Saturday, 24 December 2011 09:48

የካዝና ሰባሪው ንስሃ

Written by  ኦ. ሄንሪ
Rate this item
(1 Vote)

(II)

በምህረት ከወህኒ ቤት የወጣው ጂሚ ቫለንታይን፤ በዚያው እለት ነው ወደ ቀድሞው ስራ የተመለሰው። የስራ ባልደረባ የለውም። ሻንጣ ውስጥ በስርአት የተቀመጡት የካዝና መስበሪያ መሳሪያዎቹ ናቸው የጂሚ የስራ ባልደረቦች። ወጣቱ ጂሚ፤ ከእስር በወጣ በሳምንቱ አንድ ባንክ ተዘረፈ። ከሁለት ሳምንት በኋላ በብዙ ኪ.ሜ ርቀት ሌላ ባንክ፤ ቀጥሎ በሌላ ከተማ ሌላ ባንክ ተዘረፈ። ታዋቂው መርማሪ ፖሊስ ቤን ፕራይስ፤ የተዘረፉትን ካዝናዎች አይቷል። የዝርፊያውን ጥበብ ሲያይ፤ የማን ስራ እንደሆነ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም። የጂሚ ቫለንታይን ስራ ነው ብሏል ቤን ፕራይስ። እናም ጂሚን ይዞ ወህኒ ለማስገባት ዝቷል - ብዙ አመት እንዲታሰር።

“አይነኬ” የተባለላቸው የባንክ ካዝናዎች፤ በጂሚ ልዩ ጥበብና በተራቀቁ ልዩ መሳሪያዎቹ እየተበረገዱ ኦና ሆነዋል። ጂሚ ሻንጣውን አንጠልጥሎ ወደ ኢልሞር ከተማ ብቅ ያለውም በሌላ ምክንያት አይደለም። ያሰበውን ሰርቶ፤ ተመልሶ ወደ ሌላ ከተማ ለመብረር ነው! የኢልሞር ባንክ ደጃፍ ላይ አንዲት ውብ ወጣት እስኪያይ ድረስ ሌላ እቅድ አልነበረውም። የባንኩ ባለቤት፤ የሚስተር አዳምስ ልጅ ነች ውቧ አናቤል። በቅፅበት እይታ የጂሚ ቫለንታይን እቅድ እንደ አመድ በነነ። እራሱን ረሳ። ሌላ ሰው ሆነ፤ ራልፍ ስፔንሰር ነኝ በማለት። በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በራሱ ላብና ጥረት፤ በራሱ የቢዝነስ ስራ ንፁህ ገቢ ለማግኘትና ለመኖር ወሰነ። በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በአንድ ከተማ ውስጥ ከሳምንት በላይ ሰክኖ ቆየ፤  ከዚያም በርካታ ሳምንታት፤ እናም ወራት። አሁን፤ የሰርጉ ቀን ተቃርቧል - ለራሱ የሙሽራ ልብስ፤ ለሙሽሪትም ውብ ስጦታ የሚገዛበት ቀን ደርሷል።

