Saturday, 14 January 2012 11:04

ውርርዱ

Written by  ደራሲ - አንቷን ቼኾቭ ተርጓሚ - ቢንያም መ.
Rate this item
(0 votes)

የበልግ ምሽት ነው፡፡ ሽማግሌው ባለባንክ ወዲያ ወዲህ እየተንጐራደደ ከአስራ አምስት አመት በፊት፣ በበልግ ምሽት ስላሰናዳው ድግስ ያስባል፡፡ በድግሱ ብዙ የተማሩና የተከበሩ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ ከብዙ ጨዋታዎቻቸው መሀል አንዱ በአገሪቱ ለነበረው ከፍተኛው የፍርድ ቅጣት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነበር፡፡ አብዛኞቹ እንግዶች የሞት ቅጣትን  የሚቃወሙ ነበሩ፡፡ እንዲህ ያለው ቅጣት ጊዜው ያለፈበት፣ ሰብአዊ ያልሆነና ለክርስቲያን መንግስታት የማይመች ሲሉም አውግዘውታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከሞት ይልቅ የእድሜ ልክ እስር ይሻላል ብለው ተሟግተዋል፡፡

“በእናንተ አልስማማም” አለ ጋባዥ ባለባንኩ “አንዱንም ሞክሬው ባላውቅም አንድ ሰው ስለ ሀቅ ፍረድ ቢባል ከእድሜ ልክ እስራት የሞት ቅጣት ይሻላል ነው የሚለው፡፡” የሞት ፍርድ ባንዴ ሲገድል የእድሜ ልክ እስራት ግን ቀስ በቀስ ይገድላል፡፡ የትኛው ገዳይ ነው የሚሻል፤ በጥቂት ደቂቃ ፀጥ የሚያደርግ ወይስ ለብዙ አመት ነፍስን አሰቃይቶ የሚያወጣ?”

“ሁለቱም ሰብአዊ አይደሉም” አለ አንዱ እንግዳ “ሁለቱም አንድ አላማ አላቸው - ህይወትን መንጠቅ፡፡ መንግስት እግዜር አይደለም፡፡ መመለስ የማይችለውን መውሰድ የለበትም፡፡”

ከእንግዶቹ መሀል እድሜው 25 የሚሆን ጠበቃ ነበር፡፡ ሀሳቡን ሲጠየቅ እንዲህ አለ፡- “የሞትም የእድሜ ልክ ቅጣትም ሰብአዊ አይደሉም፡፡ ግን ከሁለቱ ምረጥ ብባል ያለምንም ማንገራገር ሁለተኛውን እመርጣለሁ፡፡ ከመሞት መሰንበት ይሻላናልና”

ሞቅ ያለ ክርክር ተጀመረ፡፡ ባለባንኩ በድንገት ስሜታዊ ሆኖ ጠረጴዛውን በጡጫ ከደለቀ በኋላ እንዲህ እያለ ጮኸ፡

የምትለው “እውነት አይደለም! ሁለት ሚሊዮን ብር አወራርዳለሁ፤ አንተ በተገለለ ቦታ አምስት አመት ተቆልፎብህ መኖር አትችልም”

“ከልብህ ከሆነ” ብሎ ቀጠለ ወጣቱ “ውርርዱን እቀበላለሁ፣ ግን የምቆየው አምስት አመት ሳይሆን አስራ አምስት አመት ነው፡፡”

“አስራ አምስት? ጥሩ!” ሲል ባለባንኩ አንባረቀ፡፡ “ሰማችሁ እንግዶቼ፤ ሁለት ሚሊዮን ብር አስይዣለሁ”

“ተስማምቻለሁ፡፡ አንተ ብርህን እኔ ነፃነቴን አስይዛለሁ” አለ ወጣቱ፡፡ እናም ይህ ያልተለመደና ትርጉም የለሽ ውርርድ ተካሄደ፡፡ ይህ ብር የጠገበና በቁማር ፍቅር ያበደ ባለባንክ በውርርዱ ተደስቶ እንደ ልጅ ፈነደቀ፡፡ እራት እየተበላም ወጣቱ ላይ እንዲህ ሲል ቀለደበት፡-

