Saturday, 31 December 2011 10:38

“ውረድ! … አልወርድም!”

Written by  ደራሲ አዚዝ ኔሲን (ቱርካዊ) ተርጓሚ ገዛኸኝ መኰንን
Rate this item
(1 Vote)

የቀዬዋ ነዋሪ አንድ ንክ ጣሪያ ላይ ወጥቶ በማየቱ በአድናቆት ተውጧል፡፡

ጐዳናውን ከጫፍ እስከ ጫፍ ጣሪያ ላይ የተሰቀለውን ንክ ለማየት በጉጉት በተዋጡ ሰዎች ተጥለቅልቋል፡፡

በቅድሚያ ከአጥቢያው ፖሊስ ጣቢያ፣ ቀጥሎ ከዋናው ፖሊስ ማዘዣ ፖሊሶች በመኪና እየተሞሉ መጥተው በህንፃው ዙሪያ ፈሰሱ፡፡ የእሳት አደጋ መኪኖችም ተከታትለው ደረሱ፡፡ የንኩ እናት ልጇን መለማመጥ ቀጥላለች፡፡

“እባክህ! ልጄ ና ውረድ፣ በአጠባሁህ ጡቴ ይሁንብህና እሺ በለኝና ውረድ”

ንኩ ግን ፖሊስ ካላደረጉት በቀር እራሱን ከህንፃው ላይ ፈጥፍጦ እንደሚገል ተናገረ፡፡

የእሳት አደጋ ሠራተኞቹ ድንገት ቢፈጠፈጥ በሚል መረባቸውን ወጠሩ፡፡ ዘጠኝ የእሳት አደጋ ሠራተኞች መረቡን በህንፃው ዙሪያ ለመወጠር በላብ እስኪታጠቡ ድረስ ተራወጡ፡፡ በከፊል ማግባባት፣ በከፊል ማስፈራራት አይነት ንኩ እንዲወርድ ሳጅኑ ውትውታውን ቀጠለ፡፡

“ፖሊስ ካደረጋችሁኝ ምን ቸገረኝ፣ አለዚያ ግን መፈጥፈጤ አይቀርም፡፡”

ማስፈራሪያውም ሆነ ማግባቢያው ምንም አልፈየደም፡፡ “ወዳጄ እባክህ … ለምን አትወርድልንም!”

“ስማኝማ … እኔ እንድወርድ ከመጨቅጨቅ ለምን እናንተ ወደላይ  አትወጡም!”

ከተሠብሳቢዎቹ አንዱ ሃሳቡን እንዲህ ሲል ሠነዘረ

“እንዳልከው ፖሊስ እናደርግሃለን ብንለውስ ምናለ?”

ሌላኛው በበኩሉ በተቃውሞ

“ምን ይላል ይሄ … ማንንም መንገደኛ ፖሊስ ማድረግ እንዴት ይቻላል?”

“ጥሩ! ጥሩ! የምር ፖሊስ ልናደርገው አንችልም ግን …”

ከዘራቸውና ተደግፈው ይታዘቡ የነበሩ አዛውንት ሲያደምጡ ቆይተው “የምትሉት ጨርሶ የማይሆን ነው በሽንገላም ሆነ የምር ቢሆን አይቻልም፡፡”

“ነገር ግን እንዲወርድ ማድረግ ይቻላል”

“አይሆንም ስላችሁ፡፡ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ጠንቅቄ አውቃቸዋለሁ፡፡ አንዴ ወደላይ ከመጡ፣ ወደታች መውረድ ፈፅሞ አይፈልጉም፡፡”

“አንዴ ይውረድልን እንጂ … ሌላው ቀላል ነው፡፡”

“አይወርድም እኮ ነው የምላችሁ፡፡”

ከታች ከቆሙት ሰዎች አንዱ ድንገት

“ሰውዬ በቃ ፖሊስ እናደርግሃለን ውረድ!” ሲል አምባረቀ፡፡

ንኩ እየደነሰ በጩኸት “አልወርድም! የከተማው ምክር ቤት አባል ካላደረጋችሁኝ እንዲያውም አልወርድም፡፡”

