Tuesday, 20 October 2026 10:29

ከ400 በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶች የክረምት ስልጠና አጠናቀው ተመረቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአዲስ አበባ ቴአትር እና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት ሲሰጥ የቆየውን ሁለገብ የኪነ ጥበብ ስልጠና ያጠናቀቁ ከ400 በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በፍላሚንጎ የሕጻናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ አስመረቀ። በ2018 ዓ.ም. የክረምት ወቅት በተካሄደው በዚህ ሰፊ መርሐ ግብር፣ ሰልጣኞቹ በቴአትር ጥበብ፣ በግጥም፣ በሙዚቃ፣ በድምጽ ቅላጼ፣ በዘመናዊ ዳንስ እንዲሁም በባሕላዊ ውዝዋዜ ዘርፎች የንድፈ ሐሳብና የተግባር ስልጠናዎችን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን፣ በዕለቱም ክህሎታቸውን የሚያንጸባርቁ ጥበባዊ ስራዎችን ለታዳሚ አቅርበዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረ እግዚአብሔር፣ የቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ዘገየ፣ ተመራቂዎች፣ ወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። የቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ዘገየ እንደገለጹት፣ ከ400 በላይ ሰልጣኞችን አበቃቅቶ ወደ ኪነ ጥበብ ዘርፍ ማቀላቀል መቻሉ ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ ወጣቶችና ታዳጊዎች የተፈጥሮ ክህሎታቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙበትና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

ይህ የኪነ ጥበብ ስልጠና በክረምት ወራት ብቻ የሚከናወን ጊዜያዊ ዝግጅት ሆኖ የሚያበቃ ሳይሆን፣ በቀጣይም በቋሚነት የሚደገፍና የሚቀጥል መሆኑ ተብራርቷል። ይህም አዳዲስና ተስፋ ያላቸው ወጣት አርቲስቶች ሞያዊ ብቃታቸውን በማሳደግ ሀገራቸውንና ማህበረሰባቸውን በስነ ጥበቡ ዘርፍ በብቃት እንዲያገለግሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።

Read 7264 times