ከዚያ በፊት ግን፤ ለልጅነት ጓደኛው ደብዳቤ ለመፃፍ፤ ክፍሉ ውስጥ ቁጭ አለ።

ውድ ቢሊ፡

ረቡእ ማታ በ3 ሰአት፤ ሊትልሮክ ከተማ ወደ ሱሊቫን ቤት እንድትመጣ እፈልጋለሁ። ትንሽ የቆዩ ጥቃቅን ጉዳዮች ስላሉብኝ እንድታስጨርስልኝ ስለፈግኩ ነው። እናም ደግሞ፤ የስራ መሳሪያዎቼን ጠቅልዬ፤ ስጦታ ላበረክትል እፈልጋለሁ። እንደምትደሰትባቸው አውቃለሁ  - የመሳሪያዎቼ ተማሳሳይ ሞደፊክ ለማስቀረፅ ብትሞክር የሁለት መኪና ዋጋ አይበቃህም። ስታያቸው ትደሰታለህ። ሳልነግርህ ቢሊ... የድሮውን ስራኮ አቁሜያለሁ፤ አመት ሆነኝ። ጥሩ የጫማ ቢዝነስ ከፍቻለሁ። በራሴ ላብ መኖር ጀመርኩ እልሃለሁ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ አገባለሁ - እንደሷ አይነት ጥሩ ሴት አለምን ብትዞር አታገኝም። ህይወት ማለት እንደዚህ ነው ቢሊ፤ ትክክለኛው ብቻ እንጂ ሌላ ህይወት የለም። አሁን፤ የሰውን ገንዘብ... አንዲት ሳንቲምም አልነካም፤ ሚሊዮን ቆጥረው ቢሰጡኝም አልነካም። ከሰርጌ በኋላ፤ የጫማ ቢዝነሴን ሸጬ ወደ ምእራብ ራቅ ብዬ እሄዳለሁ። የድሮውን ጣጣ ፈልፍለው እንዳያመጡብኝ ራቅ ማለት ይሻላል። እውነቴን ነው ቢሊ፤ ብታያት መልአክ ነች። ታምነኛለን፤ በኔ ትተማመናለች። ከእንግዲህ፤ የአለም ወርቅና አልማዝ ቢሰበሰብ እንኳ፤ የውንብድና ነገር አልነካም። በል፤ አደራህን፤ ሱሊቫን ቤት እንዳትቀር። መገናኘት አለብን። መሳሪያዎቹን ይዤ እመጣለሁ።

