ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ አንጋፋ የፖስታ ቤት ባልደረባችን ሚስት አረፈችና ወደ ቀብር ቦታ አመራን፡፡ ግብአተ- መሬቱ እንደተጠናቀቀም በባህልና ወጋችን መሰረት፣ ሀዘንተኛው ጓደኛችንን ለማጽናናት ተሰባስበን ወደ ቤቱ አቀናን፡፡
ቤቱ ደርሰን ጥቂት አረፍ እንዳልንም፣ ለእዝን የተዘጋጁ ቀይ ክሬም የፈሰሰባቸው ጣፋጭ ብስኩቶች ቀረቡልንና ለመቅመስ ስንዘጋጅ፣ ወዳጃችን እንደ አዲስ ለቅሶና እዬዬውን አቀለጠው፡፡ “ወይኔ! የሚስቴ ውብ ጉንጮች’ኮ እነዚህ ብስኩቶች ላይ የፈሰሱትን ቀያይ ክሬሞች ነበር የሚመስሉት! ቁርጥ ጉንጮችዋን!” ሲል ተነፋረቀ፡፡
“እውነት ነው! ሚስትህ ልቅም ያለች ቆንጆ ነበረች” አልን - ሁላችንም በአንድ ድምጽ፡፡
“አዎ! በደንብ አስተውላችኋታል… በውበቷ የማይደነቅና አይቷት አይኑን ለመንቀል የማይቸገር ጎበዝ አልነበረም፡፡ እኔ ግን የማፈቅራት በመልኳና በደምግባቷ አልነበረም፡፡ እነዚህ አይነቶቹን መመዘኛዎች የምታሟላ እንስት ብትፈለግ አትጠፋም ፤ ይልቁንም ሚስቴን ነፍሷን ይማረውና ልቤ እስኪጠፋና ከማንም ጋር ላወዳድራት እስኪሳነኝ ድረስ እንድወዳት ያደረገኝ፣ ቀልድና ቁምነገርን አዋህዶ ከያዘ ቀለል ያለ ተወዳጅ ሰብእናዋ በተጨማሪ ለእኔና ለትዳሯ የነበራት ክብርና ታማኝነት ነው፡፡ እንደሚታወቀው እሷ በሀያዎቹ እድሜ ክልል እምትገኝ አፍላ ወጣት፣ እኔ ደግሞ ስልሳ ልደፍን አንድ አመት የቀረኝ አዛውንት ሆኜ በመካከላችን ሰፊ የእድሜ ልዩነት ቢኖርም፣ አንድ ቀን እንኳ ሳንጣላና ክፉ ደግ ሳንነጋገር እንደተከባበርን፣ ይኸው ለመለያየት በቃን፡፡”
ይህን ጊዜ አብሮን ማእድ ሲቋደስ የነበረ ዲያቆን፣ የሰማውን ለማመን እንደሚቸገርና ግራ መጋባቱን ለመግለጽ፣ ድምጹን ጎላ አድርጎ በማሳል፣ ጉሮሮውን አጸዳዳ፡፡
“አላመንከኝም ማለት ነው?” ሀዘንተኛው ጠየቀ፡፡
“የለም ጌታዬ፤ አለማመን እንኳን አይደለም፡፡ ነገር ግን በዛሬ ዘመን አብዛኞቹ ወጣት ሚስቶች እግር የሚያበዙ አይነት መሆናቸው ትዝ ብሎኝ ነው” ዲያቆኑ ኃፍረት እየታየበት ምላሽ ለመስጠት ሞከረ፡፡
“ግራ ከተጋባህ እንደዛ የሆነበትን ምስጢር ላብራራልህ፡፡ ሚስቴ ታማኝ እንድትሆንልኝ ያደረግኩት የራሴን አንዳች ብልሀት ተጠቅሜ ነው፡፡ ዘዴው ከራሴው ብልጠት የመነጩ፣ አስረው ሊያስቀምጧት የሚችሉ ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ብልጠት፤ ቅዱስ የጋብቻ መኝታዬን በክብር ጠብቄ እንዳቆይ አስችሎኛል፡፡ አንዳንድ ሚስጥራዊ ቃላትን አውቃለሁ፡፡ እናም እነዚህኑ ቃላት እንደ ሚስጥር መክፈቻ ቁልፍ እየተጠቀምኩ፣ የሚስቴን ታማኝነት አረጋግጬ፣ ያለ አንዳች ስጋት ለጥ ብዬ እየተኛሁ ኖሬያለሁ፡፡”
“ቃላቶቹ ምን አይነት ናቸው?” በጉጉት ተሞልተን በአንድነት ጠየቅነው፡፡
“በጣም ቀላል ነው፡፡ የሆነ ወሬ ፈጥሬ በሰፈር በመንደሩ እንዲዛመት አደረግሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ አብዛኞቻችሁ ይህን ጉዳይ ሰምታችኋል፡፡ ሚስቴ አልዮና ከፖሊስ አዛዡ አሌክሲች ስዋሽበክል ጋር ድብቅ የፍቅር ግንኙነት አላት የሚል ሀሜት እንዲሰራጭ አደረግሁ፡፡ እነዚህ ቃላት ብቻ ማንኛውም ሰው የፖሊስ አዛዡን በመፍራት ሚስቴ አጠገብ ድርሽ እንዳይል ለማድረግ በቂ ነበሩ፡፡ ከዚህም ባለፈ ማንም ቀርቦ ሊያዋራት ስለማይደፍር፣ ስዋሽበክልም የሚሰራጨውን ሀሜት የሚሰማበት እድል ጭራሽ አልነበረውም፡፡ ሀ-ሀ-ሀ-ሀሀሀ ፡፡ ከዚያ ደደብ ጺማም ጋር መላተም ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል እያንዳንዱ ሰው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አንዴ ነክሶ ከያዘ የግል ንጽህናህን አልጠበቅክም ከሚል ምክንያት አንስቶ ድንገት ከቤት ወጥታ ውጪ የታየች ድመትህን ጎዳና እምታቆሽሽ ላም ናት ብሎ እስከ መቅጣት የሚደርስ ውርጅብኝ እንደሚያወርድብህ የማይጠረጠር ነው፡፡”
“ስለዚህ ሚስትህ ከፖሊስ አዛዡ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበራትም ማለት ነው?” እጅግ ተገርመን ጠየቅነው፡፡
“በጭራሽ አልነበራትም፡፡ ያ የእኔ ማታለያ ፈጠራ ነበር.. ሀ-ሀ-ሀ-ሀሀሀ፡፡ በደንብ አድርጌ ሸውጃችኋለሁ፤ ወጣቶች፡፡ እናም ይኸው በመጨረሻ ራሴው መከለያውን አነሳሁላችሁ፡፡”
ፍጹም ጸጥታ የነገሰባቸው ሦስት ደቂቃዎች ተቆጠሩ፡፡ እያንዳንዳችን በዚህ ዘረጦ ባለቀይ አፍንጫ ሽማግሌ ባልጠበቅነው መንገድ መታለላችንና ተሸውደን ስንጃጃል መኖራችን የፈጠረብንን ሃፍረት እያብሰለሰልን ነበር፡፡
“ደህና፤ ፈጣሪ ከፈቀደ አሁንም ሌላ ሚስት ማግባትህ አይቀርም!” ሲል ዲያቆኑ አልጎመጎመ፡
Saturday, 22 March 2025 13:06
ሀዘንተኛው
Written by ደራሲ፡- አንቶን ቼኾቭ ተርጓሚ፡- ሳሙኤል እንግዳ
Published in
ጥበብ

