... ቀን እንደማስረዘም ፥ ሌት እንደማሳጠር
ነገ ተገናኝቶ ዛሬ ፥ እንደመቃጠር
እግረኛ ተራራ ፥ ቆሞ እንደመጠበቅ
ሥጋ ለበስ መንፈስ ፥ ሊያዩ እንደመናፈቅ
ምነው ያንቺ ጠረን ፥ ለ’ኔ ሰማይ ኾነ?
ተስፋዬን ጠቅልሎ ፥ እንደ ጉም በነነ...
-ዲበኩሉ ጌታ-
ርዕሱ፣ ገጹና ይዘቱ... የአንጀት የሚያደርሱት ጥራዝ ከእጄ ገብቶ ሳነበው፣ መጀመሪያ የግል በሆነ ፍላጎት በግጥም ቢኖር ብዬ የምመኘው ‛ፍልስፍናዊ ይዘት’ ነበር የተቀበለኝ። ሠርግና ምላሽ ሆነልኝ፤ እልል በቅምጤ አልኩ። ቀጥሎም የሰሉ ‛ማኅበራዊ ሕፀፆች’ን ባልቸከ መልክ የሚያሳቅለው ገጽታው ከፍልስፍናው ጋር ኮትና ሸሚዝ ሆኖ ያጅበኝ ያዘ።
በግጥም ስብስብ ረገድ ብዙ ጊዜ አድርጌው በማላውቀው ዓይነት፣ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ግጥም በአንድ ቁጭታ አነበብኩት። ስምም በስምም። ከአልፋ እስከ ዖሜጋው ገጽ የስሜት መወላከፍ ሳይገጥመኝ መጨረሴ ቢገርመኝ ጊዜ "በልቶ መካድ የሚጫነው የንፉግነት ባሕላችን በኔ ይብቃ!" ብዬ ትንሽ ለማለት ተነሳሁ።
ስብስቡ በብዙ ዘርፍ ሊታይ የሚችል ቢሆንም፣ ጎላ ባሉብኝ ሁለቱ ዘርፎች ጠቅለል አድርጌ ትንሽ ለማለት ልስከንተር፦
፩. ፍልስፍናዊ መመዘኛ
መቼም ስም ግብርን ይመራል ከተባለ በቀዳሚትን የሚሠራው ለፍልስፍና መሆን አለበት። ለምን ቢሉ፣ ለፍልስፍና ራሱ ቁርጥ ያለ ፍቺ አልተቀመጠምና። በሌላ አነጋገር፤ የማያነሳው ርዕሰ-ነገር የሌለው ፍልስፍና ራሱ ላይ ተፈላስፎ ቅልብጭ ያለ ብያኔ ለኔው ሰጥቻለሁ ለማለት አልደፈረም። ይህንን ስል ግን «በጥበብ/ዕውቀት ፍቅር መውደቅ» የሚለውንም ሆነ «ፍልስፍና የመጠየቅ ሳይንስ ነው» የሚባለውን ጥቅል ብየና ዘንግቼ አይደለም። ይልቁንም «ከዚህም በላይ ነው፤ እንዲህ ነው ብለው በቀላሉ ተገላግሎ ለመቀመጥ የሚሮጡ ፈላስፋ ለመባል አይበቁም...» የሚሉትን የስመ-ጥር ሰዎች መተላለፊያ ሠርጥ ላለመዝጋት ነው።
እና እናንተም «ፍልስፍናዊ ግጥሞች ስትል በምን፣ ለምንና እንዴት...ነው?» ብላችሁ ለምትጠይቁት ጥያቄ፣ መልሴ ከላይ እንዳልኩት ነው የሚሆነው። ለ’ኔ በታየኝ ልክ [ከተስማማችሁም እሰየው] ፍልስፍናዊ ግጥሞች አሉበት - ጥራዙ።
«ማለፊያ በቀል» ከተሰኘው ግጥሙ ተነስቼ ዋቢዎቹን እየጠቃቀስኩ ልግፋ፦
... ብርሃን ትርጉም አይሰጥም ጨለማ ካልታከለበት
ማግኜትን የሚያስናፍቀው ማጣት ነው ነፍስ የዘራበት ...