የጥንቱ ጓደኛህ ጂሚ

ጂሚ የሚለውን የድሮ ስሙን ትቶ፤ ራልፍ ስፔንሰር መባል ከጀመረ አመት አልፎታል። ኢልሞር ከተማ ውስጥ፤ ጂሚ የሚለውን ስም የሚያውቅ ሰው የለም - ራልፍ ስፔንሰርን እንጂ። ጂሚ ደብዳቤውን በፃፈበት ሰኞ እለት አመሻሹ ላይ ነው፤ ቤን ፕራይስ ወደ ትንሿ ኢልሞር ከተማ ጎራ ያለው። ትልልቅ የዝርፊያ ውንጀሎችን በመከታተል የሚታወቀው ይሄው መርማሪ ፖሊስ፤ ከባቡር ወርዶ ወደ ከተማዋ በእግሩ ሲያመራ ብዙ ሰው ልብ አላለውም። ያለ ስራ ጊዜውን የሚያሳልፍ ሰው ይመስል፤ ከተማዋን ከዳር እስከ ዳር ሲዞር ውሎ ያመሻል - የሚፈልገውን ነገር እስኪያገኝ ድረስ። የሚፈልገውንም ነገር አግኝቷል። ወሬዎችንም በሙሉ ሰምቷል። ቤን ፕራይስ፤ አሁን ከጫማ መደብር ማዶ ያለችው አንዲት ሱቅ ውስጥ ሆኖ ያያል። የጫማ መደብሩ ውስጥ ያለውን ወጣት... ራልፍ ስፔንሰርን እያየ ነው ቤን ፕራይስ። የባንክ ካዝናዎችን ኦና ሲያደርግ የነበረው ጂሚ፤ ዛሬ ራልፍ ስፔንሰር ሆኗል? ቤን ፕራይስ ማዶው ላይ እንዳተኮረ፤ “ጂሚ፤ ጠቅልለህ የባንክ ቤተሰብ ውስጥ ልትገባ አስበሃላ! የሚስተር አዳምስን ልጅ ልታገባ ነው” አለ ለራሱ - “ልትሞሸር? እንጃ”ጂሚ፤ በማግስቱ ጥዋት፤ ቁርስ የበላው በሚስተር አዳምስ ቤት ነው። ከእጮኛው ከአናቤል ጎን፤ ከአባቷ ሚስተር አዳምስ ፊት ለፊት ተቀምጦ ቁርስ ሲበላ፤  የአናቤል እህትም ነበረች - ከሁለት ሴት ልጆቿ ጋር። ጂሚ፤ ሳይረፍድበት ወደ ሊትልሮክ መሄድ አለበት። ለራሱ የሙሽራ ልብስ፤ ለአናቤል ደግሞ ውብ ስጦታ ለመግዛት ሲሄድ፤ እግረመንገዱንም ከልጅነት ጓደኛው ከቢሊ ጋር ለመገናኘትና “የሙያ መሳሪያዎቹን” ሊያበረክትለት  ቀጠሮ ይዟል - በደብዳቤ። ለአመት ያህል ከትንሿ ከተማ ከኢልሞር ንቅንቅ ብሎ የማያውቀው ጂሚ፤ ዛሬ ወደ ሊትልሮክ ሲሄድ ብዙም አልሰጋም። የድሮ “መተዳደሪያው” እና የባንክ ካዝናዎችን የመስበር “ሙያው”፤ ... ዛሬ ዛሬ “የተረሱ ትዝታዎች” ሆነዋል። ካዝና ከሰበረኮ አመት አልፎታል።ከቁርስ በኋላ፤ ሁሉም አብረው ወጡ - ሚስተር አዳምስ፤ አናቤል፤ ጂሚ እና የአናቤል እህት ከሁለት ሴት ልጆቿ ጋር። ወደ ኢልሞር ባንክ ነው የሚያመሩት። ሚስተር አዳምስ ለባንኩ ገዝተው ያስገቡትን አዲስ ዘመናዊ ካዝና ለማሳየት ጓጉተዋል። ነገር ግን፤ በጂሚ መኖሪያ በኩል ማለፍ ነበረባቸው። እንደገና ከመመለስ ይልቅ፤ አሁኑኑ ሻንጣውን ይዞ፤ በዚያው ወደ ሊትልሮክ ባቡር ለመሳፈር እንዳሰበ ነግሯቸዋል። ጂሚ ወደ ክፍሉ ገብቶ፤ ሻንጣውን አነሳ። ለአመት ያህል ያልተከፈተችው ሻንጣ፤ አቧራ ሸፍኗት የነበረ ቢሆንም፤ ወልውሎ አሳምሯታል። እንደብረት የሚከብደውን ሻንጣ አንጠልጥሎ ከመጣ በኋላ፤ የደስተኛው ቤተሰብ አባላት ተያይዘው ወደ ኢልሞር ባንክ መንገዳቸውን ቀጠሉ። (ጂሚ ያንን ሻንጣ ይዞ ወደ ኢልሞር ባንክ ሲራመድ የመጀመሪያው አይደለም። ከአመት በፊትም ያንኑን ሻንጣ ይዞ ነበር። በኢልሞር ባንክ፣ ካዝና ለመስበር በሙያ የተካኑ እጆችን ይዞ፤ የ”ሙያ” መሳሪያዎችን በሻንጣ አንጠልጥሎ፤ የዛሬ አመት እግሮቹ ኢልሞር ከተማን ሲረግጡ... በዚያው እለት አይኖቹ አናቤልን በማየታቸው የጂሚ አለም ተናወጠች። እጆቹ፤ ከእንግዲህ የጫማ መስሪያ መሳሪያዎችን እንዲጨብጡና በጫማ ቢዝነስ እንዲጠመዱ እዚያው በዚያው የወሰነው ጂሚ፤ በከተማዋ ውስጥ የተከበረ ሰው ለመሆን፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአናቤልን ልብ ለመማረክ ጊዜ አልፈጀበትም። ይሄውና ወራት አልፈው ወራት እየተተኩ፤ እግሮቹ ከአናቤል ቤተሰብ መኖሪያ ቤት፤ አይኖቹም ከአናቤል ላይ የተነቀሉበት ጊዜ የለም።)አብረው እንደመጡ አብረው ወደ ባንኩ ገቡ - ጂሚም ጭምር። ሚስተር አዳምስ፤ የጂሚ አማት ለመሆን የቀራቸው ጊዜኮ ሁለት ሳምንት አይሞላም። እንደ ቤተሰብ አባል የሚታየው ጂሚ፤ የትም ቢሆን ቤተኛ ሆኗል። የባንኩ ሰራተኞች ሁሉ ከጂሚ ጋር ሰላም ለመባባል ይጓጓሉ። በእርግጥ፤ ዛሬ ሻንጣ አንጠልጥሎ ከነቆቡ ሲታይ፤ ተዘዋዋሪ ነጋዴ ይመስላል። አዲሱ ካዝና ወዳለበት አካባቢ ሲደርሱ ነው፤ ጂሚ ሻንጣውን ወለሉ ላይ ያስቀመጠው። ልቧ በፍቅርና በደስታ እየተፍለቀለቀ የምትቅበጠበጠው አናቤል፤ ቆቡን ተቀብላ ራሷ ላይ እያጠለቀች፤ “ስታየኝ ምን እመስላለሁ? ምርጥ ተዟዟሪ ነጋዴ አይወጣኝም?” አለች - ሻንጣውንም ከወለሉ ብድግ እያደረገች። “እህ... እንዴ ሲካበድ! ሻንጣህን በወርቅ ሞልተኸዋል እንዴ?”“መአት የጫማ ብረታብረት...” አለ ጂሚ በእርጋታ፤ “ለፋብሪካው የሚመለስ ነው። ለመላኪያ ገንዘብ ከማወጣ ራሴ ልውድላቸው። ሃይለኛ ቆጣቢ እየሆንኩ ነው”ጂሚና አናቤል፤ በጨዋታና በፍቅር ሲጠመዱ፤ ያየና የሰማ የለም። የሌሎቹ ትኩረት አዲሱ ካዝና ላይ ነው። “አይነኬ” ከሚል የማስተማመኛ ዋስትና ጋር በተገዛው ካዝና ኩራት የተሰማቸው ሚስተር አዳምስ፤ ሰው ሁሉ ቢያይላቸውና ቢያደንቅላቸው ደስ ይላቸዋል። በካዝናው በር ላይ፤ ከእጀታው አጠገብ በቁጥሮች የተከበበ የሚስጥር ቁልፍ ይታያል - የሚስጥር መክፈቻ ቁጥሮች የሚስተካከሉበት ነው። ቁጥሮቹ ከተስተካከለ በኋላ በሩ ተዘግቶ እጀታው አንዴ ሲዞር፤ ወፋፍራም የንጥር ብረት ዘንጎች በሩን ያለጭላንጭል ይጠረቅሙታል። በቃ፤ ትክክለኛዎቹን የሚስጥር ቁጥሮች በሚያውቅ ሰው ካልሆነ በቀር፤ በሩ አይከፈትም። “አይነኬ አስተማማኝ ካዝና” የተባለውስ ለዚህ አይደል? የድሮው ጂሚ፤ በዚህ ስያሜ ላይስማማ ይችላል። ሚስተር አዳምስ ይህን አያውቁም። በኩራትና በደስታ፤ የካዝናውን አሰራር ያስረዳሉ። ጂሚ በጣም የተመሰጠ እንዳይመስል እየተጠነቀቀ፤ ማብራሪውን በአክብሮት ይሰማል - ከጎኑ አናቤልን ይዞ። የአናቤል እህት ልጆች፤ የዘጠኝ አመቷ ሜይ እና የአምስት አመቷ አጋታ... እንደመስተዋት በሚያንፀባርቀው የካዝናው ልሙጥነትና ጠንካራነት ተደስተው ይቦርቃሉ።