Saturday, 30 June 2012 10:29

የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ሌላው ገፅታ - በኑዌር

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ-lizyequbay@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

አለም ከሚጨቃጨቅበት የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ጋር ከስያሜ በስተቀር በምንም መንገድ ሊዛመድ የማይችል የጋብቻ ሞዴሎች በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል ለሚገኙት ለኑዌሮች ተጋቢዎች ከግብረ ሰዶማውያን የተለየ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ይፈፅማሉ፡፡በምስራቅ አፍሪካ ከሚኖሩ በከብት ማርባት ከሚተዳደሩ ህዝቦች ብዛት ያላቸው እንደሆኑ በሚነገርላቸው ኑዌሮች፤ ምንም እንኳን ከስልጣኔ ጋር በተያያዘ እና በሌሎች ምክንያቶች የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ እየቀረ ቢመጣም፤ አሁንም ሴት  ሴትን በሚስትነት እንደምታገባ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በጥንታዊው የኑዌር ባህል ልጅ መውለድ ያልቻለች ሴት ሌላን ሴት እንደ ባል ታገባለች፡፡ በሚስትነት የተገባችው ሴት በሚስጥር ከአንድ ወንድ አርግዛ ልጅ ትወልዳለች፡፡ መውለድ ያልቻለችውና ሌላን ሴት በባልነት ያገባችው ሴት እንደ ልጁ አባት ትቆጠራለች፡፡ ማህበረሰቡ የተወለደው ልጅ አባት ብሎ እውቅና የሚሰጠው ባል ለሆነችው ሴት ይሆናል፡፡ በማንኛውም የማህበረሰቡ እንቅስቃሴ  ሴቷ ባል የወንድን ሚና ተክታ ትታያለች፤ ሽምግልና ትቆማለች፡፡ ሴቷ ባል የአባቷንና የአባቷን ወገኖች  ስም እንዲቀጥል እንዳደረገች ትቆጠራለች፡፡ በዚህኛው የኑዌሮች የጋብቻ ሞዴል በሁለቱ ተመሳሳይ ፆታዎች መሀል  የግብረሶዶማውያን አይነት የወሲብ ግንኙነት የለም፡፡ ሴቷ ባል የአባቷን ስም ለማስቀጠል ስትል ከምትጫወተው የወንድነት ሚና በስተቀር፡፡ሴቷን ማን እንዳስረገዛት ማወቅ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም ለኑዌሮች ሴቷን ባል ማወቅ በቂ ነው፡፡

ወንድ ልጅ የሌለው አባትም  ሴት ልጁን በባልነት ይድራል፡፡ አባት የሚጠበቅበትን ጥሎሽ ሰጥቶ ጋብቻው ከተፈፀመ በኋላ ሴቷ ሙሽራ ከማይታወቅ ወንድ በድብቅ ታረግዝና አባትነቱን ለሴቷ ባል ትሰጣለች፡፡ ይህኛው ሞዴልም ልክ ከላይ እንዳየነው በሁለቱ ተመሳሳይ ፆታዎች መሀል ምንም አይነት የወሲብ ግንኙነት የለውም፡፡ ሆኖም ሴቷ በማህበረሰቡ ውስጥ እንደ ባል እና አባት ትቆጠራለች፡፡ ዋናው ጉዳይ የአባትን ዘር ማስጠራት እና ማስቀጠል ነው፡፡

አንዲት የኑዌር ሴት ባሏ ከሞተ በኋላ የባሏን ወንድም ታገባለች፡፡ ነገር ግን ወንድምየው በማህበረሰቡ ውስጥ እንደ ባሏ አይቆጠርም፡፡ ልጅ ቢወልዱም የሚጠራው በሞተው ባሏ እንጂ በወንድምየው አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ለኑዌሮች በሞተ ሰው እና በህይወት ባለ ሰው መሀል ያለው ልዩነት አሁን በቅርብ የመገኘት እና ያለመገኘት ጉዳይ እንጂ እስከነአካቴው መለያያት አይደለም፡፡ሟች እዚሁ በዚሁ ማህበረሰብ እየኖረ ነው ብለው የሚያምኑት ኑዌሮች፤ ከሱ ሞት በኋላ የተወለዱ ልጆችም የሱው ናቸው ይላሉ፡፡

በኑዌር ጋብቻ በጥሎሽ የሚሰጥ ከብት ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ መጠኑ የተለያየ ቢሆንም ከባል ወገን ለሚስት ወገን  የሚሰጥ ከብት የሚወለዱ ልጆች ዘር የሚቆጠረውና አባል የሚሆኑበት የቤተሰብ አካል ከወንድ ወገን እንዲሆን ያደርገዋል ይላሉ ኑዌሮች፡፡ ጥሎሽ ወደ ኤኬ 47 ጠብመንጃ ከተለወጠ አመታት ያስቆጠረ ቢሆንም አሁንም ድረስ ከብቶች በኑዌሮች ዘንድ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡

ሰዎች በተደጋጋሚ ሴት ልጅ መውለድ ይፈልጉና ሳይሳካ ይቀራል፡፡ ኢትዮጵያ በሚገኙ አንዳንድ ማህበረሰቦች፤ ወንድ ልጆች  ልክ እንደ ሴት ቀሚስ እየለበሱ በሴት ስም እየተጠሩ ያድጋሉ፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ሴት ልጆቻቸውን በተደጋጋሚ በሞት የሚያጡ ቤተሰቦች ወንድ ልጆቻቻውን በሴት ስም እየጠሩ ያሳድጋሉ፡፡ ስያሜውና አስተዳደጉ ሰዎቹ የሚፈልጉትን ነገር እንዳገኙ እንዲያስቡ የሚያደርግ የስነልቦና እርካታ የሚሰጥ እንጂ በልጆቹ የተፈጥሮ ሁኔታ ላይ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡ ለኑዌሮቹም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻው በማህበረሰቡ ውስጥ ተፈላጊ የሆነውን አስተሳሳብ፤ አኗኗር ወይም ባህል በማሟላት የስነልቦና እርካታ ለማግኘት ያገለግላል፡፡ አባታዊ ስርአት እንዲቀጥል ዋስትና ይሆናል፡፡

 

 

Read 7825 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 10:39