Wednesday, 02 April 2025 21:26

አምሳለ ሕይወት - ሰው እስካለ ድረስ

Written by  አብርሃም ገብሬ ደቢ
Rate this item
(6 votes)

በኪነት ፍልስፍና (art philosophy) ታሪክ ውስጥ፣ የኪነት ዋነኛ ተግባር አስተማስሎ (representation) እና እውነትን ክሱት ማድረግ ነው የሚል የቆየ ስምምነት አለ፡፡ ለአብነትም ፕሌቶ የኪነት ሚናን፤ “ዕውነታን በኪናዊ ስራዎች ውስጥ ማስተማሰልና ቀጥታ መቅዳት ነው” ሲል ይበይናል፡፡ ታዲያ ክሱት የሚደረገው ይህንን ዕውነት፣ ከያኒው በኪናዊ የፈጠራ ሥራው አማካይነት የሚሰራው ዕውነት አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ አስቀድሞ በማህበረሰቡ አማካይነት የተዋቀረና የወል ሥምምነትን ያገኘ ዕውነትን ውብ አድርጎ ማቅረብ ነው እንጂ፡፡ ከአዘቦታዊ ኩነቶች አተልቆ የማሳየትና የመግለጥ ሚናን ነው ፕሌቶ የኪነትን ዋነኛ ዓላማና ግብ አድርጎ የበየነው፡፡
ይህ የፕሌቶ ኪናዊ እሳቤ፣ በኪነጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ምንነትና ዓላማ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ Miguel de Beistegui የተባለው የሥነ-ጥበብ ፈላስፋ፣ ‘Aesthetics After Metaphysics’ በተሰኘው መጽሐፉ፣ በተለያዩ ፈላስፋዎች መካከል የኪነት ፍልስፍናን በሚመለከት ሰፊ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም፣ በመሰረታዊ እሳቤያቸው ግን ሁሉም የሚጋሩት አንድ ጉዳይ አለ ይላል፡፡ ይህም ኪናዊ እሳቤያቸው “ፕሌቶናዊ” መሆኑን በመጽሐፉ ውስጥ በርካታ አስረጆችን በማቅረብ ይሞግታል፡፡ በተለይ ኪነትን ዲበ-አካላዊ ገጽታን በመስጠት በሰው የህይወት ዕሳቤ ውስጥ ተምኔታዊነትን እንዲሰርጽ ማድረጉንም ተችቷል፡፡
እኔም፣ የኪነጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች የመጨረሻ ግብ የወል ዕውነትን መግለጥ ወይም ማሳየት ነው በሚለው ዕሳቤ ብዙም አልስማማም፡፡ ከዚያ ይልቅ ኪነጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ‘አማራጭ የህይወትን መንገድ መቀየስ አለባቸው’ ከሚሉት ወገን ነኝ፡፡ ህይወት፣ አምሳለ-ብዙ መልክ እንዳላት ማሳየት፡፡ ሕይወትን “ቅዱስ”ም “እርኩስ”ም ከሚሉ ብያኔዎች ባሻገር ተጉዞ የሚፈትሽ መሆን አለበት-ኹነኛ የፈጠራ ሥራ፡፡ አስቀድሞ የተባለውን ማስተጋባት ሳይሆን፣ ባልተሄደበት መንገድ ሄዶ ሕይወትን ከነጉድፎቿ ውብ አድርጎ የማሳየት ጣጣም ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ ለዳሰሳ የመረጥኩትን የዲበኩሉ ጌታን ‘ሰው እስካለ ድረስ’ የግጥም ስብስብ መጽሐፍም በዚህ አውድ ውስጥ ሆኜ ነው ያነበብኩት፡፡ ማለትም መጽሐፉ የህይወታችንን አምሳለ-ብዙ ገጾችን በማሳየት፣ በመተቸትና ሌላ የሕይወት መንገድ መኖሩን የሚያሳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
በቅርቡ ለተደራስያን በቀረበው በ’ሰው እስካለ ድረስ’ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች ህይወትን ይሄሳሉ፡፡ ከኑረታችን ውስጥ ዥንጉርጉር ሰበዞችን እየመዘዙ፣ የህይወትን ሌላኛው ገጿን በድፍረት ያሳዩናል፤ግጥሞቹ፡፡ገጣሚው ሕይወትን እንደ ቂጣ በሁለቱም ጎኗ እያገላበጠ ያጠይቃል፡፡ በልማድ የተስማማንባቸው ጉዳዮችን ይሞግታል፡፡ ከወል ዕውነታ ባሻገር ሌላ ዕውነት መኖሩን ጭምር ያሳየናል፡፡
…የለም ሙሉ ስህተት ከቶም ፍጹም ስኬት
የለም መርጦ መሆን ዘሎ ማለፍ ቅጽበት
የለም በተናጠል ዕንባ ያለ ደስታ
የለም ያለ ጥምረት ተስፋ አልባ ትዝታ…፣
ያም ሁሉ አንተ ነህ፤ ‘ባይሆን’ እና ‘እንኳኑ!’