“በደንብ አስብበት፣ ገና ጊዜ አለህ፡፡ ለኔ ሁለት ሚሊዮን ብር ቀልድ ናት፡፡ አንተ ግን ወርቃማ ሶስትና አራት አመታት እያጣህ ነው፡፡ እንዲህ የምልህ ቢበዛ ከአራት አመት በላይ መቆየት ስለማትችል ነው፡፡ ሌላም ነገር ልንገርህ… አንተ አሳዛኝ! በገዛ ፈቃድህ ራስን ማሸግ በግድ ከመታሰር ይልቅ ይከብዳል፡፡”

እናም አሁን ባለባንኩ ወዲያ ወዲህ እየተንጐራደደ ይህን ሁሉ አስታወሰው፡፡” እንዲህ ሲልም ጠየቀ፡፡ “የዚያ ውርርድ አላማው ምን ነበር? የዚያ ሰው አስራ አምስት አመት መባከን፣ የኔም ሁለት ሚሊዮን ብር መወርወር ምን እርባና አለው? የሞት ፍርድ ከእድሜ ልክ ይሻል፣ ይባስ ምን የሚያረጋግጠው ነገር አለ? ምንም ትርጉም የሌለው ከንቱ ውርርድ ነበር፡፡ የኔ ቅብጠት፣ የሱ ስግብግብነት…”

ከዚያም በሚቀጥለው ምሽት የተከተለውን አስታወሰ፡፡ የወጣቱ እስር ጥብቅ ጥበቃ ባለው በባለባንኩ የአትክልት ቦታ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ለአስራ አምስት አመታት የአትክልቱን ድንበር እንዳይዘል፣ የሰው ዘር እንዳያይ፣ ድምጽም እንዳይሰማ፣ ደብዳቤ መቀበልም ሆነ ጋዜጣ ማንበብ እንዳይችል ከስምምነት ተደረሰ፡፡ አንድ የፈለገውን የሙዚቃ መሳሪያ ብቻ እንዲሰማው፣ ያሻውን መጽሐፍ እንዲያነብ፣ ደብዳቤ እንዲልክ እንዲሁም መጠጥ እንዲጠጣና እንዲያጨስ ተፈቀደለት፡፡ በስምምነቱ መሰረት ከቀሪው አለም ጋር የሚገናኘው በአንዲት ትንሽ መስኮት በኩል ብቻ ሆነ፡፡ የእስሩ መጀመሪያ ህዳር 14 ቀን 1870 ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን ማብቂያው ህዳር 14 ቀን 1885 በዚሁ ሰዓት ሆነ፡፡ ከእስሩ ጊዜ ማብቂያ ሁለት ደቂቃ እንኳ ቀድሞ ቢወጣ ስምምነቱ ይፈርሳል፡፡

እስረኛው በመጀመሪያው አመት በብቸኝነትና በድብርት ተሰቃየ፡፡ ካለበት ቦታ የፒያኖ ድምጽ ይሰማል፡፡ መጠጥና ሲጋራ አልፈልግም ብሏል፡፡ እሱ እንደፃፈው ከሆነ መጠጥ ስሜትን ያነሳሳል፡፡ ምንም አይነት ስሜት ደግሞ የእስረኛ ክፉ ጠላት ነው፡፡ መጠጥ እየጠጡ ማንንም ሰው ካለማየት በላይ አስፈሪ ነገር የለም፡፡ በመጀመሪያው አመት ያነበባቸው መፃህፍት ውስብስብ ሴራ ያላቸው የፍቅርና እና ሌሎች አስደሳች ታሪኮች ነበሩ፡፡ በሁለተኛው አመት የፒያኖው ድምጽ ጠፋ፡፡ እስረኛው የቆዩ መፃሕፍትን ብቻ ይጠይቅ ጀመር፡፡ በአምስተኛው አመት ከመብላት፣ ከመጠጣት፣ አልጋው ላይ ከመጋደም፣ በየደቂቃው ከማዛጋትና በብስጭት ከመናገር በቀር ሌላ ስራ አልነበረውም፡፡ መፃሕፍት አያነብም፡፡ አንዳንዴ ለመፃፍ ይቀመጣል፡፡ ለሰዓታት ይጽፍና በበነጋው የፃፈውን ቦጫጭቆ ይጥለዋል፡፡ ከአንድ ጊዜ በላይ ሲያለቅስም ተሰምቷል፡፡

