Wednesday, 02 April 2025 21:12

ክፉ አመል

Written by  ደራሲ፡- አንቷን ቼኾቭ ተርጓሚ፡- ሳሙኤል እንግዳ
Rate this item
(2 votes)

“የአስር አለቃ ዉምፖቭ መስከረም ሶስት ቀን የመንደሩን የፖሊስ መኮንን፤ የደብሩን ክቡር አዛውንትና የሚሊሽያ አባሉን ተሳድበሀል፣ ባልተገባ ድርጊት አዋርደሃል፤ ይህን ለመፈጸምህም ስድስት ገበሬዎች መስክረውብሀል፡፡ የቀረበብህን ክስ ትቀበላለህ?”
አስር አለቃ ዉምፖቭም ጨምዳዳ ፊቱን ይበልጥ ከስክሶ ምላሽ ለመስጠት ከመቀመጫው ተነሳና፤ በታፈነ ጎርናና ድምጽ መልስ ከመስጠት ይልቅ፣ ለትእዛዝ በሚቀርብ ቃና መናገር ጀመረ፡፡
“ክቡር ዳኛ፤ በርካታ የምርመራ ታሪኮች እንደሚያሳዩት፣ አንዳንዴ ክስ የተገላቢጦሽ ሆኖ ከሳሽ ራሱ ወንጀለኛ ሆኖ የሚገኝባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በኔ ጉዳይም ጥፋተኛው እኔ ሳልሆን ከሳሾቼ ናቸው፡፡ በመካከላችን ለተፈጠረው አተካራ መነሾው ነፍሱን ይማረውና አንድ አስከሬን ነው፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት ከሚስቴ ጋር በሰላም ወደ አንድ ቦታ በመሄድ ላይ ሳለን ወንዙ ድልድይ አካባቢ የጎረምሳ መንጋ፣ ትልቅ ክብ ሰርቶ ተሰብስቦ ተመለከትኩ፡፡ እንዲህ የመሰብሰብ መብት የሰጣቸው ማን ነው? ስል ራሴን ጠየቅኩ፡፡ ይህ መሆን የለበትም፤ እንስሶች እንጂ ሰዎች መንጋ ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ ህግ ፈጽሞ የለም አልኩና ቀረብ ብዬ፣ “ተበተኑ” እያልኩ ለመበተን ገፋ ገፋ እያደረግሁ፣ በስፍራው የነበረውን የሚሊሽያ አባል እንዲበትናቸው ትእዛዝ አስተላለፍኩ…”
“ይቅርታ! አንተ የአካባቢው አስተዳዳሪ ወይም የፖሊስ አባል አይደለህም፡፡ ሰዎችን የመበተን ስራ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረገህ ?”
“አያገባውም! አይመለከተውም!” ከየጥጋጥጉ በማጉረምረም የታጀቡ ህብረ ድምጾች አስተጋቡ፡፡
“ክቡር ዳኛ፤ ከዚህ ሰው ጋር መኖር አንገሽግሾናል፡፡ አስራ አምስት አመታት ሙሉ እየተሳቀቅን እንደ ጦር ስንፈራው ኖረናል፡፡ ከጦር ሜዳ ከተመለሰበት ወቅት አንስቶ መንደራችንን ለቀን መሰደድ እስክንመኝ ድረስ እያንዳንዳችንን አሰቃይቶናል፡፡”
