Friday, 06 January 2012 11:08

የፍቅር አባዜ!

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(1 Vote)

መሳይ ጓደኛዬ ነው፡፡ ይሄን ሰሞን ግን ዘወትር እንገናኝበት ከነበረው ቤት ጠፍቶአል፡፡ ስልክ ሲደወልለት አያነሳም፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ስልኩ ጭራሹኑ ጥሪ አይቀበልም ማለት ጀመረ፡፡ ከጠፋ አንድ ወር ከሞላው በኋላ ነበር አማኑኤል ሆስፒታል እንደገባ የሰማሁት፡፡ ሄጄ ልጠይቀው ወሰንኩኝ፡፡ ከዚህ በፊት አማኑኤል መሄዴን አላስታወስም፡፡ አርብ ከሰአት በኋላ ወደዛው አመራሁ፡፡ በላይኛው በር በኩል ገባሁኝ፡፡ በረንዳው ላይ ብዙ ሰው ተኮልኩሎዋል፡፡ አንድ ክፍት በር ያለው ክፍል ውስጥ አንዲት ሴት ድረሱልኝ እያለች ስትጮህ ትሰማለች፡፡ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ፡፡ መሳይ ያለው ዋርድ ስምንት የሚባል ክፍል እንደሆነ ሰምቼ ስለነበር ሁለት ነጭ ጋዋን የለበሱ ሰዎችን አግኝቼ ዋርድ ስምንት የት እንደሆነ ጠየቅኩኝ፡፡ ቀጥ ብለህ ወደ ታች ውረድ አሉኝ፡፡

ግቢው ውስጥ መቅበዝበዝ ግን አልቀረልኝም፡፡ ወደታች ብወርድም ቦታውን በትክክል ማወቅ አልቻልኩም፡፡ በመጨረሻ ሁለት በሽተኞች ተራርቀው ተቀምጠው ተመለከትኩኝ፡፡ ዋርድ ስምንት የት እንደሆነ አንደኛቸውን መጠየቅ አለብኝ፡፡ አንዱን ስመለከት ተስፋ ቆረጥኩኝ፡፡ ምክንያቱም ፒጃማውን ለብሶ በተቀመጠበት ለሃጩ ተዝረክርኳል፡፡ ሁለተኛው ግድግዳ ተደግፎ ተቀምጦ ሲጋራ እያጨሰ ነው፡፡ በጣም ረጅም ሲሆን የለበሰው ፒጃማ አጥሮታል፡፡ ፊቱ የሞገገ አገጩ ያበጠ ነው፡፡ ገና እንዳየኝ ፈገግ አለ፡፡

 

“ዋርድ ስምንት የት ነው?” ስል ጠየኩት፡፡

ወዲያው ብድግ ብሎ ተነሳ፡፡ ቁመቱ ከገመትኩት በላይ ረጅም ነው፡፡ “ና ላሳይህ” አለኝና እየመራኝ ይዞኝ ሄደ፡፡

“አንድ ብር ትሰጠኛለህ” አለ እየሄድን ሳለ

“የለኝም” አልኩኝ ድርቅ ብዬ

“እሺ አንድ ሲጋራ ትገዛልኛለህ”

“አሁንም የለኝም” አልኩኝ፡፡ እውነት ለመናገር ከሆነ ኪሴ ውስጥ ምንም አልነበረም፡፡

“ያሳየሁበትን እኮ ነው”

“እኮ ስለሌለኝ ነው… ነገ”

“ነገማ የት ትመጣለህ”

መልሱ ገረመኝ፡፡ እኔ ዕብድ ነው ብዬ ልሸውደው ነበር፡፡ እሱም ይሄን አውቋል፡፡ ቆም ብሎ ወደ አንድ አዳራሹ እየጠቆመኝ:- “ያውና” አለኝ፡፡ አመስግኜ ወደ አዳራሹ ገባሁ፡፡ ከሰላሳ  የማያንሱ አልጋዎች አለበት፡፡ አዳራሹ የቆሙም የተኙም በሽተኞች አሉበት፡፡ አንድ አጠር ብሎ ወፈር ያለ ሰማያዊ ጋዋን የለበሰ አስታማሚ ወደ እኔ ቀረብ ብሎ “ማንን ፈልገህ ነው?” ሲል ጠየቀኝ፡፡

“መሳይን ፈልጌ ነው”

“መሳይ ቀይ ወፍራም?”