አዛውንቱ ይሄኔ “አላልኩም ነበር፡፡” አሉ

”እሺ እንዳለው እናድርግ፡፡”

“የፈለገውን ሁሉ ብታደርጉ አይወርድም፡፡ አንዴ ጣሪያ ላይ ለመሠቀል የቆረጠ ንክ ጨርሶ መውረድ አይሻም”

ሳጅኑ በብስጭት ጮኸና “እንዳልክ የከተማው ምክር ቤት አባል እናደርግሃለን ብቻ እዚህ  በፀሃይ አታንቃቃን፡፡ ውረድ” ንኩ ዳንሱን ቀጠለ፡፡ “አልወርድም፡ … ከንቲባ አርጉኝና ያኔ እወርዳለሁ፡፡”

አዛውንቱ አሁንም፤ “አያችሁ፡፡ ዘግይታችኋል፡፡ ከዚህ በኋላማ በፍፁም አይወርድም፡፡” አሉ፡፡

ዋናው የፖሊስ አዛዡ ላብ በግንባሩ እየተንቆረቆረና ጫን ጫን እየተነፈሰ “ከንቲባ እናደርግሃለን ብንለውስ” አለና እጁን በአፉ ዙሪያ ደግኖ በጩኸት፡-

“እሺ እንዳልክ ልጄ ውረድማ፡፡ ከንቲባ እናደርግሃለን፡፡ ብቻ ቶሎ ወርደህ ቢሮህን ተረከብ፡፡” አለ፡፡ ንኩ እንደዕብድ እየደነሰ በጩኸት ”እንዲያውም በቃ አልወርድም፡፡ ንክ ከንቲባ አርገው በመረጡ ሰዎች መሃል ምን እሠራለሁ? … አልወርድም በቃ!”

“እናስ ታዲያ ምንድነው የምትፈልገው?”

“ከአሁን በኋላ የምወርደው የካቢኔው አባል ስታደርጉኝ ብቻ ነው፡፡” ከጥቂት ውይይት በኋላ ከታች የተሠበሰቡት ሰዎች በአንድነት ጮክ ብለው

“እንዳልክ በቃ የካቢኔው አባል እናደርግሃለን፡ አሁን ውረድልን ይታይሃል ሰውን ሁሉ እንዴት እንደተቆጣጠርከው፡፡” ንኩ አፍንጫውን በሹፈት አነቃነቀና “ንክ የካቢኔ አባል በሾሙ ሰዎች መሃል መውረድ አልፈልግም፡፡” አላቸው

“ወንድሜ ውረድ እንጂ ለምን ታስቸግራለህ? የካቢኔ አባል አድርገንሃል፤ ሌሎቹ የካቢኔ  አባላትም እየጠበቁህ ነው እና ውረድና ተቀላቀል፡፡”

“ማንን ነው የምታሞኘው? ስወርድልህ ዘብጥያ ልትወረውረኝ አይደል? የመጣው ቢመጣ አልወርድም፡፡” ሽማግሌው በዚህ ጊዜ “እራስህን እንዳታታልል፤ እኒህን ቂሎች እኔ መች አጣሁአቸው? የካቢኔ አባል ከሆንክ በኋላ ለምን ብለህ ትወርዳለህ፡፡” አሉት፡፡

ይሄኔ ንኩ በግልፅ ጮኾ ተናገረ፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስቴር ካላደረጋችሁኝ ራሴን እፈጠፍጣለሁ፡፡” ሽማግሌው “አይወርድም አልኳችሁ” አሉ፡፡ ንኩ ዳንሱን ቀጠለ አሁንም፡፡ ከቆይታ በኋላ ረገጥ ባለ ድምፅ “ንጉስ አርጉኝ አለዚያ ግን እራሴን መፈጥፈጤ ነው!” አዛውንቱ ያሉት እውነት ሆነ፡፡ ስለዚህ ምክር ጠየቋቸው፡፡ “ምን ያስባሉ አባት? ንጉስ እናርገው ይሆን?”

“አሁን ጊዜው አልፏል፡፡ እሺ የሚላችሁን ብቻ ፈፅሙ፡፡ አንዴ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኗልኮ፡፡” አሉ፡፡ “እንዳልክ ይሁን፡፡ ንጉሥ አድርገንሃል፡፡ በቃ ውረድ” አሉ በጩኸት፡፡ ዳንሰኛው ንክ መልሶ በጩኸት “እምቢ አልወርድም!” አለ፡፡ “እና ምን ይሆን የምትፈልገው ንጉስም አረግንህ!”

“አልወርድም፡፡ ንጉሠ ነገስት አርጉኝ አለዚያ እዘላለሁ፡፡”

አሁን ሽማግሌው ለመጠየቅ ዞሩ “እንዳለው ይዘል ይሆን?” ሽማግሌው መዝለሉ እንደማይቀር አረጋገጡላቸው፡፡ “እሺ ተስማምተናል፡፡ ንጉሠ ነገስት አርገንሃል፡፡ በል አሁን ውረድ፡፡”

ንኩ በፍጥነት ምላሽ ሠጠ፡፡ “እኔን የመሠለ ንጉሠ ነገሥት በናንተ አይነት ትርኪምርኪዎች ዘንድ ምን ይሠራል?”

“እህስ ምን ይሆን የምትፈልገው? ንገረንና እንፈፅማለን፡፡ ግን እባክህ ውረድልን?”

“እኔ ንጉሠ ነገስት ነኝ?” ሲል ንኩ ጠየቀ፡፡ “አዎን አንተ ንጉሠ ነገስታችን ነህ” አሉ፡፡ ተሠብሳቢዎቹ ሁሉ በጋራ ከታች፡፡

“እንግዲያውስ ንጉሠ ነገስት ከሆንኩ እኔ ስፈልግ እንጂ የምወርደው እንዲሁ አልወርድም፡፡”

የፖሊስ ሳጅኑ በንዴት ጦፈ፡፡ እንደ እብድ አረገውና “ይፈጥፈጣ ከፈለገ” ሲል አሠበ፡፡ “ባቄላ አለቀ … ምን ቀለለ አሉ፡፡ አንድ ንክ ነው የሚቀንስልን፡፡ ይሄው ነው እውነቱ፡፡ ነገር ግን ኋላ ችግር ያገኘዋል፡፡ … የእሳት አደጋው አዛዥ ወደ አዛውንቱ ዞረና

“እና ምን አድርጉ ብለው ይመክሩናል?” በቃ ይሄ ንክ እስከወዲያኛው ላይወርድ ነው?” ሲል ጠየቃቸው፡ “ይወርዳል” አሉ በርግጠኝነት “እንዴት?”

“እኔ እንዴት እንደማወርደው አሳያችሁአለሁ፡፡”

በዚያ ያለ ሰው ሁሉ አዛውንቱ እንዴት አርገው ንኩን እንደሚያወርዱት ለማየት ቋመጠ፡፡ ሽማግሌው ሰባተኛ ፎቅ ላይ ያለውን ንክ እንዲህ ሲሉ አናገሩት፤

“ግርማዊነትዎም ሆይ! እባክዎ ወደ ስድስተኛው ፎቅ ሊመጡ ይችላሉ?”

