* በ12 ብር ብቻ ስራ ለማመልከት የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ተደርጓል
ማርቭል ክሬቲቭ ቴክኖሎጂ "መላ ጆብስ" እና "መላ ገበያ" የተሰኙ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድሎችን የሚፈልጉባቸውና የሚያመለክቱባቸው እንዲሁም የሚገበያዩባቸው ዲጂታል መተግበሪያዎችን ይፋ አደረገ። በሌላ በኩል፣ ማርቭል ክሬቲቭ ቴክኖሎጂ አርቲስት ሰለሞን ሙሄን ብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾሟል። በዚሁ ሹመት መሰረት፣ አርቲስቱ የማርቭል ክሬቲቭን ምርቶች በማስተዋወቅ ለአንድ ዓመት ያህል አብሮ እንደሚሰራ ለማወቅ ተችሏል።
መተግበሪያው ይፋ የተደረገው በዛሬው ዕለት፣ በአዲስ አበባ፣ ሳውዝጌት ሆቴል በተከናወነው መርሐ ግብር ላይ ሲሆን፣ ዕውቅ አርቲስቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች ተገኝተዋል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተደገፈው ይህ መተግበሪያ፣ ደንበኞች ምርቶችን የሚገዙበት እንዲሁም የሚሸጡበት "ጭምር ነው" ተብሏል።
ማርቭል ክሬቲቭ ቴክኖሎጂ ይፋ ያደረገው "መላ ጆብስ" የተሰኘው መተግበሪያ፣ ኢትዮጵያውያን ስራ የሚፈልጉበትንና የሚያመለክቱበትን መንገድ ቀላል ስለማድረጉ ሲነገር፣ ተጠቃሚዎች ለአገር ውስጥ የስራ ማመልከቻ 12 ብር ብቻ፣ ለዓለም አቀፍ የስራ ማመልከቻ ደግሞ 30 ብር በመክፈል በመላ ጆብስ አማካይነት በቀላሉ ማመልከት እንደሚችሉ ተነግሯል።
መላ ጆብስ ከመሰረታዊ የስራ ማስታወቂያዎች ባሻገር ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ሲገለጽ፣ ተጠቃሚዎች ለስራ ቀጣሪዎች ጎልተው እንዲታዩ የሚያስችላቸውን፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች ጋር የሚስማማ ሞያዊ የስራ ልምድ (CV) በ"ራስ ሰር" የሚያዘጋጅ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተደገፈ የሲቪ ማዘጋጃ እንዳለው ተጠቅሷል።
መተግበሪያው ተጠቃሚዎች የስራ ልምዳቸውን በእያንዳንዱ ደረጃ የሚገልጽ ማብራሪያ ከመፍጠር ጀምሮ እስከ ለቃለ መጠይቅ መዘጋጀት ድረስ የሚመራ የኤአይ ቻትቦት ያካተተ መሆኑ "ለየት ያደርገዋል" ነው የተባለው።
ሌላኛው "መላ ገበያ" የተሰኘው መተግበሪያ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የኢ-ኮሜርስ (ኤሌክትሮኒክ ገበያ) ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል በጉልህ የሚጠቀሰው ያልተስተካከለ የዕቃ ክምችት (inventory) እና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ጥሬ ዕቃዎች መሆናቸውን በመርሐ ግብሩ ላይ የተነገረ ሲሆን፣ "መላ ገበያ" ይህንን ችግር የሚፈታው ትንታኔዎችን (analytics) እና ብልህ የዕቃ ክምችት አስተዳደርን በማቅረብ መሆኑ ተመላክቷል። ይህም የየምርቶቹ ሻጮች የምርት ብክነትን እንዲያስወግዱና ስራቸውን ቀልጣፋ እንዲያደርጉ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
የዚሁ መተግበሪያ ዋነኛ ዓላማ "በመስመር ላይ መገበያየትን ቀላል ማድረግ ብቻ ሳይሆን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን (SMEs) በመደገፍ የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ማጠናከር ጭምር ነው" ተብሏል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