“እውነት ነው ክቡር ዳኛ!” ሲል የመንደሩ ሊቀ መንበር አረጋገጠ፡፡ አያይዞም፤ “ሁላችንም ቅሬታ አለን ጌታዬ፡፡ ከዚህ ሰው ጋር አብሮ መኖር በጣም አስቸጋሪ ሆኖብናል፡፡ ጸበል ጸዲቅም ይሁን ሰርግ ወይም ማንኛውም አይነት ድግስ ሲዘጋጅ እየተገኘ ስርአት ያዙ እያለ እንደ ብራቅ መጮህ፣ ታዳሚውን ማስደንገጥና መርሀ ግብሩን ማደፍረስ የተለመደ ተግባሩ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ምንም ባልተፈጠረበት የህጻናትን ጆሮ እየቆነጠጠ ያስለቅሳል፤ የሆነ የስርቆሽ ተግባር እየተፈጸመ ያለ ይመስል ልክ እንደ ተጠራጣሪ አማች እንስቶች ላይ እያፈጠጠ ምቾት ይነሳል…. በዚሁ ሳምንት ከትናንት በስቲያ ማታ እንኳን በየቤቱ እየዞረ ዘፈን መዝፈንና ሻማ መለኮስ የለባችሁም እያለ ሲከለክል፣ ይህን እንድታደርጉ ህግ አይፈቅድም በማለት ሲጮህ እንደነበር ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡”
“ቆይ-ቆይ በኋላ እድል እሰጥህና በደንብ ታብራራለህ” ዳኛው አቋረጡትና አስር አለቃውን እየተመለከቱ፤ “አሁን ዉምፖቭን እያዳመጥን ነው፡፡ ቀጥል- ቀጥል” በማለት ንግግሩን እንዲቀጥል ምልክት ሰጡት፡፡
“እሺ ጌታዬ! እሺ!” አስር አለቃው አምቧረቀ፡፡ ቀጠለናም፤ “ክቡርነትዎ፤ ቀደም ብለው የተሰበሰቡ ሰዎችን መበተን ውስጥ ምን ጥልቅ አደረገህ ማለትዎ ትንሽ አስገርሞኛል፡፡… እሺ ይሁን ግን ህግ ሲጣስስ ጌታዬ? ሰዎች በማናለብኝነት እንዳሻቸው እንዲረብሹ ይፈቀዳል ማለት ነው? ይህን መብት የሚደነግግ የህግ አንቀጽ የት ነው የተጻፈው? ይቅርታ ጌታዬ፤ እኔ በበኩሌ አይኔ እያየ ይህ እንዲሆን አልፈቅድም፡፡ እኔ ካልበተንኳቸውና ካልቀጣሁዋቸው ሌላ ማን ሊያደርገው ይችላል? በዚህ መንደር ውስጥ ከእኔ ሌላ እውነተኛውን ስርአት የሚያውቅ አንድም ሰው የለም፡፡ እዚህ ላይ ምናልባት አንዳንዶች እርስዎን ሊጠቅሱ ይችሉ ይሆናል ግን ክቡርነትዎ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች ባህሪ የኔን ያህል እንደማይረዱት እርግጠኛ ነኝ፤ እንዴት ልክ እንደሚገቡ ከኔ በቀር ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድም ሰው አይገኝም፡፡ በዛ ላይ እኔ እንደሌላው ገበሬ ሳልሆን ዋርሳውን በመሰለ ትልቅ የጦር ማዘዣ ተመድቤ ግዳጄን በአግባቡ በመወጣቴ ሙሉ የአስር አለቅነት ማእረግ ከክብር ጋር የተበረከተልኝ ምስጉን የጦር አዛዥ ነኝ፡፡ ጌታዬ፤ ከጦርነቱ በኋላ ስለነበረኝ የሲቪል ህይወት ማወቅ ከፈለጉም የጤናዬ ሁኔታ እንዳቆም እስካስገደደኝ ጊዜ ድረስ በእሳት አደጋ መከላከያ መስሪያ ቤት ተቀጥሬ አገልግያለሁ፡፡ በመቀጠልም በወጣቶች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በወዛደርነት ሰርቻለሁ፡፡ ስለዚህ ክቡር ጌታዬ፤ ስርአትን ከእኔ ውጭ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው የለም ስል ከልቤ መሆኑን አምነው ሊቀበሉኝ ይገባል፡፡
