Print this page
Saturday, 12 November 2011 07:35

“ልጄ እኔ እንዳደኩት ማደግ የለበትም” የአበሻ ተለምዶአዊ አባባል ከአውሮፓ ስርዓት ይዞ እዚህ የመጣ ህፃን፤ በአንድ ወር አልቃሻ ሆኖ ተመለሰ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ረፋድ ላይ ነው፤ ሻይ ለመጠጣት አንድ ካፌ ገባሁ፡፡ ከተቀመጥኩበት ፊት ለፊት፣ ወጣቶች ተቀምጠዋል - ሁለት ወንዶችና አንድ ሴት ሦስት ዓመት ዕድሜ የማይሞላው የሴቷ ልጅ አብሯቸው አለ፡፡ ሴቷ የተማረችና ዘመናዊ የምትመስል በ20ዎቹ መጨረሻ የምትገመት ወጣት ናት፡፡ ሴቷ ከአንደኛው ወጣት ጋር ቁም ነገር የያዙ ይመስላል - እሷ ታወራለች፤ እሱ በአንክሮ ያዳምጣታል፡፡ ሕፃኑ ልጅ፣ ከሌላኛው ወጣት ጋር ይጫወታል -አጐቱ ነው ሕፃኑ ከጐናቸው ያለው ጠረጴዛ ላይ መውጣት ፈልጓል፡ አጐት ግን እንዳይባልግ ብሎ ወይም ሥነሥርዓት ለማስተማር …እንጃ አልፈቀደለትም፡፡ የተለያዩ ነገሮች እየሰጠ ሐሳቡን ለማስለወጥ ቢሞክርም ሕፃኑ ግን በቀላሉ የሚታለል አልሆነም፡፡

እየሳቀና እየተጫወተ የነበረው ልጅ ፍላጐትና ሙከራው ባለመሳካቱ ስሜቱ ተረበሸ፤ ንዴቱ መጣ፡ ፈገግታው ከፊቱ ሳይጠፋ ማልቀስ እየዳዳው ሙከራውን ቀጠለ፡፡ የእህቱ ቅጣት ከባድ መሆኑን የሚያውቀው አጐት “እናትህ ከሰማች ትገድልሃለች” በሚል ሁኔታ በአገጩ ወደ እሷ አመለከተ፡፡ ጨዋታ ላይ ብትሆንም ሁኔታውን ትከታተል የነበረችው እናት “ዋ ዝም በል! እንቢ ካልክ ዋጋህን እሰጥሃለሁ” በሚል ግልምጫ አነሳችው፡፡ ሕፃኑ፣ ፍላጐቱን እንዳያሳካ ከመከልከሉም በላይ የእናቱ ግሳፄ ስሜቱን የበለጠ አስቆጣውና በቋፍ የነበረውን ለቅሶ ለቀቀው፡፡ እናት በንዴት ጦፋ እያጉረጠረጠችበት ጣቷን ቀስራ “ዝም በል ነው የምልህ” ስትል ጮኸችበት፡፡ ሕፃኑ ግን አልሰማትም፤ የገነፈለ ስሜቱን በሚችለው መንገድ ለማብረድ ለቅሶውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ እናት፣ “ቆይ፤ እሠራልሃለሁ፤ ታውቀኛለህ” በሚል ሁኔታ የሕፃኑን እጅ ለቀም አድርጋ እየጐተተች ይዛው ወጣች፡፡ እንዴት እንደቀጣችው ባላውቅም፤ ቤቷ ቅርብ ነው መሰለኝ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ተመልሳ መጣች፡፡ በቅርቡ ነው፡፡ ታክሲ ለመጠበቅ ሰዎች ሰብሰብ ወዳሉበት ሳመራ፣ ሦስት ወይም አራት ዓመት የሚሆናትና እናቷን የመሰለች ጠይም ቆንጆ ልጅ ከዳር በኩል ስታለቅስ ሰማሁ፡፡ 
ከሕፃኗ ለቅሶ ይልቅ “ዝም በይ ነው የምልሽ ዝም፤ ዝም፤ አፍሽን ያዥ ብያለሁ፤ ዋ ታውቂኛለሽ፣ አስወጣልሻለሁ” የሚለው የእናት ጩኸትና ዛቻ ትኩረቴን ስቦ አያቸው ጀመር፡፡
