Monday, 26 October 2026 16:44

በአቤ ቶኪቻ የአለማወቅ ሰማይ ሥር የተጠለሉ የአቶ ልደቱ ሕፀፆች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
(የግል ምልከታ እንደወረደ )
በጌታሁን ሔራሞ -
...
ይህ ጽሑፌ በቃለመጠይቁ ውስጥ በመገንጠል አጀንዳና መብት ዙሪያ በተነሱ በአቶ ልደቱ ሐሳቦች ላይ ብቻ የሚያተኩር እንጂ ሙሉ ቃለመጠይቁን የሚዳስስ አለመሆኑ ይታወቅልኝ...
አበበ ቶላ ከአቶ ልደቱ ጋር ያደረገውን ቃለመጠይቅ በብዙ ትዕግሥትና ፈተና ዛሬ ረፋዱ ላይ ተከታትዬ ነበር። ሲጀመር አቶ አበበ ቶላ ካለው የፖለቲካ ዕውቀት ዝግጅት አኳያ አቶ ልደቱን ለቃለመጠይቅ ማሰቡ ገራሚ ነው፤ ሲቀጥል አቶ ልደቱም ግብዣውን እሺ ብሎ መቀበሉም ገርሞኛል። እውነት ይሁን አይሁን ባላውቅም ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ በአንድ ወቅት የቀድሞውን ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን፦ " ከአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ጋር ተቀምጠህም አንደኛ ተብለህ መሸለም ያምርሃል" በማለት ተችቶታል ይባላል።
አቶ ልደቱ አቶ አበበን በዝረራ ስለማሸነፉ ከሚነገረው "ገድል" ጎን ለጎን በአቤ ቶኪቻው የአለማወቅ ሰማይ ሥር የተጠለሉትን የአቶ ልደቱን ሕፀፆችንም ማንሳት ሚዛናዊ ያደርገናል ብዬ አስባለሁ። በእኔ እይታ አቶ ልደቱ በተለይም ስለ መገንጠል መብት ሲያብራራ ከመገንጠል ንድፈ ሐሳብ (Theory of secession) መርህ አኳያ ሁለት ስህተቶችን ፈጽሟል ባይ ነኝ፤ ለመጥቀስ ያህልም፦
1. አቶ ልደቱ በቃለመጠይቁ ከ12:20-12:29 ባሉ ደቂቃዎች መካከል የሚከተለውን ብሏል፦
የ"TPLF"ን ፕሮግራም አንብቤአለሁ ደግሜ ደጋግሜ...የ"OLA"ን ፕሮግራም አንብቤአለሁ ደግሜ ደጋግሜ...የመገንጠል ጥያቄ የሚባል ነገር የላቸውም።"
እንግዲህ በአቶ ልደታ አመለካከት አንድ ፓርቲ የመገንጠል አጀንዳ ስለማራመዱ ብቸኛው የመፈተሻ መንገዱ የፓርቲውን ፕሮግራም ማንበብና በዚያው ልክ ድምዳሜ ላይ መድረስ ነው። ከመገንጠል ንድፈ ሐሳብና ከፓርቲዎች የፖለቲካ ባሕሪይ አኳያ ግን ይህ የአቶ ልደቱ ማጠቃለያ ግን ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ማለት ይቻላል።
በነገራችን ላይ የመገንጠል አጀንዳ በፓርቲዎች በሁለት ዓይነት ስልቶች ሊቀነቀን ይችላል፤ የመጀመሪያው "Radical/Fundamentalist Secessionist ፓርቲዎች የሚከተሉት ስልት ነው፤ እንደዚህ ዓይነት የመገንጠል ስልት የሚያራምዱ ፓርቲዎች ዕቅዳቸውን በማኒፌስቶአቸው በግልጽ ያስቀምጣሉ፣ ከመገንጠል ጋር በተያያዘ የሚደብቁት ወይም የሚሸሸጉት ፕሮግራም የላቸውም፤ የትጥቅ ትግሉን ሲያጠናቅቁም በቀጥታ የሚያቀኑት ወደ ሪፍረንደምና "ነፃነት" ነው። ለዚህም ሻዕቢያ በቂ ምሣሌ ነው።
በሁለተኛ ምድብ ያሉ ፓርቲዎች ግን መገንጠልን በአጭር የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ዕውን ማድረግ የማይፈልጉና እናድርግ ቢሉም አቅሙ የሌላቸው ናቸው፤ እንደዚህ ዓይነት ፓርቲዎች ስለመገንጠል አጀንዳ በይፋ አያነሱም፣ ማኒፌስቶአቸውም ውስጥ በግልጽ አያስቀምጡም። ይሁንና ውጫዊና ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ሲመቻቹ በረዥም የጊዜ መርሐግብር ለመገንጠል ዕቅዳቸውን ነድፈው ይንቀሳቀሳሉ። እንደዚህ ዓይነት ፓርቲዎች Opportunist / Gradualist Secessionist groups ተብለው ይጠራሉ። ለዚህም "TPLF" ዓይነተኛ ምሣሌ ነው።