“አዎን”

“ሳይወጣ አይቀርም፡፡ ዛሬ ይወጣል ሲባል ነበር፡፡ ለነገሩ ጠዋት እዚህ ነበር፡፡ እስኪ ወደ ካፌ አካባቢ ፈልገው” አለኝ፡፡

በመጣሁበት መንገድ ተመለስኩ፡፡ ካፌውን አጠያይቄ ካገኘሁ በኋላ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ፡፡

ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ሲጋራ እያጨሰ አገኘሁት፡፡ የለበሰው ፒጃማ እንደጠበበው ያስታውቃል፡፡ ፊቱ ትንሽ ጠቆር ከማለቱ በስተቀር ያው እራሱ ነበር፡፡

ከመቀመጫው ተነስቶ እያቀፈ ተቀበለኝ፡፡

“እሺ ልጅ መሳይ” አልኩት - ስላገኘሁት ደስ እያለኝ

“አለሁልህ” ሲጋራውን በሃይል እየሳበ

“ተስማምቶሃል”

“ባክህ አሞኝ ነበር… እቤቴ አርፌ ራሃ ሆኜ እያቃምኩ ሳለሁ በፖሊስ አስይዘው እዚህ አስገቡኝ፡፡ አንድ ወር ሆነኝ ከገባሁ”

“ማናቸው እዚህ ያስገቡህ?”

“እነሱ ናቸዋ” ቤተሰቦቹን ለማለት እንደፈለገ ገባኝ፡፡

“እየረበሽክ ይሆናላ” አልኩት

“አልረበሽኩም፡፡ እርግጥ አወራለሁ፡፡ የማወራው ደግሞ መልስ ለመስጠት ነው”

“ከማን ጋር ነው የምታወራው”

“ያልገባህ ነገር አለ፡፡ ይሄ አለም ግድግድ ያለ ፈጣጣ አለም ብቻ እንዳይመስልህ! በጣም ረቂቅ ነው፡፡ ድምጽ ሊሰማህ ይችላል፡፡ ከድብቁ አለም ውስጥ የሚያናግሩኝ ድምጾች አሉ፡፡ የአንዷ ሴት ድምጽ ምን እንዳለኝ ታውቃለህ? አንተ የማትረባ አስተማሪ… አሁን አንተን ማን ያይሃል? አለችኝ፡፡” ሲጋራውን በሃይል ምጐ አፍጦ እያየኝ

“ማንም ምንም ቢልህ አንተ ማን መሆንህን ታውቃለህ” አልኩት፡፡

“ድምፁ በጆሮህ አይሰማህም፡፡ ግን በአዕምሮህ ይገባሀል” አለኝ

“ችግርህ ይገባኛል፡፡ ስኪዝዮፎርንያ ነው፡፡ አዕምሮህ በውስጡ የሚፈጥረው ድምጽ፡፡ እኔም ይሄ ችግር አለብኝ፡፡ ዋናው ነገር እራስህን አውቀህ መቆጣጠር ነው፡፡ የጆንናሽን ታሪክ አላየህም? ዘ ቢዩቲፉል ማይንድ ፊልም ላይ፡፡ እሱ እንድያውም ድምጽ ከመስማት አልፎ ሰዎች ይታዩት ነበር፡፡ ግን በመጨረሻ ሰዎቹ እውነት አለመሆናቸውን አውቆ ዘጋቸው፤ ተቆጣጠራቸው”

“እውነት አይደሉም?” አዕምሮህ የፈጠራቸው ናቸው? እውነት ናቸው ባክህ! ያንተ አዕምሮ ከሌላው አዕምሮ ይበልጥ የነቃ ስለሆነ ነው የምታያቸውና የምትሰማቸው” አለ ፈገግ ብሎ እያየኝ “ሊሆን ይችላል! ሳይንሱ ስላልደረሰበት ስኪዞፎርንያ ይለዋል እንጂ አጋንንትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይም ኢልየንስ (ዩፎ)… ብቻ በሌላ ዳይሜንሽን የሚገኙ ፍጡራን! ግን ዋናው ነገር ማንም ምንም ቢል አንተ እራስህን አውቀህ ለመቆጣጠር መሞከር ነው፡፡” አልኩት፡፡

