አንድ ጠማማ ጎረቤት አለኝ፡፡ ሰው አይደለም! ግዑዝ ሕንፃ ነው፡፡ በግትርና በእንቅስቃሴ አልባ ሕይወቱ ስለ ዘመናችን ብዙ የሚናገር ይመስላል! (ይቅርታ ይመስለኛል) አንድያ ልጇን ሞት እንደቀማት እና ወደ መቃብር ጉድጓዱ አዘቅዝቆ እርምን የሚያወጣ አይነት ነው፡፡ ሰግደድ ብሎ እንባው ጉንጮቹን ሳይነካ ሲንጠባጠብ ይታየኛል፡፡ እራሱን ወደ ቀብሩ ጉድጓድ እንዳይጥል ከበስተኋላው አንቆ የያዘው ደባል ህንፃ አለው፡፡ ባያይዝ ድፍት፣ ክንብል እንደሚል የሚያሳምን ሁኔታ ይረብብናል፡፡ ብዙ ምስሎች ወደ አእምሯችን እንዲመጡ ግድ ይለናል፡፡ ኢየሱስና እናቱ ማርያ ከወንጌል፣ በዛብህ፣ እናቱና አባቱ ከፍቅር እስከ መቃብር፣ የቀይ ሽብር ዘመን እናቶች ከቅርብ ታሪክ፣ አፄ ቴዎድሮስና ሟች ሚስታቸው ከሩቅ ታሪክ…
በካዛንችስ በፊት በር ድንበር ላይ ያለው ይሄ ጠማማ ጎረቤቴ፤ የብዙዎች ግርምት መጫሪያ ነው፡፡ እንደውም አንዳንዱን የፎቁ የውጭ ይዘት የውስጥ ሁናቴው ላይ ጥርጣሬ እንዲጭር ስለሚያደርገው፣ ያለ ሥራ ወደ ሕንፃው እንደሚዘልቅ አውቃለሁ፡፡ እውነት ነው፤ ፎቁ ፊት ለፊት ወይ ከጎን በኩል ያለ ሰው፤ ውስጣዊ ክፍሉ ማዕበል እንደሚያናውጣት መርከብ ያጋደለ ተንሸራታች ወለል ያለው ቢመስለው እውነት አለው፡፡ ጠረጴዛው፣ ፀሐፊዋ፣ ኮምፒዩተሩ፣ ቆሻሻ ቅርጫቱ፣ የፋይል ካቢኔቱ አንዱ ባንዱ ላይ ተነባብሮ ዘቅዛቃው ላይ የተጠራቀሙ የሚመስል ግንዛቤ ይረታናል፡፡ እኔ ራሴ ገብቼ እንዳረጋገጥኩት እንደዚያ አይደለም - ሊሆን አይችልም፡፡ እዚሁ ጠማማ ጎረቤቴ ሦስተኛ ፎቅ ላይ የባህል ቡና አፍልታ የምታቀርብ ቤት አጋጥማኝ ሊሆን የሚችለውን እያሰብኩ ስቄአለሁ፡፡ የጠማማ ጎረቤቴ ውጭያዊ አኳኃን ውስጣዊ ጠባዩን አይወከልም፡፡ ውስጡ ሆነን ሐዘንተኛነቱን አናውቅም፡፡
ኪነ-ህንጻ (Architecture) እንደ ሌሎቹ ጥበቦች ማለት ሥነ-ጽሁፍ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ-ስዕልና ቅርፃ ቅርጽ ሁሉ ሐሳብና ፍልስፍናዊ አቋሚ የሚገልጽበት እንጂ የግብር ይውጣ መዳረሻ አይደለም፡፡ አንድ ህንጻ ወረቀት ላይ ከሰፈረ ግጥም፣ መድረክ ላይ ከቀረበ ቴአትር፣ አቡጀዲ ላይ ከገዘፈ ሥዕል፣ ቋጥኝን ካንበረከከ ሀውልት ያልተናነሰ ማንነትና ዘመንን ይዘግባል፡፡ ህንፃ የመጠለያ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በሂደት ላይ ያለ ሥነ- ቃል፣ ታሪክና እምነት ነው፡፡ እንደዚህ ዘመን ባልተናቀበትና ከካርቶን በማይታነጽበት በጥንቱ ዘመን የነበሩ ግንባታዎች፣ ከየትኞቹም ታሪክን ማስተላለፊያ ስልቶች በተሻለ ቋሚ ሆነው፣ እላያቸው ላይ የሰፈሩትን ሀሳቦች ለዚህ ዘመን አድርሰዋል፡፡
ህንፃ እንደ ሌሎቹ ጥበቦች ሁሉ የሚበላለት ስልት ያለው ኪን እንደሆነ ያወቅሁት አሁን በቅርቡ ነው፡፡ “Four stages of Renaissance Style” የተሰኘ መፅሐፍ እጄ ገብቶ ሳገላብጥ አንድ ህንፃ እንደ ግጥምና ሙዚቃ (Rhythm) ፣ እንደ ልቦለድ ቅርጽና ጭብጥ፣ እንደ ስዕል ህብርና ንጽጽር (contrast) የመሳሰሉ አላባዎች (Elements) እንዳሉት ገባኝ፡፡ ህንፃዎች በእነዚህ አላባዎች ስለ ዘመኑ የሰው ልጅ እሳቤና የኑሮ ፍልስፍና ተመዝግቦባቸው፣ የሚተነተን መረጃ ለትውልድ ያቀብላሉ፡፡ እንደ ሌሎቹ ኪኖች ሁሉ የሰው ልጅ በተለያየ ዘመን የተለያየ የኪነ ህንጻ አቋም ላይ እየደረሰ፣ የተለያየ የአገነባብ ስልት ተከትሏል፡፡ ባሩክ (Baroque)፣ ጎቲክ (Gothic)፣ ማነሪዝም፣ ረነሰንስ (renaissance)፣ ሮማንቲሲዝም፣ ዘመናዊነት (modernism) እና ድህረ ዘመናዊነት (Post- modernism) ከተለዋወጡት