“በአንጻሩ እዚህ መንደር የሚኖረው ህዝብ ከግብርና ውጪ አንዳች የማያውቅ መሃይም ገበሬ ማህበረሰብ ነው፡፡ ስለዚህ እኔን መስማትና ትእዛዜን ማክበር ያለበት ለራሱ ጥቅም መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡ ለአብነት አሁን ግርግር የተፈጠረበትን ጉዳይ ብንመለከት ሰዎቹን እንዲበተኑ ያደረግኩት በወንዙ ዳርቻ አሸዋ ደለል ላይ እተንሳፈፈ ያለ የሰው አስከሬን በማየቴ ነው፡፡ መቼስ ሟች ለእረፍት ጋደም አለማለቱ ይታወቃል፡፡ ቦታው ላይ ግን ስርአት አልነበረም፡፡ እንደደረስኩ ጉዳዩ የሚመለከተው ፖሊስ መኮንን መኖሩን አየሁ፤ ነገር ግን የበላይ አስተዳደር አካላት እውቅና እንዳልነበራቸው አረጋገጥኩ፡፡ ሟች ከክረምቱ ብርድ ስቃይ ለመገላገል ራሱን አጥፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም በወንጀለኞች ተገድሎ ተጥሎም ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የፖሊስ መኮንኑ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ዘና ብሎ ሲጋራውን ይምግ ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶም፤ “አረ ለመሆኑ ፖሊሱ አንተነህ እኔ? ደርሰህ ስርአት ካላስያዝኩ ብለህ ያዙኝ ልቀቁኝ የምትለው አንተ ማነህ ? እስከዛሬ በሰላም የኖርነው አንተ ተቆጣጥረሀን ነው እንዴ?” በማለት የሚያደርገውን የማያውቅ ጅል አድርጎ በተሰበሰበው ህዝብ ፊት በአሽሙር ወረፈኝ፡፡ እኔም “አንተ በቸልተኝነት ሀላፊነትህን ካልተወጣህ ዝም ብዬ አልመለከትም” ስል መለስኩለት፡፡ እሱም “በበኩሌ ትናንት ለፖሊስ አዛዡ ሪፖርት አድርጊያለሁ” አለኝ፡፡ እኔም” ለፖሊስ አዛዡ ብቻ ለምን? እንዲህ አይነቱ ከመስመጥና ራስን ከማጥፋት ጋር የሚገናኝ የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ለፖሊስ አዛዡ ማሳወቅ ምን ያደርጋል ? ይልቁንም ማወቅ ያለባቸው ክቡራን ዳኛውና አቃቤ ህጉ ናቸው፡፡ በል አሁን ቶሎ ፍጠንና ጉዳዩን የሚገልጽ አጭር ሪፖርት አዘጋጅተህ ለክቡር ዳኛው ላክላቸው፡፡” አልኩት፡፡ እሱ ግን ያልኩትን ሁሉ በጥሞና ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ፣ ልክ አስቂኝ ቀልድ የሰማ ይመስል ሳቁን ለቀቀው፡፡ በሰአቱ አብረውት የነበሩና ዛሬም እዚህ የሚገኙት ገበሬዎችም እሱን ተከትለው አሽካኩብኝ፡፡ ክቡር ዳኛ፤ ይህ ቃሌ እውነት መሆኑን በመሃላ አረጋግጣለሁ፡፡ እኔም “ምን ያስገለፍጣችኋል?” ስላቸው ይግረምህ ብለው “ፍርድ ሸንጎ ይህን አይነቱን ጉዳይ አይመረምርም!” አሉኝ፡፡ ይሄኔ ንዴቴ ከቁጥጥሬ በላይ ሆነብኝ፡፡ “አላልከኝም ኮንስታብል? ዋሽቻለሁ? “ አስር አለቃው ኮንስታብል ዢጊን ላይ ዞሮ አፈጠጠበት፡፡
