡ በፖስታ አሽጐ አድራሻውን ፃፈበት፡፡ ከጠረጴዛው መሳቢያ የአንድ ጉዞ የአውቶቢስ ቲኬት ካወጣ በኋላ ኪሱ ከተተ፡፡…ሻንጣውን አንስቶ፣ በሩን ገርበብ አድርጐ ከቤቱ ወጥቶ ሄደ፡፡

ማግስት

ሰኞ፡፡ ጋዜጠኛው አረፋፍዶ ከእንቅልፉ ባነነ፡፡ ሰዓቱ ወደ አምስት አካባቢ ቆጥሯል፡፡ በፍጥነት ከአልጋው ወርዶ መነቃቃት ጀመረ፡፡ በትናንትናው እለት በአንድ የሃውልት ምርቃት ላይ ተገኝቶ ስለነበር፣ ግብዣውና መጠጡ አድክሞት አደረ፡፡ ዛሬ በጠዋት ቢሮ ገብቶ ዘገባውን ማጠናቀር ነበረበት፡፡ ቀራፂውን interview ለማድረግ ቀጠሮ ይዞ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከቀራፂው ጋር የነበረው እውቂያ ወደ ግል ወዳጅነትና መግባባት በማደጉ ጥሩ ቃለ መጠይቅ ይዞ እንደሚመለስ ተስፋ አድርጐ ነበር፡፡ ከምርቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ ቀራፂውም ይህንኑ ቃል ገብቶለት ነበር፡፡ ነገር ግን ሳይመጣ ቀረ፡፡ ሁሉም ነገር ፎረሸ፣ ምርቃቱን ተከትሎ በነበረው ግብዣ ላይ ብዙ አልኮል ወሰደ …ሰክሮ አደረ…እነሆ አርፍዶ ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ በድንገት በምርቃቱ ሳይገኝ ስለቀረው አርቲስት ጓደኛው ማሰብ ጀመረ፡፡ ድንገተኛ የቤተሰብ ሀዘን፡፡ ሀዘኑ የት እንደሆነና አደጋው ምን እንደሆነ በዝርዝር የታወቀ ነገር አልነበረም፡፡ ሰው እንዳይጠይቅ ከራሱ በላይ አርቲስቱን በቅርበት የሚያውቀው ሰው በምርቃቱ ላይ አልነበረም፡፡ ስልክ ሞክሮ ነበረ፣ ውጤት የለውም እንጂ፡፡ የእጅ ስልኩ switched off ሆኗል…የቤቱ አይመልስም፡፡ በቤቱ ደጃፍ ላይ ቆሞ ይህን አይነት ሃሳብ በአእምሮው ሲመላለስ ቆይቶ፣ በቀጥታ ወደ ቢሮ ለመሄድ ተንቀሳቀሰ…ቢያንስ እዚያ አንድ ወሬ አያጣም፡፡ ታዲያ የት ብሎ፣ በምን አድራሻ ሊያገኘው ይችላል?

ቢሮ እንደደረሰ ፀሐፊዋ ከጠዋት አንስቶ የያዘችውን የደዋዮች ስም ዝርዝር የሰፈረበት ወረቀትና አንድ እሽግ ፖስታ አምጥታ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠች፡፡ የስም ዝርዝሩን አንስቶ ተመለከተ…የፈለገው ስም አልነበረም፡፡ በመሰላቸት ወረቀቱን አስቀምጦ ፖስታውን አነሳ፡፡…በስሙ የተላከ ደብዳቤ ነው፡፡ ከፍቶ ማንበብ ጀመረ፡፡ ደብዳቤው እንደሚከተለው ነው፡፡

“ይድረስ ለጋዜጠኛ ገረመው፤

ስለ ሃውልቱ ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ቃል በገባሁልህ መሠረት በቦታው ተገኝቼ ለማብራራት ባለመቻሌ ይቅርታህን እየጠየቅሁ፣ ስለ ሃውልቱ ማወቅ የምትፈልገውንና ማወቅ ያለብህን እንድነግርህ ውስጤ ስላስጨነቀኝ ይህን አጭር ማስታወሻ ልተውልህ ተገደድኩ፡፡ እኔም እፎይታን ማግኘት እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡

ይህን በምታነብበት ሰዓት እኔ ከሃገር ውጭ እገኛለሁ፣ ወይም ለመውጣት በመንገድ ላይ ነኝ፡፡ ሲሆን ክቡር ሚኒስትር ጐን በክብር ቦታዬ ተቀምጬ በጉጉት ለሚያዳምጠኝ ህዝብ ማብራሪያዬን መስጠት ሲገባኝ፣ ሳይሆን ደግሞ እንደማንኛውም ሰው በአካል ተገኝቼ ወይም በቲቪ ምርቃቱን መከታተል ሲኖርብኝ፣ የምርቃቱ ቀን እንደደረሰ እንደሌባ በድንገት ያለኮቴ ሹልክ ብዬ መውጣቴ ግራ ሳያጋባህ አይቀርም፡፡ ይኸው በኔ ጣቶች የተቀረፀ ጉደኛ ሃውልት ለመሰደዴ ምክንያት ሆኖ፣ በአንድ ቁራጭ ወረቀት ቃሌን አስፍሬ ሳበቃ፣ እኩይ መንፈስ ሆኖ ከኋላ እያባረረ ከሃገር አስወጥቶኛል፡፡ ያ የሃውልቱ ገጽታ ተራቁቶ አንዳች ነገር ሳይደብቅ ምስጢሩን ፍጥጥ፣ ግጥጥ አድርጐ መናገሩ ነፍሴን መድረሻ አሳጣት፡፡