የኪነ ህንፃ ስልቶች (Style) ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በግሪክ ዘመን የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ተፈጥሮን በመቅዳት ለሰው ልጅ እንደ ግብ የተቀመጠው ሥነ-ምግባራዊ ታላቅነት ማሳየት ነበር፡፡ በግሪክ ውስጥ የሚካሄዱ ግንባታዎች ሁሉ በማያፈናፍን ስሌት ህብር እንዲኖራቸው ይደረግ ነበር፡፡ “Of Men and Numbers”የተሰኘ መፅሐፍ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ የሚል ውርስ ግንዛቤ የሚሰጥ ሀሳብ አለ፡፡ “የአቴናው ቤተ መቅደስ የፓርቴኖን ዙሪያ፣ ፓርቴኖን የተገነባበት የአክሮፖሊስ አካባቢ (ዳግም የተመሰረተው ከተማ) ቅፅሮቹና መደቦቹ ሁሉ በጂኦሜትሪ መሞገቻ ነጥቦች ግልጽ የሆነ አንድነት ይንፀባረቅባቸዋል” (It may be said that all parts of the Parthenon, the Arcropolis, the city as rebuilt, the walls, and the port, are expressible in terms of a geometrically unity.) ግሪኮች ፕሌቶ፤”God ever geometrizes” ያለውን ሲተረጉሙ እንደ ማለት ነው፡፡
ኪነ- ህንጻ ዘመንና የዘመኑን ሰዎች ተርጓሚ የግንባታ ቅኔ ከሆነ፣ የእኛ ህንጻዎች ስለኛ ምን ይሉ ይሆን? አረ ከተማውን ሁሉ ያጥለቀለቁት ኮሽኮሼ ፎቆች እኛን በምናቸው ወከሉን?...
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ጋር እንደተጨዋወትን ትዝ ይለኛል፡፡ እሱ ጥሩ የሚባል የኪነ-ህፃ ግንዛቤ አለው፡፡ “ጠማማው ጎረቤትህ በድህረ ዘመናዊነት ስልት የተገነባ ነው” ብሎኛል፡፡ የኪነ-ህንፃው አዳም ረታ የደረሰው “ፎቅአዊ “ መረቅ መሆኑ ነው፡፡
እዚህ ግንባታ ላይ የሚታየው እውነታን ገልጦ የሚተርጎም ፈጠራ፣ የድህረ ዘመናዊነት ስልትን መሰረት ያደረገ ነው ማለት ነው፡፡ ኢንጂነር ጌታሁን፣ ድህረ ዘመናዊነት ስልትን ተከትለው የተገነቡ ህንፃዎችን ከኢንተርኔት ላይ አውርዶ አሳየኝ፡፡ የመሬት ስበትን ተቋቁመው ወደ ሰማይ በመምጠቅ ላይ ያሉ መስለው ተገንብተዋል፡፡ እውነታውና ከተለምዶ በተቃራኒው መምጣት የድህረ ዘመናዊነት ጠባይ ነውና፣ ህንፃዎቹ በዚህና በተለያዩ መለኪያዎች በስልቱ ውስጥ የተካተቱ ሆነዋል፡፡
ሌሎቹ ኮሽኮሼዎችስ?
የዘመንና የዘመነኞችን ገመና በጥበብ ሳይሆን ግልብ መንገድ የሚገልፁ ናቸው፡፡ ሱሪን ከባት በታች ዝቅ የማድረግን ዘመን አመጣሽ ፋሽን፣ ኮሽኮሼዎቹ ህንፃዎች የሽንት ቤት ፍሳሽን በውጭ ግድግዳ ላይ በመለጠፍ ከዘመኑ ጋር ህብር ይፈጥራሉ፡፡
ገመናን አደባባይ አውሎ በመኩራራት አባዜ አንድ ናቸው፡፡ ዘመን አመጣሹ ገመና ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ አይን ያወጣ መስገብገባችንና ማጋበሳችን በእነዚሁ ኮሽኮሼ ህንፃዎች ቦታ አያያዝና አጠቃቀም ተተርጉሞ ይታያል፡፡ የፎቆቹ መወጣጫዎች እንደ ጀጎል የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሁለት ሰዎችን በአንድ ላይ የሚያስናተናግድ ከመሆኑም በላይ የአንዳንዶቹ ህንጻዎች ደረጃ በውጭ በኩል በብረት የተቀጣጠለ ነው፡፡ ዓይንና መንፈስን አጨናንቆ ጥቅምን ብቻ ማንሰራፋት፣ የዘመናችንም የኑሮ ፍልስፍና አይመስላችሁም?
(ከአዲስ አድማስ የ2008 ዓ.ም ዕትም በድጋሚ የወጣ)
Saturday, 29 March 2025 10:47
የኪነ-ህንፃው አዳም ረታ እና ፎቅአዊ “መረቅ”
Written by ዓለማየሁ ገላጋይ
Published in
ነፃ አስተያየት