ገጣሚው በጊዜ፣ በፈጣሪና ተፈጣሪነት፣ በፍቅር... ይፈላሰፋል። ይልቁንም ፍልስፍናዊ ላልኩት ዐተያይ መነሻ የሆኑኝ የፍቅር ነክ ግጥሞቹ ናቸው። ለአብነት «ለምለም ሳቅ»። እንዲህ ያለ ልስልስ ርዕስ የመጣለት “ስስነት ባሕሪው ነው” የሚባለው ወለሎታዊ ተፈጥሮ እንዴት እንዲህ ጭክን ያለ አካሔድን ከፍቅር ጋር አዳበለ? ብዬ ስጠይቅ ያገኘሁት ምላሽ... በቃ ገጣሚው ውስጥ የሚወራጨው ጥልቁ አፈጣጠር ፍልስፍናዊ ቢሆን ነው፤ የሚል ነበር። [መላክ ሆይ፤ ስሜትህን ባውቅ ደስ ይለኛል።] ስለሆነም በአቋሜ ጸንቼ ለመፈተሽ ተጋሁ። አለመሳሳቴን አረጋገጠኹ።
እነሆ ቅንጭቡ ከለምለም ሳቅ፦
ይኸው ሲነሽጠኝ፣
ይኸው ሲመጣልኝ፣ ሲነሳልኝ ልቤ፣
ጠላቴን ስጥለው ራሴን ደርቤ፤
ይኸው ሲነሳብኝ ሳልነሳ ቁሜ፣
ስንዝር ሳልራመድ፣
ነገዬን ደረስኩት ፍራ’ቴን ቀድሜ።
ስለ ለምለም ሳቅ ለመናገር ነው እንግዲህ... ሰው በሰው መካከል ልዩነት የለውምና ሌላ ጣልኩ ብል ዞሮ ወዳቂው እኔ፤ ብሎ በመንደርደር የሰው ልጅ ፍርሐቱን ካሸነፈ ጊዜ ምንድነው? የሚል ፍልስፍናን ለቁሶ መንገዱን ወደ ዋና ጭብጡ የሚንደረደረው። በዚህ ግጥም ሥር ሌሎች አስደንጋጭ ስንኞች ወደ ታች አሉ። እውነቱ ግን ከላይ የተቀመጡት ስንኞች በራሳቸው ምልዑ መሆናቸው ነው። ግፋ ቢል ርዕሱን መቀየር ቢጠይቅ ነው።
ወረድ ብሎ ወደ ዋናው ነጥቡ ሲቀጥልም እንዲሁ ማስደመሙ አይጎድልም...
ይኸው ሳሸንፈው፣
እኔ ለ’ኔ ክብሪት፣ እኔ ለኔ ሻማ፣
እቀልጣለሁ እንጂ፣
ሳቋ እስኪገፍልኝ፣ የፊቴን ጨለማ፣ ...
በዚህም አይበቃው...
ታምሜአለሁና፣
በስመ አብ ብዬ፣ ሳቋን ተጠበልኹት፣
ፈገግታዋ ቢያቅፈኝ፣
ተፈወስኹኝ መሰል፣ ራሴን አጣኹት።
ለመሆኑ መፈወስ እንዴት ነው ራስን የሚያሳጣው? ራስን ማግኘት ማለትስ ማበድ ማለት ይሆንን? ... ብቻ ግጥሙ ሲቀጥል ይብስ እየናረ እንጂ አይፈዝም። ልቀቱ እንኳን፣ ጊዜን ከተፈጥሯዊ ሥርዓቱ የሚያገለባብጠውን የፍቅር ኃይል በደማቅ ዜማ እየኳሸ ዘልቆ ነው ማሳረጊያውን የሚያደርግ። መጽሐፉ ያላችሁ አሁኑኑ ገልጣችሁ፣ የሌላችሁ ገዝታችሁ «ለምለም ሳቅን» እስከመጨረሻዋ ድመቁባት። እኔ ልቀጥል።
«ፍቅር ቦታ» ሲል የሰየመው ግጥምም በተለመደው መልኩ ዘው ብሎ ፍቅር ይኸው ነው ለማለት አይጣደፍም። ይልቁንም...
ሞትም አልመኝም መኖርም አልፈልግ
በኹለቱ መኻከል አይጠፋም አንድ ጥግ...
