በኦሮሚያ ክልል ወለንኮሚ መንደር በገበሬ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉትና የእናታቸው የትምህርት ፍላጎት መሠረት ሆኗቸው እዚህ ደረጃ የደረሱት ፕሮፌሰር ገቢሳ እጄታ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው በጉልህ የሚጠቀስ ታላቅ ሳይንቲስት ናቸው። መደበኛ ትምህርታቸውን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ካጠናቀቁ በኋላ፣ በአሜሪካው ፑርዱ ዩኒቨርሲቲ በዕፅዋት ዘረ-መል (Plant Breeding and Genetics) የማስተርስና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በአሁኑ ወቅት በዚሁ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በክብር ፕሮፌሰርነትና በዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ማዕከል በአማካሪነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ፕሮፌሰር ገቢሳ በዓለም ላይ ካስመዘገቧቸው ድንቅ ስኬቶች መካከል ዋነኛው "ስትራይጋ" የተባለውንና የማሽላ ሥርን በመጥባት ሰብልን የሚያጠፋውን አስከፊ አረም መቋቋም የሚችል የማሽላ ዝርያ ማበልጸጋቸው ነው። በላብራቶሪ ምርምር አረሙ ከማሽላው ሥር ጋር እንዳይጣበቅ የሚያደርገውን ባዮ-ኬሚካላዊ ሂደት በመለየት፣ ድርቅንና አረምን በአንድነት የሚቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ አዲስ ዝርያ ፈጥረዋል። ይህ ታሪካዊ ግኝታቸው በኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኒጀርና በሌሎች ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ከረሃብ የታደገ ታላቅ የፈጠራ ሥራ ሆኗል።
Ethio Agri News

