Saturday, 10 December 2011 09:51

ሰውየው

Written by  ቦንቦሊኖ Bombolino bob@yahoo.com
Rate this item
(0 votes)

ከእኩለ ሌሊት አንስቶ ምድርን ይረግጣት የጀመረው ኃይለኛ ዝናብ የጥፋት ውሀን ያስታውሳል፡፡ ሌላው ቢቀር ነግቶ እስኪረፍድ እንኳ አላባራም ነበር፡፡ ለወትሮው ሠዎች የሚተራመሱበት አውራ ጎዳና ግራና ቀኝ ካሉት የውሀ መውረጃ ቦዮች ገንፍሎ የወጣው ቀይ ጎርፍ ይገማሸርበታል፡፡ ነጫጭ ጋቢና ነጠላ የደረቡ መንገደኞች ጎርፉን በመሸሽ ጥግ ጥጉን ይዘው ይጓዛሉ፡፡ ቀሚሶች ጭቃ ሽሽት ወደ ላይ ተንጠልጥለው ቀይ፣ ጠይምና ጥቁር ባቶች ተጋልጠው ላያቸው ላይ ትንሽ የጭቃ ነጠብጣብ …

ወንዶች ሱሪያቸውን ካልሲ ውስጥ ወሽቀው ወደ ቤት ለመከተት ይፈጥናሉ፡፡ መንደሯን በጠቅላላው ቅዝቃዜና ፀጥታ ወርሷታል፡፡ መሬት ረስርሳለች፡፡ ይህን ሁኔታ የተመለከተ የፀሀይን ዳግመኛ መምጣት ይጠራጠራል፡፡ 
በአማኝ እርጋታና ኩራት ከሚተመው ምዕመን መሀል አንድ ጉልምስናው ከኋላ ራቅ ብሎ እየሸኘው ሽምግልና ደግም ቀረብ ብሎ “ቤት ለእርጅና” እያለው ያለ የሽግግር ሠው የያዛትን ቄንጠኛ ከዘራ፣ በስልት ወደ ፊት እያነዘረ በተለየ ፍጥነት ሲገሰግስ ታየ፡፡
ከፊት ለፊቱ የሚመጡ ሠዎች ሠላምታ ሊሰጡት ሲመለከቱት ሁኔታው ግራ እያጋባቸው አንዳንዶች ተኮሳትረው ሌሎች ስቀው፣ ብዙዎች ከንፈራቸውን አንሸራመው ያልፉታል፡፡ እሱ ግን ማንንም አይመለከትም፡፡ ከራሱ ጋር እያወራ በመሀል እየሳቀ ደግም ኮስተር እያለ ጭንቅላቱን በግርምት እየወዘወዘ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡
ጥቂት ከተጓዘ በኋላ ከዋናው መንገድ በስተግራ ታጥፎ ስስ የድንጋይ ንጣፍ በተነጠፈባት ዳገት ብዙም ሳይጓዝ፣ ከአንድ የቆርቆሮ በር ፊት ለፊት ቆሞ ማንኳኳት ጀመረ፡፡ ለመድገም እድል ይሁን ድካም ሳያገኘው በሩ በአንዲት መልከ-መልካም ልጅ እግር ተከፈተ፡፡
ሠውየውን ስትመለከት በመሽቆጥቆጥ ሰላምታ አቀረበች፡፡ መልስ ሳይሰጥ አልፏት ገባ፡፡ በርካታ ቤቶች የተገጠገጡበትን ግቢ ከላይ ወደ ታች እየተዘዋወረ ተመለከተ፡፡ ጥቁሩ ውሻ ጭራውን እየቆላ በሄደበት ይከተለዋል፡፡ በጫማው የተሸከመውን ጭቃ ሳሩ ላይ ከጠራረገ በኋላ በሩ ገርበብ ብሎ ወደ ተከፈተ አንድ ቤት አመራ፡፡
ወደ ውስጥ ሲዘልቅ ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ከውጪው የተለየ ነው፡፡ ቤተ-መቅደሱ በልዩ እጣን ሲታጠን እንደነበረው ሁሉ የቤቱ አየር በሚወደው የሉባንጃ እጣን ሽታ ተሞልቷል፡፡ ሚስትየው ሲኒዎቿን አደራጅታ ቡና በመቁላት ላይ ነበረች፡፡