እያለ ፍልስፍናውን ያዘግጋል እንጂ።
ባለ“መንታ ነፍሱ” ገጣሚ ብዙውን ጊዜ መንታ ነው። እያየነው እንዳለው፤ ፍቅርን እንኳን ‛እንደወረደ ተፈጥሮው’ በስሜት፣ እንደተጠየቅነቱ በስሌት አማክሎ ሲያቆመው ደጋግመን እንታዘባለን። ዐይነ አዋጅ ከሚሆኑት ማሳያዎች አንዷን ላቅርብላችሁ።
«የተከዳ ተስፋ»
... ቀን እንደማስረዘም ፥ ሌት እንደማሳጠር
ነገ ተገናኝቶ ዛሬ ፥ እንደመቃጠር
እግረኛ ተራራ ፥ ቆሞ እንደመጠበቅ
ሥጋ ለበስ መንፈስ ፥ ሊያዩ እንደመናፈቅ
ምነው ያንቺ ጠረን ፥ ለ’ኔ ሰማይ ኾነ?
ተስፋዬን ጠቅልሎ ፥ እንደ ጉም በነነ...
ነገር እንዳላበዛ ፈርቼ እንጅ ‛ፍልስፍናዊ መመዘኛ’ ላልኩት ለተጠየቅ ብዙም የማይገፋፋ/የማይመቸውን ፍቅር ነክ ጉዳዮች ብቻ አንስቼ ልወሰን የወደድኩት፤ በሌሎች ርዕሰ-ነገሮችማ አመዛኙን ሙግት ጫሪ ግጥሞች ናቸው የተጠቀጠቁት።
ሌላው በእግረ መንገድ መናገር የሚገባኝ፣ በስብስቡ የተካተቱት ወሎሎታት እንደ ጥቅል መጠሪያቸው መንታነትን የሚያቀነቅኑ መሆናቸውን ነው። መላክ ግጥሞቹን ብቻ ሳይሆን ‛መሰናበቻ’ ሲል በመጽሐፉ የመጨረሻ ቅጠል ላይ በዝርው ያስቀመጠውንም በ“መንታ መንፈስ” ነው የቀነበበው።
«...ጊዜ መልካም ነው ያገናኛል፤ ጊዜ ክፉ ነው ያለያያል። ጊዜ ለጋስ ነው ይሰጣል፤ ጊዜ ንፉግ ነው ይነሳል። ጊዜ ኃያል ነው ያጠፋል፤ ጊዜ ተራ ነው ይጠፋል።...» እናስ ፍቅርን በመለየት መልኩም፣ [ሁሉን የሚያሳልፍ] ጊዜን በተርታ አላፊ ገጹም፤ እንደተሻ ማየቱ የፍልስፍናዊ እምቃቱ ማዳበሪያ አይሆንም ወይ?
፪. ማኅበራዊ ሕፀፅ ነቀሳ
እዚህ ስብስብ ውስጥ ገሐድ ያልተሰጣ... የግልና የወል ሕፀጽ እምብዛም አይደለም። ለራሱ ሳይራራ፣ የማይኩራራበት ቀር ገጹን ለአደባባይ ከንፈር መጠጣ ያጋለጠው ከያኒው፣ የሚኖርበት ዘመኑንም ሆነ እንዲኖር ያመጣውን ‛ፈጣሪ’ም ከመወረፍ አልተለመሰም። ግርንቢጡን ሲያሳቅለው ለጉድ ነው። ከዕይታው ስላት የተነሳ የተሰማው ሲሰማን ጊዜ አይፈጅም።
ለመነሻ «ያልተረሳ ያልተወሳ»
ኮሶ ለታያቸው
በማር ተለውሶ፥ ኮሶ ተሰጣቸው።
(ሻሩ ተሻላቸው)
ለባለ መድኀኒት፥ ምስጋና ሲያደርሱ
❝ኮሶ አዳነን❞ አሉ፥ ማሩን እየላሱ። ...
