እስኪ ላፍታ የአካዳሚውን ዓለም እንደ ግዙፍና ባለብዙ ቀለም ካርታ አድርገን እናስበው። ታዲያ ይህ ካርታ ለግድግዳ ጌጥነት የተሰቀለ አይደለም— ይልቁንስ ኅሊናን ከስፍራ ወደ ስፍራ አንሸራሽሮ እንዲያመራምር ታስቦ እንጂ!
እንዲያ ከሆነ ዕውቀትን የሚሹ ግለሰቦች የአገራት ድንበርና ኬላ ሳያግዳቸው በየትኛውም አህጉር በአይነ ኅሊናቸው ያላንዳች ፓስፖርትና ቪዛ፣ በነጻነት ይመላለሱበታል ማለት ነው። ማገዶ ሳይፈጁ አዲስ መረጃ እና ሰፊ ግንዛቤን በነጻ ማትረፍ አያስደስትም?
ዛሬ ዛሬ፣ ጥቂት የማይባሉ የካርታው ታዳሚዎች ድንበር የለሽ ቅኝታቸውን ገታ እያደረጉ በካርታው ውስጥ አጥሮችን እያጠሩ ይገኛል። ምን ይሄ ብቻ … ቀደም ብሎ ቤተ መጻሕፍቱ የአካዳሚያዊ ሹክሹክታ መታደሚያ ነበሩ። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ጉዳይ ሌላ ሆኗል። ልክ በብሔር ሥያሜ በተከፋፈለ መደርደሪያ ላይ እንደሚቀመጡ መጻሕፍት ሁሉ … አንዳንድ የምሁራን ቡድኖችም ከነዚህ መደርደሪያዎች ጋር እየተመሳሰሉ ነው። ሹክሹክታዎቹም እንዲሁ… “እኛ” እና “እነሱ” በሚሉ ድምፃ–ድምፆች እየተተኩ ይመስላል።
ለአብነት ሁለት በብሔር ታፔላ የታጠሩ አካዳሚያዊ መጽሔቶችን እንመልከት። የኦሮሞ ጥናት መጽሔት (Journal of Oromo Studies) እና የዐምሐራ ጥናት መጽሔት (Journal of Amhara Studies)። የመጽሔቶቹ ምስረታ ገፊ ምክንያት አስቀድሞ በኮረኮራቸው ጉዳይ ሳቢያ (proactive) ሳይሆን በሐገሪቱ ከተከሰቱ ድህረ ፖለቲካዊ ሁነቶች (reactive) ተከትለው ብቅ ያሉ ናቸው። የኦሮሞ ጥናት መጽሔት በኢትዮጵያ የብሔር/ቋንቋ ፌደራሊዝም በተመሠረተ በጥቂት አመታት ውስጥ የተቋቋመ ሲሆን፤ የዐምሐራ ጥናት መጽሔት ደግሞ በቅርቡ ከተመሠረተው ከፋኖ ምስረታና ንቅናቄ በኋላ የተቋቋመ ነው።
አካዳሚያዊ መጽሔቶች የሐሳብ ክርክርና ፍጭትን በማካሄድ የዕውቀት ብርሃንን ይፈነጥቃሉ። ሆኖም የአካዳሚያዊው መድረክ ወደ ብሔር ፖለቲካ አውድማነት ሲቀየር በርካታ ጥያቄና ስጋትን ያስከትላል። እውን በመጽሔቶቹ አማካይነት እውነትን እንሻለን፣ ወይስ በየራሳችን ትናንሽ የልሂቅ ቋጠሮዎች ተቧድነን የየራሳችንን የብሔር ድምጾች እናስተጋባለን?
እርግጥ ነው አካዳሚያዊ መጽሔቶች ለዘመናት ተዘንግተው የነበሩ የብሔር ጥያቄዎችን ለማስተጋባት እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለማጉላት አይነተኛ መድረክ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ለፖለቲካው ፍልሚያ አማራጭ መድረክ የለውም ይሆን?
የብሔር ፖለቲካ ትንተናን እንጀራው ያደረገ፣ ለሃቅ እና ሚዛናዊነት “ጨዋ” የሆነ እንደ አሸን የፈላ ዩ–ቲዩበር አለ፣ ቲክታከር አለ፣ ፖድካስተር አለ … ምኑ ቅጡ? ታዲያ በዚህ ሁሉ አፈ ሰማይ መድረክ ያልተበለተና ያልተፈተፈተ የብሔር ጉዳይ ተገኝቶ ይሆን? ይልቁንስ ለዲጂታል ሠራዊቱ ሃሺሽ–አከል “አካዳሚያዊ ጡንቻ” (steroid effect) አቀብሎ የሃገሪቱ ፖለቲካ አውድማን የበለጠ አያወሳስበውም? ለቀጣዩ ትውልድ ነቀርሳን በማጣቀሻነት ከትቦ በቅርስነት እንደማውረስ አይሆንም?
የተጠቀሱት መጽሔቶች እንደው ልፉ ቢላቸው እንጂ የድሮ ቁስልን ለማመርቀዝና በደንብ አድርጎ ለማከክ ከአክቲቪስቱ በላይ ጥፍር ኖሯቸው? ወይንስ የራስን ብሔር ከሌላው አግዝፎ ለመፎከር ከአክቲቪስቱ በላይ እሳት የሚተፋ ምላስ ኖሯቸው?
ይልቅስ በብሔር ድንበር በማይታጠረው አሰቃቂ ድህነትና በምግብ ዋስትና እጥረት፣ በዴሞክራሲ እጦት፣ በሰላም ዋስትና እጦት፣ በበሽታና አደጋ ተጋላጭነት፣ በመሬት መጎሳቆልና የለምነቱ መመናመን፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት፣ ወዘተ … ለሚማቅቅ ህዝብ ምሁራኑ ብሔር ሳይለያቸው በጋራ ሊያጠኑና ሊወያዩበት በሚችሉ አካዳሚያዊ መጽሔቶች እንዲገናኙ ቢሆን የተሻለ መፍትሔ አያፈልቅም?
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ከተለያየ ብሔርና አስተሳሰብ የሚመነጩ ምሁራን በጋራ ሲመራመሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግኝቶችን ያመነጫሉ፣ ብዝሃ እውቀታቸው እየተዳቀለ በአካዳሚው መስክ ላይ ፍሬው ይጎመራል። በተቃራኒው ደግሞ ምሁሩ ብሔር-ተኮር በሆነ ስብስብ ተቋጥሮ ሲቧደን በአባላቱ መሃል የሚኖረው የአመለካከት ልዩነት ይጠብና አካዳሚያዊ ፍጭቱን ያመክነዋል። ፍጭት–አልባ የሆነ የቡድን ውይይት ደግሞ ጉንጭ ማልፋት እንጂ የዕውቀት ብልጭታንም ሆነ ፈጠራን አይፀንስም፣ አይወልድም።
ከ80 በላይ በሆኑ ብሔር/ብሔረሰቦች በተዋበች ኢትዮጵያ፤ በህዝብ ቁጥርም ሆን በቆዳ ስፋት ከፍተኛ ደረጃን የያዙት የኦሮሞ እና የአማራ ክልሎች ናቸው። ምሁራኖቻቸው ራሳቸውን እየለዩ አካዳሚያዊ መጽሔቶቻቸውን ሲመሰርቱ … እንደው በተቀሩት አያሌ ቡድኖች ላይ ሊፈጥር የሚችለውን መዘዝ (repercussion) ልብ ሳይሉት ቀርተው ነው? ….ወይንስ እንደ ፍጥርጥራቸው ይሁኑ ብለው?
