Wednesday, 03 September 2025 18:15

ሚድሮክ በየወሩ እስከ 600 ሚ. ብር ደሞዝ ለሠራተኞቹ ይከፍላል

Written by 
Rate this item
(0 votes)
"ኢትየጵያን ከድህነት መንጋጋ ፈልቅቆ ማውጣት ግዴታዬ ነው"
የሼህ አል-አሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ከ74 ሺህ ለሚልቁ ሰራተኞቹ በየወሩ ከ500 - 600 ሚሊዮን ብር ደሞዝ እንደሚከፍል ምን ያህሎቻችን እናውቃለን?
ኢትዮጵያም የእናታቸው አደራ ሆናባቸው አል-አሙዲ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ በኢትዮጵያ ከተሰማሩበት ጊዜ አንስቶ በሶስት ምዕራፍ የፖለቲካ ትርጓሜ እየተሰጠባቸው ብዙ ውጣ ውረድ ገጥሟዋል፤ ሸራተን ሆቴል እስኪዘጋ ድረስ፡፡
አል - አሙዲን ከሳኡዲ ስለመጡ “ወሀቢያን ወደ ኢትዮጵያ ሊያስፋፋ ነው፤ የእስልምና አክራሪነትን ሊያመጣ ነው” በሚለው ጥርጣሬ ሸራተን ለጊዜው እንዲዘጋ ተወስኖ እና ሆቴል ሳይሆን መስጊድ ነው የሚል ወሬም ተናፍሶ ሆቴሉ ተዘግቶ ከተፈተሸ በኋላ ተረጋግጦ እንደገና ተፈቅዶ መከፈቱንስ እናውቅ ነበር?
ያኔ የኢህአዲግ መንግስትን ይቃወሙና ተችተው ይጽፉ የነበሩ እንደ እነ ጋሽ ጻውሎስ ኞኞ ያሉትን ሼሁ ጀርመን ልከው ማሳከማቸው፤ ቀጥሎም አርቲስቶቹን እነ ታማኝ በየነና ፀሀዬ ዮሀንስ ላይ ከመንግስት ሹሞች ጫና ሲበዛባቸው አላሙዲን አሜሪካ ወስደው መደገፋቸውን ተከትሎ፣ በመንግስት በኩል ጥርጣሬው መባሱን፤ በዚህ ሳያበቃም - አፍቃሬ ደርግ ተብለው እንደነበርም በሚድሮክ በጣም መረጃ ሰጪ ዶክመንተሪ ላይ ተጠቅሷል፡፡
“አፍሪካ ከልቤ ብትሆንም - ኢትዮጵያ ግን የእናቴ አደራ ናት አሉ” - ቢሊየነሩ ሼህ መሀመድ አላሙዲን፡፡
ለኢህአዲግ መንግስት ሼህ አላሙዲን በ1997 ምርጫ ድጋፍ ሁነት ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ ብዙ ሰው ሚድሮክ የህወሀት ነው፣ የወያኔና የአዜብ መስፍን ነው እስከሚለው ድምዳሜ ድረስ የዘለቀው ነቆራ ሚድሮክን ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር አላጥፎ በባለሀብቱና በድርጅቶቹ ላይ ከፍተኛ ፈተና ደቅኖም ማለፉን ዶክመንተሪው ከትቦታል፡፡
በሚድሮክ ዶክመንተሪ ላይ እንደ ወግ በጣም ቀልብን በሚገዛ ሁነት ማብራሪያውን የሚሰጡት አቶ ጀማል አህመድ እንዲህ ሲሉ በአጽንኦት ያነሳሉ - “አላሙዲ ለኢትዮጵያ ስላላቸው በጎ ሕልም በህዝቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ አልተያዘውም፤ እናም አሁንም ድረስ ፈተና ሆኖ የቀጠለው አብዛኛው የሼሁን የሀገር ወዳድነት ውስጠታቸውን አልተረዳውም”
መንግስት በደንብ ያመናቸው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነው ይሉና የሚድሮኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲያብራሩ - “በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ከባድ የፋይናንስ ማጥ ውስጥ ነበረችና አልአሙዲ የተጠየቁትን ድጋፍ ሁሉ በደስታ በማድረግ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በቁርጠኝነት ቆመዋል”፡፡
የሚያደርጉት ድጋፍ ሼህ አላሙዲን የማህበራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት የሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎችን መደገፍ መውደዳቸው ግን በአንዳንድ ፖለቲከኞች በበጎ ጎን አለመታየቱ ፈተና አመጣባቸው በማለት በቁጭት የሚያነሱት ስራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል፤ ለካ ደግነትም ፈተና መሆኑን ያወቅሁት በእሳቸው ነው በማለት በአግራሞት በምልሰት ሄደው ያወሱታል፡፡
ሌላው በሚድሮክ የውስጥ ድርጅት የአስተዳደራዊ ልቅ አሰራር ችግርና ሙስና ብሎም የገንዘብ ብክነትና ስርቆትን ተከትሎ ኩባንያዎቹ የመውደቂያ ቀናቸውን የሚቆጥሩ ነበሩና ከግራ አጋቢ ሁኔታ የገባው ሚድሮክ የራሱን customized መዋቅር አበጅቶ በስሩ ያሉ 45 ድርጅቶች በ6 ዘርፎች ተጣምረው በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ መፈጠሩ ይነገራል፡፡
ከወሎዋ ወልዲያ ትውልዳቸውን አድርገው ደሴ ወ/ሮ ስህን ት/ቤት ተከታትለው - የስራን ልምድ ከአንድ ስዊድን ካለ ትልቅ ኩባንያ ተቀጥረው ስለቢዝነስ ተሞክሮ ጨብጠዋል፡፡ አውሮፓ ላይ ሀብት ቢያፈሩም፣ ወደ ኢትዮጵያ ግን መጥተው አያውቁም ነበር፡፡ ይሁንና አንድ ቀን ግን እናታቸው የጤና አያያዛቸው አላምር አላቸው፤ እንግሊዝ ሀገር ለህክምና ከመሄዳቸው በፊት ግን ኢትዮጵያ ውሰዱኝ አሉ፡፡