አቶ ልደቱ በ"TPLF" ፕሮግራም ውስጥ የመገንጠል አጀንዳ ተጽፎ አላየሁም ማለቱ ስህተት የሚሆነው ከዚሁ የተነሳ ነው። በአጭር ቃል "Opportunist / Gradualist Secessionists" ፓርቲዎች በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ስለመገንጠል አጀንዳ ፈጽሞ አለማንሳታቸው በአያሌ የመገንጠል ንድፈ ሐሳብ ጸሐፊዎች ዘንድ በተደጋጋሚ የሚሰመር እውነት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ በዝምታ ውስጥ የሚሰማ ግራ-ገብ የተገንጣይ ፓርቲ ባሕሪይ በአንዳንድ አጥኚዎች "Strategic Ambiguity of Secessionist groups" ተብሎ ይጠራል።
ይሁንና Opportunist / Gradualist Secessionists" ቡድኖች በማኒፌስቶአቸው ስለመገንጠል አጀንዳ ምንም ባይሉም በተዘዋዋሪ በሌሎች ፍንጭ ሰጪ መረጃዎች አላማቸውን መተንበይ ወይም መገመት ይቻላል። ለምሣሌ ያህል የፓርቲውን ስያሜ ማጤን አንዱ የመፈተሻ መንገድ ነው። ከዚህም ጋር በተገናኘ ከላይ በአቶ ልደቱ የተጠቀሱት ሁለቱም ፓርቲዎች ስያሜያቸው "ከነፃነት ግንባር" እና ከ"ነፃነት ሠራዊት" ጋር የተያያዘ ነው። ስያሜዎቹ፣ ፓርቲዎቹ የመገንጠል ጥያቄን በሆነ ወቅት ሊያነሱ እንደሚችሉ ፍንጭ የሚሰጡ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ድብቅ የመገንጠል ዓላማ ያላቸው ፓርቲዎች በእንግሊዝኛው "Liberation, Alliance, Movement, Front" የሚሉ ቃላትን በፓርቲያቸው ስያሜ ላይ በመጠቀም ትግላቸውን ለመቀንበብ ይሞክራሉ። እንዲያውም አቶ ልደቱ በአንድ ወቅት "TPLF" ስያሜው ላይ "LF" የሚለውን ቅጥያ የማያስወግድበት ምክንያቱ ምንድነው? በማለት በጽኑ ይሞግት እንደነበረ አስታውሳለሁ። ዛሬ ላይ አቶ ልደቱ... በሕወሓት ፕሮግራም ውስጥ የመገንጠል አጀንዳ የለም... ብሎ ከሚሞግት እንደበፊቱ ሕወሓቶች የፓርቲውን ስያሜ እስከ ዛሬ ድረስ ለምን ይዘው እንደዘለቁ መጠየቅ አለበት።
"Opportunist" ተገንጣዮች በአጭር የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ድብቅ አጀንዳቸውን ይፋ ከማድረግ የሚቆጠቡት በተለያዩ ምክንያቶች ነው። ለምሣሌ ያህል፦ ሊገነጥሉት የሚያልሙት ክልል ኢኮኖሚ ጠንካራ መሠረት ላይ እስኪገነባ አላማቸውን በይፋ ላይገልጡ ይችላሉ፣ እንዲሁም የማዕከላዊ መንግሥት መዳከምንም እንደ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ወቅቱ ሲደርስ ጥያቄአቸውን ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዳንድ ስውር የመገንጠል አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች ደግሞ ወታደራዊ አቅማቸውን እስኪያጠናክሩና ሕዝባዊ ቅቡልነትን በስፋት እስኪሸምቱ ድረስ የመገንጠል አጀንዳን በማኒፌስቶአቸው ላያስቀምጡ ይችላሉ። .