መሀን መሆኑን እስኪረዳ “ዘረ ቢስ” እያለ ሶስት ሚስቶችን ቀያይሯል፡፡ በኋላ የችግሩን ምንጭ በማወቁ በዚህችኛዋ ረግቶ ተቀምጧል፡፡ የተከናነበውን ነጠላ ጋቢ እያወለቀ “አቤት ሠው ለሠው ሞት አነሠው አለ ሰው በቀበሮ አስመስሎ፡፡ ይሄ ንግግር እውነትነቱ ዛሬ ነው ይበልጥ ጎልቴ የታየኝ” ይህን ተናግሮ ደረት ኪሱ ውስጥ የነበረውን ፍካሬ ኢየሱስ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው፡፡
ልጁ የምትመስለው ሚስቱ፣ ነጠላ ጋቢውንና ፍካሬ ኢየሱስን ይዛ ወደ ውስጠኛዋ የቤቱ ክፍል ተሠወረች፡፡ በእድሜ ከአባቷ የሚስተካከለውን ሰው በማግባቷ ኑሮዋ ከሚስት እመቤትነት ይልቅ ሠራተኝነቱ ያመዝናል፡፡ “ምነው ቤተ-ክርስቲያን አይደለም እንዴ ቆይተው የመጡት… ተረቱን እዚህ ምን ዶለው?” ይህን እየጠየቀች ከስኒው በስተጀርባ ተመልሳ ተሰየመች፡፡
ጭንቅላቱን በይገርማል እየወዘወዘ “ታውቂያለሽ ውዷ ባለቤቴ፤ በዚህ የሰንበት ማለዳ ጆሮዬ እጅግ አስከፊ ነገር ነው የሰማው፤ ምነው እንደው ጆሮ መልካሙን ነገር ነጥሎ ማድመጥ ቢችል? የለም እንደውም ምናለበት ለጆሮም የሚመች ነገር ቢሠራ፡፡ ለምን ብትይኝ ወሬ ሁሉ የተሰራና የሚሰራ ነገር ብቻ ነው” ይህን ተናግሮ የጫማዎቹን ክሮች አላልቶ ሶፋው ላይ ተመቻችቶ ተቀመጠ፡፡
ለወሬው የጓጓችው ሚስት “በታቦሯ ማርያም፤ ለቅዳሴ ወጥተው ምን ጉድ ነው ሰምተው የመጡት?” ከቆላችው ቡና ውስጥ ጥሬ ጥሬውን እየለቀመች ትወረውራለች፡፡
በፈላስፋ ትካዜ መሬቱን ሲመለከት ከቆየ በኋላ፣ ፊት ለፊት እየተመለከተ “ታውቂያለሽ ውዷ ባለቤቴ፤ የፈጣሪን ቃል እሰማለሁ ብዬ ከራሴ ጋር ቀጠሮ የያዝኩት ትናንት ማታ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ይህን ቀጠሮዬን ለማንም ሰው ባላወራም ከአጅሬ ሰይጣን ጆሮ ግን አላመለጠም፡፡”
ለአፍታ ቡና መውቀጧን በመግታት “እና ይሄን ከማለዳው ትንግርት ጋር ምን ያገናኘዋል?” በጥያቄዋ ድምፀት ውስጥ መሰላቸቷ አብሮ ይጮሀል፡፡
ወሬውን በማቋረጧ ክፉኛ የተናደደው ባል “ምን ነካሽ ሴትዮ፤ ነገሩን ከስር መሰረቱ ነው ማወቅ ያለብሽ፤ አለበለዚያ የዚህ ነገር ተዓምራቱ አይገባሽም” ካለ በኋላ ሁሌ እንደሚያደርገው ለአፍታ ዝም አለ፡፡ ወዲያውም ፊቱ በትውስታዊ ፈገግታ በራና “ትናንት ማታ ያለመድኩትና ለጆሮዬ አዲስ የሆነ ኮቴ ነበር ግቢ ውስጥ የተሰማኝ፤ አየሽ …” ብሎ ሊቀጥል ሲል ቡናዋን ጀበና ውስጥ በመክተት ላይ የነበረችው ሚስት በግማሽ ልቧ “ያው አራሷን ለመጠየቅ የመጣ ዘመድ ይሆናል” አለች፡፡
