Saturday, 11 February 2012 10:38

የኔዋ

Written by  አለማየሁ (አሌክስ ጥበብ)
Rate this item
(1 Vote)

እዚህ ጭርንቁሳም ሰፈር ውስጥ እየኖርህ የሰማይ ግዝፈቱ፤ የምድር ስፋቱ፤ የተፈጥሮ ትንግርቱ አይታይህም፡፡ ትንሽ አሳቢ ነኝ ብለህ አንገትህን ብታቀና ከዛጉ የቆርቆሮ ጣሪያዎች ላይ የተኮለኮሉ ድንጋዮች ለአይንህ ይቀርባሉ፡፡ ጣራው መሬት እስኪመስልህ ድረስ፡፡ ለማን ትፈርዳለህ? ለአንጀትህ ወይስ ለሆድህ? “አንጀቴም አንጀቴ ሆዴም ሆዴ ነው” እያልህ መኖርን ትኖራታለህ እንጂ፡፡ የሃብታሙ ጐረቤቴ “ሆዳም” ህንፃ ላይ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ …” የሚል ጥቅስ ልፅፍ ፅፌም ልለጥፍበት ቃጣኝ፡፡ ደሀ ነኝና! የቁስ ብቻም ሳይሆን የሀሳብም፡፡

… ይሄ ሁሉ ትርኪምርኪ ሀሳቤ ልክ ክንዶቿ ከትከሻዬ ላይ እንዳረፈ አቆመ፡፡

ህይወት፣ ብርሃን ነች አሏት፣

የረቀቀው ጐልቶ የጐላ የሚያንስባት፡፡

በልቤ የገጠምሁላትን በአይኖቼ ተቀኘሁላት፡፡ ገባት፡፡ ገባት? ባትረዳው ኖሮ ከንፈሮቼ በከናፍሯ ትኩሣት ባልተቃጠሉ ነበር … የቀጩ መድሃኒት፡፡

በርራ በርራ መምጣቷ ነው፤ ክንፎቼን ከትከሻዬ ላይ ገንጥላ፡፡ ለክቡዱ አየር ደግሞ ሙሉ ልቤን እንደጋሻ ተከልላ፡፡ እኔ አልዋሽም እሷም አትክድም፤ ከአምላክ ዶልታ አጥንቴን መስረቋ! ማንም አላያትም …. ትክዳለች ወንድነቴን ማስጣሏን፡፡ የሷን ቀሚስ መልበስ ሲቀረኝ እሷን መስያለሁ፡፡ ግን … “አንቺን መሳይ “አንቺን” ፍጠሪልኝና ከፊቴ ጥፊ” ብያታለሁኮ! ጨርሶ እንዳልረታላት፡፡ ትውለድልኝ፡፡ አይኔን በአይኔ የማየት ጊዜም የለኝ፡፡ አይኗን በትንሹ ልጄ አይን ውስጥ ግን ማየት እፈልጋለሁ፡፡

ለምን አይኗን ብቻ … ኧረ ድምጿም ይደገም! … ከንፈሯንም! … ይህች ሴት ይህች መልአከ ሰይጣን የልብ ሃሳቤን የኩላሊት ጢሴን አንድም ሳታስቀር ትቃርም ኖሯል!፡፡ ፍሬ ለማፍራት የምታጐበድድ አበባ፣ የሰራ ፍጥረቷ እንደሚያብብ ሁሉ የኔይቱም ቅልጥፍጥፍ፣ እምር፣ ድምቅ ብላ ይቹት፡፡ ለዶሮ አስራሁለት ብልት አላት … ፀጉሯን፣ አይኗን ባቷን እያልሁ ገነጣጥዬ ለምን ላሞካሻት?፡፡ ከዚህ ጭርንቁሳም ሰፈር ተቀምጬ የሰማዩን ግርማ እንጂ፤ የጨረቃን ድምቀት እንጂ፤ የምድርን ለምለምነት እንጂ ማስተዋል ያቃተኝ የየኔዋንም ልቅም ብሎ ይታየኛል፡፡ ሰአሊነ ለቅድስት … ቅድስት የውበት፡፡ የተፈጥሮ የሚስጥር ትስስር ግርም ይላል፡፡ እኔን እሷን ያስመኘ፤ እሷን ለኔ ያስገኘ ሲለጥቅ ደሞ እሷን ከኔ ያስተኛ … የሞላ ግን ያልፈሰሰ ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡

