የቴክሳስ ምሽት ዛሬ የተለየ ነው። ሰማዩ ሰፊ፤ ከዋክብቱ በሩቅ ጸጥ ብለው የማላውቀውን የትዝታ በር ከፈተብኝ። ሰውነቴ እዚህ ቴክሳስ፤ ሐሳቤ ግን ውቅያኖስ ተሻግሮ፣ ዓመታትን ወደኋላ ተጉዞ፣ አዲስ አበባ .... መርካቶ።
የመርካቶ ልጅ ነበርኩ። መርካቶን ኖሬበታለሁ፣ በመንገዶቹ ላይ አድጌበታለሁ። ገሊላ ትምህርት ቤት እየተማርኩ፣ ከዜድ ሙዚቃ ቤት እስከ ሸንኮራ ተራ፣ ከአብነት እስከ ኮካ ኮላ ያሉት መንገዶች የልጅነቴ ካርታ ነበሩ። ጩኸቱን አውቃለሁ፤ ሽታውን አውቃለሁ፤ የሱቆቹን ትርምስ፣ የነጋዴዎቹን ድርድር፣ የሻይ ቤቶቹን ወሬና የሰዎቹን ቀልድ አውቃለሁ። የመርካቶን ማለዳ በእግሬ አልፌበታለሁ፤ ምሽቱንም በድምፁ አውቀዋለሁ።
ለእኔ መርካቶ የአዲስ አበባ አንድ ሰፈር ብቻ አልነበረም፤ ልጅነቴ የተጻፈበት ቦታ፣ ዓለምን ማየት የጀመርኩበት መስኮት ነበር። መርካቶ ገበያ ብቻ አልነበረም፤ በጥቂት ካሬ ኪሎ ሜትሮች ውስጥ የተሰበሰበች ትንሽ ኢትዮጵያ ነበረች። ከጎንደር የመጣው፣ ከወሎ የወረደው፣ ከጎጃም የመጣው፣ ከሐረር፣ ከወለጋ፣ ከጉራጌ፣ ከትግራይ፣ ከአርሲና ከሲዳማ የመጡ ሰዎች በየመንገዱ፣ በየሱቁና በየሻይ ቤቱ ይገናኙ ነበር። የንግግር ዘዬያቸው ይለያይ ነበር፤ ምግባቸው፣ ልማዳቸውና እምነታቸውም ይለያይ ነበር፤ ግን መርካቶ ሁሉንም በአንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ እንደሰበሰበች እናት ታቅፋቸው ነበር። ዛሬ ሳስበው
መርካቶ በልጅነቴ ያስተማረችኝ ትልቁ ትምህርት ይህ ይመስለኛል፤ ኢትዮጵያ በካርታ ላይ ብቻ አልነበረችም፣ በሰዎች ዕለታዊ ኑሮ ውስጥ ነበረች። ምናልባትም ያኔ ሳናውቀው የምንኖረው ነገር፣ ዛሬ በብዙ ቃላት የምንፈልገው ነገር ነበር፣ አብሮነት።
ልጅ ሆኜ እነዚያን ሰዎች ስመለከት ስለ “አብሮነት” ትልቅ ፍልስፍና አልገባኝም ነበር። አብሮነት ለእኛ ንግግር አልነበረም፤ የዕለት ተዕለት ኑሮ ነበር። የሙስሊሙን ሱቅ ክርስቲያኑ ይጠብቅለታል፤ የክርስቲያኑንም ችግር ሙስሊሙ ይጋራል። ከየአቅጣጫው የመጡ ሰዎች ከጠዋት እስከ ማታ በአንድ መንገድ ላይ ሕይወትን ይካፈሉ ነበር። ፍጹም ነበር ማለት አይደለም፤ ችግርም ጠብም ነበር። ግን ልዩነት ሁልጊዜ ግድግዳ አልነበረም።
ምናልባት ለዚህ ነው ዛሬ የቴክሳስን ሰፊ ሰማይ ስመለከት የሚናፍቀኝ ሕንፃዎቹ ወይም መንገዶቹ ብቻ ያልሆኑት። ሰዎች ናቸው የሚናፍቁኝ። ያ አንዱ ሌላውን የሚያውቅበት፣ በቀልድ የሚጠራራበት፣ ቡና የሚጋበዝበት፣ በችግር የሚደራረስበት የመርካቶ ሕይወት ....
ዓመታት አለፉ። ከተሞች ተቀየሩ፤ ሰዎች ተበተኑ፤ እኛም ዓለምን ተሻገርን። ግን ትዝታ ድንበር አያውቅም። ፓስፖርት አይጠይቅም፤ ቪዛም አያስፈልገውም። አንድ የሌሊት ንፋስ፣ አንድ የቡና ሽታ፣ አንድ የቆየ ዜማ በቂ ነው፤ በአንድ ቅጽበት ወደ ልጅነትህ ይመልስሃል።
ዛሬ ቴክሳስ ነኝ። ከፊቴ ሰፊው የቴክሳስ ሰማይ ተዘርግቷል። በዓይኔ ከዋክብቱን አያለሁ፤ በልቤ ግን የመርካቶን መንገዶች እጓዛለሁ። ዛሬ አዲስ አበባን “የእኔ ናት” ብለው በብቸኝነት የሚጠይቁ ሰዎች፤ እንዲህ ያለ ትዝታ ይኖራቸው ይሆን?
ዶ/ር መኮንን ብሩ