አንድ ቀጭን፣ ረጅም ጥቁር፣ ፒጃማ የለበሰ ታካሚ አጠገቤ መጥቶ ቆመና “እኔ አፋር ነኝ” አለ በኩራት እንደወታደር ቀጥ ብሎ፡፡

በመገረም ሳየው የተመለከተው መሳይ፤ ሳቅ አለና “አፋር ነው፤ ጫት በጣም ይወዳል፤ ጫት ካጣ ጽድ ወይም የኮሽም ቅጠል ይቅማል” አለና አንድ ሲጋራ አውጥቶ ሰጠው፡፡

“እኔ አፋር ነኝ” አለና ሲጋራውን ተቀብሎ ሄደ፡፡

አንድ ሌላ ታካሚ በእጁ አምስት ሳንቲም ይዞ መጣና አምስት ሳንቲሙን አሳየኝ፡፡ አልገባኝም፡፡

“አምስት ሳንቲም አለኝ፡፡ ሲጋራ መግዣ አርባ አምስት ሳንቲም ሙላልኝ እያለ ነው” አለ መሳይ እየሳቀ፡፡

“እኔ ምንም ገንዘብ አልያዝኩም… አንተ ስጠው” አልኩት፡፡

መሳይ ሁልጊዜ አንድ ፓኬት ሲጋራ እንደሚይዝ ስለማውቅ፡፡

“ወልዴ ይባላል፡፡ በገንዘብ ነው ያበደው፡፡ ስለገንዘብ የሚለውን እንስማና እሰጠዋለሁ” አለ መሳይ፡፡

ወልዴ ረጅም ነው፡፡ ሁሉም ነገሩ ረጅም፡፡ የበለጠ ግን አንገቱ ረጅም ነው፡፡ አገጩ የሞገገ፡፡ አንድ ሲጋራ ከመሳይ ተቀበለና “ ምን ልበል?” ሲል ጠየቀ፡፡

“ስለገንዘብ ንገረን” አለ መሳይ፡፡

“አስር ብር ካለህ አንድ የሻይ ቤት ማህበራዊ ትበላለህ፡፡ ትንሽ ፓስታ፣ ትንሽ መኮረኒ፣ ትንሽ ጐመን፣ የምስር ወጥና አንድ የተቀቀለ እንቁላል ያለበት፡፡” አለ ሲጋራውን እየማገ

“ሃያ ብር ካለህስ?” አለ መሳይ

“ሃያ ብር ካለህ አንድ ማህበራዊ ከአንድ ቡና ጋር ከአራት ሲጋራ ጋር ይኖርሃል፡፡ ሰላሳ ብር ካለህ አንድ ማህበራዊ፣ አንድ ቡና፣ አራት ሲጋራዎችና እሩብ ጫት ይኖርሃል፡፡ አርባ ብር ካለህ እሩቡ ጫት ግማሽ ጫት ይሆናል፡፡ አምሳ ብር ካለህ ጨብሲ ትጨብሳለህ፡፡ መቶ ብር ካለህ ምሳህን ጥብስ በልተህ ሙሉ ጫት ከጨብሲ ጋር ይኖርሃል፡፡ በቀን መቶ ሃምሳ ብር ካለህ ቁርስህን ዱለት፣ ምሳህን ጥብስ፣ ሁለት ሙሉ ጫት ከጨብሲ ጋር ይኖርሃል፡፡ በወር ስድስት ሺህ ብር ሲኖርህ ሬዲዮ ሙዚቃና ፊልም ያለው ሞባይል ትገዛለህ፡፡” አለና ሲጋራውን ተረኮሰ፡፡

“ከዛስ አታቋርጥ” አለ መሳይ

“መቶ ሺህ ብር ሲኖርህ ሊሊ ኤልሲና ራሄል ስልክህን ያጨናንቁታል፡፡ አምስት መቶ ሺህ ብር ሲኖርህ ወሲብ ይሰለቸሃል፡፡ አንድ ሚሊዮን ብር ሲኖርህ አንድዋን ታገባለህ፡፡ እኔ እዚህ ደረጃ ላይ ነው የደረስኩት” አለና ሲጋራውን ምጐ ወረወረው፡፡

መሳይ ወደኔ እያየ “ይሄ እንግዲህ ወደላይ ሲወጣ ነው፡፡ ወደታች ሲወርድ ደግሞ ምን እንደሚል ስማው” አለና “ስትከስርስ?” አለው

“አንድ ሲጋራ ስጠኝ”

“አሁን አላጨስክም?”