መርማሪው ፓሊስ ቤን ፕራይስ በዝግታ በባንኩ ዋና በር በኩል ሲገባ፤ እነጂሚ አላዩትም። የባንኩ ሰራተኞች በቅልጥፍና ሊያስተናግዱት ቢሞክሩም፤ ቤን ፕራይስ “አንድ የማውቀው ሰው እየጠበቅኩ ነው” አላቸው - ጠርዙ ላይ ክርኑን አስደግፎ።በዚህ መሃል ነው፤ የአንዲት ሴት እሪታ የተሰማው። ከዚያ የሁለት ሴት እሪታ... ከዚያም ጫጫታና ትርምስ። የካዝናውን የሚስጥር ቁልፍ እየነካኩ በእጀታው ሲጫወቱ ከነበሩት ሁለቱ ህፃናት መካከል አንዷ የለችም። ታናሽየዋ አጋታ ካዝናው ውስጥ ስትገባ፤ የ9 አመት እህቷ ቀልድና ጨዋታ መስሏት በሩን ዘግታ እጀታውን አዙራዋለች፤ የሚስጥር ቁልፉን እየነካካች።ሽማግሌው ሚስተር አዳምስ ወደ ካዝናው ተንደርድረው እጀታውን ሲያንገጫግጩ፤ በሩ እንደማይከፈት ገብቷቸዋል። “ሊከፈት አይችልም። የሚስጥር ቁጥሮቹ ተነካክተው፤ የመክፈቻው ኮድ አይታወቅም” ... በጭንቀት አጉረመረሙ። ካዝናው ውስጥ የተዘጋባት ሚስኪን ህፃን፤ በፍርሃት እሪ እያለች ቢሆንም፤ ካዝናው ጥርቅም ብሎ ስለተዘጋ፤ ድምጿ እንደ ሩቅ የህልም ድምፅ ሆኗል።“ወይኔ ልጄ” አለች የአናቤል እህት፤ “ወይኔ ልጄ፤ የኔ እንቁ... በፍርሃት ልትሞትብኝ ነው። በሩን ክፈቱላት። ካዝናውን ስበሩት። ምን ቆማችሁ ታያላችሁ?” አለች ሚስተር አዳምስንና ጂሚን አፈራርቃ እየተለማመጠች፤ “የሆነ ነገር አድርጉ”“ይህን መክፈት የሚችል ሰው ከየት ይገኛል?” መናገር ከብዷቸዋል ሚስተር አዳምስ። ድምፃቸው ይርገበገባል፤ “የፈጣሪ ያለህ” አሉ ሚስተር አዳምስ ወደ ጂሚ ዞረው፤ “ምን ይሻለናል? ህፃኗ እንዴት ትችለዋለች? አየር ማግኘት አትችልም። በዚያ ላይ በፍርሃት ታብዳለች”የአናቤል እህት (የህፃኗ እናት) ራሷን መቆጣጠር ትታለች። የካዝናውን በር በጭንቀት ትደበድባለች። አንዱ ደግሞ፤ ካዝናውን በፈንጂ... የሚል ያበደ ሃሳብ ተናግሯል። ግራ የተጋባችው አናቤል ወደ ጂሚ ዞራ አየችው፤ ትልልቅ አይኖቿ በጭንቀት ተረብሸዋል፤ ነገር ግን ገና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አላረፈባቸውም። የምታፈቅረውና የምታመልከው እጮኛዋ ከጎኗ ነው። ምንም ነገር ያቅተዋል ብላ አታስብም። አፍቃሪ ሴቶች እንዲህ ናቸው።“የኔ ውድ፤ የሆነ ነገር ማድረግ አትችልም?... ሞክር፤ የሆነ ነገር ሞክር” ... አይን አይኑን ስታየው፤ እሱም አያት። ያልተለመደች ትንሽ ፈገግታ ፊቱ ላይ ብልጭ ብላለች።