በስድስተኛው አመት አጋማሽ ቋንቋዎችንና የፍልስፍና መፃሕፍትን ማጥናት ጀመረ፡፡ ራሱን በዚህ ስራ በጣም ስለጠመደው ባለባንኩ የሚታዘዘውን መፃሕፍት ለማምጣት ብዙ ኳተነ፡፡ በሚቀጥሉት አራት አመታት ወደ ስድስት መቶ የሚሆኑ ጥራዝ መፃሕፍትን እያስመጣ አነበበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ባለባንኩ ከእስረኛው ደብዳቤ የደረሰው፡፡

“የተከበርከው አሳሪዬ፣ እነዚህን መስመሮች በስድስት ቋንቋዎች ጽፌልሀለሁ፡፡ ቋንቋዎቹን ለሚያውቁ ሰዎች አስነብብልኝ፡፡ አንድም እንኳ ስህተት ካላገኙ በአትክልቱ ቦታ የተኩስ ድምጽ አሰማኝ፡፡ በዚህም ልፋቴ ከንቱ እንዳልቀረ እረዳለሁ፡፡ የዘመናት እውቀት በየቋንቋው ቢነገርም አንድ ነበልባል ግን በሁሉም ይነዳል፡፡ ቋንቋዎቹን በመረዳቴ የነፍሴን ሐሴት አንዴ’ኳ ብታውቅ” የእስረኛው ፍላጐት ተሟላለት፡፡ የተኩስ ድምፅም ተሰማ፡፡

ከአስረኛው ዓመት በኋላ እስረኛው ያለ ሌላ ተጨማሪ መፃህፍት ወንጌልን ብቻ ማንበብ ያዘ፡፡ ባለባንኩ በዚህ ተገረመ፡፡ በአራት አመታት ስድስት መቶ ጥራዝ መፃሕፍትን ፉት ያደረገ ሰው፤ በአንድ ትንሽ መጽሐፍ አመት የሚሆን ጊዜ መፍጀቱ ለምን ይሆን በሚለው ግራ ተጋባ፡፡ ቀጥሎ ስነ መለኮት አና የአለም ታሪክ ተከተሉ፡፡

በመጨረሻዎቹ ሁለት አመታት እስረኛው እጅግ ብዙ የተለያዩ መፃህፍትን አነበበ፡፡ አንዴ በተፈጥሮ ሳይንስ ራሱን ሲወጥር ሌላ ጊዜ ደሞ ወይ ባሮንን ወይ ሼክስፒርን ያነባል፡፡ አንዴ ኬምስትሪ፣ አንዴ የመድሀኒት ዝርዝር፣ አንዴ ልብ ወለድ እያለ ከረመ፡፡

ሽማግሌው ባለባንክ ይሄን ሁሉ አስታወሰና ለራሱ እንዲህ አለ፡- “ነገ በአስራ ሁለት ሰዓት ነፃነቱን ይቀዳጃል፡፡ በስምምነቱ መሰረት ሁለት ሚሊዮን ብሬን ቆጥሬ ማስረከቤ ነው፡፡ ከከፈልኩት አበቃልኝ ማለት ነው፡፡”

ከአስራ አምስት አመት በፊት ለባለባንኩ ብዙ ሚሊዮን ብሮች መጫወቻዎቹ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ቁማርተኝነቱና ያለጥናት በድፍረት ብቻ የሚገባበት ንግድ፣ … ሀብቱን አመናምነውበታል፡፡ “የተረገመ ውርርድ!” ብሎ አጉተመተመ፡፡ “ለምንድን ነው የማይሞተው? አሁን ገና አርባ አመቴ ነው፡፡ እኔ እሱ ፊት ለማኝ ሆኜ “እስኪ ልርዳህ” ሊለኝ? በፍፁም! ከዚህ ውርደት የሚያድነኝ አንድ ነገር ብቻ ነው - የሡ ሞት!”

