Tuesday, 01 September 2026 13:18

ቢል ጌትስ ሮቦቶችና ኤአይ ላይ ግብር እንዲጣል ጥሪ አቀረቡ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ ሮቦቶች እና አርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ (AI) የሰዎችን ስራ በከፍተኛ ፍጥነት እየተኩ በመሆናቸው፣ መንግስታት በነዚህ ቴክኖሎጂዎች ላይ ግብር የመጣል ውሳኔ እንዲያስቡበት ጥሪ አቀረቡ። ጌትስ ባወጡት አዲስ ጽሁፍ እንደገለፁት፣ እንደ ደንበኞች አገልግሎት፣ የህግ ረዳትነት እና ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ያሉ ስራዎች በኤአይ እየተተኩ ነው፤ በቀጣይም በኮንስትራክሽን እና በሆቴል ዘርፍ ያሉ አካላዊ ስራዎች በሮቦቶች ሊወሰዱ ይችላሉ። አሁን ያለው የግብር አሰራር ኩባንያዎች ሰራተኞችን በሮቦቶች እንዲተኩ ያበረታታል፤ ምክንያቱም ሰራተኛ ሲቀጠር የሚከፈለው የደመወዝ ግብር ሮቦት ሲገዛ ስለማይከፈል ነው።

በመሆኑም በሮቦቶች እና ኤአይ አጠቃቀም ላይ ግብር እንዲጣልና የሚሰበሰበው ገንዘብ በቴክኖሎጂው ምክንያት ስራቸውን ላጡ ሰዎች መልሶ ማሰልጠኛና ድጋፍ እንዲውል ሀሳብ አቅርበዋል። ቢል ጌትስ በሮቦቶች ላይ ግብር እንዲጣል ጥሪ ሲያቀርቡ የመጀመሪያቸው አይደለም፤ እ.ኤ.አ በ2017 ሰራተኞችን በሮቦት የሚተኩ ኩባንያዎች ሰውየው ይከፍል የነበረውን ያህል ግብር ሊከፍሉ ይገባል ሲሉ ተከራክረው ነበር። አሁንም መንግስታት ከፍተኛ የስራ ማጣት ችግር ከመከሰቱ በፊት አስቀድመው ተዘጋጅተው አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 5827 times