የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማፋጠንና የሕዝብን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ በማሰብ ባዋለው አዲሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት ስድስት አዳዲስ ግዙፍ ዞኖችን አዋቅሯል። እነዚህ አዳዲስ ዞኖች ምስራቅ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኦሮሚያ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ እና የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞኖች በመባል በድጋሚ የተደራጁ ሲሆን፤ ቀደም ሲል የነበሩ በርካታ ዞኖችንና ከተሞችን በአዲስ መልክ አካተዋል።
ለእነዚህ አዳዲስ ዞኖች ከፍተኛ ክትትልና ቀልጣፋ አመራር ለመስጠት በጨፌ ኦሮሚያ በኩል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የሚመሩ አዳዲስ አስተዳዳሪዎች ተመድበዋል። በዚህም መሠረት አቶ አብዱርራህማን አብደላ (ምስራቅ ኦሮሚያ)፣ አቶ መስፍን መላኩ (ምዕራብ ኦሮሚያ)፣ ዶ/ር ረሻድ ከማል (ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ)፣ ዶ/ር መንግሥቱ በቀለ (ማዕከላዊ ኦሮሚያ)፣ አቶ አህመድ ኢድሪስ (ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ) እና አቶ አህመድ ሀጂ (ደቡብ ኦሮሚያ) ዞኖቹን በበላይነት እንዲመሩ ተሾመዋል።
ይህ የመዋቅራዊ ሽግግርና ከፍተኛ የአመራር ድልድል የክልሉን አስተዳደራዊ አቅም በማጠናከር የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በፍጥነት ለመመለስና የልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ተገልጿል። አዲሱ አደረጃጀት ሕዝቡን ከማንኛውም ጊዜ በላይ የውሳኔው ባለቤት እንደሚያደርገውና ቀጣይ የልማት አቅጣጫዎችን እንደሚያፋጥን ይጠበቃል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas
See less