ከዚያ ምን የሚፈጠር ይመስላችኋል? የሚሆነውን የሚነግረን ገጣሚው ነው። ለጥድፊያው ስል ጠቅልዬ ጭብጡን ልንገራችሁ። የሆነውማ የማሩ መዘንጋት ያስከፋቸው፣ ንቧ፣ ቆራጩ እና ማር አቅራቢው አኩርፈው ምርትም አቅርቦትም መቆም ነው። እና ቢቆምስ ኮሶው ሽሮ አይደለም ወይ? የሚል አይጠፋም ያለው ገጣሚው፤ በአስቀድሞ አስተዋይነቱ ከተጨባጩ ኮሶኣዊ ባሕሪ ቀድቶ ድርሰታዊ ሤራውን ያጉነዋል። ኮሶ ተመላላሽ ተጣቢ ነውና የሻረላቸው ሰዎች ድጋሚ ተያዙ። ኪኑ በግጥም ምጣኔ ተቀልብጮ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ልብን አንጠልጥሎ የሚጓዘው የትየለሌ ነው። እና ምን ይሁኑ? በሳቱበት አፍረው ወይም በራስ ስሕተት ውጭ ዓለሙን አኩርፈው? ወይንስ ከሳቱበት ተመልሰው ይቅር በሉን ኮሶ ያው ኮሶ ነው ማሮች ሆይ ማሩን... ይላሉ? ከያኒው ከዚህም ያለፈ አካሔድና አደማደም አለውና ከመጽሐፉ ዐይተው ይደመሙ።
ማሕበራዊ ነቀሳዎቹ ማሳያ ዘይቤዎችን፣ ልዩ ልዩ ማንጸሪያዎችን እያቀያየሩ ተመላልሰው የሚያንባርቁብን መሆናቸውም ዕሙን ነው። ቀደም ብለን የጠቀስነውን ከሚያጸኑት መካከል እነኝህ ይገኙበታል።
ርዕሱ «በጦር ሜዳ ለተሰዋች ጀግና» ተብሏል።
... የ’ኛን ዘመን ተዪው ዘመነ ድንግርግር፣
የሚበላን ከ*ራስ የምናከው እግር። (*ከ የኔ ጭማሪ ናት]
እንባ ለሚያነባ ሀገር ለሞተበት፣
ማሟጫ እየሰጠን ጥርስ የሚፍቅበት፤
አደናቅፎት ወድቆ ጥርሶቹን ላጣ ሰው፣
መነጽሩ ደ’ቆ ዐይኑን ላፈሰሰው፣
(ካይንና ከጥርሱ)
መነጽር ገንዘቡን አስበን ስናዝን፣
ተገዛገዝን እንጂ! መቼ ተጋገዝን?! ...
እያለ ነፍስ የሚበጣ ትችቱንና ሰማይ ነቅናቂ ጥያቄውን እያዋጀበ ይቀጥላል። ሽንጣም ግጥም ነው። ምነው ርዕሱ ነጋሪ ሆነ? የሚል የጅመራ ስጋቴን አስረስቶ እንዴት መሰላችሁ ይዞኝ የከነፈ! ...
እኛ ማለትኮ...
በጎች ኾነን ሳለ ተኩላ ምናረባ፤
አዳራሽ ለማፍረስ ጎጆ ’ምንገነባ፤
ሌት ተቀን ፉክክር፥
ኑሯችን ሕልም ነው፥ ሳይዘሩት ’ሚበቅል፤ ...
ሌላም ክውታ እዚህ ጋ አለ፦
... እኝኝኝኝኝኝኝ
ምላሴን በረደኝ
ጥርሴን አሳከከኝ።
አባ መስጠት’ና ናደው አባቀማው፣
ኹለት መታወቂያ ኹለት ስም ያለው፣
አንድ መለኛ ሰው አለ ከ’ኛ ሰፈር፣
እንደ ልጅነቱ፥ እንደ 'ቃቃ ጊዜው፥ የሚጫወት ባፈር። ...
ዝቅ እያለም ሲሔድ፦
... አኹን ለምሳሌ ❝እንትኑ እንዴት ኾነ?❞
❝እንትኑን ምንበላው? ተስፋው የት በነነ?...❞
ብሎ ካለ ሕዝቡ ጀማው ከጠየቀ፣
በገጹ እያዘነ በልቡ እየሳቀ፣
❝ለ’ኔም ጥያቄ ነው❞ እንጂ አይልም እንጃ፣
ቆርጦ ለመመለስ የጠያቂን ቋንጃ።
ታዲያ በዚህ ጊዜ...