“እፈልጋለሁ”

መሳይ አንድ ሲጋራ አውጥቶ ሰጠው፡፡

ሲጋራውን ለኮሰና “ብር የሌለህ ጊዜ ጓደኞችህን ትፈልጣለህ፡፡ እነሱም ይሰለቹሃል፡፡ ልብስህን ትሸጣለህ፡፡ እሱም ተሸጦ ያልቃል፡፡ የሰው ልብስ እየሰረቅክ መሸጥ ትጀምራለህ፡፡ እሱም አይቀጥልም፡፡ ከዚያ ደምህን ትሸጣለህ፡፡ ቀይ መስቀል አካባቢ የደም ደላሎች አሉ፡፡ ገና ስትመጣ በሬው መጣ ነው የሚልህ፡፡ ደምህን መጠው አንድ ምሪንዳ ይሰጡሃል፡፡ ችግሩ እየጠና ሲሄድ ደሙንም መሸጥ አትችልም፡፡ ምክንያቱም ደምህ አልቆዋል፡፡ ከዚያ መሳደብ ትጀምራለህ፡፡ እሱም አይሰራም፡፡ ድንጋይ ስትወረውር አብደሃል ይሉና እዚህ ያመጡሃል” አለ ወልዴ፤ የሲጋራውን ጭስ በአፍንጫው እየለቀቀ፡፡

“አሁን መሄድ እችላለሁ?” ጠየቀ ወልዴ

“ትችላለህ” አለው መሳይ፡፡ ወልዴ ሲጋራውን እየማገ ተነስቶ ሄደ፡፡

“እንግዲህ ከነዚህ ሰዎች ጋር ነው ያለሁት… ወንድሜ” “አለኝ መሳይ፡፡ ወዲያውኑ እሱም አንድ ሲጋራ አውጥቶ ለኮሰና “ሁለት የሚያስደስቱኝ ነገሮች ግን አሉ” አለ፡፡

“ምን?” አልኩት፡፡

“የፋንቱ ቡናና የያስሚን ፈገግታ”

“ማነች ያስሚን?”

“የኔ ዶክተር ነች፡፡ እጥር ምጥን ያለች፡፡ ፈገግታዋ እንደጠዋት ፀሐይ የሚያሞቅ፡፡ በቀን ሁለቴ ትጐበኘኛለች” “ያስሚን ምን ማለት ነው?” ጠየኩት፡፡

“አበባ ነው፡፡ ነጭ የሚያምር አበባ፡፡ ጠዋት በፀሐይ ብርሃን ይከፈታል፡፡ ማታ ማታ ደግሞ ይዘጋል፡፡

“እስዋም ጠዋት ጠዋት ብሩህ ናት፡፡ ማታ ማታ የለችም፡፡ የት ትሆን? ባል ይኖራት ይሆን?” አለ ሲጋራውን እያጨሰ በመተከዝ፡፡

“ወደሃታል?”

“ምን ዋጋ አለው ብወዳት? እሷ ዶክተር እኔ እብድ”

“ቅጠፋት” አልኩት አይን አይኑን እያየሁት፡፡ “አበባ ነች… ስለዚህ ቅጠፋት”

ሳቅ ብሎ አየኝ፡፡ ተሰናብቼው ወጣሁ፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ ከመሳይ ጋር እንደገና ተገናኘን፡፡ ከአማኑኤል ወጥቶ ዘወትር የምንገናኝበት ቤት ውስጥ፡፡

እንደተለመደው ስለፖለቲካ ፍልስፍናና ፍቅር አወራን፡፡ ለአንድ ሳምንት በተከታታይ መጣ፡፡ ከዚያ ግን እንደገና ጭልጥ ብሎ ጠፋ፡፡ ብደውል ስልኩን አያነሳም፡፡ አንድ ቀን ግን በማላውቀው ቁጥር መልእክት መጣልኝ፡፡ መሳይ ነበር፡፡

“አበባዋን ለመቅጠፍ ተመልሼ አማኑኤል ገብቻለሁ፡፡ አሁን አልታመምኩም፡፡ ታምሜ ከሆነም በሽታዬ ፍቅር ነው፡፡ መሳይ” ይላል መልእክቱ፡፡

ተመልሼ ልጠይቀው ወሰንኩ፡፡

 

 

 

 

Read 5811 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:15