ኢትዮጵያ መጥተው መርካቶን ጭምር ጎበኙ እና “ልጄ አደራህን!” አሉ ለሼህ አላሙዲን - “አደራ ሀገርህን ኢትዮጵያን አግዝ!” የሚል አደራ ተቀበሉ - ይህ የእናቲቱ አደራ አላሙዲንን ከበዳቸው፡፡
ለምን መንግስት ብቻ - የግል ባንክ ለምን አይኖርም፣ ኢኮኖሚው እንዲያድግ መንግስት መደገፍ አለበት የሚለው ሌላ የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት አስነስቶባቸው - ስማቸውንም የጠለሸበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር - ከበጎ ምክር ይልቅ ጥርስ አስነከሰባቸው - በዚህ መዘዝ የስራቸው ቀዳሚ የነበረው የመጀመሪያውን ሼራተን ሆቴል ታሽጎባቸው ነበር፤ የተሳሳተ ስሌቱም ስማቸውን አጠለሸባቸው፡፡
እኔ የተሸለምኩት መንግስት ኢትዮጵያ ሀገርህ ናት - ናና አልማ ስባል ነው - ለነገሩ የተወለድኩባትን እናት ሀገሬን እንዴት ነው የምረሳው ብለው ነበር፤ በአንድ ሽልማት ስነ ስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
ለበርካታ ወገኖች ስራ እድል በመፍጠር ኢትየጵያን ከድህነት መንጋጋ ፈልቅቆ ማውጣት ቅድሚያ ግዴታዬ ነው ይላሉ ዛሬም ድረስ ሼህ አል-አሙዲን፡፡
የሻይና ቡና ተክል ልማት ላይ በመሰማራት ኢትዮጵያን በዚህ ዘርፍ በአለም ቀዳሚ ረድፍ ላይ ማሰለፍ ህልማቸው ነበር፡፡
ሁሌም በተስፋ ይስተካከላል፤ የጊዜ ጉዳይ ነው ይሉኝ ነበር በማለት አቶ ጀማል የሼሁን ጨለምተኛ አለመሆን ይገልፁና፣ አሁን ያለው ፈተና ደግሞ ሳኡዲ ውስጥ ካለ ችግር ጋር የተያያዘ እና ከዛ ሀገር እንዳይወጡ በመደረጉ ድርጅቶቻቸውን ተከታትለው እንዳይመሩ እንደሆነ በቅሬታ ያነሳሉ፡፡ ይሁንና አሉ አቶ ጀማል - “አልአሙዲን ሁሌም ይፈተናሉ፤ አላህምዱሊላሂ ሁሌም ግን ፈተናውን ያልፉታል”፡፡
መንግስት ትኩረት የሰጣቸው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መዋቅር (home grown economic reform pillars) ከሚባሉት ከአይቲ በስተቀር በአራቱ ስለምንሳተፍ ትኩረቱ ለእኛ ጠቃሚ ነው ባይ ናቸው ከፍተኛው አመራር፡፡
ለ22 አመታት በኪሳራ የኖረው ኤልፎራ በዶሮ ዝርያ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ስለመያዙ ተጠቅሷል፡፡ ጫጩትን ከውጭ ለምታስመጣው ኢትዮጵያ መድህን ሊሆን ጥረት ላይም ይገኛል፡፡ የሻይ ቅጠል ምርትን ከኬንያ እያስመጣች የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን በሚድሮክ ፍላጎቷን የሚሞላ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ ገቢም እየተገኘበት ነው፡፡
የአፍሪካ ቢዝነስ ሊደርሺፕ ኦርጋናይዜሽን የአመቱ ምርጥ ዋና ስራ አስፈጻሚ “CEO of the Year” በሚል ሚድሮክ የእውቅና ሽልማት እና በቅርቡም እንዲሁም የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ሌላ የእውቅና ሽልማት አንስቷል፡፡
ፋብሪካዎቹ ጋ ሲኬድ - እኛ የዚህ ድርጅት ባለቤቶች ነን - የዚህ ድርጅት እድገት በእኛ ይወሰናል - የሚል አባባል አለ - ሆራይዘን ጋ የነበሩ ሰራተኞች የፈጠሩት መሪ ቃል ነው - ሌሎቹም ተጋሩትና ቀጠሉ - ጀማል አዝዞት የሆነ አይደለም፡፡
ሚድሮክ ባለፉት አስር አመታት ሰርቶ አምርቶ ካመጣው የሽያጭ ገቢ በላይ የዘንድሮ አንድ አመቱ ውጤት እጅግ ያስከነዳልም ተብሏል፡፡
በውጭ አልሚነት የተመዘገቡት ሼህ አላሙዲን ብዙ ሚሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ይዘው መጥተው ድርጅቶች ከፍተው አምርተው በውጭ ምንዛሪም ሸጠው ከፍተኛ ገቢም አግኝተዋል፤ ግን አንድ ዶላር ከሀገር አውጥተው አያውቁም ተብሎላቸዋል፡፡
የዚህን እውነትነት ለማረጋገጥ አሉ አቶ ጀማል በዶክመንተሪው - “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክም ጋ ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል፤ ከእኛ ብር ይወስዱ ስላልነበር፤ ማበረታቻ ቲፕ የሚሰጡት እንኳ በዩሮ ነበር፡፡
(Via:- ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ)
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 1213 times