ለሰርግ እና ለሞት-አንድ ነው ድንኳኑ፡፡
ሕይወት ውስጥ ፍጽምናን ማሰስ ተምኔታዊ እንደሆነ ዘግይቶም ቢሆን መገንዘባችን የማይቀር ነው፡፡ የ18ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮጳውያኑ የዘመነ-አብርሆት (Enlightenment) እንቅስቃሴ ካስተዋወቃቸው በርካታ ተምኔታዊ እሳቤዎች መካከል፣ ሰው እየተሻሻለ (progress እያደረገ) እና በአመክንዮ እያሰበ ሲሄድ ወደ ፍጽምና (perfectablity-ነት) ይደርሳል የሚለው ‘ቅዠት’ አንዱ ነው፡፡ በዚህ መንገድ በመጓዝ፣ የዩኒቨርስን ውስጠ ምስጢር ጭምር ማወቅ ይቻላል የሚለው ተምኔታዊ እሳቤም የዚህ ተቀጥላ ነው፡፡
ታዲያ ይሄ ተምኔታዊ እሳቤ ብዙዎቻችን ሳናላምጥ የዋጥነው ቅዠት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሰው ወደ ፍጽምና ወይም ምሉዕነት እንደማይደርስ በርካታ ታሪካዊ ማሳያዎችን ለመዘርዘር ቦታው ስላልሆነ ልለፈው፡፡ ነገር ግን የዚህ ተምኔታዊ ዕሳቤ አንዱ ተጽዕኖ ስሜትን የመካድና የማጣጣል ተዋስኦ (discourse) ማዋለድ መቻሉ ነው፡፡ የሰውን ስሜት እንደ አደገኛ ነገር በመፈረጅ የአመክንዮ ጠንቅና ያለመዘመን ማሳያ ተደርጎ በታሪክ ሂደት ተስሏል፡፡ እንዲሁም አመክንዮኣዊነትን የመጨረሻ ዕውነት አድርጎ ራሱን ማስረጽ ችሏል፡፡
የሰው ልጅ ተፈጥሮ ግን ከአመክንዮ ይልቅ ለሥሜት እንደሚቀርብ የታወቀ ነው፡፡ ይህንን ለማብራራት ሌላ ሃተታ አልጨምርም፡፡ እጥር ምጥን ባለ ቋንቋና ውብ አገላለጽ “ዓይንም አይጠግብም፡ ውበትም አያልቅም” ሲል ገጣሚው እንዲህ ከይኖታል፤
…ከብርሃን ዛሃ ከጨረሩ ፈትል
ከውኃ ነጠብጣብ ከጠይሙ ድውር
የተሠሩ ሴቶች በመለኮት ምስል
አገሩን ሞልተውት ልብ እንዲ’ነሆልል
ማነው ት’ዛዝ ፈርቶ ዓይኑን የሚከልል?
ተፈጥሮ ከሕጎች ለስሜት ያደላል
ግድ ነው የሰው ልጅ ለሥጋው ይቀርባል
የመጣው ይምጣ እንጂ
ማን ለሰማይ ብሎ-ምድርን ይጥላል፡፡
አመነዝራለሁ!
ከገነት! ከተምኔት! ሴቶችን አምናለሁ!
