Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 October 2011 15:53

Greater Ethiopia by

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ክፍል አንድ - 
Wax and Gold
የተከበራችሁ አንባብያን፡-
ላለፉት በርካታ ሳምንታት Anthropology ስለሚባለው Social science ስንጫወት ሰንብተናል፡ ዛሬ ይህን አይነት ሳይንቲስት ይወክልልን ዘንድ ከአንድ ናሙና Anthropology እና ከስራዎቹ ጋር እንተዋወቅ፡፡
ከሶስት ሺ አመት በፊት አክሱማዊቱ ንግስት ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ የነፃ አውጪውን የሙሴን ኦሪት ካመጣችልን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሀበሻና አይሁድ የታላቅና ታናሽ ወንድማማች ያህል መቀራረብና መወዳደር ታሪካቸውን እንዳስተሳሰረ እናስታውሳለን፡፡
ስለዚህ ነው መሲህ ኢየሱስንና ክርስትናን በተመለከተ፣ እኛ ክርስትያን ሀበሾች “መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል ሀይልነ! አይሁድ ክህዱ፣ ንህነሰ አመንነ” የምንለው (መስቀል መድሀኒታችን ነው፣ መስቀል ሀይላችን ነው አይሁድ ካዳ፤ እኛ ግን አመንን)

ይህ ወደ ዛሬ ጭብጣችን ያመጣናል፡፡ ዶናልድ ለቪን የተባለ አሜሪካዊ ይሁዲ በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ስለተመሰጠ፣ በፈረንጅ አቆጣጠር በአስራ ዘጠኝ መቶ ሃምሳዎቹ መንዝ መጥቶ በአገሬው ገበሬዎች መሀል ሁለት አመት ኖረ፡፡ 
እንደነሱ አርሶ የሚኖርበት ማሳ መደቡለት፣ በሬዎች ገዛ፡፡ ሞፈር ቀምበር እርፍ እና ሌላዎቹን እቃዎች እነሱ ሲሰሩ እያየ ባጭር ጊዜ ተማረ፡፡ ሚስት አላገባም እንጂ በሌላም የኑሮ ጉዳይ ሁሉ ልክ እንደ አንዳቸው ሆኖ ኖረ፡፡ ማረስ፣ መዝራት፣ መጐልጐል፣ ማጨድ፣ ተስተካክሎ በእበት የተለቀለቀለው ክብ አውድማ ዙሪያ መከመር፣ ክምሮቹን ወደ አውድማው ካፈረሱ በኋላ፣ በሬዎች ጠምዶ መሄድ፣ እና ሌላ ሌላ እያንዳንዱ ገበሬ በግሉ የሚያደርገውን መፈፀም፡፡
ገበሬዎቹ በማህበር የሚኖሩትም የሚሰሩትም አለ፡፡ አቶ ዶናልድ አብሮዋቸው ቤተክርስቲያን ይስማል፣ በአላቱን ያከብራል፡፡ አንዳንድ ስራ (ለምሳሌ አጨዳ) በደቦ ወይም በቡድን ቢሰሩት ደስ የሚል ድባብ አለው፡፡
በህብረት ብቻ የሚካሄዱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ክርስትና፣ ሰርግ፣ ቀብር፣ ቅዱስ ዮሐንስ (እንቁጣጣሽ) ደመራ፣ ቡሄ፣ ወዘተ
ይሄ ሁሉ ሲሆን አቶ ዶናልድ አማርኛውን (እና ትንሽ ትንሽ ግእዙን) እያሻሻለ ነው፡፡ ግብርናውን ችላ ሳይል፣ የታወቁ ደብተራዎችና ሊቃውንት እንዳስፈላጊነቱ እየጐበኘ መንዜነቱ እየጣመው እያማረበት ሄደ፡፡ በሁለቱ አመት መጨረሻ ላይ ሰምና ወርቁን (Wax and Gold) ተካነበት፡፡ ኧረ አልፎ አልፎ ቅኔ መዝረፍም ይሞካክራል!

