Wednesday, 02 April 2025 20:38

የአፍላ እድሜ ተግዳሮቶች

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
Rate this item
(2 votes)

“እኩል ምላሽ አትስጪኝ/ጠኝ! ፣ ታደገልኝ! ፣ አሁንማ ተደረሰ! ኡፍ….ኡፍ.. “ የሚለው ታዳጊ ልጆች ያላቸው ወላጆች፣ ከልጆቻቸው ጋር ያለውን አለመግባባት ከሚገልጹበት ንግግር መካከል ይገኝበታል፡፡

እድገትን መገንዘብ
ታዳጊዎችን የምናይበት አመለካከት (Attitude) ከእነርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ይወስናል፡፡ እድገታቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የልጆች አእምሮ እንደ ደህንነት ካሜራ ( Surveillance Camera ) የተሰጠውን መረጃ ይመዘግባል፤ ይሰበስባል፡፡
የተመዘገበው መረጃ በሚፈለገው ጊዜ ጥቅም ላይ እንደሚውል ሁሉ እድሜያቸው 13 ሲሆን በውስጠኛው የአእምሮ ክፍል (Subconscious mind) የነበረውን መረጃ በመገጣጠም የራሳቸውን ትንታኔ መስጠት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ወቅት ታዳጊዎች መወያየት፣ መከራከርና ሃሳባቸውን መሰንዘርና ማሰላሰል ይጀምራሉ፡፡ ይህ ጤናማ የእድገት ምልክት ነው፡፡
ለወላጅ ደግሞ ይህ የታዳጊዎች ባህሪ የወላጅነት ክብርን የሚፈታተን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
የተቃርኖ ህይወት
አብዛኛውን ጊዜ ታዳጊዎች የቅርብ ሰዎቻቸውንና የሚወዷቸውን ሲያበሳጩ ይስተዋላል፡፡
ታዳጊዎቹ ይህንን የሚያደርጉት ከጥላቻ በመነጨ ሳይሆን ከእድሜ እድገታቸው ተከትሎ በሚከሰት የስሜት መዋዠቅ (Mood swings) ነው፡፡ በዚህ ወቅት ታዳጊዎች የተዘበራረቀና ግራ የሚያጋባ ስሜት ያስተናግዳሉ፡፡
ለምሳሌ ቁጣ፣ ብስጭት፣ መናደድ…ይህንን ስሜት እንዴት መግለፅ እንዳለባቸው አለማወቃቸው ከቤተሰብ ጋር የአለመግባባት ምክንያት ይሆናል፡፡

የታዳጊ ወጣቶች መሰረታዊ ፍላጎቶች
ታዳጊዎች ከሚያስፈልጋቸው መሰረታዊ ፍላጎቶች በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል ፍቅር፣ ተቀባይነት እና አብሮነት ናቸው፡፡ የእነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች እጦት፣ በልጆቹ እድገት ላይ ከፍተኛ ተፅኖ ያመጣል፡፡
በተለይም እንዳልተወደደ፣ ተቀባይነት እንደሌለው የተረዳ ታዳጊ፤ መሰረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት አላስፈላጊ የህይወት ትግል ውስጥ ይገባል፡፡ ታዳጊዎች ራሳቸውን ሆነው እንዳያድጉ ፣ እያስመሰሉ ሰውን ለማስደሰት እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡
የአፍላ እድሜ ተግዳሮቶች
ታዳጊዎች ካሉባቸው ተግዳሮቶች መካከል አቻ ግፊትና ስሜታዊነት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ታዳጊዎች ከአዋቂዎች በተለየ መልኩ ያስባሉ፡፡ አዋቂዎች አመክንዮን ( Reasoning) ሲጠቀሙ ታዳጊዎች ደግሞ ስሜታዊነት የነገሰበት ነው፡፡ ታዳጊነት የሽግግር የህይወት ምዕራፍ ሲሆን፤ ታዳጊዎች ህጻንም አይደሉም አዋቂም አይደሉም፡፡ ማንነታቸውን ፍለጋ ላይ የተጠመዱ በመሆናቸው በርህራሄና በፍቅር ልንረዳቸው ይገባል፡፡

ከታዳጊዎች ጋር ያለንን ተግባቦት ለማሳለጥ ምክረ-ሃሳብ
ታዳጊ ወጣቶችን በተከታታይ ለማረም ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ከእነርሱ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት ማድረግ ይመከራል፡፡ (Connection before correction)
በንግግር ወቅት ወደ ግጭት ከሚያስገባ ወቀሳ ነፃ የሆኑ ቃላትን መጠቀም፡፡
ታዳጊዎችን ለማዳመጥ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ስናዳምጣቸው መልስ ለመስጠት ሳይሆን ምን ማለት እንደፈለጉ ለመረዳት መሆን አለበት፡፡ የሚያዳምጥ ወላጅ ከልጁ ጋር የስሜት ትስስር የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ወላጅ ለልጅ ችግር መፍትሄ ይሰጣል፡፡ ይሁንና ታዳጊ ወጣቶች የራሳቸውን ችግር ራሳቸው እንዲፈቱ ለማስቻል ወላጅ በንግግር ወቅት ብዙ ጠያቂ ከሆነ፣ አሳቢና ችግር ፈቺ ታዳጊን ለማፍራት ያስችላል፡፡
ወላጅ የራሱን ህይወት ተሞክሮ ማጋራት፡፡
የታዳጊ ወጣቶችን መልካም ጎን ማድነቅ፤ ደካማቸውን ደግሞ ከጎናቸው ሆኖ መርዳት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ፀሐፊው ብርሃኑ በላቸው አሰፋ፣ “የክቡር ልጆች” ደራሲ ሲሆን፤ ከስድስት ሺ በላይ አባላት ያሉት በልጆችና ቤተሰብ ላይ የሚያተኩር የቴሌግራም ግሩፕ Child Development Network (@childdevtnetwork) መስራች ነው፡፡

Read 2625 times