በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ጥንታዊ ጥበባት ላይ ያተኮረው “የምድር ጌጥ ኢትዮጵያ” የልጆችና የቤተሰብ ልዩ አውደ ርዕይ በተመልካቾች ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት ከተጨማሪ ዝግጅትና ማሻሻያዎች በኋላ በአዲስ መልክ ዳግም ተከፍቷል።
በአዲስ አበባ ሆላንድ ፓርክ እየቀረበ የሚገኘው ይህ ልዩ አውደ ርዕይ፤ ከጎብኚዎች በተነሱ ጥያቄዎች መሠረት ለተጨማሪ ሦስት ቅዳሜና እሁዶች (መስከረም 30 እና ጥቅምት 1፣ ጥቅምት 7 እና 8፣ እንዲሁም ጥቅምት 14 እና 15) ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን አዘጋጁ ሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ተቋም አስታውቋል።
አውደ ርዕዩ ሕፃናትና ወጣቶች ስለ አገራቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ሥልጣኔና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪካዊ አሻራዎች በተጨባጭ እንዲያውቁ የተዘጋጀ ነው። ከተለመዱት መርሃ ግብሮች ለየት ባለ መልኩ ጎብኚዎች ቅርሶችን ከማየት ባለፈ በመዳሰስ፣ በመስማት፣ በማሽተትና በመቅመስ በአምስቱም የስሜት ሕዋሳት ታሪካዊ ይዘቶቹን እንዲረዱ ተደርጎ የተሠራ ሲሆን፤ አክሱም፣ ላሊበላና ደብረ ዳሞን የሚያስታውሱ የኪነ ሕንፃ ሥራዎች፣ የብራና መጻሕፍትና ጥንታዊ ጥበባት ቀርበዋል።
የካናዳ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ አውደ ርዕዩን ጎብኝተው የቤተክርስቲያንን ታሪክና ቅርስ ለትውልድ በማስተዋወቅ ረገድ ያለውን ትልቅ አስተዋጽኦ አድንቀዋል። አውደ ርዕዩ ለዝግጅት ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችና የተቋም ቡድኖች በልዩ የጉብኝት ፓኬጅና ቅናሽ እንዲጎበኙ ዕድል ተመቻችቷል። አዘጋጆቹ ሕዝቡ በተጠቀሱት ቀናት በመገኘት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና ውርስ በቅርበት እንዲመለከት ጥሪ አቅርበዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