ሃውልቱን አሰሪው ኮሚቴ ባወጣው ጨረታ ላይ እንድወዳደር በደረሰኝ ጥሪ መሰረት፣ ይህንኑ “ድል” የተሰኘውን ሥራዬን ለውድድር አቀረብኩ፡፡ ውድድሩ ከተደረገ በኋላ በስነ ጥበባዊ ይዘቱ የኔ ስራ ሊመረጥ ቻለ፡፡ በእርግጥ ሃውልቱ አሁን እንደሚመረቀው አይነት ሳይሆን፣ በእጆቹ ጦርና ጋሻ ይዞ ሽምጥ በሚጋልብ ፈረስ ላይ የተቀመጠ አንድ ወዶ ዘማች ወታደር ነበር፡፡

የቀለም ቅቡም እንዳሁኑ ደብዛዛ ሳይሆን፣ በላዩ ላይ ወርቃማ ቅብ ይደረብ ነበረ፡፡ ከኮሚቴው ጋር በተደረገ የመጀመሪያ ዙር ስብሰባ ከተመደበልኝ አጠቃላይ በጀት ሩቡ ተለቆልኝ አሁን ቆሞ የምታየውን የሃውልቱን ክፍል መቅረጽ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን በድንገት ሊቀመንበሩ በጠሩት ስብሰባ ሃውልቱን አጠናቅቄ እንዳስረክብ ማሳሰቢያ ደረሰኝ…በሩብ በጀት ሙሉ ስራውን እንዳጠናቅቅ መፈለጋቸውን መች አውቄ? ነገር ግን በዚሁ በጀት አጠቃላይ ስራውን እንዳጠናቅቅ በኮሚቴው አባላትና በሊቀመንበሩ የቀጠነ ትዕዛዝ ተላለፈልኝ፡፡ ይህ ጉዳይ ከስብሰባው አዳራሽ እንዳይወጣ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጠኝ፡፡ ኮሚቴውን ለኮሚቴው ብከስም “የኪነጥበብ እድገት ማደናቀፍ” ነው ተብሎ ፋይሉ ተዘጋ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ጅምር ሃውልቱ በሲሚንቶ ተለብዶ ለብዙ ወራት እንደ ጐዳና ልጅ ብቻውን እንደተገተረ ቀረ፡፡ ሳሩም ከርካሚ በማጣቱ አለቅጥ አደገ፡፡ ከኮሚቴው አባላት የሃውልቱን ሁኔታ በየጊዜው እየመጣ የሚጐበኝ አንድ እንኳ አልነበረም፡፡ …ከሳምንት በፊት የምርቃት ጥሪ ወረቀት ደረሰኝ፡፡ ተድበስብሶ ተረስቶ፤ ከጩኸቴ ጋር ተቀብሮ የነበረው ሃውልት ድንገት አስታዋሽ ማግኘቱ…የማሰሪያው ካዝና ተራቁቶ፣ የማስመረቂያው ደግሞ እንደተከፈተ ማንም ሳይነግረኝ እንዲሁ በጨረፍታ ታየኝ፡፡ ያን ቀን ሌሊቱን እንዲሁ ሲያስመልሰኝ አደረ፡፡ በዚህ የጅቦች ጥሪ ላይ መገኘት ደግሞ…ደም ብዛት ወይም ስኳር ባይኖርብኝም፣ አንዳች ነቀርሳ አዙሮ እንዳይደፋኝ ሰጋሁ፡፡…አለመገኘትም እንዲሁ፡፡ ጭንቀቴ ይኸው ነበረ፡፡ የኮሚቴው ሊቀመንበር፣ ሽምጥ ጋላቢውን ፈረስ በራሳቸው ጋሪ ጠምደው፣ ጋሻውን ጦሩን የቀለም ቆርቆሮዎቹን ጭነው፣ ጓደኞቻቸውን አሳፍረው፣ መንገድ እያዘጉ ሲጋልቡ እየታየ አፌን መለጐሙ የሞት ሞት ሆኖብኝ ነው፡፡ አሁንም ግን ሃውልቴ አንድ የማይደብቀው ሃቅ አለ፡፡ ህይወት አልባ፣ ድምጽ አልባ፣ ጐዶሎ፣ ዝገታም፣ ደቃቃ የድንጋይና የሲሚንቶ ክምር ቢሆንም እየጮኸ ይናገራል፡፡ ድልን ባይገልጽ ዘመንን ይገልፃል፡፡”

 

 

 

Read 3741 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 12:54