Saturday, 06 June 2026 19:36

“ሕገመንግሥታዊ ተቃርኖዎች”   ለአውደ ርዕይ ያቀረበው ሙግት

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

ማስፈንጠሪያ

 የአብርሆት ዘመን ፍሬ የሆነው የፈረንሳይ አብዮት  ለሰው ዘር  አኑሮት ያለፈው አበርክቶ በቁጥር አይገፋም፡፡ በተለይ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ ካስማ የሚቆጠሩትን፤በግብር ለእየቅል ፣በኅላዌ ግን የማይነጣጠሉትን ወንድማማችነት፣ እኩልነትና ነጻነትን ለአውደ ርዕይ በማቅረቡ ምክንያት በፋናወጊነት ይጠቀሳል፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ ብሶት የወለደው ሕዝባዊ አብዮት፤ የዘመናዊው ሥነመንግሥት የሚመራበት ሕገመንግሥታዊ ሰነድን በማስተዋወቅ ረገድ የጉልላት ሥፍራን ይይዛል፡፡ ከፈረንሳይ አብዮት ለጥቆ የመጣው ሕገመንግሥት በዋንኛነት ጣምራ ግቦችን ከግምት ጥፎ ነው ገቢራዊ የሆነው፡፡ ቀዳሚው ግቡ፤በሀገረመንግሥቱ የሥልጣን መንበር ላይ የሚቆናጠጠው መንግሥት ሥልጣን እንዲገደብ አስተማማኝ ልጓም ማበጀት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የዜጎች ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች የሚከበርበት ሥርዓት እንዲፈጠር አስተማማኝ መደላድል ማኖር  ነው፡፡  

 
 የሕዝብ ሉኣላዊነት መገለጫ የሆነው ሰነድ ከሀገራችን ሥርዓተመንግሥት ጋር የተዋወቀው በንጉሡ ዘመነ መንግሥት በ1923 ዓ.ም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሀገራችን የሥርዓተመንግሥት የታሪክ ሒደት ውስጥ የአሁኑን  የሕወሓት/ኢሕአዴግን ጨምሮ አራት ሕገመንግሥታዊ ሰነዶች ተቀርጸው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡   
 
ለዛሬ የመጽሐፍ ዳሰሳ ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ፤ የ1997 ዓ.ም ድህረ ምርጫ ሁከት አጣሪ ኮሚሽን ሰብሳቢ የነበሩት ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል ለሕትመት ብርሃን ያበቁት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ ሽንጣም ድርሳን፣ “ሕገመንግሥታዊ ተቃርኖዎች” በሚል ርዕስ፣ በ297 ገጽ የቀነበበና በሰላሳ ሁለት ምዕራፎች የተከፋፈለ ጠንከር ያለ ሒስ የታጨቀበት ነው፡፡ በርግጥ፤ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ለሕትመት ብርሃን ከበቁት መጻሕፍት  መካከል የነገደ ጎበዜ ኩርማን ድርሳን ትርጉም ሰጥታኛለች፡፡ ይቺ በመዳፍ ልክ የተከረከመች ድርሳን ለአንባቢያን በብዛት እንድትዳረስ ምክንያት የሆነው አቶ  በረከት ስሞን በምርጫ 97 የቴሌቪዥን ክርክር ላይ በክፉ ማብጠልጠላቸው ነበር፡፡ የማስታወቂያ ፉንጋ የለውም እንዲሉ፤ በወቅቱ ጸሐፊው ነገደ ጎበዜ፣ “የበረከት ውለታን ከፍዬ አልጨረሰውም፤ በቴሌቭዥን ላይ ያለምንም ክፍያ መጽሐፌን ባያስተዋውቁልኝ ኖሮ፤በርካታ አንባቢያን ዘንድ አይደርስም ነበር” ብለዋል፡፡ ከነገደ ጎበዜ መጽሐፍ በኋላ ለእኔ በአቀራረቡም ሆነ ባነሳቸው ቋጥኝ ቁምነገሮች ፣የዳኛ ፍሬሕይወት “ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች ድርሳን” በብዙ ረገድ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
 