“አናቤል” አላት በእርጋታ፤ “ደረትሽ ላይ ያደረግሻትን የፅጌረዳ አበባ ስጪኝ፤ እባክሽ”የሰማችው ነገር እውነት ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባትሆንም፤ እምቡጥ ፅጌረዳዋን ከልብሷ ነቅላ መዳፉ ላይ አስቀመጠችለት። ጂሚ (ራልፍ ስፔንሰር) አበባውን የሸሚዝ ኪሱ ውስጥ እንዳስገባ ኮቱን አውልቆ ወረወረው፤ የሸሚዙን እጅጌ መጠቅለል ጀመረ። በቃ፤ ከእንግዲህ ራልፍ ስፔንሰር መሆኑ ቀርቶ፤ ጂሚ ቫለንታይን ቦታውን ሊረከብ ነው።“ከካዝናው ገለል በሉ። ሁላችሁም” አለ በፈጣን የትእዛዝ አነጋገር። ወለል ላይ አስቀምጦት የነበረውን ሻንጣ አንስቶ ጠረጴዛ ላይ አደረገውና ዝርግትግት አድርጎ ከፈተው። እነዚያ ልዩና የተራቀቁ የዝርፊያ መሳሪያዎች በመልክ መልካቸው ተደርድረዋል። ጂሚ አንዴ ስራ ሲጀምር፤ አካባቢውን ይረሳል። አጠገቡ ሌሎች ሰዎች ስለመኖራቸው ጨርሶ የረሳ ይመስላል። የሚያስፈልጉትን መሳሪያዎች ከሻንጣው ለይቶ እያወጣ በስርአት አስቀመጣቸው። ድሮ ካዝናዎችን ሲሰብር በነበረበት ጊዜ እንደሚያደርገው፤ አሁንም በለሆሳስ እያፏጨ ነው። ሌሎቹ ሰዎች እዚያው በቆሙበት ቦታ ደንዝዘው፤ አንዲት ቃል ትንፍሽ ሳይሉ ያዩታል።ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፤ የጂሚ ልዩ ፈጠራ የሆነችው የመሰርሰሪያ መሳሪያ፤ በጠንካራ ንጥር ብረት የተሰራውን ካዝና እየቦረቦረች መግባት ጀምራለች። ቁልፍ የሚነድልበት መብሻ፤ መፈንቀያ ሽብልቅ፤ መጭመቂያና መጎተቻ፤ ማነጣጠሪያና ተወርዋሪ መሳሪያዎችን በየተራ እያፈራረቀ ይጠቀማል። ጂሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካዝና በመስበር የሚስተካከልው እንደሌለ ያውቃል፤ ድሮም ይኮራበት ነበር። ዛሬ ደግሞ፤ የራሱን ሪከርድ ሰበረ። በ10 ደቂቃ ውስጥ የካዝናው በር ተበረገደ።ህፃኗ አጋታ እየተብረከረከችም ቢሆን፤ የእናቷ እቅፍ ውስጥ በደህና ገባች።ጂሚ ቫለንታይን፤ ኮቱን አጥልቆ፤ ማንንም ሳያናግር ወደ ባንኩ ዋና በር አመራ - ከባንኩ ወጥቶ ለመሄድ። “ራልፍ!” የሚል ጣፋጭ የሴት ድምፅ የሰመመን ያህል ተሰምቶታል። ግን ለመቆም ወይም ወደ ኋላ ለመዞር አላመነታም። ከባንኩ ለመውጣት በሩ ላይ ሲደርስ፤ ከፊት ለፊቱ ረዥሙ ሰውዬ ተገትሯል። መርማሪው ፖሊስ ቤን ፕራይስ ነው። ጂሚ ቫለንታይን ፊት ላይ የምትታየው ትንሽ ፈገግታ አሁንም አልጠፋችም።“ታዲያስ ቤን” አለ ጂሚ፤ “በመጨረሻ ሆነልህና አገኘኸኝ? ይሁና። እንሂድ። ካሁን በኋላ፤ ምንም ቢመጣ ለውጥ የለውም”የቤን ፕራይስ ምላሽ ጨርሶ ያልተጠበቀ ነው። የወትሮው መርማሪ ፖሊስ አልመስል ብሏል።“ራልፍ ስፔንሰር፤ የምንተዋወቅ አይመስለኝም። መልካም ጉዞ” አለ መርማሪው ፖሊስ ቤን ፕራይስ። እናም ፊቱን አዙሮ በታችኛው መንገድ አቅጣጫ ብቻውን ሄደ።

 

 

Read 4021 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 16:04