አበባ ናትና አትቀጠፍ? ዝምብላ ትሸተት? እንዲሁ ትደነቅ? … ግን ከቅጣቱ ማምለጥ አለባት፡፡ ለሷ ቅጣቱ ስትቀጠፍ ሳይሆን እንደተተከለች ሳትንቀሳቀስ ባለችበት ስትደርቅ ነው፡፡ አዎ፡፡ አጀቡ ብዙ ነው፡፡ ምህላው፡፡ … ወደ መኝታ እስክንደርስ፡፡ የሸክላ ምጣድ ቆሎ እንዳይሰማ ለክፋቱ! የከናፍሯን የምስራች ይዤ፤ የጡቶቿን የይለፍ ፍቃድ፤ የእንብርቷን ማሰናከያና የዳሌዋን እሺታ እስካገኝ፡፡

ተሞኘ … ሰው ሁሉ! መላእክት ሁሉ! ቄሱ ሁሉ!፡፡ በነፍስ ነጣቂ ሀገራችሁ፣ በልብ ሰርሳሪ መንደራችሁ በነፍስ አልባ ስጋህ ለነፍስህ እደር ትባላለህ፡፡ የስጋህ ፍሰሃ እዚህ አልጋ ላይ ነው፡፡ … የማየውን ገላ እውነትነት ለማረጋገጥ ከዘለዓለሜ ላይ በርከት ያለ ዕድሜ ተበድሬ በምድሩ ዘመኔ ላይ መዶል አለብኝ፡፡ ይኸው እርቃኗን ናት፣ ውበቷን ሁሉም እየተጋራው ነው፤ የክፍሉ የመስኮት መጋረጃ አረገደ፡፡ በሩ እንዳረገዘ ሁሉ አማጠ ተንሳጠጠ፡፡ ጣራና ግድግዳው ሀይ ባይ የለውም፤ ሰውነቷ ላይ አፍጥጧል፡፡ የወንድ ምጥ ጀመረ፡፡ የስጋ ርዕደ መሬት ተከተለ፡፡ … አውሎ ንፋሷ መጣች፡፡ ምሽጌ ወዴት አለህ? … እሷው አዋጊ፣ እሷው ተዋጊ፣ እሷው ማራኪ፣ ምሽጉ የሷው፡፡ ልመሸግ፡፡ አፈር ስሆን በቃኝ … አልኳት፤ ስሞትልህ በርታ አለች … ህይወት በአልጋው ላይ ቀጠለች፡፡

ጀምበር ሹክ አለቻት - በወገግታዋ ዳብሳ፡፡ ያን ቤተመቅደስ ሰውነቷን ይዛ ከወደቀችበት ተነሳች፡፡ የጨረቃ እንጂ የፀሀይ አድናቂ ያልሆንኩበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ ፀሀይ ነጣቂ ተኩላ! ጨረቃ ሰብሳቢ እረኛ፡፡ ሁለቴ ይነጋል ሁለቴ ይመሻል፡፡ ማለዳ ብርሃን ናት የየኔዋ ፈገግታ ብርሃን ነው፡፡ እሷ ስትነጉድ ይጨልማል - ጀምበር ስታዘቀዝቅ ይመሻል፡፡ ይሄ ጨለማ ለኔ ኩርኩም ነው፡፡ አናቴን ቀብሮ የማያላውስ ህመም፣ መሄዷ፡፡

… ለምን ስራ አትሰራም? … ለምን ዞር ዞር አትልም? ለምን? ለምን? ከዚህ ኮተታም ጭርንቁሳም ሰፈር፣ እንደጉንዳን ተዛዝለው ከሚኖሩ ሰዎች የሚዥጐደጐድ ስንኩል ምክር ነው፡፡ ለምን ስራ ልስራ? ለምን ልዙር? አንጀቴም … ሆዴም የእንብርቴ በታችም … አእምሮዬም ይሰራል፡፡ ያለ ክፍያ ይኸው እንደኳተኑ ናቸው፡፡ ምንም አልተቆረጠላቸውም፡፡