ክፍል ሁለት - Greater Ethiopia
ዶናልድ ለቪን አገሩ ተመለሰ፣ (Wax and Gold ታትሞ ተነበበ፡፡ አመታት ካለፉ በኋላ Greater Ethiopia ተከሰተ፡፡ ጭብጡ እንዲህ ይላል፡-
እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደጠበቀችና ሉአላዊነትዋን እንዳስከበረች ኖራለች፡፡ ያስመሰግናታል፣ ግን አይበቃም፡፡ ምክንያቱም ነፃይቱ ኢትዮጵያ “ታላቂቱ ኢትዮጵያ” ትሆን ዘንድ የሚያስፈልጋት “ሁሉ በእጅዋ ሁሉ በደጅዋ” ነው፡፡ ሲዘረዘር የሚከተለውን ይመስላል፡-
የህዝብ ቁጥር ብዛትን ስንመለከት፣ ኢትዮጵያ ሶስት ትልቅ ክፍሎች አሉዋት፡፡ እነሱም ኦሮሚያ፣ አምሀራ እና ትግራይ ይባላሉ፡፡ አንዲት ታላቅ ሀገር National Identity, Political Wisdom እና Democratic procedure ሊኖርዋት ይገባል፡፡ (ሀገራዊ ማንነት፣ ፖለቲካዊ ጥበብ እና ዴሞክራሲያዊ ስነስርአት)
ሀ) National Identity - ከቀዳማዊ ምኒልክ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ድረስ (ሶስቱን ሺ አመት) ሁለት ስርወ መንግስት ብቻ (የምኒልክና የወንድሙ የዛጉዌ) ታሪክ የሰሩባት አገር፡፡ ይሄ መዋጮ ከትግራይ፡፡
ለ) Political Wisdom - የአምሀራ (በተለይም የሸዋ) መዋጮ ይሆናል፡፡ በጂኦግራፊ አቀማመጡ ሸዋ በሰሜንና በደቡብ፣ እንዲሁም በምስራቅና በምእራብ (ማለት በአራቱም አቅጣጫ) የተለያዩ ታሪኮች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ያሉዋቸው ህዝቦች ከበውታል፡፡ ስለዚህ ከየህዝቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት በመወያየት፣ በመደራደር፣ በመመዛዘን፣ በመተዋወቅ ላይ የተመሰረተ፣ “እንካ በእንካ” የሚያመዝንበት እየሆነ ይሄዳል፡፡
ሐ) Democracy - የኦሮሚያ መዋጮ ይሆናል፡፡ ትውልዶች በየስምንት አመቱ ስልጣን የሚረካከቡበት፣ ምንም አይነት “ኩ” (የስልጣን ግልበጣ) ሊካሄድበት የማይችል ዴሞክራሲያዊ ስርአት ማለት ነው…
…ዶናልድ ለቪን የዛሬ መሪዎቻችንን ሰብስቦ ማነጋገር ቢችል ኖሮ “ታላቂቱን ኢትዮጵያ በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት፣ እነሆ ዘመን፣ እነሆ ሁኔታዎች፣ እነሆ ሜዳ፣ እነሆ ፈረስ” ይላቸው ነበር እላችኋለሁ፡፡
አምድ ሙሉ ይይዛል ያልኩት የሀገር ወዳድ ዜጋ መልእክቴ ይኸውና እንዲህ ባጭሩ ተጠቃለለ፡ ያነበብነውን በልባችን ያሳድርልን እያልኩ፣ የማዝናናት ተግባሬን እቀጥላለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ላቀርብላችሁ የምፈልገው አንድ ጣልቃ ገብ ሀሳብ አለ፡፡ ሀሳቡን የፈጠረብኝ ይህን ሰሞን በመገናኛ ብዙሀን ተደጋግሞ የተስተጋባው (አስቀያሚ፣ ዘግናኝ “ኢሰብአዊ” ወንጀል ነው፡፡) ወንዶች የያዛቸው ፍቅር አፀፌታውን ካላገኘ፣ “ፍቅር አሳብዶኛል” በሚል ሰበብ ሴቲቱ ፊት ላይ acid በመርጨት አይኗንም ያጠፋሉ፣ መልኳንም ይበክላሉ፡፡
