ሁሉም ነገር አንጻራዊ ነው። የ "ሪፖርተር" ጋዜጣ ለ30 ዓመት የታመነ የመረጃ ምንጭነትም እንዲሁ አንጻራዊ ይሆናል። እና በበኩሌ ላለፉት 30 ዓመታት በሪፖርተር ጋዜጣ ልክ መሐል ቆሞ መረጃን በታማኝነት የሚያከፋፍል የሚዲያ ተቋም አላውቅም። በመሐል ታይተው የጠፉ እንደ " አዲስ ነገር " ያሉ ጋዜጦች ይኖራሉ። እነሱ ቢኖሩም ቁጥራቸው ጥቂት ፣ እድሜያቸውም አጭር ነው።
የሪፖርተር መስራችና ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ አማረ አረጋዊ ከሕወሓት ነባር ታጋዮች መሐል አንዱ የነበረ ነው። ያም ሆኖ ስለ ሕወሓት የጓዳ ምሥጢሮች ሳይቀር የምንሰማው ከሪፖርተር ነበር ፤ ነው። በቂ አልሆነ ይሆናል። አንጻራዊ ነው ብለናል። በሀገሪቱም ሆነ አቶ አማረ በታገለለት ሕወሓት አንኳር ጉዳዮች ላይ " በሚዛናዊነት " ሪፖርተር የሰጠንን ማንም አልሰጠንም።
ሕይወታችን ስላደረግነው አይታወቀን ይሆናል እንጂ እጅግ የምንበዛው በፖለቲካ፣ በብሔር ፣ በሀይማኖት ፣ በአስተሳሰብ ጽንፈኞች ነን። እንደ ሕዝብም የዴሞክራሲ ልምምድ የለንም። ከለመድነው መውጣት ፣ ከምንፈልገው በተቃራኒ የሆነን መስማት ልምምዱ የለንም። እኛ የሪፖርተር ጋዜጣ ወሳኝ ሰው ብንሆን ከምናደርገው አቶ አማረ አረጋዊ ብዙ ርቆ ሄዷል።
አቶ አማረ አረጋዊ ጣፋጩን የወጣትነት ክሬሙን ጊዜ የሰጠው ሕወሓት ለሚመራው ትግል ነው። ይሁንና በሕወሓት ክፍፍል ጊዜ ( አሁንም በአንጻራዊ መልኩ ) የሁለቱንም ጎራ ሀሳቦች በእኩልነት የምናነበው ከሪፖርተር ነበረ። አምነን የምናነበው ሪፖርተርን ነበረ። በምርጫ 97 ወቅት ሁሉም ብዙሀን መገናኛ ለሁለት የተከፈለበትና እንደ ዘመነ ቀይ/ነጭ ሽብር " ከኢሕአዴግ ወይም ከተቃዋሚዎች " የተባለበት ጊዜ ነበረ። መሐል ለመሆን የሚሞክር " ወያኔ " የሚባል ታፔላ የሚለጠፍበት ጊዜ ነበረ። ዜና ሲሰራም ትንሽ ተቃዋሚዎችን ከነካ ወይም መንግሥትን ( ሕግን ) የደገፈ ከመሰለ " የመንግሥት ዜና " የሚባልበትና በራሱ በፕሬሱ የሚዘመትበት ጊዜ ነበረ። ዋንኛው የቀድሞ " ወያኔ " አቶ አማረ የሚያሳትመው ሪፖርተር ጋዜጣ ነበረ የግራውንም ፣ የቀኙንም በእኩልነት (በመጠኑ ለተቃዋሚዎች ድምጽ እየሆነ ) ያቀርብ የነበረው።
የመንግሥትን አይነኬ ቦታዎች በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመስርቶ የሚነካው ሪፖርተር ነው። ሪፖርተር ትላልቅ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ከ " ትላልቅ " ሰዎች ጭምር ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን ያገኘውንም በአግባቡ የሚጠቀምበት ኃላፊነት የሚሰማው ጋዜጣ ነው። በወቅቱ በግሉ ፕሬስና በተቃዋሚዎች " ለወያኔ ያደላል " ሲባል በሕወሓት ሰዎች ደግሞ " እንደ ሌላው ፕሬስ ሁሉ ለተቃዋሚዎች ያደረና ኢሕአዴግን ለመጣል ከተባበሩት ጋር የወገነ " ተደርጎ ነበረ የሚቆጠረው። ይሁንና በኢሕአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎቹ " ታምኖ " የሚነበበውም ሪፖርተር ጋዜጣ ነበረ። " ሪፖርተር ምን አለ ? " የሚባል ነው። ይሄ ጋዜጣ ነው በህትመት ላይ እያለ 30 ዓመት የደፈነው።