ዋጋቸውን ከመዳፏ ይቀበላሉ፡፡ ልብ-በፍቅሯ ቃላት ይሞላል፡፡ አይኖቼ-በፀዳል ውበቷ ላይ ይረጋሉ፡፡ አንደበቴ በጥኡም ውዳሴ ይቀኛል፡፡ ሆዴ-ሁሉን ቻይ ይሆን ዘንድ … ዘርፈፍ ብሏል፡፡ አእምሮዬ … የመኖሬን ትርጉም ከመኖሯ ሚስጥር ጋር አዛምዶ የተፈጥሮንና የፍቅርን ቁርኝት ይቀምራል፡፡

… ይህ ነው ስራ፡፡!

እንደውቅያኖስ የረጋ ልቡና እንዳይኖረኝ ማን ነው የሚበጠብጠኝ? ማነው እርሱ? ከዚህ ቁና ከማይሰፍረው ሀሳቤ ያናጠበኝ … የበሩ መንኳኳት ነው፡፡ ከፈትሁት …

“ማን ነው? …” አልሁ

“እኔ ነኝ … እናትህ ነኝ ልጄ!”

“ማነሽ አንቺ?” … እናት?”

“አዎ እናትህ ነኝ፡፡ … ምን ነው ምን ሆንክ?” ገባች፡፡

እናት! … እናት?

“ውይ ልጄን … ምን አስነክተውብኝ ይሆን?!” አለች፡፡

በሁለት መዳፎቿ አቅፋ ደረቷ ላይ ለጠፈችኝ … ቀና ብዬ አየኋት፡፡ በአይኖቿ ውስጥ የኔ አይኖች አይታዩኝም፡፡ በሀዘኔታዋ ውስጥ ጭርሱኑ የኔ የምለው ማንነት የላትም፡፡ ግን እናትህ ነኝ ትላለች፡፡

“ከዚህች ከይሲ ጋር ተጣብቀህ ይኸው ከሰውነት ተራ ወጣህ …” ምነው ወደቤትህ ብትመለስ? አይበቃህም? ተጎዳህ እኮ ልጄ! ምነው እሺ ብትለኝ?”

“ና ወደ እናትህ ቤት … ምንም ቢሆን እኔ እናትህ እሻልሃለሁ፡፡”

“እሺ” አልኳት፡፡

“እመብርሃን እሺ ትበልህ …” ምስጋናዋ ቀጠለ … በምርቃት፡፡

እብድ አይደለሁም ሁሉን አውቃለሁ … ሁሉን፡፡

እመብርሃን የጌታ እናት፡፡ … እናቴ የኔ፡፡ … ሚስቴስ? እሷ የማንናት?፡፡

“ይኸውልሽ እማዬ …” በሚገባት ቋንቋ ማስረዳት አለብኝ፡፡ እኔ ከሷ ጋር ወደ ቤት ልሄድ አልችልም፡፡

እንደገና ወደ ማህፀኗ ልገባ አይቻለኝም፡፡ መልሼ ጡቶቿን ልምግ አይሆንም፡፡ ሁሉም ወደ ኋላ? እሷ ራሷ አይደለች እንዴ ገፍታ ከሆዷ ያስወጣችኝ? ምን እንድሆን አስወጣችች? … እንድቆም ወይስ እንድወድቅ! ምን ሲባል ነው ወደቤቷ የምመለሰው? ምን አለ እዛ? ትዕዛዝ! … አታምሽ! አትደር! … ብላ! ጠጣ! ተኛ! … ከእንግዲህ የተበጠሰው እትብቴ ከሷ ጋር መቋጠር ይችላል! …. አንገቷን ደፋች፡፡ ከአይኖቿ የረዘሙ የእንባ መስመሮች ተሽቆለቆሉ፡፡ አልተናገረችም፡፡ በአንድ ጊዜ ማልቀስም ማውራትም አትችልም እናቴ፡፡ እናቴን የሚያስጨንቃት ውለታዋ ነው፡፡ እኔን ያረገዘችበት ሂደት ከፊል ደስታ ቢኖረውም ግማሹ ግን ህመም ነው፡፡ እኔን ለወራት የተሸከመችበት ቆይታዋ እሱም ህመም አለው፡፡ እኔን ከሆዷ ያስወጣችበትም ወቅት ታላቁ ህመም ነው፡፡ ምጥ ነው … ስቃይ፡፡ ታዲያ ማን ይህንን ሁሉ ይክፈላት? ስለእሷ እናት ተመሳሳይ ድካም አስባስ ይሆን? ይህንን ሁሉ እንድከፍል ስለምትፈልግ ነው ማልቀሷ፡፡ አይኖቼን በማየት ምጧን ትረሳለች፤ ድምፄን በማዳመጥ ልቧን ታረጋጋለች ከዚህ በላቀ እኔን በጉያዋ አቅፋ በመያዝ ነፍሷን አለምልማ ደህንነቷን ታረጋግጣለች፡፡ … ግን እኔም የእኔ አይደለሁም፡፡ ዳሩ እርሷ የራሷ ነች፡፡ እናት ነች፡፡ ፈጣሪ፡፡ ተፈጥሮ ነች፡፡ ደግሞም ችግር ፈጣሪ ነች፡፡

