Saturday, 10 December 2011 09:50

ጨረታ

Written by  ጋጋኖ
Rate this item
(0 votes)

የሞባይሉ ጥሪ ከአስደሳች እንቅልፉ ቀሰቀሰው፡፡ “የማን ሰዓት አልባ ነው በዚህ ሰዓት የሚደውለው?” እያጉረመረመ ስልኩን አነሣው፡፡  
“በጣም ይቅርታ ለአስቸኳይ ጉዳይ ስለሆነ ነው የደወልኩት፤ በጠዋት የተለመደውን አገልግሎትህን ፈልጌ ነው፡፡”
የሚያውቀውን ድምፅ ስለሰማ ፊቱ ፈካ፡፡ ከብዙ ደንበኞቹ አንዱ ነው፡፡ ችኮላ የተሞላበትን የደንበኛውን ትዕዛዝ በሚገባ አደመጠ፡፡

የጠዋት ሲሣይ ተገኘ፡፡ በውስጡ ደስታ ሲሰራጭ ተሠማው፡፡ በሀሳብ ወደ ኋላ ተጓዘ፡፡ ያሳለፈው አስከፊ ድህነት ዛሬ የት እንደሄደ ለራሱም ይገርመዋል፡፡ ድህነት የሚወዳቸውን ሰዎች ነፍስ ነጥቆ የሱን ተወለት፡፡ 
የግድግዳው ሰዓት 1፡00 ሲል ለስራው የሚያስፈልገውን ዝግጅት አጠናቆ ከቤቱ ወጣ፡፡ ስለዛሬው ስራው በማሰብ አምሮውን ማድከም አልፈለገም፡፡ በዚህ ሙያው እጅግ የሚያፈቅረውን ገንዘብ ያለ ብዙ ድካም አግኝቶበታል፡፡
የተነገረው ሆቴል ደረሠ፡፡ የሆቴሉን ዘመናዊነት በማድነቅ ጊዜ ማጥፋት የስራው የመጀመሪያ ህግ የሆነውን ፍጥነትን መሻር ነው፡፡ እራሱን ያገኘው የሆቴል ክፍል ቁጥር 107 በር ላይ ነበር፡፡ በዝግታ አንኳኳ፡፡ መልስ የለም፡፡ ደገመ፡፡
“አቤት ምን ነበር” ወፈር ያለ ድምፅ
“ከሆቴሉ አገልግሎት ክፍል ነበር፤ ካላስቸገርኮት አንድ ጊዜ ሊከፍቱልኝ ይችላሉ”
“ይቻላል ትንሽ ታገሰኝ”
ከጥቂት ቆይታ በኋላ በሩ ተከፈተለት፡፡ በሚነገርለት ቅልጥፍናው ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡ በሚያስገርም ፍጥነት በሩን ዘግቶ ሽጉጡን መዘዘ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሰውየው ፈዞ በግርምት ከመመልከት በስተቀር ያደረገው ነገር አልነበረም፡፡ የሰውየው የፊት ላይ ጠባሳ የተነገረው ምልክት ትክክል መሆኑን መሰከረለት፡፡
የሰውየው ፍጹም የሆነ እርጋታ የያዘው መሳሪያ ሽጉጥ መሆኑን እንዲጠራጠር አስገደደው፡፡ በስራው ዘመኑ ይህን አይነት እርጋታ አጋጥሞት አያውቅም፡፡ በምቾት የተጠበቀ ፊቱ ከመካከለኛ እድሜ አለፍ ያለ ገጽታን ተላብሷል፡፡
የቀረው ነገር ቢኖር ሳያውቀው ሱስ የሆነበት፣ ከሚገድለው ሰው ጋር የሚያደርገው አጭር ጭውውት ብቻ ነው፡፡ እንደመልአከ ሞት ድንገት በፊታቸው ሲቆም የሚገድላቸው ሰዎች የሚያደርጉት፣ የሚሆኑት፣ የሚያወሩት፣ ሁሉ ያስገርመዋል፡፡
ሁሉም ፊት ላይ የመኖር ጉጉት ደጋግሞ አስተውሏል፡፡ የዚህ ሰውዬ ፍጹም አለመደንገጥ ግን እሱን ራሱን አስደነገጠው፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ለሚገድለው ሰው ልዩ ክብር አደረበት፡፡
“ለመጨረሻ ጊዜ የምትናገረው ካለ ልቀበልህ ዝግጁ ነኝ” አለ ድምፅን ከፍ አርጎ፡፡ “እኔን ለመግደል ማን እንደላከህ አውቃለሁ፡፡ ለመሆኑ ስንት ከፈለህ?” አለ ፍጹም የሆነ እርጋታው ሳይለየው፡፡
ለዚህ ልዩ ሰው አንድ ውለታ ሊውልለት አሰበ፡፡ ለጠየቀው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ በመመለስ፡፡
“መቶ ሺ”
ሰውየው ገጽታ ላይ የመገረም ፈገግታ አየ፡፡
“እኔ 300ሺ ብሰጥህ በእኔ ፋንታ የላከህን ሰው ትገድለዋለህ?”
አስቦትም አልሞትም የማያውቀው ድርድር አስደነገጠው፡፡ ይህን አይነቱን ድርድር ባይጠብቀውም፣ ባያስበውም ሊያልፈው አልደፈረም፡፡ የስራው አላማ ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡ ገንዘብ ከምንም በላይ የሚያፈቅረው ነገር ነው፡፡ ሰው ለሚያፈቅረው ነገር መኖር ብቻ ሳይሆን መሞት አለበት ሲል አሰበ፡፡ ቼኩን ሲቀበል ቀጣይ ስራውን እያሰበ ነበር፡፡

 

Read 2966 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:53