በሆዱ እያዘነ ምላሽ እንደጠማው፣
ሳቁን ሳያስመልስ ይመለሳል ጀማው። ...
ብቻ እኔም እንደ ዜጋ፤ እኔም እንደዘመን ተጋሪ በነዚህና መሰል የወል ጉድፋችን በተነቀሰባቸው ስንኞች እየተሳቀቅኹ... ምላሴን ሲበርደው ጥርሴን እያላበው ተመላለስኩበት - መጽሐፉን።
በምልልሴም... ሌሎችም ላልጠቅሳቸው ያልቻልኩት ስንኞች አሉና ጥቂት ሰዓት ወስጄ ላስፍርላችሁ። ርዕሱ «ማንነት ሲታመም» ነው፤ ወርዱ ዘለግ ያለ ሆኖ የከበረ የሚባለውን ባሕልና መንፈሳዊነታችንን ዐፈር-ድሜ ያስጋጠበት ሆኗል።
... ይኸው በዚያ ምሽት
እንደበሬ እንደላም ፥ ሐቅ ተዘረፈ፤
ኀሳር ቄሳር ኾኖ ፥ ሌሊቱም ዐለፈ፤
ፀሐይዋም ንጋቱን ፥ በእጇ ዘረፈችው፤
አህያማ ሆዱን ፥ አፈራረሰችው፤
እንዳይነጋ የለም!
ነጋ’ና ተያዩ ፥ ዝምምምምም አሉ አላወጉም፤
ሰው ባሰኛት ጊዜ ፥ ሰው’ና ሰውነት ፥ አብረው አላነጉም። ...
ይኽኛው ደግሞ በተነሳበት ዕይታና በነገር አጠቃቀሱ የባሰበት ነው።
የቀረበው በግጥም መሆኑ በጄ እንጅ ሐቁ አስበርግጎኝ ምን በወጣኝ ብዬ ወዳንድ ጥግ እወረውረው ነበር። ይህ ዘወር ተደርጎ ሲታይ፣ የበሰለ ተናጋሪ መለኪያ ሳይደነፋ ማስተላለፍ የፈለገውን ማስቀመጡ ነው - የሚል ፍች ያዋልዳል። ይበል።
. . .
ገጣሚው ለሙግቱም ሆነ ለትችቱ «ተቃርኖን» አዘውትሮ መጠቀሙም ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ይህንንም ከግጥሞች አርዕስት ጀምሮ በቀላሉ እናገኛለን። ሊያውም በተደጋጋሚ። ጥቂቶችን ብቻ ልጥቀስላችሁና ፍረዱ።
የዝምታ ጩኸት
ግልጽ ምሥጢር
ስሕተት ያልሆነ ስሕተት
ዓለም ክብ አይደለም
ትርፋማ ኪሳራ
ያልተወሳ ያልተረሳ
ላኖረው ገደልኹት... ወዘተረፈ።
ዐቢይ መስከንተሪያ ካደረግኋቸው ፍልስፍናዊ ዝንባሌና ኀያሲያዊ ተብሰልስሎቱ ባልተናነሰ በንዑስ ርዕስነት ቢታሰብልኝ ብዬ የምመኘው ግን የተነሳው ተቃርኖኣዊነት ብቻ አይደለም። የሚከተለው ከቀደመው የሚልቅበት እሴት የነበረ ነውና፣ ይባሱኑ «ትውፊታዊነት/ፎክሎራዊነት»ን ያስተዋልኩበት አለ ’ንጅ። መላክ፤ ጓዳዊ ብሎም ሕዝባዊ የሆኑ የሃገር አንጡራ ጥሪት ሥረ መሠረት ተብለው የሚቀመጡትን፣ እንደ እንቆቅልሽ... እንካስላንትያ... ተረት ተረትን በውል ተገንዝቦ ከቃላዊ ሐብትነት ወደ መዛግብት ህያው ቅርስነት አሻግሯቸዋል። ይህን ሲያደርግም የነበረውን ታሪክና ጭብጥ በመድገም ሳይሆን በአዝማናት የተፈተነ ስልቱን አንጥሮ በመውሰድ ነው። የነበረን ማጽናት የልጅ ግዴታ መሆኑ አይታበልምና ለቀደሙት አባቶች ገላ ትኩስ አተያይን አልብሶ ጡንቻም ፈሊጥ ህያው አድርጓል።
እነሆ «አባ ናደው»
“እንቆቅልህ አባ ናደው”
“ምን አውቅልህ?”