ፖሊሱም ፍጹም ተረጋግቶ፤ “ብያለሁ” ሲል አረጋገጠ፡፡
“ያለውን በወቅቱ የተሰበሰበው ህዝብ ሁሉ ሰምቶታል፡፡ “የመንደሩ ሸንጎ ይህ ጉዳይ አይመለከተውም” ሲል ሁሉም ሰምቷል፡፡ ክቡር ዳኛ፤ ጆሮዎቼን ተጠራጠርኩ፤ ላብ አጠመቀኝ ፤ እንደ መፍራትም አደረገኝና፣ እስቲ ያልከውን ድገመው አልኩት፡፡ ሳይጨምር ሳይቀንስ ደገመልኝ፡፡ እኔም “እንዴት እንዲህ አይነት የድፍረት ቃል በተከበረው ፍርድ ሸንጎ ላይ ትናገራለህ? አንተ ራስህ ህግ አስከባሪ ተብለህ ሀላፊነት የሰጡህን አካላት የሚቃረን ንግግር ከአንደበትህ እንዴት ይወጣል? ለመሆኑ ለእንዲህ አይነቱ የክህደት ንግግርህ ሸንጎው ከነአካቴው ከፖሊስነትህ ሊያባርርህ እንደሚችል ታውቃለህ? በፖለቲካዊ ተቃውሞ ሊወነጅልህ እንደሚችልስ አስበሀል?” ብለው፣ በሱ ፋንታ የደብሩ አዛውንት፤ “የፍርድ ሸንጎው ከተሰጠው በትናንሽ ጉዳዮች ፍርድ የመስጠት ስልጣን አልፎ ትላልቅ ወንጀሎች መመልከት አይችልም” የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡ ይህን ሁሉም ሰው ሰምቷል፡፡ እኔም “ ምን ቢደፍሩ ነው ሸንጎውን ለማዋረድ የሞከሩት? ከኔ ጋር ሌላ ነገር ውስጥ አይግቡ፡፡ ይህ ድርጊት የተፈጸመው ወታደ ርቤት ወይም እሰራበት የነበረው ትምህርት ቤት ውስጥ እያለሁ ቢሆን ኖሮ ፖሊስ ጠርቼ ምስክር እቆጥርና፣ አስቀፍድጄ የድፍረትዎን ዋጋ እንዲያገኙ አደርግ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል እዚህ ፖሊስ የሌለበት ገጠር ውስጥ መገናኘታችን ጠቀመዎት” አልኩና መረን የለቀቀ ጋጠወጥነታቸው አበሳጭቶኝ፣ በአካባቢው ከበቀለ ዛፍ ቀለል ያለ ልምጭ ዘንጥፌ እንዲህ ያለ የድፍረት ቃል በተከበረው ሸንጎ ላይ ሁለተኛ እንዳይናገሩ ትምህርት የሚሰጥ ግርፊያ አሳረፍኩባቸው፡፡ ይሄኔ የፖሊስ መኮንኑ ሊከላከል ተነሳ፤ እሱንም ደገምኩት፡፡ ንዴቴ እየጦፈ መጣና በዛው ሌሎቹም ላይ ግርፊያው ቀጠለ፡፡ ጌታዬ፤ ከመግረፍ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ደግሞስ “ባለጌን ካሳደገ የቀጣ ይጸድቃል” ይባል የለ፡፡ በተለይ ጋጠወጦችን ማስተካከያው ፍቱን መድሀኒት ይህ ነው፡፡”
“ግን’ኮ ሰላም ለማስከበር መንግስት የመደባቸው አካላት አሉ፡፡ የዋና አስተዳዳሪው፤ የፖሊስ መኮንኑና የሚሊሽያ ጓዱ ዋና ስራቸው ይሄው ነው፡፡”
“ የፖሊስ መኮንኑ ሁሉንም ሊያዳርስ አይችልም!! ከእኔ በላይም ግንዛቤ የለውም!!”
“ ግን በትንሹም ቢሆን በማይመለከትህ ጉዳይ ጣልቃ የገባህ አልመሰለህም?”
