Thursday, 30 October 2025 13:27

ከ100 በላይ ዓለማቀፍ የእንስሳት ሃብት ተዋናዮች የሚሳተፉበት የንግድ ትርዒት ተከፈተ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
* ከ5 ሺሕ በላይ ሰዎች ይገበኙታል ተብሎ ይጠበቃል
ከ14 አገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ተዋናዮች የሚሳተፉበት የንግድ ትርዒት ዛሬ በአዲስ አበባ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል። በዚህ የንግድ ትርዒት ላይ ከ5000 በላይ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካና ዓለም አቀፍ አገራት ጎብኚዎች እንደሚጠበቁ ተነግሯል።
በዚሁ የንግድ ትርዒት ስር፣ 14ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ (ኢትዮቼከስ)፤ 10ኛው የአፍሪካ እንሰሳት ዓውደ ርዕይና ጉባዔ (አሌክ) እንዲሁም 5ኛው የአፒካልቸር እና አኳካልቸር ኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የንግድ ትርዒትና ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው የባዮ ኢነርጂ የንግድ ትርዒት በአንድነት የሚከናወኑ ሲሆን፣ በንግድ ትርዒቱ ላይ ጥራት ያላቸው የዘርፉ ዋነኛ አንቀሳቃሾች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
የፕራና ኢቨንትስ የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ሜሮን ስሎሞን እንደተናገሩት፣ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ዓውደ ርዕይና ጉባዔዎች ለዶሮ፣ ዕንቁላል፣ ወተትና ስጋ ንዑስ ዘርፎች ዕድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል። አክለውም፣ "እነዚህ ሁነቶች ለዘርፉ ባለሞያዎችና ለንግዱ ማሕበረሰብ ትልቁ መሰባሰቢያ በመሆናቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ አዳዲስ ቴከኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የዕውቀት ሽግግርን በማምጣት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ ለዘርፉ ልማት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማረጋገጥ ችለዋል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕራና ኤቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን ባደረገው አጋሩ ኤክስፖ ቲም ትብብር የሚዘጋጀው ሁሉን-አቀፍ የእንስሳት እርባታ ቴከኖሎጂ፣ ግብዓት እና መፍትሔዎች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ዓለም አቀፉ የንግድ ትርዒት፣ የእንስሳት ሃብት የገበያ ስንሰለቶች ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የዕውቀትና የቴከኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ኔዘርላንድን ጨምሮ ከ14 አገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ የዘርፉ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ባሕላዊ የዶሮ እርባታ እስካሁን በስፋት የሚዘወተር ልምድ መሆኑን በመድረኩ ላይ ሲጠቆም፣ ዘመናዊ የዶሮ እርባታን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስፈላጊውን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚዘጋጅ ብቸኛው የዘርፉ ዓለም አቀፍ ሁነት የኢትዮ ዶሮ ኤክስፖ መሆኑም ተጠቅሷል። እንዲሁም የአፍሪካ የእንስሳት ሃብት ዓውደርዕይና ጉባዔ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ባለቤት መሆኗ ባያጠራጥርም፣ በዘርፉ ያላት ምርታማነትና የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ከዓለም ዝቅተኛ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የወተት እና የስጋ ዘርፉን በዘመናዊ መልክ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት "መድረክ ነው" ተብሏል።
የንግድ ትርዒቱ ከጥቅምት 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።
 
 
 
Read 993 times