ስለ ''Survivor's Guilt Syndrome'' ምንነት የሰማሁበትን ጊዜ አስታውሰዋለሁ። የዛሬ 17 ዓመት ለትምህርት አሜሪካ በነበርኩበት ወቅት ነው። ትንሽ ዘለግ ያለ መንገድ በታክሲ እየሔድኩ ዝም ከምል ብዬ 'ፓኪስታናዊ' የመሠለኝን ሾፌር ''እስኪ ስለ ፓኪስታን ዝነኛው የክሪኬት ቡድን አጫውተኝ'' አልኩት። በእውነቱ ያን ሰሞን አንድ ግሩም የሆነ 'Lagaan' የተሰኘ ፊልም አይቼ ስለክሪኬት ፍቅር አድሮብኝ ነበር። ከዚያ በፊት ከስሙ ውጪ ምን ዓይነት ጨዋታ እንደሆነ ራሱ አላውቅም።
''አይ እኔ አፍጋን ነኝ፤ ከፓኪስታን አይደለሁም'' አለ። ዝም አልኩ።
''መቼም ከጦር''ነት ውጪ ሌላ ታሪክ የሌለን እስኪመሥል ድረስ ነው አዕምሮአችሁ ውስጥ የታተምነው። እንጂ እንደ ስልጣኔ አጀማመራችን ቢሆን የት በደረስን። በትንሹ እንኳን ስለ አፍጋን ዝነኛ ምንጣፎች ሰምተሽ ታውቂያለሽ?'' ዝም አልኩ።
ብዙ ስለሀገሩ ሲነግረኝ ከቆየ በኋላ ነው እርሱና ቤተሰቡ በስንት መከራ አሜሪካ እንደገቡ፤ ከዚያም ለቀደሙት 7 ዓመታት አፍጋኒስታን የቀሩ ቤተሰብ እና ጓደኞቹን በአጠቃላይ ወገኑን እያስታወሰ እርሱ እና ልጆቹ በመትረፋቸው የጥፋተኝነት ስሜት እንደሚሰማው (Survivor's Guilt Syndrome) ለዚህም ደግሞ በሳምንት አንድ ጊዜ እርሱና ባለቤቱ የስነ-ልቡና ህክምና እንደሚያደርጉ አጫወተኝ።
አገሬ ላይ አንፃራዊ ሰላም ያለው ከተማ ውስጥ ስለምኖር ሌሎችን ሳስታውስ ይህ ስሜት ተሰማኝና አፍጋኑ የታክሲ ሾፌር ትዝ አለኝ። ሰላም የጤና መሠረት ነው። የሰላም መጥፋት ከብዙ ጉዳቶቹ አንዱ የአካል እና የአዕምሮ ጤና ላይ የሚያደርሰው መናጋት እንዲሁም ከላይ የጠቀስነው ዓይነት የስነ-ልቡና ጤና ላይ የሚያሳርፈው በትር ነው። ጤናችን በተጓደለ ቁጥር ራሳችንንም ሆነ አገራችንን የማሳደግ አቅማችን እንደሚደክም እሙን ነው። Ordinary ዜጎች ''አገራችንን ሰላም ያድርግልን'' ብለን ዱዓ ከማድረግ ውጪ ሌላ ምን መሣሪያ አለን?! ዱዓ/ጸሎት ብቻ!
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

