Saturday, 22 August 2026 10:42

አለማየሁ ገላጋይ አመነ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
አለማየሁ ገላጋይ በፍቅር ስም፣ በእውነት ስም እያለ በፃፋቸው "ቴማቲክ ሲሪየስ" መፅሐፎቹ ውስጥ ማኀበረሰቡን ራቁቱን ነው ያስቀረው...
የመጀመሪያውን "በፍቅር ስም" ሳነብ፣ ፍቅርን፣ እንዴት እንዳመቸን ስንተረጉመው እንደነበረ፣ በፍቅር ስም ስንት ጥላቻ ዘርተን እንዳበቀልን ሲገባኝ፣ ስገረም ሰንብቼ ፣ አለማየሁ ገላጋይ "በእውነት ስም"ን ይዞ መጣ። ነባሩን፣ ተከልለን የኖርንበትን ግንብ ለመናድ መዶሻውን ስሎ እንደወጣ እና ፍርስርሱን ሳያወጣ እንደማይመለስ ወገግ አለልኝ። ብዙ አልቆየም "በእምነት ስም"ን ይዞ ወጣ። ምን ቀረን ታዲያ? ፍቅራችንን፣ እውነታችንን፣ እምነታችንን እንደጥጥ እያባዘተ መሬት ዘረገፈልን።
ፈሪ ነኝ። "በእምነት ስም"ን መጨረስ አልቻልኩም። አለማየሁ የጨከነብን መሰለኝ። እኔና እግዜሬን ለሙግት ጠረጴዛ ዙሪያ አስቀመጠን... መፅሐፉን ገፅ ሀምሳ ሰባት ላይ እንዳጠፍኩ አስቀመጥኩት... አልተመለስኩበትም።
ያኔ፣ አለማየሁ ግን በዚህ ማኀበረሰብ ይሄን ያህል አቂሟል? ይሄን ያህል? ልብሱን ገልቦ ከአንገቱ ላይ ማተቡን የመበጠስ ያህል? አልኩ...አለማየሁ ማኀበረሰቡን እንዳኮረፈ እኔም አለማየሁን አኮረፍኩት።
በቀደም አንድ ቁራጭ ቪዲዮ ስልኬን በጣቴ ስገልጥ አገኘሁ...
አለማየሁ ያወራል። ቃል በቃል አይደለም፤ እንዲህ አለ። "ይሄ ማኀበረሰብ በእምነት ስም ብዙ ሰርቷል... ለግፉ፣ እግዜሩን፣ አለኝ የሚለውን አንድ እምነቱን ሊነጠቅ ይገባል፤ ቅጣቱ ነው። 'አምናለሁ፤ ፈጣሪ አለኝ' የሚል ማኀበረሰብ ሰው ዘቅዝቆ ሰቀለ፤ ህፃናትን ፈጀ፤ ከእናት ማህፀን ልጅ አወጣ... እግዜር አለኝ ብሎ ይሄን ካደረገ፣ እግዜሩን መነጠቅ አለበት፤ ይሄንን ነው በመፅሐፌ ያደረግሁት" አለ።
በፈጣሪ ስር ተከልለን የምንሰራውን ነውር ፈጣሪያችንን በመንጠቅ ሊቀጣን ሞከረ። አለማየሁ ገላጋይ አመነ። ይሄን ጠርጥሬ ነበር መፅሐፉን ያቋረጥኩት፤ አለማየሁን በሌለበት ያኮረፍኩት።
አሌክስዬ እንታረቅ ...
አንተ እግዜራችንን ባትነጥቀንም በዚህ መካከል እግዜር አይኖርም። ቪዲዮ እየቀረፁ በሚተራረዱ ሰዎች መካከል ፈጣሪ እንዴት ይኖራል? ለመገዳደል ቀጠሮ በሚያያዙ ሰዎች መካከል እሱ ምን ይሰራል? አንተ ባትወስድብንም ቅሉ እግዜር ቀድሞ ተሰዷል።
Etsegenet Kebede-
Read 5235 times Last modified on Saturday, 22 August 2026 11:00