2. ሌላው አቶ ልደቱ በመገንጠል ዙሪያ የሕወሓቱን ምክትል ሊቀመንበር የአቶ አማኑኤል አሰፋን ሐሳብ ሲያብራራ በዩኬ፣ በስፔንና በካናዳ ዲሞክራቲክ በሆነ መልኩ ስለሚነሱ የመገንጠል ጥያቄዎች አዎንታዊ በሆነ መልኩ አንስቷል። ይሁንና አቶ አማኑኤል በተለይም የኢትዮጵያን ብሔሮች የመገንጠል ጥያቄ መብትን ያነሱት በአንቀጽ 39 ጥላ ሥር ሆነው እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ለምሣሌ አቶ አማኑኤል አንቀጽ 39 በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመወያያ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡን መቃወማቸውን ከአንዱ ቃለመጠይቃቸው ለመገንዘብ ችዬአለሁ። አንቀጽ 39 ደግሞ መገንጠልን የሚፈቅደው "ያለገደብ በማናቸውም መልኩ" ነው። አቶ ልደቱ ለንጽጽር ባቀረባቸው ሀገራት ማለትም በዩኬ፣ በስፔንና በካናዳ "ያለገደብ በማናቸውም መልኩ" መገንጠል ደግሞ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። እናም አቶ ልደቱ በአንቀጽ 39 ላይ ተመስርተው ስለ መገንጠል መብት ጥያቄ መነሳት ገለጻ የሰጡትን የአቶ አማኑኤልን ሐሳብ ለማጽናት ከአንቀጽ 39 ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት የሌላቸውን ሀገራት የመጥቀሱ አላማው ምን ይሆን?
በአንድ በኩል "አንቀጽ 39 ከሕገ መንግስቱ ይውጣ" እያለ፣ በአንጻሩ ደግሞ በአንቀጽ 39 ላይ ተመስርተው ስለ መገንጠል ማብራሪያ የሚሰጡ ሕወሓቶችን ሐሳብ ለማጽናት የአውሮፓዎቹን የመገንጠል ጥያቄን ከአውዱ ውጭ በምሣሌነት መጥቀሱ ፋይዳው ምንድነው? ለማንኛውም በዩኬ፣ በስፔንና በካናዳ "ያለገደብ በማናቸውም መልኩ" መገንጠል ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። እናም አቶ ልደቱ ንጽጽሩን የሰራበት መንገድ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ደግሞም አቶ ልደቱ አቤ ቶኪቻውን በተደጋጋሚ... አቶ አማኑኤል መች እንገነጠላለን?...እያለ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሹን እኔ ልስጥ፦
ውድ አቶ ልደቱ.. አቶ አማኑኤል በይፋ እንገነጠላለን ይላሉ ብለን አንጠብቅም፣ ምክንያቱም እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው "Opportuinst secessionist groups" እንደሆኑ እናውቃለንና።
በመጨረሻም የሕወሓቱ ም/ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ ኢትዮጵያ እንደ ዮጎዝላቪያ ልትበታተን ስለሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ በፌስ ቡክ ገፁ በሜይ 10 2026 ድምጻቸውን ማሰማታቸው ይታወቃል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 5527 times