ከያኒ ለኪነትም ለህይወትም ሥሱ መሆን አለበት፡፡ ፈረንጆች “Aesthetic sensibility” ብለው ይጠሩታል፡፡ ከያኒው ይህን ስሱነት የሚያረጋግጠው አንድም ሕይወትን ሳይፈርጅ በመኖር ነው፡፡ አስቀድሞ ፍረጃ ግን የሕይወትን ጣዕም ያጎመዝዛል፡፡ የተባለውን ከመድገም ባለፈ ኪናዊ ውበትን ፈልቅቆ ማሳየት ትንሽ የሚያዳግት ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ከያኒው ለሕይወት ስሱ መሆን አለበት ሲባል ሕይወትን እስከነ ጉድፎቿ ውብ አድርጎ መከየን ማለት ነው፡፡
ትልቁ ከያኒ ሰሎሞን ዴሬሳ በ’ዘበት እልፊቱ ወለሎታት’ የግጥም ስብስብ መጽሃፉ መግቢያ ላይ፣ “ግጥምን የሚያረክሰው ያንዳንድ መስመሮች መበላሸት ሳይሆን፣ የሃሳብ ወይም የስሜት ሃቅ ማጣት…” ነው ይላል፡፡ ከያኒው ለሃሳቡም ሆነ ለስሜቱ መታመን የኹነኛ ኪናዊ ስራዎች ምንጭ መሆኑን ለማጽናት ይመስለኛል፤ ሰሎሞን ይህን ማለቱ፡፡ ዲበኩሉም በግጥሞቹ ወደ ቅድስናውም ‘እርኩሰቱ’ም መንደር ዘልቆ ገብቶ የህይወትን አምሳለ-ብዙ ገጾችን የውበት መጎናፀፊያ አልብሶ ያሳየናል፡፡ ይህን ለማድረግ ትልቅ አቅምና ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ገጣሚው ግን የማይደፈሩ የሚመስሉ ቅጽሮችን ዘልቆ በመግባት የተገፉ የስሜት ሃቆችን ወደ ማዕከል ያመጣቸዋል፡፡
ደግሞስ የስንዴን ዘለላ ያለ እንክርዳድ እንዴት ማሰብ ይቻላል? አንድ ገበሬ ስንዴን ዘርቶ፣ የተትረፈረፈ ስንዴን ለማጨድ አስቀድሞ እንክርዳዱን ማጥፋት ከቶም አይቻለው፡፡ የስንዴ ዘለላና እንክርዳድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸውና፡፡ ህይወትም እንደዚያ ነች፡፡ ፍሬና አረም በህይወት ገጽ ላይ አብረው ይበቅላሉ፡፡ በሂደት ውስጥ ፍሬውን ከገለባው እየለዩ መኖር ነው የህይወት ውሉ፡፡ ገጣሚው “ከሕልሞችህ ጋራ” በተሰኘው ግጥሙ ይህንኑ ያሳየናል፡፡
ከመታቀብ ልክነት
የመሞከር ስሕተት
ካልፈተሹት ምግባር
የመድፈሩ ውግዘት
ከዓለም አስር ሺህ ሕግ
የልብ አርነት፣
ከጽድቅ ያምራልና
ከተዋበ ድርሰት፤
ባይሰምርም አትዘን
ብትወድቅ አትፀፀት፡፡
ገጣሚው መሳሳትም (“ሳ” ጠብቆ ይነበብ) የሕይወት አካል ነው ይለናል፡፡ አዎን መሳሳትም የሕይወታችን ሌላኛው ገጽ ነው፡፡ ገና ስንወለድ አንስቶ በመሳሳት ጭምር ነው እየተማርን የጎለመስነው፡፡ ኪነጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎችም ከእነዚህ ዥንጉርጉር የህይወት ሰበዞች እየተመዘዙ ሲከየኑ፣ ክየናው ህይወት ይኖሯል፡፡ የጥበብ ስራዎችም ሰዋዊ ቃና ስለሚኖራቸው ለልብ ይቀርባሉ፡፡
ሌላው ኪናዊ የፈጠራ ሥራዎች የአንድን ነገር ዕውነታን ወይም ስሁትነትን ለማረጋገጥና ለማጽናት አይደለም የሚከየኑት፡፡ ከዚያ ይልቅ ሕይወትን በአዲስ መንገድ እንድንረዳትና ዓለምን ከሌላ አውታር እንድንመለከታት ማስቻል ነው፡፡ ገጣሚው በዚህ የግጥም ስብስቡ ከደስታና ስቃያችን፣ ከሳቅና እንባችን ብዕሩን እየነከረ በሕይወት ሸራ ላይ ኑረታችንን ይስላል፡፡ ፈጣሪውን ሲሞግተው ቆይቶ፣ ተመልሶ “ትንሽ ዕድሜ” እንዲሰጠው ይማጸኗል፡፡
