የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገ/መስቀል፣ የኢትዮጵያው ገዥ ብልጽግና ፓርቲ በባሕር በር ጉዳይ ላይ የሚከተለው "አምታች የኾነ አካሄድ" በቀጠናው ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል በማለት ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በኤርትራ ላይ "የጦርነት ዛቻ" ማሰማት ቀጥለዋል በማለት የከሠሡት ቃል አቀባዩ፤ በሌላ በኩል ደሞ ብልጽግና ኢትዮጵያን ከምጽዋ፣ አሰብና ከጅቡቲዋ ታጁራ ወደብ ጋር የሚያገናኝ የባቡር ሐዲድ ለመገንባት እንዳቀደ በመግለጽ፣ "አምታች አካሄድ" ይከተላል በማለት ተችተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚህ ሳምንት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ በወደብ ጉዳይ ከተናገሩ በኋላ ቃል አቀባዩ በሰጡት ምላሽ፤ ብልጽግና ፓርቲ በአሰብ ወደብ ዙሪያ የሚያሠማው "ቅዠት" እየተባባሰ ሄዷል ብለዋል፡፡
አቶ የማነ፣ ማክሰኞ'ለት በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ የተሠማው ትርክት፣ "ከተቻለ በድርድር፤ ካልተቻለ በወታደራዊ ወረራ የአሰብ ወደብ ባለቤት እንኾናለን" የሚል ይዘት አለው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የቅኝ ግዛት ትርክት ሲቃኝ የኖረው ማራኪ በሚመስሉ አመክንዮዎች ወይም ሕዝቦችን የማሠልጠን ተልዕኮ በሚል ምክንያት ነበር ያሉት ቃል አቀባዩ፤ "ሞኛሞኝ የሆነው የብልጽግና ትርክት ግን በዘመናዊ ታሪክ ተሠምቶ አያውቅም" ብለዋል።
(ዋዜማ)


