በሸገር ሬድዮ "ማንን ምን እንጠይቅልዎ?" ፕሮግራም ላይ የቀረበውና በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 2 የተፈጸመው አሳዛኝ ክስተት፣ ከቀላል የአጥር ማጠር ጉዳይ ባለፈ የዜጎችን መሠረታዊ መብትና የሥልጣን ወሰንን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል እጅግ አሳሳቢ ድርጊት ነው።
ጉዳዩ ቀደም ሲል በወረዳው አመራር ይሁንታ ተሰጥቶት የፈረሰ፣ በኋላም ይቅርታ ተጠይቆበትና በባለቤቱ ኪሳራ በድጋሚ እንዲታጠር የተደረገ ቢሆንም፣ የደንብ ማስከበርና የጸጥታ አካላት በድጋሚ የፈጸሙት ነገር ህገ-ወጥነት የነገሠበት ሆኗል።
አጥሩ በድጋሚ የፈረሰው ዓርብ ቀን ከምሽቱ በ4:00 ሰዓት፣ በበርካታ መኪኖች በመታጀብ ፖሊሶች መሣሪያ ይዘው መጥተው፣ ከቤት ውስጥ ሰው አፍነው ወስደው፣ መኪና ውስጥ አስገብተው በዱላ ደብድበው መሆኑ ነው። በዚያ ላይ ጎረቤት ሲወጣ ተመለስ እያሉ እያስፈራሩ ይመልሱ ነበር ተብሏል።
ይህ ድርጊት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት በኋላ ወደ ግል ይዞታ መግባትን የሚከለክለውን የሕግ አሠራር በግልጽ የጣሰ ከመሆኑም በላይ፣ ጥፋት እንኳ ቢኖር በጠራራ ፀሐይ ሕግን ተከትሎ መሥራት ሲቻል በምሽት ተደብቆ መምጣት ምን ዓይነት አሠራር እንደሆነ አጥብቆ ያጠያይቃል።
የክፍለ-ከተማውና የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ለጉዳዩ ፈጣን ምላሽ ከመስጠት በመሸሽ ዝምታን መምረጣቸው፣ የአመራሩን ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። እንዲህ ዓይነቱ አምባገነናዊና ኢ-ሰብአዊ የኃይል እርምጃ በከተማችን ላይ ስጋት የሚደቅንና በገጠር የሚሰሙት የጸጥታ መደፍረሶች በሕጋዊ አካላት ስም ወደ ዋና ከተማዋ እንዳይገቡ "ሳይቃጠል በቅጠል" ልንከላከለው የሚገባ አደገኛ ምልክት ነው።
በመሆኑም፣ ይህ በዜጎች ሰላም፣ መብትና ንብረት ላይ የተፈጸመው በደል "ነግ በኔ" የሚያሰኝ በመሆኑ በጥቃቅን ስህተቶች ሰበብ የሕዝብን እምነት የሚያጠፉና የቤተሰብን ፀጥታ ያወኩ አካላት ላይ አፋጣኝ የስነ-ስርዓትና የሕግ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።
አዲስ አበባ ነዋሪዎቿ በሰላምና ያለስጋት የሚኖሩባት ከተማ እንድትሆን፣ በፖሊስና በጸጥታ አካላት በኩል የተጀመሩ መልካም እንቅስቃሴዎች በእንዲህ ዓይነት ድርጊቶች መበላሸት የለባቸውም። በመጨረሻም፣ ይህንን እጅግ አሳሳቢ የመብት ጥሰትና የአሠራር ጉድለት አውጥቶ ለሕዝብ ድምፅ ለሆነው ለጋዜጠኛ ግርማ ፍስሐና ለሸገር ሬድዮ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።
Get Toughe Zer ·
ከዝግጅት ክፍሉ፡- ጽሁፉ ከኦሪጂናሉ በመጠኑ አጥሮና ኤዲት ተደርጎ የቀረበ ነው፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