በለቅሶ እንኳ ንዴቷን እንዳታበርድ የተከለከለችው ሕፃን እንደታዘዘችው፣ አፏን በትናንሽ እጆቿ ሸፍና ሲቃ እየተናነቃት፣ በሁለቱም ጉንጮቿ መንታ - መንታውን ታወርዳለች፡፡ ሕፃን ልጅ ይዞ ወጥቶ መንገድ ላይ እንዲህ ዓይነት ቅጣት ምን ይባላል? እቤት ቢሆን ኖሮ ቅጣቱ ከዚህ እንደሚከብድ መገመት አያቅትም፡፡
ሕፃናት በአብዛኛው ያዩት ነገር ሁሉ ያምራቸዋል፡፡ ያቺን ልጅ ለዚያ ቅጣት የዳረጋት ምናልባት እናቷን ብስኩት፣ ከረሜላ፣ ማስቲካ፣ አሻንጉሊት፣ መኪና፣…ግዢልኝ … ብላት እንቢ ስላለቻት፣ የፈለገችውን ነገር ለማግኘት ፣ ተነጫንጫ ወይም ማልቀስ ሞክራ ይሆናል፡፡
እናት ግን፣ በወቅቱ ፍላጐቷን ማሟላት የማትችልበትን እውነተኛ ምክንያት ገልፃ፣ በሌላ ጊዜ ግን የፈለገችውን ነገር፣ ያም የማይቻል ከሆነ ሌላ የምትፈልገውን ነገር እንደምታደርግላት ቃል ገብታና አሳምና ማባበል ስትችል፣ የመንገድ ላይ ቅጣት ምን ይባላል - የሕፃኗን ስሜት የበለጠ ከመጉዳት በስተቀር?
አሁን ደግሞ ጓደኛዬ የነገረኝን ከአውሮፓ የመጣ ልጅ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ አውሮፓ የምትኖር እናት ልጇን ይዛ መጥታ አንድ ወር ቆይታ ነው የተመለሰችው፡፡ እንደመጡ ሰሞን፣ እናት ሥራ ይዛ ወይም ከእንግዳ ጋር ሆና ልጅ የሆነ ነገር ሲጠይቃት፤ “በኋላ” ስትለው፣ ምንም ሳይል ይመለሳል፡፡ ትንሽ ቆይቶ መጥቶ በድጋሚ ሲጠይቃት፣ “በኋላ አልኩህ”ኮ” በማለት ስትገስፀው፤ ልጅ ያለ አንዳች ማንገራገር የተነገረውን ተቀብሎ ይመለስ ነበር፡፡
እንዴት መሰላችሁ? “በኋላ” የሚለው ቃል እናትና ልጅ የሚግባቡበት ትርጉም አለው፡፡ “በኋላ” ማለት፤ “አሁን ሥራ ስለያዝኩ ወይም ከእንግዳ ጋር ስለሆንኩ፤ የፈለከውን ነገር ልሰጥህ አልችልም፡፡ ሥራውን ጨርሼ ወይም እንግዳውን ሸኝቼ እሰጥሃለሁ” ማለት ነው፡፡ “በኋላ አልኩህኮ” የሚለው ግሳፄ ደግሞ፤ “የምትጨቀጭቀኝ ከሆነ ቃል የተገባልህ ነገር አይደረግልህም” የሚል ማስጠንቀቂያ ነው፡፡
ፀባዩ ጥሩ ከሆነ፤ ወላጆቹ የሚነግሩትን ነገር ከተቀበለ፣ ካላለቀሰ፤ ካልተነጫነጨ፤ በቤት፣ በሰፈር፣ በት/ቤት ጥሩ ልጅ፣ የሚያጠናና ጥሩ ውጤት የሚያመጣ … ከሆነ፤ ቸኮሌት መጫወቻ፣ ቢስክሌት ሊገዛለት፣ በእረፍት ቀን፣ ወደሚወደው መዝናኛ ቦታ ወስደው ሊያዝናኑት አያቱ አጐቱ፣ አክስቱ፣ ጓደኛው ቤት፣ ወስደው ከእኩዮቹ ጋር እንዲጫወት ሊያደርጉት … ቃል ይገቡለታል፡፡ ስለዚህ፤ የተገባለት ቃል እንዳይቀርበት፤ አያለቅስም፣ አይጨቃጨቅም፣ የተባለውን ይፈፀማል - ቅጣቱ መጥፎ መሆኑን ያውቃላ!