እንዲህ እያሰበ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ሆነ፡፡ ሁሉም ሰው በመተኛቱ ድምጽ የለም፡፡ ኮሽታ ሳያሰማ ወደ ካዝናው ሔደ፡፡ ባለባንኩ የዛሬ አስራ አምስት አመት የተቆለፈውን ካዝና ከፍቶ የእስር ቤቱን ቁልፍ አወጣው፡፡ ከዚያም ካፖርቱን ደርቦ ከቤቱ ወጣ፡፡

የአትክልት ቦታው ጨለማና ብርዳማ ነው፡፡ ስለታም እርጥብ ነፋስ ዛፎቹን ሰላም ነስቷቸዋል፡፡ ባለባንኩ አይኑን ጎልጉሎ ቢያፈጥም አንዳችም ነገር ማየት አልቻለም፡፡ ወደ ዘበኛው ቤት በዳበሳ ሔዶ በስሙ ይጠራው ጀመር፡፡ መልስ የለም፡፡

ዘበኛው በበልጉ ብርድና ዝናብ ተማርሮ ወይ ወጥ ቤት ወይ ሌላ ቦታ ተኝቷል ማለት ነው፡፡ ባለባንኩ የዘበኛውን አለመኖር ለማረጋገጥ ክብሪት ጭሮ ወደ ውስጥ ተመለከተ ግን የለም፡፡

የክብሪቱ ብርሀን እንደጠፋ በፍርሀት እየራደ በእስር ቤቱ በር አጮለቀ፡፡ ፈዛዛ የሻማ ብርሀን ክፍሉን ሞልቶታል፡፡ እስረኛው ተኝቷል፡፡ የተገለጡ መፃህፍት በጠረጴዛው፣ በሁለቱ መቀመጫዎችና በምንጣፉ ላይ ይታያሉ፡፡

ባለባንኩ መተኛቱን ለማረጋገጥ መስኮቱን በጣቱ መታ መታ አደረገው፡፡ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡ የአስራ አምስት አመታት እስር አርፎ መቀመጥም ሆነ ተቀምጦ መተኛትን አስተምሮታል፡፡ ባለባንኩ በጥንቃቄ ቁልፉን አስገብቶ በሩን ከፈተው፡፡ ትንሽ ግጭግጭታና ሲከፈት ሲጢጥ የሚል ድምጽ ተሰማ፡፡ የእግር ኮቴ ወይም ጩኸት ጠብቆ ነበር - ባለባንኩ፡፡ ሆኖም ምንም ሳይፈጠር ሶስት ደቂቃ አለፈ፡፡

ባለባንኩ እስረኛውን ለጥቂት ጊዜ አስተዋለው፡፡ አጥንቱ የገጠጠና ቆዳው የጠበበው፣ ጠጉራምና ጢማም፣ ፊቱ ቢጫ ጉንጩ ሰርጓዳ፣ ጀርባው ቀጭንና ረጅም፣ የሰለሉ እጆች፡፡