የሚደንቀው ነገር … የትግራይ ምሁራን የተለየ ፈለግ መከተላቸው ነው። በኢትዮጵያ የብሔር/ቋንቋ–መር መንግስታዊ ሥርዓት እንዲመሰረት ፊታውራሪ ከነበረው የሕወሓት ረጅም ጥላ አርፎባቸው ሳለ — “የትግራይ ጥናት” የሚል አካዳሚያዊ መጽሔት አለመመስረታቸው!… አዎን አልመሰረቱም። በምትኩ ሰፊ መረባቸውን በመጣል፣ ብሔር-ተኮር ጉዳያቸውን በብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ አካዳሚያዊ መጽሔቶች እያቀረቡ፣ በነጻነት እንዲሞገት በማስቻል አጀንዳ እና ድምፃቸው ድንበር ተሻጋሪ እንዲሆን የላቀ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አካሄዳቸው ስልታዊ እርምጃ ይሁን ወይም የአጋጣሚ ተለይቶ ባይታወቅም መጠነ ሰፊ ተደራሽነትና የተሻለ የፖለቲካ ካፒታል ስለማትረፋቸው ማን ይጠራጠራል?
ከላይ የተጠቀሱት መጽሔቶች የብሔራችንን ጉዳዮች በጥልቀትና በስፋት እንመረምራለን ይላሉ። መጠየቅ ያለብን፡ የጥናቶቹ ትሩፋቶች ድንበርን ይሻገራሉ ወይ? ለጋራ አገራዊ ችግሮች መፍትሔ ያመጣሉ … ወይንስ በሚያለያዩን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አትኩረው እርስ በርስ ያያያዙንን ሙጫዎችና ጅማቶች እንዲሳሱና እንዲላሉ ያመቻቻሉ?
ቅዱስ መፅሃፉ የቄሳርን ለቄሳር … ይላልና በብሔር ፖለቲካ አጋፋሪነትና በምሁራዊ ሥራ መካከል ግልጽ ወሰን ሊኖር ይገባል። ምንም እንኳን የብሔር ተቆርቋሪነት የራሱ ቦታ ቢኖረውም፣ አካዳሚው ለብሔር ፖለቲካ መሣሪያ ሳይሆን ለአእምሯዊ ታማኝነት እና ለዓለም አቀፍ አካዳሚያዊ መርሆዎች መናኸሪያ ሆኖ መዝለቁ ተመራጭ ነው።
መጽሔቶቹ ገለልተኝነታቸውን ለማሳመን በኢዲቶሪያል ቦርዳቸው የተዘረዘሩ የዓለም አቀፍ ምሁራንን ስም በኩራት ያሳያሉ። የውጭ ዜጎች ምሁራንም በዝርዝሩ ይስተዋላሉ። ነገር ግን በውጪ አገራት ያሉ ምሁራን ገለልተኞች ናቸው ብለን እንመን? የጎሳ-ተኮር ትርክትን እንደ ዳንቴል ሲፈትሉ ውለው ሲተረትሩ የሚያድሩ ከመሃላቸው የሉም? የውጭ ዜጎቹስ ቢሆኑ … አንዳንዴ ከእኛ ብሰው አይገኙም? በታሪክ አጋጣሚም ሆነ በፖለቲካዊ ጋብቻ ሳቢያ ካንዱ ቡድን ማንነት ጋር በብርቱ ሊተሳሰሩ ይችላሉ። አልፎ ተርፎ የወገንኝነት ዝንባሌያቸው እየገነነ ለዘመናት “ከፍየሏ በላይ” ሲጮሁስ የታዘብናቸው የሉም?