ሁለቱ  የገሃነም  ጫፎች
 
ጸሐፊው  በሕገመንግሥታዊው ሰነድ ዙሪያ የሚራመዱትን ማዶ ለማዶ የሆኑ የተቃርኖ አቋሞችን ለአውደ ርዕይ በማቅረብ ነው ኂሱን የሚያሟሸው፡፡ ሕገመንግሥቱ ተቀዶ ካልተጣለ  ለሀገራዊ ምስቅልቅሉ ምንም አይነት መላ ማበጀት አይቻልም፤የሚል ሥርነቀላዊ አቋም በአንደኛው ጠርዝ የሚያስተጋቡ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፡፡ በአንጻሩ ከሕወሓት ጋር ኩታገጠም የፖለቲካ እሳቤን የሚያቀነቅኑ ልሂቃንና ቡድኖች ደግሞ፤ ሕገመንግሥቱ የሚለወጠው በመቀብራችን ላይ ነው፤ይላሉ፡፡ የሁለቱም አቋም አንዱን በአንዱ የሚያጣፋ ነው፡፡ በአንዱ መቃብር ላይ ሌላው አበባ ያኖራል፡፡ ንጽጽራዊውን ዕይታ፣ የሩቅ ምሥራቅ ፈላስፎች በሁለት ገሀነም መካከል ገነት አለ፤ በሚል ግሩም ምልከታ ይገልጹታል፡፡ ጠርዝ እና ጠርዝ ላይ የተሰየሙት አቋሞች የገሃነሙ ጫፍ ናቸው፡፡ አማካኙ፣ ገነቱ ከአመክንዮ ያልተራቆተ፣ በሰከነ ውይይት ቋጠሮዎች የሚፈቱበት አውድ ነው፡፡ ጸሐፊው  ይህንን ምራቅ የሚያስውጥ ግብዣ እንካችሁ ብሎ ነው፤ ወደ ውስጥ የሚያንደረድረን፡፡
 
የሰነዱ  ዘረመል  እንዴት  ተበጃጀ?
 
በ1960ዎች የተማሪዎች ንቅናቄ እንደዋዛ በጥራዝ ነጠቅነት የተዘራው የግራ ዘመም ፖለቲካ ዛሬ ለገባንበት ቅርቃር መነሾ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡ Modernity,Eurocentrism, and radical politics in Ethiopia, 1961-1991 በሚለው ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ “instead of Marxism adapting to Ethiopia, it was made to adapt to Marxism” በሚል ግሩም ሐረግ ገልጾታል፡፡ማርክሲዝምንከኢትዮጵያነባራዊሁኔታጋርከማስማማትይልቅ፤ኢትዮጵያናትለማርክሲዝምነባራዊሁኔታእንድትመችየተከረከመችው፡፡እንደማለት ነው፡፡
 
በአልባኒያው የሄቨር ሆንጃ አክራሪ የሶሻሊዝም እሳቤ ተጠምቆ ሥልጣን ላይ የወጣው “የያትውልድ” ፍሬ ሕወሓት/ኢህአዴግ፤ በተንሸዋረረው ርዕዮተዓለማዊ አረዳድ ምን ያህል እንደቆረበ አንዱ ማሳያ፣ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ለተባለ እንግዳ ማንነት ያለው ታማኝነት እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይህ ምንነቱ በቅጡ ያልተብራራ ግራ እሳቤ የ1987 ሕገመንግሥት የማዕዘን ድንጋይ እንዲሆን መደረጉ ውሎ አድሮ ፖለቲካው ሐዲዱን እንዲስት ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል፡፡ ጸሐፊው የምስቅልቅሉ ዘፍጥረት የሚጀምረው ፓርቲው  ከትግል እንስቶ የቆረበበትን የግራ ዘመም ርዕዮተዓለም ለመተው ባለመፈለጉ የተነሳ ነው፤ ሲል ይሞግታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋቢ ያደረገው ፓርቲው ለጽንሰሐሳቡ ያሳየውን አምልኮ ነው፡፡ ገጽ 11 ላይ ከሰፈረው በጥቂቱ፡-  
 
በማርክሲዝምሌኒኒዝምመዝገበቃላትውስጥየግለሰብናየኅብረተሰብልዩነትናአንድነትየግለሰቡጥቅምሊረካየሚችለውበወልጥቅምማደግ፣የወልጥቅምማደግየሚችለውበግለሰቡንቁተሳትፎነውበሚልተገልጾይገኛል፡፡በዚህመሠረትየሕገመንግሥቱአርቃቂዎችየብሔሮችብሔረሰቦችሕዝቦችየወልመብትናጥቅምሲጠበቅየግልጥቅምይጠበቃልየሚለውንኮሚኒስታዊጽንፈኛእሳቤመዋቅራዊእንዲሆንየማዕዘንድንጋይጥለዋል፡፡
 
