Monday, 20 July 2026 09:56

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ዓሊ አህመድ አዲስ አበባ ገብቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን እና የእንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ ክለብ ተጫዋች ዓሊ አህመድ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገብቷል። ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርስም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ዲፓርትመንት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።

የተጫዋቹ ወደ ሀገር ቤት መምጣት በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ የተደረገ ሲሆን፣ ዓላማውም በሀገሪቱ የስፖርት ልማት ላይ አዎንታዊ አሻራ ለማሳረፍና ወጣቶችን ለማበረታታት ነው። የውጭ ጉዳይ፣ የባህልና ስፖርት፣ የቱሪዝም ሚኒስቴሮች እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ የሚያደርገው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን እየሰሩ ይገኛሉ።

ዓሊ አህመድ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን 28 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፣ በ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫም በአራት ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ታሪካዊ ጉዞ አድርጓል። በሜጀር ሊግ ሶከር ባሳየው የላቀ ብቃት በጥር 2026 ወደ እንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ ያመራው ዓሊ፣ የደረሰበት የስኬት ደረጃ ለበርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ትልቅ ተነሳሽነት የሚፈጥር ነው።

Read 704 times