Saturday, 05 April 2025 10:14

የአሰብ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ በአሰብ የመገልገል መብቷ

Written by  ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ (ከአሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ)
Rate this item
(13 votes)

አሰብ፣ “አሰብ” ከመባሉ በፊት የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱን ስሙ ተርሴስ ነበር። ከ4000 ዓመታት በፊት ተርሴስ ብላ የሰየመችውም “ተርሴስ” የተባለች የጻድቁ የኢዮብ ልጅ ሚስት የሆነች ሴት ናት። ጻድቁ  ኢዮብ በሰይጣን ተፈትኖ ፈተናውን አልፎ፣ እንደገና ልጆች ወልዶ ወንዶች ልጆቹ ሚስቶቻቸውን ይዘው ወደ አፋር አገር ፈልሰው እንደነበር ታሪክ ይዘግባል።  ታዲያ ከሴቶቹ አንዷ የባህሩን ወደብ ስታይ ስለወደደችው ስሟን ህያው ለማድረግ “ተርሴስ” አለችው። ከዚያ በኋላ ለ4000 ዓመታት ተርሴስ የተባለው ስም በመካከለኛው ምስራቅ ሲያስተጋባ ኖረ። “አሰብ” የተባለው ስም ከባህር ጨውነት ጋር የተያያዘ በኋላ የመጣ ቃል ነው።
“ተርሴስ” የሚለው መጠሪያ ግን ለምስክርነት በብሉይ ኪዳን ውስጥ በብዙ ቦታ ተጠቅሷል። እሱም ከአፋሮች ነጋዴነት ጋራ የተያያዘ ነው። አዎን፣ በመጽሀፍ ቅዱስ “የተርሴስ ነጋዴዎች” ይላቸዋል። የዚህም ምክንያቱ  አፋሮች የሚያስደንቁ መርከቦች ሠርተው፣ ብርቅዬ እና ውድ የሆኑ ማእድናትንና የእርሻ  ውጤቶችን፣ እንዲሁም ለማዳ እንስሳትን እየጫኑ በድሮው ዐለም ይነግዱ ስለነበር ነው። ንጉሥ ሰለሞን የዛሬ ሶስት ሺ ዓመት ቤተመቅደሱን ሲገነባ የግባት እቃዎቹን፣ የአፋርን ሉል፣ ወርቅ፣ ዞጺ (ውድ ጥቁር እንጨት) እንዲሁም እጣን፣ ከርቤ፣ ሰንደልና የመሳሰሉትን አፋሮች ከተርሴስ ወደብ በመርከባቸው ጭነው ይልኩለት ነበር። እሱም  የራሱን መርከቦች እዛው አሳንጾ በዛው አካባቢ ከነበረ  ጽዮን ጋብር ከተባለ ወደብ በተጨማሪ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች ያጓጉዝ ነበር።
በስፔን አካባቢ ያለው ተርሴስ፤ የአሰቡን ለማስታወስ ኢትዮጵያውያን በስፔንና ፖርቱጋል የሰየሙት ነው። እንዴት ቢባል፣ የዛሬ 2030 ዐመት መጋል የተባለው የጂማና የደርዴና ንጉሥ በአፋር መርከብ ተሳፍሮ፣ የአማራን ጦረኛ ይዞ፣ የኦሮሞ ካህናትን ጭኖ እስፔንንና ፖርትጋልን ለአጭር ጊዜ ቅኝ ገዝቶ፣ የአሰብን ተርሴስ ለማስታወስ የስፔኑን ወደብ ተርሴስ ስለ አለው ነው። ይህን እኔ “Promise Fulfilled” በተባለው መጽሐፌ ለዐለም ገልጫለሁ። “የአማራ እና የኦሮሞ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የተሰኘውና “የተሰወረውና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ” በተባሉትም መጻሕፍቴ ጠቅሻቸዋለሁ።