ፍላጎቷ እሱን አግዛ ወደ ዋናው ነጥብ ማድረስ ቢሆንም እንዳጣጣለችው ግን አልገባትም፡፡ ንዴቱን ዋጥ አድርጎ አስተያየቷን በዝምታ አለፈው፡፡ ንግግሩን በመቀጠልም “እውነቴን ነው መጠርጠር ነበረብኝ፤ ምክንያቱም ያልጠረጠረ ምስጢርም ሆነ ጠላት የለውም፤ በግድ የለሽነቴ ይኸው ዛሬ ዋጋዬን አገኘሁኝ” እሱ እንዲህ እያወራት ሚስትየው ጢሱ የሚትጎለጎል በቅቤ ያበደ ትኩስ ፍርፍር አቀረበች፡፡ እሱ ግን ከምግቡ ይልቅ አትኩሮቱ በጀመረው ወግ ላይ አዘመነ፡፡ ወሬውን በመቀጠልም:-
“እንዳልኩሽ ከራሴ ጋር በያዝኩት ቀጠሮ፣ ግን ደግሞ ሰይጣንም በጉልበቱ ባወቀብኝ እቅዴ መሰረት በጠዋት ተነስቼ ወደ ቤተ-ክርስቲያን አመራሁ፤ ለአፍታ መቀመጥ ሣያምረኝ ቆሜ እያስቀደስኩ … የሚገርም እኮ ነው በቁጥር ከምዕመኑ የሚስተካከለው ለማኝ መች ያፈናፍንሻል፡፡ ቢሆንም ግን በፅናት ቆሜ እስከመጨረሻው አስቀደስኩ፡፡ በወቅቱ የከነከነኝ አንድ ነገር ቢኖር ግን በሰንበት ቅዳሴ ላይ ቀርተው የማያውቁት የኛ ሰፈሩ ቄስ አለመኖራቸው ነበር”
“አባ ዳዊት? የንስሀ አባትዎ?” አለች ሚስት ግራ በመጋባት፡፡ ለወትሮው ስለሳቸው አውርቶ የማይጠግበው ባሏ፤ ስማቸውን መዘንጋቱ ተዓምር ሆነባት፡፡
ለወሬው ውበት ይመስላል ጉሮሮውን ካፀዳ በኋላ “ስም ያለ ስራ ተሰጥቶ ያለ ወንጀል የሚገፈፍ ነው የሚል ነገር በራዲዮን ሰምቼ ትክክል ነው ብዬ አምኜ ነበር፤ አሁን እንደገባኝ ግን በስራ ተሰጥቶ በወንጀል ይገፈፋል፡፡ ቀድሞ ከሹማምንት በችሮታ ያገኙትን ያን የተንጣለለ ግቢ፣ ደርግ ቆርሶ ለአንድ ቤት አልባ ከሠጠው በኋላ ስርዓቱ ሳይሆን ሰውየው በግሉ የቀማቸው ይመስል በተገኙበት ሁሉ መለኮታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው፣ ሠውየውን ከማህበራዊ ህይወት ለመነጠል ሲሞክሩ ኖሩ፡፡”
አቦል ቡናውን አጠገቡ ካስቀመጠችለት በኋላ ተመልሳ የሚለውን ለመስማት መጠባበቅ ያዘች፡፡ ከቡናው ፉት ብሎ በምስጋና አይን ከተመለከታት በኋላ ቀጥሎ “ሁለት መጎናፀፊያ ያለው አንዱን ይስጥ ብለው ሲያስተምሩን የኖሩ ሰውዬ፣ ያን ፈረስ የሚያስጋልብ ቦታ ወደ ኋላ ትተው፣ የሰውን መሬት ሲጋፉና ይህም አልበቃ ብሎ ዱላ ሲማዘዙ ማየት እንደምን ያለ እርግማን ነው?” ብሎ አማተበ፡፡
ከድንጋጤዋ ብዛት በሁለት እጆቿ ጭንቅላቷን ይዛ አንዳች ጥፋት ያጠፋ ይመስል ባሏ ላይ አፈጠጠችበት “እኔ በፍፁም ይህንን ማመን አልችልም፤ እንዲህ ያለውን ርካሽ ተግባርማ አባ ዳዊት አይፈፅሙትም፣ ከፅናታቸው የተነሳ ከሠይጣን የተላከባቸው ምቀኛ ያስወራባቸው ወሬ ነው” በንዴት ተርገፈገፈች፡፡