“......”
(ጠያቂው ምንም ይጠይቅ)
“ሀገር ልስጥህ?” ይላል የማይገደው ናደው፣
አይሰጠው ምን አለ? ምን አለ ’ማይወስደው?
በአባ ናደው ዘመንን የታዘበበት፣ ትውልዱን ያሳቀለበት መንገድ ከነ`ኪነታዊ ማዕረጉ ካባ የደረበ ነው። እጅጉንም ካስደነገጡኝ መካከል ሆኗል።
ስንኞቹን ለተነሳሁበት ትውፊትን ወርሶ ከነበሩበት ለሚልቅ ሚና እንዴት አቆንጅቶ መጠቀም እንደሚቻል ለማሳየት ባለመ አግባብ ጠራኋቸው እንጅ ሙሉ ግጥሙስ በነዚህ መስመሮች ጠቋሚነት የሚደረስበት አይደለም። እኔ ስንኞቹን የዘገንኩት የዋናው ወላጅነት ከሚያጎጠጉጥበት ደረት ላይ ነው። ቀድሟቸው ያለው አባ ናደውና ከደረት ተከትሎ የሚመጣው ተደላድሎ መቆሚያው የሚያትተውን ጉድና ጉግማንጉግ ሙሉ ግጥሙን ያነበበ ብቻ ነው የሚረዳው። የሆነው ሆኖ ጭብጥ ብቻውን የተሳካ ፈጠራ አይሆንምና የጠቀስንበት የትረካ ስልቱ ከይዘትም በላይ በድባብ ውዳሴ የሚገባው ነው የሚለውን እንያዝ። ሌሎችም እዚሁ ትውፊታዊነት ቅርጫት ውስጥ ቦታ አጣብበው የሚገኙ አልታጡም።
«አጥንት እና ጠጠር፣ የእኔ እየሩሳሌም» የመሳሰሉትን በንቡር ጠቃሽ ዘይቤ ትውፊታዊነት፣ «የእረኝነት ቅኔ»ን በእንካስላንትያ አስተኔነት እንዲሁም «ማንነት ሲታመም እና የበጎች ህልውና»ን በተረት ነገራ ስልት ተራቅቆባቸዋል። ይህ በዘርፉ ልሂቃን ዘንድ የሰንደቅ ዓላማ ቀለም ከንጉሣዊ ዙፋን ጋር ተስተጻምሮ የሚሰጠው እየሆነ የመጣ ስልት ነው። ቢሠፋ ጥሩ ሃገራዊ ስዕል በፈጠራው ዐውድ የሚከሰት ይመስለኛል።
ታዲያ እዚህ ላይ ላፍ መያዣ አንጓ እንደ ፈንድሻ ወርወር ለማድረግ ብንሻ... «ኩሩ ትሕትና» እኔ አለሁ ይለናል!
እቴ ያንቺ አገር ሰው ፥ እንዴት ይናፍቃል
ቀና ካሉት መሐል ፥ ጎንበስ ማለት ያውቃል።
ወረድ ብሎም...
መምጠቅ እንደ ንሥር ፥ እንደማይችል መብረር
እንደ ሕጻን መዳህ ፥ ለመቅደም መግደርደር። ...
‛ለመቅደም የሚግደረደረው’ መላክ፤ አሁን ያስቀመሰን የአፍላነት ውልብኙን ነው ብል በአካልም ባይሆን በፎቶ ያየሁት ገጽታው የሚፈቅድልኝ ይመስለኛል። ወጣት ነው። ገና ሌላ ሌላ ደህነኛ ምርቶችን እጠብቃለሁ፤ ጠቅላይ ካላላችሁኝ እንጠብቃለን! አያያዙን ዐይተው ስንቁን ይቀሙታል ሳይሆን አያያዙን ዐይተው ለነገ ያጩታል፤ እንበልና ለአድባሯ ድቤ እንምታ። (ወንዶች በጭብጨባ ፡ ሴቶች በእልልታ!) በጄ...