የህንድ እና የናይጄሪያን ልምድ እንመልከት። ተሞክሯቸው የሚያሳየው የብሔር ማንነት አጥር ሳይበጅለት በአካዳሚያዊ መንገድ ሊስተናገድ መቻሉ ነው። ሁለቱ አገራት በብዝሃ ባህልና ቋንቋ የበለፀጉ ናቸው። የብዝሃ ብሔር ጉዳይን የሚያስተናግዱ አካዳሚያዊ መጽሔቶች ይጠቀማሉ። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍላቸው የአካባቢያዊ ጉዳያቸውን ከአገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ ጋር እያጣጣሙ ይሞግታሉ፤ የተለያዩ ትንተናዎችም በነጻነት እንዲፈተሹ ያስችላሉ።
ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲዎቻችን የመኝታ ክፍሎች ተማሪ ሲደለደል ተለይቶ ሳይሆን በዘፈቀደ ነበር። ከተለያየ አካባቢ የመጣ ተማሪ እርስ በርስ ተዋውቆ፣ ተላምዶ፣ ወዳጅነቱን ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚችልበት ሁኔታ ነበር፣ በተለያየ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ባህላዊ ውበቶች፣ ትውፊቶችና ማኅበረሰባዊ ህመሙን ለመረዳትም ሰፊ እድል ነበረው።
ዛሬ ግን ሁኔታው ተቀይሯል። አንዱ ተማሪ ከሌላው ቀርቦ ከመረዳትና ከመጎዳኘት ይልቅ ብሔር እየለዩ ሲጎዳኙ እና ከሌላው ጋር ሲጋጩ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። የትምህርት ሚኒስቴር አሰራርም ልዩነቱን አባብሶታል። አንዳንዶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ለሁሉም ብሔር ተማሪ እኩል ምቾት እና ዋስትና መስጠት የተሳናቸው ይመስላል። ልብ ብሎ ዩኒቨርሲቲዎቹን ለተመለከተ ልዩነታቸው ጂኦግራፊያዊ ብቻ ሳይሆን በራቸውን በሰፊው ከከፈቱላቸው ከተወሰኑ የብሔር(ሮች) ተዋፅኦ ማንነትም ጭምር ለመሆኑ ማመላከቻዎችን ማሳየት ይቻላል።
ድሮ ድሮ አንድ ተማሪ ከጂንካ ተነስቶ አስመራ ዩኒቨርሲቲ፤ ከጋምቤላ ተነስቶ አለማያ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ይማር ነበር። ዛሬ በአመዛኙ የኦሮሞው ተማሪ ኦሮሚያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የአማራው ተማሪም በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ወዘተ ይደለደላል። በዚህ አያበቃም። ወረድ ብለን ድልድሉን ስንመለከት ተማሪው ከአንድ ክልል መምጣቱ በቂ ሆኖ አይገኝም። ወደ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ የሚወርድ የአመዳደብ ስርዓት እየተተገበረ ይመስላል። ይህን መሰል አመዳደብ ለሌላው አካባቢ ቋንቋ፣ ባህላዊ እሤትና ማኅበራዊ ህመም ትኩረትን መንፈጉ አያጠራጥርም። አልፎ ተርፎም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይም የቸልተኝነት እና የምንአገባኝነት ስሜትንም ሊጋብዝ ይችላል።
