Wednesday, 21 October 2026 07:00

"የስጋ ዋጋ ይቀንስ ጥያቄ ከስጋ በላይ ነው"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ "የስጋ ዋጋ ይቀንስ" የሚለው ጥያቄ በኑሮ ውድነት የተጨነቀ ህዝብ የድረሱልኝ ጥሪ እንደሆነ ገልጸዋል። ጥያቄው ከስጋ አልፎ የብር የመግዛት አቅም መውደቅን፣ የቤት ኪራይና የትራንስፖርት ዋጋ ማሻቀብን የሚያሳይ በመሆኑ፣ ነገሩን ለመረዳት የህዝቡን የዕለት ተዕለት ህይወት ማየት ብቻ በቂ እንደሆነ አብራርተዋል።
ህዝቡ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ-ሀሳቦችን ወይም የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ዝርዝር የማወቅ ግዴታ የለበትም። ይልቁንም ማንኛውም ዜጋ በህይወት ለመኖር የሚያስፈልጉ ነገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡለት የመጠየቅ መብት እንዳለውና ቤተሰቡን የመመገብ ሀላፊነት እንዳለበት ሙሼ ሰሙ ጠቁመዋል። ስለዚህ የህዝቡን ችግር በማቃለል በጥያቄው ላይ መዘባበት ተገቢ እንዳልሆነ አሳስበዋል።
የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ መፍትሔዎችን ተንታኙ ጠቁመዋል። ከአምራች እስከ ቸርቻሪ የተቀናጀ የስርጭት መስመር መዘርጋት፣ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን መደጎም፣ የምግብ አቅርቦትን ማሳደግ እንዲሁም የህዝቡን ኪስ እያራቆቱ ያሉ የመንግስት አገልግሎቶችን (የመብራት፣ የስልክ፣ የውሃ) ዋጋ መቀነስ ዋና ዋና እርምጃዎች ናቸው ብለዋል።
በመጨረሻም፣ ገበያ ውስጥ ጣልቃ መግባት ከመንግስት የኢኮኖሚ ፍልስፍና ጋር የሚጋጭ ከሆነ፣ በነጻ ገበያ መርህ መሰረት ለሰራተኛው ተመጣጣኝ ክፍያ መከፈል እንዳለበት ሙሼ ሰሙ አጽንኦት ሰጥተዋል። ህዝቡ የዋጋ ንረቱን ተቋቁሞ መኖር እንዲችል መንግስት በቂ ደሞዝ የመክፈል ሃላፊነት እንዳለበት አብራርተዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 7807 times