ይህ በእንዲህ እያለ... ለማይቀረው ነገ ቅንጣት ለማዋጣት [በታየኝ ልክ] ቢታረሙ የምላቸውን የመጥቀስ ግዴታም ይኖርብኛል።
አንደኛ የአወራረድ ድምቀታቸው ወጣ ገባ ያሉ አንድ... ሁለት ግጥሞችን ማስተዋሌ ነው።
ሌላው በጣም በጥቂቱም ቢሆን የቤት ምጣኔያቸው ዘነፍ የሚሉ ስንኞች ያጋጠሙኝ መስሎኛል። በተያያዥ ወጥ የሆነ የኪነተ ቃላት መረጣ እየደረጀ እንዲሔድ ምንባብን ከጥሞና በማስፋት ክምችቱን ማላቅ ይጠበቃል።
በተጨማሪነት [ጸሐፊያኑን ብቻም ሳይሆን አርታዒያንንም የሚመለከተው] በወቅቱ ባየኋቸው የሌሎችም ከያኒያን ሥራዎች ያስተዋልኩት ሰዋስዋዊ ግድፈት እዚህም አጋጥሞኛል። ይኸውም አናባቢ ከተነባቢ ጋር ለየብቻና ተዋውጦ ሲቀመጥ ተፈጥሮ የሚገኝ ነው። ለምን ማለቴ ነው ‛ከአንድ’ የሚለው አጻጻፍ ‛ካንድ’ ከተባለ በቂ ሆኖ ሳለ፤ “ካ’ንድ” ሊባል አይገባም። ከ+አ = ካ ከሆነ ‛ከ’ም ‛አ’ም ተጻፉ ማለት አይደል፤ በጭረቷ ለምን ትገባለች? እስከ ሚገባኝ ጭረቷ የምታስፈልገው የ‛አ’ ነገደ አናባቢ ኆኄያት ለድምጽ ምጣኔ ወይም ለሌላ ተብለው ሲቀሩ ተኪ ሆና የምታገለግል ናት። በዚህ አጠቃቀም ግን የሚገደፉት ፊደላት ከቀደመው ‛ከ’ም ሆነ ሌላ ፊደል ጋር ተካትተው ‛ካ... ላ...ያ...’ ሆነው ተጽፈዋል። ከአባት = ካባት፣ የአንቺ = ላንቺ... ለአንድ = ላንድ፣ ከዓይን = ካይን ... የመሳሰሉት ላይም ተመሳሳይ ስሕተቶች ተደጋግሞ የሚታይ ነውና ቢቀረፍ። ጭረቷን መጠቀሙ ባመዛኙ ‛እ’ ‛የ’ ለማስቀረት ቢትዘወተር። ምሳሌ ከእናት/የእናት = ከ’ናት/የ’ናት፤ ለእያንዳንዱ = ለ’ያንዳንዱ። አናባቢው ከተናባቢው ተካትቶ ሳለ አካትቶ ከያዘው ፊደል አስከትሎ «’» ማድረጉ ግን ይቅር ያልነውን ፊደል ይባሱኑ ደግሞ እንደ መጻፍ ነው። «ከአእንድ» እንደማለት። (ማስታወሻ፡- በጠቀስኳቸው ግጥሞች ያጋጠሙኝን አርሜ ነው ያስቀመጥኳቸው።)
ግድፈቱ በጣም በብዙዎች ላይ የሚስተዋል ስጋት እየሆነ የመጣ ነው። ባጋጣሚ ሆነ እንጅ... ከመላክ በላይ ለማንበብ ስሜት እንዳጣ ያደረጉ የባሱ አጋጥመውኝ አስረዝሜ ለመጻፍ መገደዴ በጽኑ ይያዝልኝ።
በተረፈ ግን...
ፍልስፍና እና ማኅበራዊ ሕፀፆች የደመቁበት፤ ርዕሱ፣ ገጹ እና ይዘቱ... የአንጀት የሚያደርሱት «መንታ ነፍስ» ነፍስ የሆነ ሥራ ነውና... በሚሊዮን ቅጂዎች ታትሞ፣ ሚሊዮኖች እንዲያነቡት ስለት ገብቻለሁ።