ታዲያ ይህንን የቁልቁለት ጉዞ ሊገቱና ሊቀለብሱት ይችላሉ፣ ህብረተሰቡን በምሳሌነት ያስተምራሉ፣ ወደ ብዝሃ ማንነትና የጋራ ግብ ያሻግራሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውና … በበርካታ የዋሆች ዘንድ “የተማረ ይግደለኝ” የተባለላቸው ምሁራኑ አልነበሩ? ሆኖም አንዳንድ ቡድኖቻቸው ፖለቲከኞቹ በሚቀዱት ቦይ በፍቃደኝነት ሲፈሱ ማየት ግራ ሊያጋባ ይችላል። አንዱ ማሳያ ደግሞ የብሔር-ተኮር አካዳሚያዊ መጽሔቶቹ ናቸው።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለመደ አባባል አለ፡ ምርምርህን ሳታቋርጥ አሳትም፣ አሊያም ዞር በል (publish or perish)። ይህ ጫና በተለይም ወጣት ምሁራንን ወደ አቋራጭ የብሔር-ተኮር ህትመቶች እንዲጎርፉ እና ጊዜያዊ ችግራቸውን እንዲቀርፉበት ሊገፋፋቸው ይችላል፣ የብሔር ማንነት ትርክት ደቀመዝሙር ሊያደርጋቸውም ይችላል።
የብሔር-ተኮር መጽሔቶች አደጋ የብሔር ወገንተኝነትን ማስፈኑ ነው። Partiality የሚባለው ነው። አንድ ተመራማሪ ለብሔር-ተኮር አካዳሚያዊ መጽሔት ፅሁፉን ሲያዘጋጅ ቀድሞውኑ መደምደሚያው ለብሔሩ አጀንዳ አዎንታዊ መሆኑን አስረግጦ ነው። የጥናቱን አካዳሚያዊ ገፅታ ለመጠበቅ ተመራማሪው ለብሔሩ የሚስማማውን መረጃና ማስረጃ ብቻ ለቅሞ (cherry picking እንዲሉ) በመተንተን ከመደምደሚያው ጋር ያጣጥማል ማለት ነው፡ ልክ confirmation bias እንደሚባለው። ይህ አካሄድ የፖለቲካ ዲስኩርን ያጎለብት እንደሁ እንጂ ነጻ የምርምር መርሆዎችን ይሸራርፋል።
የአካዳሚያዊ ምሁር ከቀለጠው የብሔር ውዝግቡ መንበር ከፍ ብሎ መገኘትና በግራ መጋባት ጊዜ እንደ ታማኝ ኮምፓስ ወይንም ጂፒኤስ ማገልገል አለበት። አክቲቪስቶች ከፖለቲካው ነፋስ ጋር ልክ እንደ የአክሲዮን ገበያ ግራፍ ላይና ታች እንደሚዋዠቁትም መምሰል የለባቸውም። ያኔ ብቻ ነው ምሁራዊ ንጽሕናው ተጠብቆ ዘላቂ የሕዝብ አመኔታን ሊያገኝ የሚችለው። በተቃራኒው ከዚህ ሰገነት ወርዶ ከአክቲቪስቶቹ ጋር አቡክቶ ጭቃ ከተራጨ በኋላ ታማኝነቱም ተሰሚነቱም እንደ ጥላ ጥለውት ይኮበልላሉ።
አካዳሚያዊ የክርክር ገበያ እንደ ብሔር-ተኮር መጽሔቶች በዝግ ችሎቶችና በጓዳ መካሄድ የለበትም። ልክ ወንበሮቹ ተለይተው ለተመረጡ ተጋባዦች እንደሚመደቡበት አይነት የእራት ግብዣ መምሰል የለበትም። ይልቁንስ ሁሉም ተጋባዥ የየራሱን ቅመምና ማጣፈጫ የሚያቀርብበት የጋራ ድግስ መሆን ይኖርበታል። በእርግጥ አንዳንድ ሐሳቦች ልክ እንደ ሳህኖቹ ሊጋጩ ይችላሉ። ይሄ የቡፌ ገበታው ውበት ነው — ናሙናዎቹን በመቅመስ፣ ስለ ጥፍጥናው በመከራከር፣ ምናልባትም እንግዳ ጣእም ያለውን ምግብ ደግመው በመመገብ፣ ወዘተ። ብሔር-ተኮር ምሁራዊ ቡድኖችም ጠረጴዛቸውን ማርዘም፣ የግብዣ በራቸውን መክፈትና ማስፋት ይኖርባቸዋል።
በመጨረሻም … የአንድ መጽሔት ርዕስ በብሔርና በጎሳ ስም የሚጀምር ሆኖ ከተመለከትን፣ ቆም ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፦ ይህ አካዳሚያዊ ጥናት ነው… ወይስ የአቋም መግለጫ? አካዳሚያዊ አእምሯችን ከብሔር ማንነት ፖለቲካ ከፍ ብሎ መገኘት ካልቻለ፣ የአካዳሚክ ህትመቶችን ለዩ-ቲዩብ አስተያየት መስጫ ክፍል ማስረክብ ይኖርብናል።
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በኦስተን ቴክሳስ– የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።

