የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኞ መስከረም 18 ቀን 2019 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅን የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰፊው ተወያይቶ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወሰኗል። ላለፉት ሶስት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በስራ ላይ የነበረውን ይህንን ህግ እንደገና ማሻሻል ያስፈለገው፣ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ሀገራዊ ተልዕኮዎቹን በህግ አግባብ ለመፈጸም እንዲያስችለው መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ በዋናነት የመከላከያ መርሆዎችን የሚመለከቱ የህገ መንግስቱን አንቀጽ 87 ድንጋጌዎች ለማካተት ያለመ ነው። በዚህም መሰረት ሰራዊቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦን የያዘ መሆን እንዳለበት፣ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ግለሰብ ሲቪል መሆን እንደሚገባው፣ እንዲሁም ሰራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ተገዢ ሆኖ ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነጻ በሆነ መልኩ እንደሚንቀሳቀስ በድጋሚ ተደንግጓል።
በሚያዝያ 2015 ዓ.ም የመጨረሻ ማሻሻያውን ያደረገው ይህ አዋጅ፣ ሰራዊቱ በምድር፣ በአየር፣ በባህር፣ በሳይበር እና በጠፈር መዋጋት በሚችል መልኩ እንዲደራጅ አድርጓል። አሁን በቀረበው አዲስ ማሻሻያ ላይ ምክር ቤቱ ግአብቶችን በማከል ወደ ፓርላማ የላከው ሲሆን፣ በቀጣይ ቀናት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታይቶ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas
Published in
ዜና