ንኩ በቁም ነገር ተሞልቶ “መልካም” አለና በጣሪያው መውጫ አቋርጦ ወደ ስድስተኛው  ፎቅ ደረጃ ወረደና በስድስተኛው ፎቅ መስኮት ወደተሠበሰበ ህዝብ ብቅ ብሎ ታየ፡፡

ሽማግሌው ዳግመኛ ጠየቁ፡፡ “ግርማዊነትዎ፤ አሁንም ወደ አምስተኛው ፎቅ ወደ ላይ ሊወጡልን ይችላሉ?” ንኩ እንደሚችል ተናገረ፡፡ ሁሉም ሰው ተገረመ፡፡ ሽማግሌው አሁንም በአራተኛው ፎቅ ወደ ውጪ በማየት ላይ ለነበረው ንጉሠ ነገስት ንክ፡- “የኔው ተወዳጅ ግርማዊ ንጉሠ ነገስት፤ ወደ ሶስተኛው ፎቅ ሊወጡሉን ይችላሉን” ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ንኩ “በርግጠኝነት” አለ፡፡

አሁን በሦስተኛው ፎቅ መስኮት ወደ ውጪ በመመልከት ላይ ነው፡፡ ጣሪያው  ላይ ሳለ ይደንስ የነበረውን የእብደት ዳንስ አቁሟል፡፡ የእውነተኛ ንጉስ ግርማ ሞገስና መኮሳተር ይታይበታል፡፡

“ክቡርነታቸው ወደ ሁለተኛ ፎቅ ሊመጣልኝ ይችላልን?”

“በሚገባ እንጂ!” ወደ ሁለተኛው ፎቅ ወረደ፡፡

“ክቡርነታቸው ወደ አንደኛ ፎቅ እንዲመጣልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡”

ንኩ ጐዳናው ላይ ብቅ አለ፡፡ ከመንጋው መሃልም ተቀላቀለ፡፡ ቀጥታ ወደ አዛውንቱ ሄደና እጁን በትከሻው ላይ ጣል አድርጎ “አምላኬ ሆይ! ያለጥርጥር አንተም እንደኔ ንክ መሆንህ ተረጋግጧል፡፡ ንክን ሊረዳ የሚችለው ንክ ብቻ ነው፡፡” አለና ወደ ፖሊስ ሳጅኑ ዞሮ ቀጠን ያለች ትዕዛዝ ቢጤ አስተላለፈ፡ “መልካም አሁን እጄን ጠፍራችሁ ወደ እብዶች ቤት ልትወስዱኝ ትችላላችሁ፡፡ … መቼም ንክ እንዴት መያዝ እንዳለበት በቂ ትምህርት ያገኛችሁ ይመስለኛል፡፡” ሲል ጥያቄ አከል አስተያየት ሰነዘረ፡፡ ንኩ እየተወሰደ እያለ ወሬ አዳማቂው በሙሉ አዛውንቱን እንደጉንዳን ከበበና “ለመሆኑ አባት እንዴት ነው ሊያወርዱት የቻሉት?” ሲሉ በየተራ በጥያቄ አጣደፏቸው፡፡ አዛውንቱም በግርምት ራሳቸውን ነቀነቁና “ለአርባ አመታት በፖለቲካ ውስጥ መቆየት እኮ ቀላል  አይደለም፡፡” ብለው እንደመተከዝ አሉና ቀጠሉ፡- “አኔም እግሮቼ ብርቱ በነበሩ ዘመን እላይ መውጣት እችል ነበረ፡፡ እንደዚያው ሁሉ ከጣሪያ ላይ ሊያወርደኝ የሚችል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡”

*   *   *

አዚዝ ኔሲን ቱርካዊ ነው፡፡ የሙሉ ጊዜ ፀሃፊ ለመሆን ሲል የወታደራዊ መኮንነቱን ተወ፡፡ ሥራዎቹ በ1956 እና 1957 በጣሊያን አለምአቀፍ የዋዘኛ ፅሁፎች /Humor/ ውድድር ላይ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

 

ማስታወሻ፡- ከተርጓሚው ይህን አጭር ልብወለድ የተረጎምኩት በቅርቡ ካዛንቺስ መናኸሪያ ሆቴል አጠገብ ዛፍ ላይ ወጥቶ 25 ሚሊዮን ብር ካልተሠጠኝ አልወርድም ላለው ሰው መታሰቢያ ነው፡፡ በኋላ እንዴት እንደወረደ ባላውቅም፡፡

 

 

Read 3751 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 10:44