የሕገመንግሥቱ አልፋና ኦሜጋ የሆነው ብሔረ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተባለው የወል ማንነት የተቀዳው ከትላንቱ ቆመ ቀር የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ ከጸሓፊው ትንታኔ እንረዳለን፡፡  ሕገመንግሥቱ ገና በመንደርደሪያው ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች  ከሉአላዊ ሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው ቆርሰው ኢትዮጵያን እንደፈጠሯት ደንግጓል፡፡ በሰነዱ መሠረት፤ ኢትዮጵያ ትላንት በ1987 ዓ.ም በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መልካም ፍቃድ ምክንያት የተፈጠረች ልጅ ናት፡፡ ለዚህም ነው ሕገመንግሥቱ ከፌደራል ሥርዓት ይልቅ የኮፌንደራል ሥርዓትን ያወለደ ነው፤ ተብሎ የሚሞገተው፡፡ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንቀጽ 8 መሠረት የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት ሆነዋል፡፡ ለሉኣላዊ ሥልጣናቸው መገለጫ ደግሞ በአንቀጽ 47 መሠረት የራሳቸው ቤት (ክልል)ተሰጥቷቸዋል፤ይህም ካልተስማማቸው በአንቀጽ 39 አማካኝነት የራሳቸውን “ባናና ሪፐብሊክ” እንዲመሠርቱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህ ሐዲድ ውስጥ በዜግነት ወይም በግለሰብ  የሚገኘው ማንነት ሜዳ ላይ ተጥሏል፡፡ ጸሐፊው የሚጎፈንነው እውነታ ተለንቅጦ የተበጃጀበትን ዘረመል፣  ሽክን ባለቋንቋ ንቃታችንን ለማብራት እያሰለሰ ደፋ ቀና ይላል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ሥልጣን መያዣ ዋንኛ ቅኝት ብሔር/ብሔረሰብ ላይ ሲቸነከር የሚያመጣውን ጣጣ በምዕራፍ 31 በግሩም ሁኔታ አመላክቷል፡፡
 
አልቦ  የቁጥጥር  እና  ሚዛን  ሥርዓት

 

 ጸሐፊው ሕገመንግሥቱ ለቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓት/Checks and balance/ ምን ያህል ባዓድ እንደሆነ ለመሞገት በዋቢነት የሚያነሳው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚናን ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚወልደው ሕገመንግሥታዊ ሰነድ፣ የሦስቱ ምክር ቤቶች ቁመናን ልክ እንደ ማበጠሪያ ጥርስ በእኩል ደረጃ እንዲከረከሙ ያደርጋል፡፡ ግንኙነታቸው አንዱን ሌላውን ለማስገበር በሚመች መልኩ፣ በተዋረዳዊ ሰንሰለት የተዋቀረ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ፤ የአንዱ ምክር ቤት ከሌላው እንዳይበልጥ በአግድሞሽ የቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓት ልጓም እንዲበጅለት ይሆናል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሥርዓት በእኛ ሀገር ዱካውም የለም፡፡ በተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት መካከል ያለውን ግንኙነትን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ በመካከላቸው የሥራ ክፍፍል እንጂ፤ የሥልጣን ከፍፍል የለም፡፡ መጽሐፉ የአልቦ የቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓቱን ስስ ጎን ከምክር ቤቶቹ ሚና አንጻር ይሄሳል፡፡
 
 የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሌሎች የፌደራላዊ ሥርዓት በሚከተሉ ሀገራት ዘንድ ያለው ቁመና እና ሚና ክእኛ ጋር ለእየቅል ነው፡፡ ም/ቤቱ በሕገመንግሥቱ መሠረት የተዋቀረበት መርህ፣ ፀረ ፌዴራላዊ መንገድን ተከትሎ ነው፡፡ በፌደራል ሥርዓት ውስጥ እንደ ፌዴሬሽን ያሉ የግዛት ተወካዮች የሚካተቱበት ምክር ቤት፣ ዋንኛ ዓላማ ከተወካዮች ምክር ቤት ጋር መሳ ለመሳ ሆኖ ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዲኖረው ነው፡፡ ለአብነት፤ የአሜሪካውን የፌዴሬሽን ም/ቤትን /ሴኔትን/ብንወስድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት/congress/ጋር እኩል ሕግ የማውጣት ሥልጣን አለው፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች ሴኔት እና ኮንግረስ ከ 2/3 ድምጽ በላይ አጽድቀው ያሳለፉትን ረቂቅ፣ የአስፈጻሚው ቁንጮ የሆነው ፕሬዝዳንቱ የመሻር ሥልጣኑን/ቬቶ ፓወርን/ ተጠቅሞ ውሳኔውን ማጠፍ አይችልም፡፡
 