ስለኪነት ፍቅር ስለጥበብ ቃና
ስለ’ሱም ለማውጋት ከማላዮች ጋራ
ትንሽ ዓመት ጨምር አባት ሆይ አደራ፤
ስለአርምሞም ሲባል ስለጥልቅ ጥሞና
ስለ’ራስን ማኩረፍ ተጣልቶ በፀና
ትንሽ ፍቀድ ወሽመጥ ትንሽ እንደገና
ከራስ መከፋፈል ጊዜ ይሻልና…
ከአዘቦታዊ የሕይወት መብከንከን ታቅቦ፣ ስለ ኪነት ማውጋት እንዴት ያስደስታል? ነገር ግን ዘመኑ ቅጽበታዊነት ላይ በመመስረቱ የፅሞናን ጊዜ ነጥቆናል፡፡ በውበት ለመማለል፣ በጽሞና ለመቆዘም ገጣሚው እንዳለው ጊዜ ይሻል፡፡ “ጊዜ ገንዘብ ነው” ከሚለው የዘመኑ መንፈስ መገለልን ይጠይቃል፡፡ ከትርምሱ መራቅ፣ ከውጥንቅጡ መገለልን ይሻል፡፡ ታላቁ ባለቅኔ ደበበ ሰይፉ፤ “ለአንዲት ቅጽበት ብቻ” ሲል ጊዜን የሚማፀናት ይህ ስሜት ተሰምቶት ይሆናል፡፡
ከጊዜ መሐል ገጽ ከዕድሜ ሰሌዳው
ተጽፏል አንድ ቃል ገላጭ የሚያነበው፤
ይላል፡-
ሰው በሰርክ ተምጦ ከጣር ይወለዳል
ጊዜ አዘቦት አያውቅ ኹለ’ዜ ይጓዛል፤
በዚህ ኹሉ መሐል-ሁሉም ሲያይ ይጠፋል፤
ቢሉም፤
ተስፋ የጋራ ውርስ-ትውልድ ያዳርሳል፤
ትዝታም ኹለንታን ጣጥሶት ላይሻር-በኹሉ ይነግሳል፡፡
“ከጊዜ መሐል ገጽ- የተነበበ አንቀጽ” ከተሰኘው ግጥሙ የመዘዝኳቸው አንቀጾች ናቸው፡፡ ይህ ግጥም ብዙ ያስቆዝማል፡፡ ስለ ጊዜ እንድናስብ ይተነኩሰናል፡፡ ጊዜ ግን ምንድነው? ከምዕራቡ ዓለም ተነስቶ ኩለንተናዊ ለመሆን እንደተቃረበው ግብ-ተኮር (linear) ወይም ጊዜ ከትናንት ተነስቶ፣ በዛሬ አድርጎ፣ ወደ ነገ የሚተምም ነው? ወይስ እንደ አፍሪካዊ ነባር ባህል ጊዜ ተፈራራቂ (circular) ነው፤ ክረምትን በበጋ፣ ምሽትን በቀን፣ ልጅነትን በእርጅና፣ ህይወትን በሞት እያፈራረቀ የሚተካ፡፡ ታዲያ በዚህ አፍሪካዊ የጊዜ እሳቤ መሰረት ሕይወት ውስጥ ቋሚ የሆነ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር የሚለዋወጥና እያየነው የሚያልፍ ወይም የሚጠፋ ነው፡፡ በሀገራችን ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ይህ የጊዜ እሳቤ ገናን ሥፍራ እንዳለው ይታወቃል፡፡
በዲበኩሉ ‘ሰው እስካለ ድረስ’ የግጥም ስብስብም ውስጥ ጊዜን የሚያጠይቁና የሚሞግቱ ግጥሞች አሉ፡፡ በእነዚህ ግጥሞች ገጣሚው የጊዜ ተለዋዋጭነትና አይጨበጤነት ላይ አብዝቶ ይቆዝማል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ጊዜን በተመለከተ የተለያዩ አተያዮችን በግጥሞቹ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ ጊዜን ማዕከል አድርጎ የጻፋቸው እነዚህ ግጥሞች በአንድ ጎናቸው የጊዜን ከንቱነት ሲያትቱ፣ በሌላ ገጻቸው ደግሞ ከጊዜ ተስፋን ይማፀናሉ፡፡
በ’ሰው እስካለ ድረስ’ የግጥም ስብስብ ውስጥ የተካተቱት አንዳንድ ግጥሞች ተንኳሽ ናቸው፡፡ የረጋ የሚመስለውን ስሜት በማማሰል የሚያናውጡ፡፡ የተናወጠ የሚመስለውን የስሜት ወጀብን መልሰው ፀጥ የሚያስብሉ፡፡ በተለይ የመጨረሻ ዕውነት አድርገን የተቀበልናቸው ገናን ተረኮችን ስለሚያጠይቁ፣ በልማድ የተቀበልናቸው ነገሮችን መለስ ብለን በጽሞና እንድናጤንና እንድንቆዝም የማድረግ አቅም አላቸው፡፡

Read 958 times