“አልሄድም እማዬ”

“እ! … እሺ፡፡”

ሄደች፡፡ በረዥሙ የእንባዋ ጐዳና ላይ፡፡

ዘአምላክየ…

የሆዷ ትልቀት ሲጨምር የኔም የፍቅር ወሰን ጨመረ፡፡ ይህ የአምላክ ስራ ነው፡፡ እኔና እሷን ጨምቆ ከሆዷ አሳደረ፡፡ ይቺ ቅድስት ራሷን ልትደግመው ነው፡፡ ሌላ ሽብር ልትፈጥር ነው፡፡ ማረፊያ አጥቶ ሲንከላወስ የኖረው ህልቆ መሳፍርት ፍቅሬ አሁን ቦታ አገኘ፡፡ ልሰጣት ያልኩት ፍቅር በሷ ልክ አልነበረም፤ ከሷ በላይ እንጂ፡፡ ፍቅሬ ከሰራ አካላቷ ተርፎ … ባክኖ በግድግዳው፣ በወለሉ፣  ባልጋው ይታይ ነበር፡፡ አሁንስ? ከአብራኳ ወዳዘለችው ፍጥረት ደረሰ፡፡ ከበላችው በልቶ፤ ከቀመሰችው ቀምሶ፤ ከቃረመችው ቃርሞ … ፅንሱም ነፍስ ዘራ ግን ነፍስ የነሳው ከማነው? ከርሷ ነው?  ከኔ ዳር ከሌለው የአባትነት የባልነት መውደድ ነው? ወይስ ከእግዜሩ?  … ከሶስቱም ነው፡፡

“ስራው ይብቃሽ፡፡ እርጉዝ ሴት እንዴት ስራ ብላ መንገድ ትወጣለች?” አልኳት፡፡ ጆሮዎቼን በጣቶቿ እያነኮረች አየችኝ፡፡

“ዋናው ቁምነገሩ እሱ አይደለም ውዴ! ዶክተሩኮ መንቀሳቀስ አለብሽ እ… ላንቺም ለልጅሽም ጤና ጥሩ ነው ብሎኛል፡፡ አይዞህ ምንም አልሆንም”

ማን ይሰጠኝ ማስተማመኛውን?

ለመንገደኛ ሰው እግዜሩም ማስተማመኛ አይሰጥም፡፡ የሷን የገፋ ሆድ ከአደጋ ለመቆጣጠር ሲል ከላባውን ሹፌር ቀስ ብሎ እንዲነዳ አያዘውም፡፡ መንገድ የመታው መኪና እንዳይተናኮላት ማድረግም አይችል፡፡ ያልተገራው ድንጋይ የእግሮቿን ወግ ያለው አረማመድ አሰናክሎ እንዳይጥላት የማድረግ ፍላጐትም የለው፡፡ ለምጧ ቀን ቆርጦ ስላልነገረን በሄደችበት ስፍራ ድንገት እንዳትወልድ የማድረግ ምን ውጥን አለው?  ወፎች ነን ብረሩ የተባልን፡፡ እርሱ ከዙፋኑ ሆኖ ለእጣፋንታችን በአደራ ሰጥቶናል፡፡ እልሻለሁ ለአንቺ መንገድ ጠራጊ ሆኖ ጌታ አይቆምም፡፡ የራሱ ስራ አለው፡፡ የርቀት መቆጣጠሪያው በእጁ የለም፡፡ ለነፃነታችን ዘብ የቆመ .. ተፈጥሮን አለማማጅ … ፍቅርን አቋዳሽ … ሜዳውንም ከፈረሱ ጋር ልቅ ፈጥሮ የቸረን … ታዛቢ ድንቅ አምላክ እንጂ፡፡

