Monday, 15 September 2025 06:57

ሮማኒያ በሩሲያ የአየር ክልል ጥሰት እንደተፈጸመባት አስታወቀች

Written by 
Rate this item
(0 votes)
ድርጊቱ ሩሲያ ጦርነቱን እያሰፋች እንደሆነ የሚያሳይ ነው- ዘለንስኪ
በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት፣ ሩሲያ በዩክሬን መሠረተ ልማቶች ላይ በምትሰነዝረው ድንገተኛ የድሮን ጥቃት ምክንያት፣ በሮማኒያ አየር ክልል ላይ ጥሰት እንደተፈጸመ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህን ተከትሎም የኔቶ አባልአገር የሆነችው ሮማኒያ፣ ሁኔታውን ለመከታተል ተዋጊ ጄቶቿን ማሰማራቷን ገልጻለች፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፣ ሁለት F-16 ተዋጊ ጄቶች ወደ አየር ከተላኩ በኋላ፣ በሮማኒያ አየር ክልል ውስጥ የነበረ አንድ ድሮን መለየታቸውንና ከራዳር እስኪጠፋ ድረስ መከታተላቸውን አስታውቋል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የሩሲያ ድሮን ከሮማኒያ ግዛት እስከ 10 ኪሎ ሜትር ዘልቆ መግባቱንና ለ50 ደቂቃ ያህል በኔቶ አየር ክልል ውስጥ እንደቆየ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቅሰዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ድርጊት ሩሲያ ጦርነቱን እያሰፋች እንደሆነ የሚያሳይ ነው ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል።
ይህ ክስተት ፖላንድ የሩሲያን ድሮኖች አየር ክልሏን ከጣሱ በኋላ የኔቶን ምስራቃዊ ድንበር ለመከላከል ዕቅድ መያዙን ካስታወቀች ከጥቂት ቀናት በኋላ መከሰቱ፣ በአካባቢው ያለውን ውጥረት የበለጠ አባብሶታል ሲል መናኸሪያ ሬዲዮ ዘግቧል።
May be an image of aircraft
 
 
 
 
Read 287 times