በፈረንሳይ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን፣ የኑሮ ውድነትን እና የሕዝብ አገልግሎቶች ማሽቆልቆልን በመቃወም ወደ 550,000 የሚጠጉ ሰዎች ያደረጉት ከፍተኛ የተቃውሞ ሠልፍ ወደ ብጥብጥ፣ እሳት ቃጠሎና ዝርፊያ መቀየሩን ተከትሎ፣ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "መረጋጋትና ስርዓት" እንዲሰፍን ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ ከቤተ መንግሥታቸው ባስተላለፉት መልዕክት በሠልፉ ላይ የተሳተፉ ሰዎች አለመረጋጋቱን እንዳያባብሱ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ በተቃዋሚዎች ሕጋዊ ጥያቄዎች እና ውድመት በፈጸሙ፣ በሰባበሩና በዘረፉ አካላት መካከል ልዩነት መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ፣ በፓሪስ፣ ማርሴይ፣ ሊዮንና ሊል ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የተቃውሞ ሠልፈኞች መኪኖችን፣ ሱቆችንና ሕንፃዎችን ያቃጠሉ ሲሆን፣ በሊሞጅስ ከተማ የሚገኘው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ታሪካዊ የከተማ አዳራሽ በእሳት ወድሟል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ፖሊስ ወደ 2,400 የሚጠጉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ በግጭቱ ወቅት ወደ 1,000 የሚጠጉ የፖሊስ መኮንኖች መቁሰላቸውና ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
ይህ በዘመናዊ የፈረንሳይ ታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋው አመጽ ተብሎ የተገለጸው ተቃውሞ፣ ባለፈው ወር በተማሪዎች የተጀመረ ቢሆንም ቅዳሜ ዕለት የሠራተኛ ማኅበራትና ሌሎች ፀረ-መንግሥት ቡድኖች ከተቀላቀሏቸው በኋላ ወደ አደገኛ አመጽ መሸጋገሩን ቢቢሲ አብራርቷል። ፕሬዝዳንት ማክሮን "ከቁጥጥር ውጪ ለሆነው" ጥቃት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊቀርብለት እንደማይችል በመግለጽ በጥፋቱ ላይ የተሳተፉት ሕግ ፊት እንደሚቀርቡ የተናገሩ ሲሆን፣ ፖሊስ የተቃውሞ ሠልፎቹን ለመበተን የወሰደውን እርምጃ በተመለከተም "ሙሉ ግልጽነት" እንደሚኖር አረጋግጠዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

