Thursday, 28 August 2025 09:28

ከነብር ጋር ታግለው ልጆቻቸውን የታደጉት አባት

Written by 
Rate this item
(4 votes)
ነገሩ የተከሰተው ባለፈው ሳምንት በምስራቅ ሀራርጌ ጉርሱም ወረዳ ጎባ ቀበሌ ነው፡፡ አቶ ሙስጠፋ ረሺድ እንደ ሁልጊዜው በሰርክ ተግባራቸው ላይ ውለው ደክሟቸው ከልጆቻቸውና ባለቤታቸው ጋር ቤታቸው ውስጥ ነበሩ፡፡
የሁለት ታዳጊ ልጆች አባት የሆኑት ሙስጠፋ፣ የገጠማቸውን ለዶይቼ ቬለ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፤
“ያጋጠመኝ ነገር ያው ፈጣሪ ኑር ካለ ያኖርሃል ነው እንጂ፣ ህይወትን የሚያስቀጥል ነገር እንኳ አልነበረም፡፡ አስፈሪው የዱር እንስሳ ነብር ከምሽቱ በግምት 1፡30 አካባቢ ከቤተሰቦቼ ጋር ቤት ውስጥ እያለን ነው ከተፍ ብሎ ወደ ቤት ዘልቆ የገባብን፡፡ ምንም ዝግጅት አላደረግንም፡፡ ስታየው የሚስፈራ ቁጡ የዱር እንስሳ ነው፡፡ በዚያ ላይ በእርሻ ማሳ ውስጥ ስለፋ ነው የዋልኩኝ፡፡ ልክ እግሮቼን ታጥቤ አረፍ ስል ነው ይህ የሆነው፡፡ በጀርባዬ የወንድሜ መኖሪያ ቤት አለ፡፡ ነብሩ ዘለል አለና ከፍ ያለች ቤት ውስጥ ባለች አልጋ ነገር ላይ ቁጭ አለ፡፡ ነብር ልጆች ያጠቃል ስለሚባል ልጆቼን እንዳያጠቃብኝ ስጋት ገባኝ፡፡ እናም የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ አልኩ፡፡ ያገኘሁትን ዱላ ነገር አንስቼ ላስወጣው ስል ግን ዘሎ ተከመረብኝ” ብለዋል፡፡
በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከገባው ነብር ጋር ትግል የገጠሙት አባት ሕይወታቸው በተዓምር ተርፏል።
ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ቢያተርፉም፣ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
Read 825 times