Thursday, 17 September 2026 11:37

አነጋጋሪው የሌሊሳ ግርማ መጽሐፍ የፊታችን እሁድ ለውይይት ይቀርባል

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የሕንጸት መጽሐፍ ክበብ እሑድ መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም. ከሣር ቤት ወደ ቫቲካን ኢምባሲ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት (EGST) አዳራሽ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ አጓጊ የውይይት መርሐ ግብር አዘጋጅቷል።
በዕለቱም በደራሲ ሌሊሳ ግርማ የተጻፈውና አነጋጋሪ የሆነው “በታችም በምድር” የተሰኘው ልብወለድ መጽሐፍ ለውይይት ይቀርባል። በመጽሐፉ ላይ ለመወያየት እና ሃሳብ ለመለዋወጥ ሁሉም የመጽሐፍ ወዳጆች በክብር ተጋብዘዋል።
ደራሲ ሌሊሳ ግርማ ከዚህ ቀደም “እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎችም ታሪኮች” እና “ይመስላል ዘላለም” የተሰኙትን ጨምሮ በርካታ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡
**--
ስለመጽሐፉ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ
ላይ ከቀረበ አስተያየት የተወሰደ
“የሌሊሳ ግርማ አዲስ የረዥም ልብወለድ ድርሰት--ማራኪ የፋንታሲ ዘይቤ ነው፡፡ ግን ምናባዊ ዓለም ብቻ አይደለም፡፡ የዛሬ የዘመናችን የዚህችው የዓለማችን ገፅታና መንፈስ ለማሳየት የተወጠነ ድርሰት ነው፡፡
በራቶስ ነዋሪዎች ዘንድ የተለያዩ ወሬዎችና የተምታቱ ሐሳቦች ቢበዙ ላይገርም ይችላል። የለውጥ ዘመን ላይ የሐሳቦች ግርግር ይፈጠራል። ሲያስለቅሱ የነበሩ አስጨፋሪ፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ። የታችኞችም የበላይ። ተራራው ተንዶ ሜዳ ይሆናል፤ ሸለቆው አብጦ ተራራ ያክላል። የሐሳቦች መልክዓ ምድር ይለዋወጣል። ነገሮች በፍጥነት ይሾራሉ።
እንደ ጥንቱ ቢሆን፣ በለውጥ ምክንያት የሚከሰት ጊዜያዊ የሐሳቦች ግርግር፣ ውሎ አድሮ ይረጋጋል። መልክ ይይዛል። የዛሬው ዓለም ግን ከጥንቱ ይለያል። በመላው ዓለም የሚታየው የዘመናችን የሐሳቦች ግርግር፣ ጊዜያዊ የሽግሽግ ሆይሆይታ ወይም የሽግግር ሁካታ አይደለም።
አንድ የሐሳቦች ማዕቀፍ በብጥብጥ ደፍርሶ፣ ሌላ የተጣራና የተንጣለለ የሐሳቦች ማዕቀፍ አይፈጠርም። ነባሩ ተደፍቶ በቦታው ሌላ አዲስ ተተክቶ አያድርም። የፈራረሱት ጠጠሮች፣ የተበታተኑት ነጠብጣቦች እንደገና በአዲስ መንገድ እንዲሰባሰቡ፣ ሥርዓት እንዲይዙና ምስል እንዲፈጥሩ ማድረግ የሚችል ወይም የሚፈልግ የለም።----
የጠጠሮች ክምችትና የነጠብጣቦች ትርምስ ነው የዘመናችን ግብ። ጠጠሮችን አዋቅሮ ወደ ቅርጽ ማድረስ፣ ነጠብጣቦችን አገናኝቶ ወደ መስመርና ወደ ምስል ማሸጋገር ድሮ ቀረ ተብሏል። ወይም እንደ ኋላቀርነት ተቆጥሯል። ይህን የዘመናችንና የዓለማችንን መንፈስ ለመግለጽና ለማሳየት የሚሞክር ድርሰት ይመስላል - የሌሊሳ ግርማ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ።
“በታችም በምድር” በሚል ርዕስ ለሕትመት የበቃው ድርሰት፣ የዘመናችንን የሐሳብ ግርግር በማሳየት ብቻ አይመለስም። በሐሳቦች ግርግር በታመሰው ዓለም፣ የዓለማ አቅጣጫ በተምታታበት ቅብዝብዝ፣ በማንነት ቀውስ እየታመሰ ትርጉም ባጣ ሕይወት ውስጥ፣ ነጠብጣቦችን ሁሉ የሚጠቀልል ትልቅ ነጥብ የማግኘት ውጣ ውረድን ይተርካል - ድርሰቱ።“
Read 7695 times