በውጭ አገር ቃል ቃል ነው፡፡ ለልጅ፣ እውነት እንጂ ውሸት አይነገርም፤ የማይፈፀም ተስፋም አይሰጥም፡፡ ልጁ ፀባዩ ይመር እንጂ ቃል በፍፁም አይታጠፍም፡፡ ጥፋት ከሠራ ግን ይቀጣል፡፡ ታዲያ ቅጣቱ ስድብ፣ ግርፊያ፣ ቁንጥጫ፣ በርበሬ ማጠን፣ ምግብ መከልከል … አይደለም፡፡ የተገባለትን ቃል ባለመፈፀም ነው፡፡ ቤተሰቡ ከአንድ በላይ ልጆች አሉት እንበል፡፡ ታዲያ ቃል የሚገባው ለአንዱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ልጆች ነው፡፡ የተነገረውን መመሪያ የማይቀበል ልጅ ይቀጣል - የተገባለትን በመከልከል፡፡
ቤተሰቡ ውስጥ ሦስት ልጆች ቢኖሩና ያጠፋው አንዱ ከሆነ፣ ሁሉም በጅምላ አይቀጡም፡፡ ሁለቱ ሲሸለሙ አጥፊው ይቀጣል፡፡
ከዚህ የከበደ ቅጣትም አለ፡፡ ለምሳሌ “በኋላ አልኩህ”ኮ” ተብሎ አልሰማ ካለና ንዝንዝ ካበዛ ወይም ካለቀሰ ወደ ክፍሉ ሄዶ ዘግቶ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡ እስር ቤት እንደማለት፡፡ ይቅርታ የሚደረግለት ደግሞ ጥፋቱን አውቆ ይቅርታ ሲጠይቅ ነው፡፡ ሰው በድሎ ከሆነ (እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም፣ እንግዳ ጐረቤት) አቅፎ ይቅርታ እንዲጠይቅ ይደረጋል፡፡
ከአውሮፓ ይህን ዓይነቱን መመሪያ ይዞ የመጣው ልጅ ግን፣ ዲሲፕሊኑን እንደጠበቀ መዝለቅ አልቻለም፡ ትንሽ እንደሰነበቱ አመሉ ተበላሸ፤ ነጭናጫና አልቃሻ ሆነ፡፡ እናቱን የሆነ ነገር ጠይቆ ወዲያው ካልሰጠችው ያለቅሳል፤ እናቱን ጠይቆ “በኋላ” ስትለው ከቤተሰቡ አባል አንዱ (አያት፣ አክስት፣ ዘመድ፣ …) ልጁ የፈለገውን ነገር ይሰጠዋል፣ ያደርግለታል፡፡ የሚፈልገውን ነገር እናት ወዲያውኑ ባትሰጠው ከሌሎች ስለሚያገኝና “ይቀርብኛል” የሚለው ሽልማት ስለሌለ፣ ለቅሶና ንጭንጭን የፈለገው ነገር ማግኛ ዘዴ አደረገው፡፡ በዚህ ዓይነት በአንድ ወር ቆይታ አልቃሻና ነጭናጫ ሆኖ ወደመጣበት ተመለሰ፡፡
ሌላው የአገራችን የልጅ አስተዳደግ ችግር፣ ልጅን በራሱ የማይተማመን ጥገኛ ማድረግ ነው፡፡ ሕፃናት ብዙ ጊዜ አዋቂ የሚያደርገውን ነገር መኮረጅ (ኮፒ ማድረግ) ይፈልጋሉ፡፡ አቅምና ጉልበቱን መፈተሽ የሚፈልግ ሕፃን በእግሬ ልሂድ ሲል ይደክመዋል፣ ይወድቃል፣ … ብሎ መከላከል ነፃነት መንፈግ ነው፡ ነጮች ልጆቻቸውን የሚመግቡት ሕፃኑ ማንኪያና ሹካ መያዝ እስኪችል ድረስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ልብሱን እንዳያበላሽ አንገቱ ላይ ጨርቅ አስረው፣ ሹካና ማንኪያ አስይዘው ምግብ ያቀርቡለታል፡፡ ሕይወቱን ለማሰንበት ብቻ ሳይሆን የትልልቅ ሰዎችን አመጋገብ ለመሞከር በመጓጓት፤ አፉን እየሳተና ፊቱን በወጥ እየለቀለቀ ይመገባል፡፡ ይህም፤ ዓለም በራስ ጥረትና ትግል የሚኖርባት መሆኗን የሚማርበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው፡፡