የፀጉሩ ብርማ መሆን እድሜው ከአርባ አመት የዘለለ አስመስሎታል፡፡ ከፊት ለፊቱ ወረቀት ላይ ልቅም ባለ እጅ ጽሁፍ የተፃፈ ነገር ይታያል፡፡“አሳዛኝ ፍጡር!” ብሎ አሰበ ባለባንኩ “ይሄኔ ስለሚያፍሰው ብር እያለመ ይሆናል፡፡ አሁን የኔ ሥራ… ይሄን በከፊል የሞተ ሰው አልጋው ላይ ወርውሬ በትራስ አፍኜ መግደል ነው! ከዚያ የፈለገ መርማሪ ቢመጣ በሰው ስለመገደሉ ምንም ማስረጃ አያገኝም፡፡ በመጀመሪያ ግን የፃፈውን ላንብበው ...” “ነገ በአስራ ሁለት ሰዓት ነፃነቴንና ከሰው ጋር የመገናኘት መብቴን አጎናፀፋለሁ፤ ግን ይሄን ክፍል ከመልቀቄና የፀሐይዋን ብርሀን ከማየቴ በፊት ለአንተ ጥቂት ቃላት ብጽፍልህ ወደድሁ፡፡ በአምላክ ፊትና በሐቅ እምልልሀለሁ… ነፃነትንም፣ ሞትንም፣ ህይወትንም፣ በአጠቃላይ ጥሩ የተባሉትን ነገሮች ሁሉ ካንተ በቀረቡልኝ መፃህፍት የተነሳ ናቅኋቸው፡፡ “ለአስራ አምስት አመታት የምድርን ስንክሳር አጠናሁት፡፡ ባንተ መፃህፍት ወይን ተጎነጨሁ፣ መዝሙሮችን ዘመርሁ፣ በየጥሻው አውሬና አጋዘን አደንሁ፣ ውብ ሴቶችንም አፈቀርሁ … ባንተ መፃህፍት ገጣምያንና ጠቢባን አስማት ትረካና ግጥማቸውን በጆሮዬ አንሾካሾኩልኝ፡፡ ባንተ መፃህፍት ታላላቆቹን ተራሮች ወጣሁ… የፀሐይን መውጣትና መጥለቅ… እንዲሁም አረንጓዴውን ጫካ፣ ወንዞችን ሐይቆችን፣ ከተማዎችን ሁሉ አየሁ፡፡ ባንተ መፃህፍት መናፍስት ስለ አምላክ ጠየቁኝ፡፡ ባንተ መፃህፍት ወለል አልባ ገደል ውስጥ በረርኩ፣ ተአምራትን ሰራሁ፣ አዳዲስ ሐይማኖቶችን ሰበክሁ … “ያንተ መፃህፍት ጥበብን ሰጡኝ፡፡ የሰውን ስንክሳር ሳጠናው ስለኖርኩ አሁን ከሁላችሁም በላይ ብልህ መሆኔን አወቅሁ፡፡“እናም መፃህፍትን ናቅሁ፤ የዚህ አለም ጥበብና እውቀት ሁሉ እርባና ቢስ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ምክንያታዊ አስተሳሰባችሁን ትታችሁ መንገድ ስታችኋል፡፡ ውሸትን እውነት ብላችኋል… በእናንተ እውነት እንቁራሪትና እንሽላሊት ከብርቱካን ዛፍ ይበቅላሉ፤ ጽጌረዳም እንዳላበው ፈረስ ትሸታለች፡፡ “አንተንና የምትለፋለትን ነገር መናቄን የማሳየው ያለምኩትንና የተመኘሁትን ያንን ያንተን ገንዘብ ሁለት ሚሊዮን ብርህን አልፈልግም በማለት ነው፡፡ ይሄንን የማደርገው ደግሞ ከእስሩ ማብቂያ አምስት ሰዓት ቀድሜ በመውጣት ነው፡፡ እናም ስምምነታችንን በገዛ ፈቃዴ እጥሳለሁ፡፡” ባለባንኩ የእስረኛውን ማስታወሻ አንብቦ ሲጨርስ ወረቀቱን ጠረጴዛው ላይ ጣለ፡፡ ከዛም የእስረኛውን ግንባር ሳመና እያነባ ከእስር ክፍሉ ወጣ፡፡ ወደ ቤቱ ገብቶ አልጋው ላይ ከተጋደመም በኋላ እንኳ እንቅልፍ በአይኑ አልዞር አለው፡፡በነጋታው ረፋዱ ላይ ዘበኛው ፊቱ በድንጋጤ ነጫጭባ መስሎ እየሮጠ ባለባንኩ ጋ በመምጣት እስረኛው አጥር ዘልሎ መጥፋቱን ነገረው፡፡ ባለባንኩ ምንም እንዳላወቀ ወደ ቦታው ሔዶ የነገሩን ትክክለኝነት አረጋገጠ፡፡ አላስፈላጊ ወሬ እንዳይነሳና እንዳይነዛ በሚል ሚሊዮን ብሮችን ዋጋ ቢስ ያደረገውን የእስረኛውን የማስታወሻ ወረቀት ካዝናው ውስጥ ቆለፈበት፡

 

 

Read 3326 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 11:11