ሆዷን ይዛው ወጣች፡፡ ልጄንም ይዛ፡፡ በቅፅበት ደሞ ተመለሰች፣ ቃሌን የሰማች መሰለኝ … ደስ አለኝ ግን የአንገት ልብሷን ረስታ ነበር መመለሷ፡፡ የአጥር በሩ ታዝዞ ወለል ብሎ ተከፈተላት፡፡ የሰውን ዱካዎች በእንቅፋት ማንደድ የለመዱ የጥርጊያው ምንገድ ድንጋዮች አጐነበሱ፡፡ በወጉ ተራመደች፡፡ የርሷን ግብር ከሚናፍቀው የመስሪያ ቤቷ ደጃፍ የሚያደርሳት ታክሲ ጥቂት ሰዎችን እንዳዘለ ቆሞ ይጠብቃት ነበር፡፡ ሁለት ነፍሶች ይዛ በአንድ ወንበር ተቀመጠች፡፡ ለሚታየው ለአንዱ ከፈለች፡፡ ከቁመታሙ ሕንፃ ስር ስትደርስ የታክሲው ጐማዎች መሽከርከራቸው ተገታ፡፡ ወረደች፡፡ አሁንም ይህ ግዙፍ ድንጋይ ቁልቁል ነው የሚያያት? አይደለም፡፡ ቁልቁል የምታየው እርሷ ሆናለች፡፡ ምስጋናን ከዚህ የድንጋይ ክምር ለራሷ አዘጋጀች፡፡

ወደ ውስጥ ገብታ በሊፍት ማሽኑ ወደ ላይ አረገች፡፡ ሰላም ነው፡፡ አለም ተሰናድታ እያገለገለቻት መሸ፡፡ በመጣችበት ጐዳና ተመለሰችበት፡፡ የኔም ስጋት በነነ ለዛሬ፡፡ ግና የነገን የፍራቻ እርሾ አሁን ማጠንሰስ ጀመርሁ፡፡

ከብርሃን ደጃፍ …

ጨረቃዋ ስትደምቅ ከዋክብት ሲወጡ

ድምፅሽ ይነፍሳል ከዛፍ ከቋጡ፡፡

ጨረቃም የለችም፡፡ የጎጆአችን ላምባ ፍካቱ ጨምሯል እንደ ማለዳ ኮከብ፡፡ ድምፅዋን ከዛፍና ከቋጡ አሁን አልሰማውም፡፡ ከአይንና ከጥርሷ አልቃርመውም፡፡ ፀጥታ ያረበበት እንቅልፍ ውስጥ ናት፡፡ ፊቷ ግን ይነበባል እንደ ፊደል፡፡ ይመሰጠራል እንደ ቅኔ፡፡ ይፈታል እንደ ምስጢር፡፡ እንደ ማህሌታይ ያሬድ መቋሚያ ይዤ ላሸበሽብ ቃጣኝ፡፡ ይህ የእግዚአብሐር ፈጣሪ ነው ሰአሊ …? ሞናሊዛን ማን ፈጠራት? ምድርን ማን አድቦለቦላት? ተራሮች በማን ተፈለፈሉ? ከአለቱ ፏፏቴን ማን ሸነቆረው? አይንን ማን ተከለ? እርግብን ማን አበጀ? መሰጠትንስ ማን አስተማረ .. ፍቅርን? በባለቀለመ ብዙው ሰአሊ … በባለ መሮስሉ … ቀራፂ ጌታ ነው፡፡

ከተነከረው የብሩሹ ቀለም አብይ ጠብታ፣ አንዷ ይቹት ከጠፍሩ … አልጋዬ ላይ፡፡ ቅጥ ላጣው ፍቅሬ ሰበቡ ብዙ ነው፡፡

 

 