“እኔ ካላጐረስኳት ልጄ አትበላም” እያለ የ8 ዓመት ልጅ በራሷ እጅ እንዳትበላ ያደርግ የነበረ አባት አውቃለሁ፡፡ ታዲያ ያቺ ልጅ ምን ሆነች መሰላችሁ? በራሷ አንዳች ነገር ማድረግ የማትችል የቤተሰቦቿ ሸክምና ጥገኛ ሆና ቀረች፡፡ ዛሬ በ23 ዓመቷ ሕይወቷን እንዴት መምራት እንዳለባት፤ ደካማና ጠንካራ ጐኗን … አታውቅም፡፡ አባት ያለ አቅሟ፤ ያለ ችሎታና ዝንባሌዋ፤ እሱ እንድትሆንለት በሚፈልገው መንገድ ሊመራት ይሞክራል፡፡ ታዲያ አንድም ቀን ውጤታማ ሆና አታውቅም፡፡
በአሁኑ ወቅት ብዙ ወላጆች “ልጄ፣ እኔ እንዳደኩት ማደግ የለበትም” በማለት ለልጆቻቸው እየኖሩ ነው፡ እነሱ ያልበሉትን ልጆቻቸውን ይመግባሉ፤ እነሱ ሳይማሩ ብዙ ገንዘብ ከፍለው ልጆቻቸውን ጥሩ ት/ቤት ያስተምራሉ፤ እነሱ ያልለበሱትን ያለብሳሉ፤ ጤናቸውን ይጠብቃሉ፣ ያዝናናሉ …፡፡
ይኼ ምንም ችግር የሌለበት ከወላጅ የሚጠበቅ በጐ ምግባር ነው፡፡ ነገር ግን “እኔ እንዳደኩት ልጄ ማደግ የለበትም” በማለት ልጅ ሥራ፣ እውቀት፣ ልምድና ሙያ … እንዳይማር ማድረግ ትልቅ በደልና ጥፋት ይመስለኛል፡፡
አክስቴ ቤት እየሠራሁ ስማር፣ ለእግሬ ሸራ ጫማ አሮብኝ፣ እግሬ ተሰነጣጥቆ ነበር ያደኩት የምትል እናት፤ እኔ እንዳደኩት … በሚለው መርህ፤ ልጇ የፈሰሰ ውሃ እንድታቀና አትፈቅድላትም ነበር፡፡ ልጅት ታዲያ በ14 ዓመቷ ወጥ መሥራትና ሌላ ሥራ መስራት ቀርቶ ሻይ ማፍላት አትችልም፡፡ “የእሷን ሕይወት አንቺ አትኖሪላትም፡፡ ለምንድነው ይህችን ልጅ ሙያ እንዳትለምድ የምታደርጊያት” ስትባል “ቀጥራ ታሠራለች፤ በእነሱ ጊዜ እጅ ሳይሆን ማሽን ነው የሚሠራው” ትል ነበር፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ማሽን ቢሠራስ? አዘጋጅቶና መጥኖ የሚያጐርሰው ሰው አይደለም እንዴ? ማሽኑንስ ማን ይሰራዋል?
ልጅን ያለ አቅሙ አታሠሩት፤ ጉልበቱን አትበዝብዙ፤ አትጨቁኑት፤ … ተባለ እንጂ እውቀት፣ ሥራ፣ ሙያ፣ … አታስተምሩት አልተባለም፡፡ ስለዚህ አንድ ልጅ በዕድሜው ጫማውን ቢያስር፣ አልጋውን ቢያነጥፍ፣ የበላበትን ሳህን ቢያጥብ፣ … መበደል አይደለም - ሕይወትን ማስተማር እንጂ!!

 

Read 2281 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 07:38