“ እንዴት ሆኖ ጌታዬ? ይህ እኔን ካልተመለከተ ታዲያ ማንን ሊመለከት ነው? ሰዎች ስርአት አልበኛ ሲሆኑ ማሞካሸት ነው የነበረብኝ? ለእርስዎ ዘፈን መዝፈን ከለከለን ብለው ከሰሱኝ፡፡ ለመሆኑ ዘፈን ምን ይጠቅማቸዋል? አንዳች ጠቃሚ ስራ ከመስራት ይልቅ በዘፈንና በምሽት ሻማዎችን አብርተው መጎለትን እንደ ስልጣኔ ይዘውታል፡፡ ሰው ወደ አልጋው መሄድ በሚገባው ውድቅት ሌሊት ሲጮሁና ከጣሪያ በላይ ሲያሽካኩ ያነጋሉ፡፡ ይህን ሁሉ በማስታወሻዬ ጽፌ አስፍሬዋለው ጌታዬ!!”
“ ምኑን ነው የጻፍከው?”
“ በምሽት ሻማ አብርተው የሚረብሹትን ስም ዝርዝር!!”
ወዲያው ዉምፖቭ ከኪሱ አንድ የተጣጠፈና በቅባት የራሰ ወረቀት መዥርጦ በማውጣት የማንበቢያ መነጽሩን አይኑ ላይ ሰክቶ ስሞችን በዝርዝር መጥቀስ ጀመረ፡፡
“በምሽት ሻማ አብርተው የሚቀመጡ ነዋሪዎች፤- የሙት ወታደር ባልዋን ቃልኪዳን አፍርሳ ከሲሚዮን ኪስሎቭ ጋር የምትማግጠው ነውረኛዋ ሽሩስትሮቫ፤ መተተኛው ኢቫን ስቬርቾክ እና ጨለማን ተገን አድርጋ ወደ ከብቶች ጋጣ በመግባት የሰው ላሞችን አልባ ወተት የምትሰርቀው ጠንቋይዋ ሚስቱ ማቭራ.”
“ በቃህ!!!” ዳኛው አስቆሙትና የምስክሮችን ቃል መስማት ጀመሩ፡፡
የአስር አለቃ ዉምፖቭም የንባብ መነጽሩን ወደ ግንባሩ ከፍ አድርጎ ንግግሩ እንዳልተመቻቸው በግልጽ የሚነበብባቸውን ዳኛ በአግራሞት መመልከት ቀጠለ፡፡ አይኖቹ ተጎልጉለው ፈጥጠዋል፤ አፍንጫው ደም የተለወሰ መስሎ ጫፉ ቀልቷል፡፡ ሹክሹክታና የታፈነ ሳቅ ከየጥጋጥጉ ለምን እንደሚሰማ ግልጽ አልሆንልህ ብሎት ግራ ተጋብቷል፡፡ ከዚህም በላይ እንቆቅልሽ የሆነበት ደግሞ የተላለፈበት የአንድ ወር እስራት ፍርድ ነው፡፡
“ምን አጥፍቼ!!?” እጆቹን ሽቅብ ዘርግቶ የሰማውን ባለማመን ጮሆ፤ “እኮ በየትኛው ህግ ነው የምቀጣው?”
ወዲያውኑም አለም መለወጧና በውስጧ መኖርም እጅግ ፈታኝ መሆኑ ተገለጠለት፡፡ ጨለማና ቀፋፊ ሀሳቦች አይምሮውን ሞሉት፡፡ ቢሆንም ግን በክፍሉ ውስጥ የተሰበሰቡት ገበሬዎች ክብ ሰርተው መንጫጫታቸውና ማውካካታቸው፣ አምርሮ የሚጠላውን የመንጋ ስብስብ የማይታገስ ሴጣኑን ዳግም ቀስቅሶበት እንደ ብራቅ በሚያስተጋባ ድምጽ፤
“ ተ-በ-ተ-ኑ ! የምን መሰብሰብ ነው ! ወደ ቤታችሁ ሂዱ!” ሲል አምባረቀ፡፡

Read 912 times