ለትንሽ ጊዜ በትዝብት ከተመለከታት በኋላ “እኔም እንዳንቺ ተንቀሳቃሽ ሰማዕት አድርጌ ስቆጥራቸው ኖሬያለሁ፤ ይሄ ምስኪን ጎረቤታቸውም አጥሩን በፍልጥ ለማጠር የተነሳው የዚህን ወራዳ ዳርዳርታ በመገንዘቡ ነው፡፡ የቀድሞውን የሠንሠል አጥር አፈር እየጫኑበት ወደሱ ግቢ አስተኝተውታል፡፡ እናም ፀቡ የተነሳው ሠውየው ሠንሰሉን መንጥሮ ቋሚውን የሰንሰሉ ስር የተነቀለበት ቦታ ሊያቆም ሲል ወደ ውስጥ እልፍ ካላልክ ብለው ክርክር በመግጠማቸው ነው፤ ከሁሉ ይበልጥ የገረመኝ ግን ይሄ ጉዳይ ከሰንበት የቅዳሜ ተራቸው በልጦባቸው መቅረታቸው ነው፡፡”
የቀረበለትን ሁለተኛ ቡና እየጠጣ በዝምታ ተዋጠ፡፡ ሚስት ይህን የይምሰል ወሬ በዚህ ጠዋት ከማን እንደ ሰማውና “ምን ያህል እውነትነት ይኖረው ይሆን?” እያለች ስታብሰለስል የባሏ ድምፅ ከሀሳቧ መለሳት፡፡ “ከሁሉ በላይ እኔን የሚያንገበግበኝ ግን የዚህን ወራዳ ቃል አምኜ ሀጢያቴን ለሱ መናዘዜ ነው፤ በግዜው ልክ መንግስተ ሰማያት እንዳለ ፃድቅ በኩራት ያዳምጠኝ ነበር፤ እኔ ግን በዘመኔ የሱን ያህል ሀጢያት የሰራሁ አይመስለኝም” ይህን ተናግሮ ምን ያህል ጊዜ ለንስሃ ቤታቸው እንደተመላለሰ ለማስታወስ ሞከረ፡፡
ወሬው በፍፁም፤ ያልተዋጠላት ሚስት “ኧረ ጡር አይናገሩ! ሰው በምቀኝነት በሰው ላይ ስንት ነገር ያወራል፤ ነግ በኔ ማለት ደግ ነው፤ ምነው የዚህን ሰፈር ሰው ፀባይ እንደማያውቁት ሆኑሳ” አለች፡፡
የአምላክ መንፈስ በነቢይ ላይ እንደሆነው፣ የወቀሳ አባዜም በዚህ ሰው ላይ ነበርና እጆቹን በማጣጣል አወናጭፎ “ኤዲያ እኔም እንዳንቺ ምድራዊ መልዓክ አድርጌ ስቆጥራቸው ኖሬያለሁ፤ አሁን ይኸው ግዜው ደርሶ በካባቸዉ የሸሸጉት ግብራቸዉ ተጋለጠ፡፡ ሰውረን ከመዓቱ! እሽ አሁን ይሄ ምን ተብሎ ይወራል? እኝህ መቅደሱን ዕለት በዕለት የሚረግጡ ሰው፤ ቅዱስ በሆነው ሰው ሳይሆን አምላክ ራሱ ዕውቅና በሰጠው በእንዲህ ያለ የተባረከ ቀን ይህን የመሰለ ኩነኔ ይሰራሉ? እውነቴን ነው ከዚህ ወዲያ እሳቸው የምድርን ትሩፋት መፈለግ አልነበረባቸውም፡፡”
“ኧረ በቃ አሁን ይተውት! ኋላ ደህና የተላቀቁት ራስ ምታትዎ ይነሳብዎና ይሰቃያሉ፡፡ ሁሉም እንደ የስራዉ ፍርዱን ከላይ ያገኘዋል” አለች አይኖቿን የፈጣሪ መኖሪያ ወደ ሆነው ከፍታ እያንጋጠጠች፡፡