የጥበብ ግዞት እና ሞት …

ምንም አልሆነችም የኔዋ፡፡ ንክ ያረገው የለም ሆዷን፡፡ ሁሉም ቅሪት መሆኗን አውቋል፡፡ ሁሉም ግን አይደሰትም፤ አይገረምባትም፡፡ ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡ ማርገዝ ወድቆ መነሳት ነው … መውለድ እንደ አክርማ መከፈል ብቻ ነው … ማሳደግ በእድል ነው፡፡ ለነሱ ይህ ሁሉ ቀላል ነው፡፡ ካልገረማቸው ደግም አይጠነቀቁላትም፡፡ ከአጋም የተጠጋች ቁልቋል እንዳትሆን አይጋርዷትም፡፡

አንድ እኔ እልፍ ከለላ ልሆንላት እንዴት ይቻለኛል? ከሙሴ በትር ተውሼ አደጋን በመንጋ አልነዳለትም፡፡ ከሳምሶም ሀይልን ተካፍዬ … ሁሉን አልጋ በአልጋ ማድረጉ … ዘበት፡፡

ይሄ ሁሉ የሚወራው ስለሷ ነው? ጠብ እርግፍ መባሉ አንድ እሷን ከክፉ ለመታደግ ነው? ማነች ግን? ይላል አህዛብ ሁሉ፡፡ ይበል፡፡ ጥበብ አዝላለች፡፡ የኔንም የርሷንም ላብ የገበረችበት የሊቁ እስትንፋስ የታከለበት … ጥበብ፡፡ ራሷም ጥበብ ነች፡፡ ይህን በእንቅፍል አለም ድባብ የተዋጠ የዋህ ገፅታዋን ያየ ይመሰክራል፡፡ ደሞ … በተክለ አካል ቁማ ምድር ተሸክማት ስትወስድ ስትመልሳት ያስተዋለም ይናገራል፡፡ … እንደገናም … ፀሀይ በፀዳሏ እያነፈነፈች በግራም በቀኝም ብርሃኗን ስታሰፍርባት የታዘበ ያወራል፡፡ ለጥቆም … ነፋስ አክናፍ አበጅቶ በርሮ ሲያካልባት … ፀጉሮቿን ተውሶ ሊያጌጥበት እንዳለ ሲያዘናፍላት ያልተደመመ ከህዝብም ከአህዛብም ማን አለ?

ጊዜ አዲስ የወይን ጠጅ ነው፤ በአሮጌ አቁማዳ መጫንን /መያዝን/ በጄ የማይል፡፡ በጊዜው አዲሱ የወይን ጠጃችን መጣች፡፡ ሴቷ ልጃችን፡፡ ግን አቁማዳው ስለምን አረጀ ተባለ? እንዴትስ አፈሰሰ?

ግራና ቀኝ አይንን የሚያጥበረብር ብርሃን የሚያስተጋቡ ግድግዳዎች፡፡ የሆስፒታሉ ኮሪደር ላይ ነኝ፡፡ ከወገኗ አንድም አልመጣም፡፡ ከወገኔ እናቴ አለች፡፡ ቀበቶዬ ላልቷል፡፡ …

ከሴትም ከወንድም ነጭ ገዋን የለበሱት መላእክት መስለዋል ግን መሆን አልቻሉም፡፡ ክንፍም እጅም አጥሯቸዋል፡፡

መላእክት መሳዮቹ በሰይፋቸው የየኔዋን ትልቅ ሆድ ቀደው ሴቷን ልጄን ከአለም ቀላቀሏት፡፡

እውነተኞቹ መላእክት ሊታደጓት ትንፋሿንም ሊያስቀጥሉ ክንፋቸውን አራግበው ከሰማያት እስኪደርሱ … ይረፍድ ይሆን?

የተከፈተውን ማህፀን መልሶ ለመዝጋት ይጣደፉ ከነበሩት ሐኪሞች አንዱ በር ከፍቶ ወጣ፡፡ … ነገረን፡፡ …

… እመብርሃን የጌታ እናት፡፡ … እናቴ የኔ እና የልጄ …፡፡ ሚስቴ … የሞት፡፡ እግዚአብሔርም ከሰራው ሁሉ በዚህኛው ቀን እርሷን አሳረፈ፡፡ አረፈ፡፡

 

 

Read 3670 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:43