በአንጻሩ የእኛ የፌደሬሽን ምክር ቤት  ከሕግ አውጪነት ሚና ተገልሎ ወይም የበይ ተመልካች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምክር ቤቱ፣ ሕገመንግሥቱ የሰጠው ሥልጣን፣ የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን ጉዳዮችን እና አሻሚ የሕገመንግሥት ትርጓሜ ላይ ብይን መስጠት እንዲችል ነው፡፡ ክልሎች ከድንበሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በራሳቸው እልባት መስጠት ከተሳናቸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ብይን እንደሚሰጥ አንቀጽ 48 ላይ ተደንግጓል፡፡ 
 
እንዲህ አይነቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ያልሆነ የካድሬዎች ስብስብ፣ ሕገመንግሥቱን በተመለከተ ሚዛናዊ ፍርድ ይሰጣል ብሎ ማሰብ የዋህንነት ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጸሐፊውን ሙግት በገጽ 126 ላይ እናገኛለን፤-
 
 ሕገመንግሥቱንየመጣስችግርበባህሪውየሚመነጨውበዋናነትከመንግሥትነውካልንሕገመንግሥቱተጥሷል ? ወይንስአልተጣሰም? የሚለውንክርክርየመዳኘትሥልጣንመልሰንየመንግሥትአካልየሆነውየፌዴሬሽንምክርቤትእንዲመረምረውማድረግመንግሥትራሱሕግከጣሰበኋላራሱንመልሶበራሱእንዲዳኘውመፍቀድስለሆነአንድአካልበራሱጉዳይራሱዳኛሊሆንአይችልምየሚለውንመሠረታዊየሕግመርህይጥሳልየሚልክርክርያስነሳል፡፡
 
በሌሎች ሀገሮች ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ለሆነ የዳኝነት አካል ነው የሚሰጠው፡፡ ጸሐፊው ሕገመንግሥት የመተርጎሙም ጉዳይ ለመደበኛ ፍርድ ቤት ወይም ሰነዱን ለመተርጎም ብቻ ተብሎ ለተቋቋመ የሕግ አካል ብቻ የሚሰጥበትን ፍኖተ ካርታ በምዕራፍ 18 ላይ አመላክቷል፡፡
 
መጽሐፉ  የሳሳባቸው  ጎኖች
 
ጸሐፊው ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተያይዞ የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ላይ የጉልላት ሥፍራን ለያዘው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት የሰጠው ሽፋን በቂ አይደለም፡፡ ትርክቱ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በሕገመንግሥቱ መንደርደሪያ ላይ እንደዋዛ ሻጥ ያለው “የተዛባ ግንኙነትን ለማረቅ” የሚለው ሐረግ ውሎ አድሮ ትልቅ የፖለቲካ ሽንቁር ፈጥሯል፡፡ ጨቋኝ ተጨቋኝ ዳይኮቶሚ የዚህ ስንኩል ሐረግ የአብራክ ውጤት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
 
ጨቋኝ እና ተጨቋኝ የሚለው ዳይኮቶሚ ምንጩ የተንሸዋረረ ሶሻሊስታዊ ግንዛቤ ነው፡፡ በሶሻሊስታዊ ትንታኔ ኅብረተሰባዊ ዕድገት የሚተነተነው በመደባዊ ቅራኔ ሲሆን መደባዊ ቅራኔው በአንብሮ(thesis) እና በተቃርኖ(antithesis) መስተጋብር አስተጸማሮን(synthesis)ይፈጥራል፡፡  ለአብነት በካፒታሊዝም ሥርዓት ውስጥ ላብአደሩ እና ከበርቴው ተቃርነው በአስተጻምሮ መልኩ ሶሻሊዝምን ይወልዳሉ፡፡  ይህንን ዲያሌክቲካዊ ጭውውት በሀገራችን ነበራዊ ሁኔታ ዱካውን አናገኘውም፡፡ ያ ትውልድ ውጥምዱን ያለፈው ተቃርኖውን ለብሔረሰባዊ ማንነት በመስጠት ነበር፡፡ የ ያ ትውልድ የአብራክ ውጤት የሆነው ሕወሓት በበርሃ በቀረጸው ማኒፌስቶ  ላይ በግልጽ ሰፍሮ የምናገኘው “ጨቋኙ የአማራ ገዢ መደብ” ምንጩ የትላንቱ የተንሻንፈፈ የዋለልኛዊ ንጽረተ ዓለም ውጤት ነው፡፡
 