ሚስቱ ስለጤንነቱ በማሰቧ ቢደሰትም አሁንም ግን የማውራት ፍላጎት ይንጠዋል፡፡ “እንዴት ይህን ጉድ እየሰማሁ ዝም ማለት ይቻለኛል? አሁን እንደሆነ ወሬው እንደ ሰደድ እሳት እየተሰራጨ ነው፤ ታዲያ ማን ነው ከእንግዲሕ የዚህን ሰውዬ መለኮታዊ ምክርና ቡራኬ አምኖ የሚቀበለው?” እሺ ተይው የሳቸውስ ይቅር “ለሀጥዓን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል” አሉ እስቲ ሌሎቹንስ በዚህ ርካሽ ሰውየው አይን ከመታየት ምን ይከልላቸዋል?፡፡” በንግግሩ አንዳንዴ ከራሱ ጋር ሲለው ከሷ ጋር የሚያወራ ይመስል ነበር፡፡
በየጊዜው የሚፈጠሩ ክስተቶችን እንደ አስፈላጊነቱ ጠምዝዞ ራሱን ማካተት እንደሚወድ የምታውቀው ሚስት “ይኸው እኮ እሱ የሠራው እርሶንም በዚህ ማለዳ እየረበሾት እኮ! ነው፤ ለርሶስ ቢሆን ተረፈ ማለት አይደለ?” ስትል ከፃድቃን መደበችው፡፡
“ተይኝ እባክሽ አውርቼው ቢወጣልኝ ይሻላል! ተዓምር እኮ ነው እንደው ማን ይሙት ይህ ሠፊ መሬት ለዚህ ተስፋ ቢስ ህዝብ አንሶት ነው? እኔን የገባኝ አንድ ነገር አለ፤ አዎ መሬት ያነሰው በመሬት ላይና በአጠቃቀም ሳይሆን በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡
አንዳንዴማ ውስጤ ያለውና ጊዜው ያለፈበት መንፈሴ ሲነግረኝ የሰው ልጅ መገኛ ከመሬት እንደሆነ መጥፊያውም በእሱ ነው ይለኛል፡፡ አንዴ ዋልድባ በሄድኩበት ጊዜ አንድ መምህር “የሠው ልጆች ወደ ምድር ለፈተና ነው የመጣነው፤ ምንም የሚጨበጥ ነገር ይዘን አልመጣንም፤ ይዘንም አንሄድም ምድራዊ ብልፅግናም ለብዙዎች የዘላለማዊነት መሰናከያ ነች” ነበር ያለው፡፡ ሚስትየው እሱን ለማስረዳት መሞከር ዋጋ ቢስ ልፋት መሆኑን በመረዳት ይመስላል ዝምታን መርጣለች፡፡ አንዳንዴም እራሷን በድጋፍ ትነቀንቃለች፡፡ አንዳንዴም በራሷ ሀሳብ ጭልጥ ብላ ትነጉዳለች፡፡ በሀሳብ የተዋጠውን የሚስቱን ትንሽ ፊት፣ አንገቱን ዘንበል አድርጎ በሀዘኔታ ካስተዋለ በኋላ ንቀት ባዘለ ድምፅ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ “አንቺማ ምን ታውቂያለሽ… የከተማዋ ግማሽ ህዝብ በቤት ችግር እንዴት እንደሚሰቃይ፣ መጠለያ ማግኘት ከዕድለኝነት ጋር እየተቆራኘ መምጣቱ ለአንቺ አይታይሽም … ውዷ ባለቤቴ፤ በአንቺ እምላለሁ የሰው ልጆች ለኑሯቸው የሚበቃቸውን መጠኑን ዘንግተውታል፡፡”
ደጉ አብርሃም ያኔ አለም ሰፊ ሰዎቿም ቅን ሆነው ሳለ እግዚአብሔር “ዘርህን እንደ ባህር ዳር አሸዋ አበዛዋለሁ” ሲለው ከመቀፅበት አምኗል፡፡ በማመኑም ውስጥ ደስታው አብሮት ነበር፡፡