ተክለጻዲቅ መኩሪያ እንደሚተርኩልን፣ እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለዘመን ድረስ አሰብ  ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሳለች፣ ሱልጣን ኢብራሂም የተባለ የአፋር ባላበት ለአንድ የጣልያን የንግድ መርከብ ኩባንያ ግዜያዊ ማረፊያ ይሆነው ዘንድ የአሰብ ወደብን እንዲ ጠቀመብት ገንዘብ ተቀብሎ ፈቀደለት።  ሸጠለት የሚሉም አሉ። ቀስ በቀስ ግን ይህ ኩባንያ መሬቱን እንደራሱ ንብረት ቆጥሮ ለጣልያን መንግስት መላውን ወደብ ሸጠለት። የጣልያን መንግሥትም ይህን ሰበብ አድርጎ ወታደሮች ወደዛ እየላከ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት ወደ ውስጧ መዝለቅ ጀመረ። በላይ በምጽዋ በኩልም ለመግባት ሲሞክር የአጼ ዮሀንስ የጦር አበጋዝ ጀግናው ራስ አሉላ አባ ነጋ እንደምንም በርትተው በዶግአሊና ሌሎች ቦታዎች ድባቅ ቢመቱትም፣ ኤርትራን በመጨረሻ ይዞ አስመራን ለመቆጣጠር በቃ።
በሀያኛው ክፍለ ዘመን ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን ወርሮ ተሸንፎ ሲወጣ  (በዩኒየኒስት ወይም አንድነት ፓርቲ) አባሎች አነሳሽነት በርከት ያሉ የኤርትራ ሰዎች በፍላጎታቸው መርጠው  ከኢትዮጽያ ጋራ በፊዴሬሽን ተቀላቀሉ። በእዚህ ምክንያት ምጽዋና አሰብም ለኢትዮጵያ ተመለሱ። የኢሳያስ አባት አቶ አፈውርቂም ኤርትራ ከኢትዮጽያ ጋራ እንድትዋሀድ ከታገሉት ሰዎች አንዱ ነበሩ። ምንም እንኳን ልጃቸው ወደ ሻብያነት ተለውጦ የኢትዮጵያን መንግሥት ተዋግቶ የኋላ ኋላ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ቢያስገነጥልም። ቀደም ሲል አጼ ኃይለሥላሴ ለአንድነቱ ጉዳይ በጣም ተግተውበት ስለነበረ በወቅቱ እንደዚህ ተብሎ ተዘፍኖላቸው ነበር---
አባ ጠቅል ሳለ ማንን እፈራለሁ፣
በኤርትራ ባህር ገብቼ ዋኛለሁ።
አባ ጠቅል ኃይሌ የትዮጵያ ምሰሶ፣
የተዘጋውን በር ከፈተው መልሶ።
ጣልያን ከኢትዮጵያ እስከተባረረበት ወቅት የአሰብ ወደብን ቢይዝም የኢትዮጵያ አፋሮች፣ ኩናማና ብሌኖች እሱን ከመጤፍ ሳይቆጥሩት፣ አሰብ የእነሱና የኢትዮጵያ እንደሆነች ያስቡ ነበር። ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን አብረው ከሆኑበትና ባለፉት የቅርብ ዓመታት ኤርትራ እስከ ተገነጠለችበት ወቅት ኢትዮጵያ አሰብንና ምጽዋን በእኩል ታስተዳድር ነበር። ምጽዋን አዳብራ በባህር ኅይል መርከቦች ሞልታ፣ አሰብን ደግሞ የንግድ መርከቦች አስፍራበት ነበር። ምጽዋ ላይ የነበሩትን የጦር መርከቦች ህወሓትና ሻቢያ ተመሳጥረው ወደ የመንና ሌሎች የአረብ ሀገራት ወስደው በርካሽ ዋጋ መጣላቸው አይዘነጋም።
በ1950 ዓ.ም፣ ማለትም የዛሬ 67 ዓመት፣ አሰብ በስም ወደብ ይባል እንጂ ከቶም ከእውነተኛ ወደብ የሚቆጠር አልነበረም። ከተማውም በቂ የመጠጥ ውሀና የመብራት አገልግሎት አልነበሩትም። አሰብ ተገንብቶ በዐለም አቀፍ ደረጃ ያገለግል ዘንድ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሤ አርቀው በማሰብ በዘመናዊነት እንዲገነባ አዘዙ። የወደቡም ዋና አስተዳደር በመከላከያ ሚኒስቴር ስር ገብቶ የወቅቱ የመከላከያ ሚንስትር የነበሩት፣ በወንድማማቾቹ በገርማሜና በመንግስቱ ንዋይ  መፈንቅለ መንግሥት የተረሸኑት አርበኛው ራስ አበበ የመሀንዲሶቹን እቅድ አጸደቁት።  
የግንባታውም ብድር የተገኘው ከዩጉዝላቪያ መንግሥት ሲሆን፤ የበላይ መሀንዲሶቹም ዩጉዝላቭያኖች ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ኢንጅነር በቀለ፡፡  ለወደቡ ግንባታ የተመደበው ገንዘብ 25 ሚሊዎን ብር ሲሆን፤ ይህም ገንዘብ ለዘመኑ በጣም በርካታ ነበር።
ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ሲጠናቀቅ፣ የአሰብ ወደብ ተስፋፍቶ አስፈላጊዎቹ ቤቶች ሁሉ ተሰርተውለት በዐለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ሆነ። የባህር ትራንዚትና የጉምሩክም ቢሮዎች ተከፍተውለት ሥራውን በስነስርስዓት ጀመረ። የከተማውም ህዝብ  በቂ መብራትና ውሀ አገኘ።
የኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ኢሳያስ አፈወርቂና መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳያማክሩ፣ የሰፊውን  የኤርትራውያንንም እውነትኛ ምኞትና ፍላጎት ሳይጠይቁ በግድና በማስፈራራት ከባርነት እና ከነጻነት የቱ ይሻላችኋል፣ ብለው መገንጠልን አስመረጧቸው። እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነገር፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ከኢሳያስ አፈወርቂ ይልቅ የመለስ ዜናዊ ጥድፊያ ነው። ለተባበሩት መንግሥታት ማህበር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ቶሎ ትገንጠልልኝ ብሎ ሲከትብ፣ አጀብ! አጀብ! አገሩን ቶሎ ለማስገንጠል የሚጽፍ መሪ! ብለው የዐለም ፖለቲከኞች ተደመሙ። መለስ ለምን ተጣድፎ ኤርትራን ለማስገንጠል እንደፈለገ ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶች ያቀርባሉ። ከምክንያቶቹ አንዱ እናቱ ኤርትራዊ ስለሆኑ ነው፣ይላሉ። አባቱ አቶ ዜናዊ አባታቸው ደጃዝማች አስረስ ለጣልያን ገብተው ስለነበር፣ በአባታቸው ጥፋት በትግራይ ህዝብ ዘንድ  አቶ ዜናዊን በፍቅር ስላላዩአቸውና ሚስትም አንድርልህም ስለአሉዋቸው ከኤርትራ ሴት ልጅ ፈልገው እስከሚያገቡ ድረስ ስለበደሏቸው፣ መለስ ቂም ይዞ ነው  የሚሉም አሉ። ምናልባትም፣ በሩስያ መሪ በዮሴፍ ስታሊን ጽሁፍ በሰፈረው የብሄሮች እስከመገንጠል መብት በሚለውም መርሆ  መለስ አምኖበትም ይሆናል። (በነገራችን ላይ፣ “መለስ”  ከመባሉ አስቀድሞ “ለገስ”፣ ለገሰ ከመባሉም በፊት  በልጅነቱ ነጋሲ ይባል እንደነበር  የመንደሩ ሰዎች ይናገራሉ።)    
ይኸው መለስ  በምርጫ ዘጠና ሰባት ሕወሓት በተቃዋሚ ፓርቲዎች በእነ ቅንጅት  በተሸነፈችበት ወቅት፣ ለምን ላለመሸነፍ እንደፈለገ ተጠይቆ ነበር። መልሱም የጀመርነውን ሥራ ሳንጨርስ እንዴት ጥለን እንሄዳለን፣ የሚል ነበር። ይህም ኤርትራን በሚገባ ሳላስገነጥል እንዴት ስልጣን እለቃለሁ፣ ማለቱ ነበር።
ኢሳያስ አፈወርቂ ግን ለመገንጠል አልቸኮለም ነበር። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት መሪ እስከሚመስል ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ተመችቶት ነበርና። በመለስ ትእዛዝ ለኤርትራ ካሳ ይሰጣት ተብሎ ኤርትራ በቢሊዎን የሚቆጠር ብሮች አንድ ጊዜ ተችራ ነበር። ያለቀረጥ የችርቻሮ እቃዎች አስገብታ በርካሽ እየሸጠች የመርካቶ ነጋዴዎችን ከንግድ አስወጥታለች። ይግረማችሁ ብላ የኢትዮጵያን ቡና፣ የኤርትራ ቡና ብላ ጆንያ ላይ ጽፋ ለዐለም የቡና ገበያ ለማቅረብም ደፍራ ነበር። አዲስ አበባ ይገኝ በነበረው ኤምባሲዋ ውስጥ ተቀናቃኞችዋን ከማሰርም አልፋ እስከ መግደል እንደደረሰችም በወቅቱ ይነገር ነበር። በራሱ ምክንያት እሷ ቶሎ እንድትገነጠል ይሻ የነበረው መለስ ግን በሚስጥር የኢትዮጵያን ብር ቀይሮ ኤርትራ አካብታው የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ከንቱ አስቀረባት። ይህም በመሆኑ ኢሳያስ ተበሳጭቶ “እኔ በጀርባዬ አዝዬ ወያኔን አዲስ አበባ አስገብቼአት፣ ብቻዋን ኢትዮጵያን ልትበላ ካደችኝ” እያለ መናገር ጀመረ። በዚህ ብስጭቱም ሕወሓትን ለመበቀል ብሎ ምድረበዳውን ባድመን ሰበብ አድርጎ ነገር በመፈለግ  በትግራይ  ትምህርት ቤት ባሉ ህጻናት ላይ  ቦምብ ጥሎ ኢትዮጵያን ወረረ። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በእዚህ ድርጊቱ ተቆጥቶ ሆ! ብሎ ዘመተበት። የአትዮጵያም ሰራዊት በሸናፊነት እየተመመ ወደ አሰብና አስመራ ሲገሰግስ፣ ይኸው መለስ ዜናዊ አስቆመው። በሕወህት ውስጥ የነበሩ እንደ ስዬ አብርሀ አይነቶች ከተዋጋን አይቀር ለምን አሰብን አንይዝም ብለው ቢቆጡ፣ ሙሰኞች ተብለው ዘብጥያ መወርወራቸው የዛን ጊዜ ትዝታ ነው።
አሁን በቅርቡ የኢትዮጵያ መከላከያና የሕወሓት ጦር ሰራዊት ሲዋጉ የኢሳያስ ጦረኞች ትግራይ ውስጥ ገብተው ህወሓት ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ያባረረቻቸውን ኤርትራውያን በማስታውስ ቂም ይዘው በአያሌው ተበቅለዋቸዋል።
ኢትዮጵያ ለኤርትራ ብዙ ነገር አመቻችታላት ነበር። ነገር ግን  ኢሳያስ አፈወርቂ በቃሉ የሚረጋ ሰው ሆኖ አልተገኘም። በተለያዩ ጊዜያት ስለ አሰብ ሲጠየቅ ኢትዮጵያ በነጻ ልትገለገልበት እንደምትችል በአፉ ይገልጻል። በተግባር ግን ፍንክች የአባ ቢላኋ ልጅ ነው። በቅርቡ እንኳን አሁን ከአለው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ አሰብን በጋራ ለመጠቀም ተዋውሎ ኢትዮጵያ በእሷ በኩል ያለውን ወደ አሰብ የሚወስደውን አውራ ጎዳና ብዙ ገንዘብ አፍስሳ አነጠፈች። ኤርትራ ግን የራሷን ድርሻ አልፈጸመችም። ከነጭራሹ የተሰባበረውንና የፈራረሰውን የአሰብ ወደብ ሁሉ ኢትዮጵያ እንድትገነባላት ትከጅላለች።
የኢሳያስ አፈወርቂ ዋናው ቅዠት ኤርትራን ታይዋን አድርጌ ብዙ ህዝብ የአላትን ኢትዮጵያን የሸቀጤ ማራገፊያ አደርጋታለሁ ማለቱ ነበር። ይህንንም ለመተግበር ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥተናታል። እሷ በጎሳ ጦርነት ተጠምዳ እርስ በእርሷ ስትፋጅ እኛ በሰላም እየኖርን በኢንዱስትሪና በኢኮኖሚ ወደፊት እመር! እንላለን፣ ሲል ታብዮ ነበር። ዳሩ ግን ቅዠቱ ተነነበት። ለሀገሩ የረባም ኢንዱስትሪ ሳያቋቁምና የኤኮኖሚ አውታር ሳይዘረጋ ጊዜው መሸበት።
ለማንም በማይበጅ ባድመ በሚባል ምድረበዳ ይገባኛል አሳቦ ኢሳያስ አፈወርቂ ጦርነትን ጭሮ ከኢትዮጵያም ከኤርትራም በኩል መአት ሰው እንዲያልቅ ምክንያት ሆነ። በዚያው በጦርነቱ ወቅትም ከባህር ማዶ መጥተው ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ የነበሩ ተሽከርካሪዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን አለአግባብ ወርሶ አስቀረ። ኢትዮጵያውያን ባለቤቶቹ አዝነው ቀሩ። ፍጹም የውንብድና ሥራ እና ዐይን ያወጣ ዝርፊያ ነበር ኢሳይ የፈጸመው።
ኢሳያስ አፈወርቁ የማይገነዘበው ወይም ሊገነዘብው የማይፈልገው ነገር 120 ሚሊዎን ህዝብ ተሸክማ
በመሬት የተከበበችው  ኢትዮጵያ የባህር በር ታገኝ ዘንድ ግድ እንደሚላት ነው። በግድም በውድም በዐለም አቀፍ ህግም ኢትዮጽያ ወደብ እንዲኖራት መፈቀዱ አይቀሬ ነው።

በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኞች ጉዳት እንዳያደርሱ ጸጥታንና  እና ደህንነትን ለመጠበቅም ቢሆን እንደ ኢትዮጵያ ያለ በውትድርና  ጠንካራ ሀገር የለም። ይህንንም እውነት የአሜሪካ እና የአውሮፓም መንግሥታት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለ እዚህም ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ወደብ የማግኘት መብት እንደአላት ይገነዘባሉ።
ወደ አሰብ ስንመለስ፣ ደርግ በመውደቅ ላይ ሳለ በሰላም ስልጣንን ለመረካከብ ወያኔ እና የደርግ ተወካዮች ለንደን ላይ በአሜሪካ ሸምጋይነት ሲነጋገሩ እንደነበር አይዘነጋም። በእዚህ ሰአት አደራዳሪው ሄርማን ኮህን ደጋግሞ በአደባባይ እንደተናገረው፣ መለስን ለብቻው ጠርቶት አሰብን ለኢትዮጵያ ያዝ፣ ለትንሿ ኤርትራ ምጽዋ ይበቃታል፣ ቢለው አንተን እዚህ ውስጥ ምንም አያገባህም፣ አሰብ የኤርትራ ነው፣ ሲል አፍቃሬ ኤርትራነቱን በቁጣ መሰከረ። በሌላ ጊዜም ስለአሰብ እና ስለኢትዮጵያ ወደብ-አልባነት ሲወራ መለስ ሆዬ “ገበያ ወጥተን የፈለግናቸውን የሌላ ሀገሮች ወደቦች አማርጠን በገንዘባችን እንከራያለን” አለ። ብሎም አልቀረ ከመቶ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ግዛት ከነበረችውና በደርግ ፈዛዛነት ወደ  ኢትዮጵያ እጅ ካልተመለስችው ጂቡቲ በሚዘገንን ዋጋ ወደብ ተከራይቶ ኢትዮጵያን አስከሰራት። ስለአሰብ ውሀ ሲወሳ ደግሞ፣ ኤርትራውያኖች ቢሹ ግመላቸውን ያጠጡበት፣ ብሎ ለአፉ ለከት ሳይኖረው አምቧረቀ።
በሕወሀት አሳልፎ ሰጭነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ አሰብን ከመመንተፏ በፊት ግን የንጉሠነገሥቱ እና የደርግ መንግሥታት አሰብ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ የሀቅ እርስት መሆኑን ተገንዝበው አልምተውት ይጠቀሙበት ነበር። እዚህ ላይ መዘከር የሚገባው በቀድሞው የሶቭየት ኅብረት ተራድኦ የተቋቋመው  የአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ ነው። ይህ ተቋም በዘመኑ ለኢትዮጵያ እጅግ የሚጠቅም፣ በቀን 800 ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ድፍድፍን ያጣራ ነበር። ኤርትራ ይህን የራሷ ስታደርገው ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቋሙ ባለሙያዎች ተበተኑ። ተቋሙም ሥራ ፈቶ ወደ ዝገት ተለወጠ። ራሱን ወደቡንም ኤርትራ ምንም አልፈየደችበት። እሱም አርጅቶ ዋጋ ቢስ ሆነ።
እንግዲህ አሰብ በጉልበት እና በሽፍጥ ከኢትዮጵያ ተነጥቆ ለኤርትራ የተዳረገ የኢትዮጵያ አንጡራ ገንዘብ እና እርስት መሆኑ እሙን ነው። ኢትዮጵያ፣ ቁጥሩ ከ 120 ሚሊዎን የማያንሰው ህዝቧ አንድ የባህር በር  አጥቶ ሲታፈን፣ ሁለት የባህር ወደቦች ከያዘችው፣ ባለ ጥቂት ሚሊዎን ሰዎች ከሆነችው ከኤርትራ ጋራ ተስማምታ በመተዛዘን በቀድሞ እርስትዋ መጠቀም ካልቻለች  እና በጉልበት ብታስመልስ ምን ይደንቃል? ምንም ከጦርነት ይልቅ ሰላም ቢመረጥም፣ ሰው በኃይል የተነጠቀውን አንጡራ ሀብቱን በኃይል ማስመለስ የተለመደ የተፈጥሮ ህግ ነው። ከኀይል በፊት ግን ያለመሰልቸት የመግባባት እና የእርቅ ድርድርን ማስቀደም ከወንድማማቾች ሕይወት ጥፋት እና ከጋራ ንብረት ውድመት ይሰውራል። እርቅ ከተገኘም ሁለቱም ህዝቦች በጋራ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።


Read 2925 times