በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው ሰው ሰራሽ «ንጋት ሐይቅ» ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ ታላቅ የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ ነው። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከሐይቁ ከ10 ሺህ 700 ቶን በላይ የዓሣ ምርት የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የምርት መጠኑን በአንድ ጊዜ በእጥፍ እንዲያድግ አድርጎታል።
ይህ አስደናቂ ስኬት የተመዘገበው በሐይቁ ላይ ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ 46 የዓሣ አስጋሪ ማህበራት አማካኝነት መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ንጋት ሐይቅ በዓሣ ምርት የክልሉን የኢኮኖሚ መሠረት ከማጠናከሩም ባሻገር፣ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት እንዲቀይሩ ትልቅ በር ከፍቷል። ከዚህ በተጨማሪም ሐይቁ የያዛቸው ከ70 በላይ ውብ ደሴቶች ለአካባቢው የቱሪዝም መስህብ እና ለውሃ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ አዲስና ተስፋ ሰጪ ዕድሎችን እየፈጠሩ እንደሚገኙ የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