አየሽ ውዷ ባለቤቴ፤ ደስታው እንዳለ ሆኖ አምላክ በሁሉን ቻይነቱ መሬትና ሰውን እንዲያብቃቃ ቢጠይቅ ኖሮ ይህም እንደ ፅድቅ ሆኖ በተቆጠረለት ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሰዎች ለኩርማን መሬት ሲተላለቁ ቢመለከት ምን ይል ነበር? ልሳኑስ በየትኛው ቃል ይከፈት ይሆን?” በሀዘኔታ ራሱን ግራና ቀኝ ወዘወዘ፡፡ ሚስትየው ቀበል አድርጋ “እሱስ እውነትዎን ነው፤ አሁን በቴሌቪዥን የምናየው ጦርነትና እልቂት ያው በመሬት የተነሳ ነው አላሉም? ኧረ እንደውም ዘመን የፈጀ ነው ይባላል” ባቀረበችው ሀሳብ ኩራት ተሰማት፡፡
በሀሳቧ በመስማማት ራሱን ከነቀነቀም በኋላ “እስራኤልና ፍልስጤምን ማለትሽ ነው? ልክ ነው እሱማ ትውልድ የተፈራረቀበት ክስተት ነው፤ እግዚአብሔር በሚወደው ሰው ላይ መከራ እንዲበዛበት በአይሁዶች ላይም ስቃይ ስደትና ጭፍጨፋ ደርሶባቸዋል፡፡ በምህረቱ የማይረሳ አምላክ ፊቱን መልሶላቸው ዛሬ ደግም ተገቢ ቦታቸውን አግኝተዋል፤ ሆኖም ይህን ክብራቸውንና ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ልዕልና መቀበል ያልተዋጠላቸዉ አሁንም ድረስ ቢተናኮሏትም አፀፋዋ ግን እጅግ የከፋ ነው፡፡ በገባላቸው ቃል ኪዳን መሰረትም የእስራኤል አምላክ ህዝቦቹን ከእንግዲህ ለማንም አሳልፎ አይሠጣቸውም እና ውዴ ጉዳዩ ከመሬትም ትንሽ ከፍ ያለ ነው” በማለት በረጅሙ ከተነፈሰ በኋላ “ውዷ ባለቤቴ፤ ዛሬ በጣም አዝኛለሁ፤ ማን ያውቃል ምናልባትም ይሄ ሀዘን ከውስጤ አይወጣልኝ ይሆናል” ፊቱ በሀዘን እንደተሞላ ከመቀመጫው ተነስቶ “ልግባና ትንሽ ልረፍ” ብሏት ወደ ውስጥ ገባ፡፡
ቡና ያፈላችበትን ስኒ በማጣጠብ ላይ ሳለች ከመኝታ ቤት ተመልሶ በመምጣት “ወይ ጉድ ረስቼዋለሁ እኮ! የቤት ኪራዩ ወር ትላንት አይደለም እንዴ ያለፈው? በቃ እኔ ከረሳሁ አንቺ ጉዳይሽ አይደለም ማለት ነው? በይ ቶሎ ይዘሽልኝ ነይ” አላት፡፡
በተቀመጠችበት ሽቅብ እየተመለከተችው “ውይ ጨዋታ ይዞን እኮ ረሳሁት! ጠዋት እኮ የሴትየዋ ባል መጥቶ ያው ሚስቱ አራስ በመሆኗ ገንዘብ ስላጠራቸው ለትንሽ ቀን እንድታገሳቸዉ ነግሮኝ እሺ ብየዋለሁ” አለች፡፡
ንግግሯን ተከትሎ ፊቱ በንዴት ሲጠቁር ተመለከተችው፡፡ ትላልቅ አይኖቹ የሚተፉትን የቁጣ እሳት ፈርታ አይኖቿን አሸሸች፡፡ “በህይወቴ የሚያስጠላኝ ነገር ይሄ ብቻ ነው፤ ይሄን ቤት በግቢው አስተማማኝነትና ውበት ስንት ሰው እንደሚቋምጥለት አያውቅም!
ቀንሼ ያከራየሁት ደግ የሰራሁ መስሎኝ እንጂ ሰው ጠፎቶ መሰለው… ደግሞ ስለወለደች ይላል፤ ማን የማይወልድ አይቷል!” ንግግሩን ሳይጨርስ ሚስትየው ከቤት ወጥታለች፡፡

 

Read 3803 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:55