አቶ አማረ አረጋዊ በአንድ በኩል በሌላው ዘንድ " ወያኔ " እየተባለ፣ በ " ወያኔዎቹ " ዘንድ ደግሞ በተቃዋሚነት ተፈርጆ እስከማውቀው ድረስ " ትግራይ አይረግጥም " የተባለ ( እንደሰማሁት ) ሰው ነበር። በሕወሓት ሰዎች ዘንድ " የእኛ " የማይባል ሰው እንደነበረ አውቃለሁ። ከአቶ መለስ ዜናዊም ፣ ከደህንነት ሹሙ ክንፈ ገ/መድህንም ጋር ግንኙነት ያለው ሆኖም በአቶ አማረ አረጋዊ ቦታ ላይ መገኘት ትልቅ የሞራል ድፍረትን የሚጠይቅ ነው። በባለስልጣን መጨበጥ ስንቱን አቅልጦ እንዳስቀረው አይተናል። የአቶ አማረ የለውጥ ሰውነት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የመጣ ሳይሆን ከዚያ ቀደም ብሎም የነበረ ነው።
ጋዜጠኛ ዘካሪያስ ኃ/ማርያም ( ነፍስ ይማር ) በአንድ ወቅት የነገረኝን ላስታውስ። አቶ መለስ ዜናዊ በለውጡ ዓመታት አካባቢ የዘመን መለወጫ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር ያደርጋሉ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዋዜማ የመዝናኛ ዝግጅቶች በርከት ያሉ ነበርና የፕሮግራም መጣበብ ያጋጥማል። ከፕሮግራሞቹ አንዱ ደግሞ ምሽቱን የሚተላለፈው የአቶ መለስ ዜናዊ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው። ይህን ያየው የቴሌቪዥን ጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ የወሰነው የአቶ መለስን ንግግር ቀንሶ በማግስቱ እንዲተላለፍ ማድረግ ነበር። " ' ይሄ ነገም ቢተላለፍ ችግር አያመጣም ፤ዛሬ በዓል ስለሆነ ሕዝቡ ይዝናናበት ' አለን" ነው ያለኝ።
ሪፖርተር " እንከን የለሽ " ጋዜጣ ነው እያልኩ አይደለም። የሰውም ፣ የአሰራርም ፣ የአመራርም ስህተቶች ይኖሩበታል። ይህ ያለና የሚጠበቅ ነው። የምናወራው ስለ ፍጽምና አይደለም። ፍጽምናም የለም። በእኔ እምነት ከ1984 በኋላ በዚህ ሀገር ከመጡ የግል ይሁን የመንግሥት ብዙሀን መገናኛዎች በሪፖርተር ልክ ለፕሬስ ነጻነት የቆመ ፣ የመንግሥትን እንከን ያሳየ ፣ ቱባ ባለስልጣናትን በመረጃ የደፈረ ፣ ብልሹ አሰራሮችን በድፍረትና በመረጃ የተጋፈጠ አለ ማለት አልደፍርም። ይህን ሀሳብ ብዙዎች ላይቀበሉት እንደሚችሉ አስባለሁ። ይሁንና እነዚያ ሰዎች ይህን ሁሉ ከሪፖርተር በተሻለ ያደረገ ማንንም አይጠሩም። የታመነ የዜና ምንጭ የሆነ ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ ፣ ራሱ አቶ አማረ መርካቶ ወስዶ በነጻ ጭምር ይሰጠው ከነበረው የጳጉሜ 6/1987 ዕትም ጀምሮ እስከ ዛሬ ጳጉሜ 2/2017 በጽናት የዘለቀው አንጋፋውና ብቸኛው የግል ጋዜጣ "ሪፖርተር" እንኳን ለ30ኛ ዓመትህ አደረሰህ።
-ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…