 የሕወሓት ማኒፌስቶ ግልባጭ ደግሞ በሕገመንግሥቱ መንደርደሪያ ላይ እናገኘዋለን፡፡ በጨቋኝ እና ተጨቋኝ የተዛባ ግንኙነት ማዶ ለማዶ የተሰየሙት ሕዝቦች በጋራ መጥተው የፈጠሩት ሰነድ ውሎ አድሮ ማኅብራዊ መስተጋብርን የሚበጣጥስ ሥርዓተመንግሥትን ወልዷል፡፡ በተለይ ላለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት በጨቋኝነት የተፈረጀው የአማራ ሕዝብ በሌሎች ብሔረሰቦች ዘንድ ጥርስ ተነክሶበት  የመከራን ጽዋ ሲቀበል ኖሯል፡፡ ዋለልኝ አልሞተም ሕያው ነው፤የሚባለው አማራን በጨቋኝነት፣ሌሎችን ብሔሮች ደግሞ በተጨቋኝነት የፈረጀ ሥርዓተመንግሥትን  ሥጋ ለብሶ በመመልከታችን  ነው፡፡ ጸሐፊው የጨቋኝ ተጨቋኝ ዳይኮቶሚን የራሱ ምዕራፍ አብጅቶለት በተብራራ መልኩ ሊያሳየን ይገባ ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፍሬው በሚመዘንበት ጊዜ ይህን ስሁት ተቃርኖ በቅጡ አለመፈተሽ ሙግቱን ምልኡ አያደርገውም፡፡
 
ጸሐፊው ብልጽግናን የብሔር ዘመም ድርጅት እንዳልሆነ ያሳየው ዳርዳርታ ሊሂስ የሚያጋልጠው ነው፡፡ በገጽ 238 ላይ በብሔር ብሔረሰብ ተደራጅቶ ሥልጣን መያዝ የሚያመጣውን ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጣጣ ያመላከተ ሲሆን የመውጪያ መፍትሄው ልክ እንደ ብልጽግና ሕብረብሔራዊ የሆነ ቁመናን ተላብሶ መደራጀት እንደሆነ ያስረግጣል፡፡ እዚህ ጋር የተቀመጠው የጸሐፊው ሐሳብ ግንሳሃ አያነሳም፡፡ ብልጽግና የሚመራው መንግሥት፣ ብሔር ተኮር ከሆነው የፖለቲካ አደረጃጀት አዙሪት ለመውጣት አሳማኝ አዝማሚያ እያሳየን አይደለም፡፡ እንደውም፤ በአንዳንድ ዘርፎች ከሕወሓት/ኢህአዴግ በባሰ መልኩ የእሳቤው ቁራኛ ሆኖ እንመለከታዋለን፡፡ ለአብነት፤ በቅርቡ የብቃት እና አቅም (meritocracy) ነጻ ቀጠና በሆነው ቢሮክራሲዊ አደረጃጀት ላይ የብሔር ቀመር በማበጀት ቆፈን ውስጥ የሚከት እርምጃዎችን ለአውደ ርዕይ አቀርቦልናል፡፡ ስለዚህ ብልጽግናን በነቢብ  ሕብረብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፤ብሎ ከመፈረጅ ባለፈ ከብሔር/ብሔረሰብ የፖለቲካ አደረጃጀት ነጻ እንደወጣ ማሳያ ሊሆን አይችልም፡፡ ምንአልባትም ጸሐፊው የብልጽግና ተሞክሮን  ማንሳቱ ካልቀረ ሕጸጹን አብሮ ማመላከት ቢችል ኖሮ ትርጉም ይሰጥ ነበር፡፡
  
በአጠቃላይ “ሕገመንግሥታዊ ተቃርኖዎች” መጽሐፍ ያነሳቸው የሙግት ሐሳቦች እና የመፍትሄ አማራጮች ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት (እዚህ ጋር የምክክር ኮሚሽንን ልብ ይሏል) ከምር የሚወስዳቸው ከሆነ ላለፉት ሦስት ዐሥርተዓመታት ሀገረመንግሥቱን በብርቱ ይንጡት ከነበሩ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎሽ ለመውጣት የሚቻልበትን ፈር ያገኛል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

 

Read 9374 times