የጉድ ችግኞች በሚፈሉባት አዲሳበባችን ካልተበከለ በስተቀር፣ ጤነኛው የገዳ ስርአት በተዘረጋበት የኦሮሞ ክፍለ አገር ውስጥ ይህን የመሰለ ገሃነማዊ ወንጀል ከቶ ሊፈፀም አይችልም፡እንዴት ብትሉኝ፣ የሚከተለውን ታሪካዊ መረጃ አቀርብላችኋለሁ፡፡ ጋብቻንና ፍቅርን ይመለከታል…
…ኦሮሞዎች በያሉበት አካባቢ ከሚጐራበቱዋቸው ህዝቦች በሚኖራቸው ግንኙነት ምክንያት፣ የጥንት ባህላቸው የተበረዘ ነው፡፡ ወሎ ስንደርስማ በዚች አራት መቶ ሃምሳ (?) አመት ውስጥ ኦሮሞነታቸው ለአብዛኛዎቹ ተረስቶ አማራ ሆነው፣ ባማርኛ ዘፈኖች መፍለቅያነት ታውቀዋል፡፡ አምባሰል ቅኝት፣ አንቺ ሆየው ለኔ፣
አብዛኛዎቹ ኦሮሞዎች የሚስማሙበት አንድ ታሪካዊ እውነት አለ፡፡ ይኸውም፣ ጥንታዊው የኦሮሞ ባህል በማንም ጐረቤት ህዝብ ያልተበረዘው ነገሌ ቦረና ውስጥ ብቻ ነው (ይሄ መረጃ ከሀምሳ አመት በፊት እውነት ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ያለው ባህል ምን ያህል ያው ይሆን ምን ያህልስ ተለውጦ ይሆን?)
“በዚየ በደጉ ዘመን” ያንድ አካባቢ ልጆች አብረው ሲያድጉ፣ ወንድና ሴት እየሆኑ ኩኩሉ፣ ባልና ሚስት፣ ምናምን እየተጫወቱ ነው፡፡ ከዘጠኝ አስር እድሜ ጀምሮ ፍቅረኛሞች ይሆናሉ፡፡ ሲጫወቱም፣ ሲጨፍሩም፣ በአል ሲያከብሩም ፍቅረኛሞች ሆነው ነው (የግብረ ስጋ ግንኙነት) በሀሳባቸው እንኳን አይመጣም፡፡ ጊዜው ገና ነው፡፡ አሁን ፍቅር ብቻ! ይሄ ፍቅር ሞት እስኪለያቸው ይዘልቃል…
…ፍቅር በልጆቹ ፍላጐት ይሁን እንጂ ጋብቻ ግን በወላጆቻቸው ምርጫ ነው፡፡ ወላጆች ዘር ተቆጣጥረው፣ ማእረግና ሀብት ተገማምተው ሲያበቁ፣ ልጃችሁን ለልጃችን ይባባላሉ፡፡ ልጆቹ የጥሎሹንና የሰርጉን ስነስርዓት እንደታዘዙት ይፈጽማሉ፡፡
አሁን የሙሽሪትን የህይወት ታሪክ እንከተላለን፡የሠርግና ምላሽ ስነስርዓት ሁሉም ጊዜውን ጠብቆ እየተፈፀመ ወራት ያልፋሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሙሽሪት አብሮ አደግ ፍቅረኛዋን እየናፈቀች ነው፡፡
በተዳረች በዘጠነኛው ወይ በአስረኛው ወር በድብቅ ለአንዷ ጓደኛዋ ይከሰታል፡፡ ቤቷ ወይ ጓደኛዋ ቤት ትደብቀዋለች፡፡ እዚያ እየኖረ፣ ባልዋ ወደ እለት ጉዳዩ ሲወጣ፣ ፍቅረኛዋን ወደ ቤትዋ ያመጡላታል፡ይህ የማይጠገብ ፍቅር እንዲህ በስውር እየተካሄደ ሳምንታት (ምናልባትም ወራት) ያልፋሉ፡፡
“አንድ አሳቻ ሰአት” እቤትዋ በፍቅር ድባብ ሲዝናኑ፣ ባል ከተፍ ፍቅረኛ በድንጋጤ ልብሱን ይዞ፣ ግማሽ ራቁቱን ወጥቶ ሲሸሽ፣ ባል እያሳደደ ጦሩን ይወረውርበትና ይስተዋል (የስነ ስርአቱ ደምብ ነው) ገላጋዮች ይደርሳሉ፡፡ ