Friday, 30 October 2026 06:24
በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የተከሰተውን የጸጥታ ግጭት በመሸሽ ወደ ሰሜናዊ ኬንያ የተሻገሩ ተፈናቃዮች ቁጥር 50 ሺህ መድረሱን ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ። በኬንያ የአይኦኤም ኃላፊ ኖማጉጉ ንኩቤ እንደገለጹት፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ማርሳቢት ግዛት በመሻገር በአካባቢው ማኅበረሰቦችና በጊዜያዊ መጠለያዎች ተጠልለው ይገኛሉ። በኢትዮጵያ በኩል ያለው ሁኔታ ባለመረጋጋቱ የሰው ቁጥር አሁንም ሊጨምር እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፣ ይኸው የመጀመሪያ ደረጃ ግምት እንደ ሁኔታው ሊለወጥ እንደሚችል ድርጅቱ አመልክቷል።
በአካባቢው ያለውን የከፋ የሰብዓዊ ሁኔታ ለመቋቋም፣ የኬንያ መንግሥት እና የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮች እስከ 80 ሺህ ለሚደርሱ ተፈናቃዮች የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ ናቸው። አይኦኤም ከኬንያ መንግሥትና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በመቀናጀት የመጠለያ፣ የመሠረታዊ ቁሳቁስ እና የሕክምና ድጋፍ አቅርቦትን ለማመቻቸት ጥብቅ ክትትልና የግምገማ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
bbc-
Published in
ዜና

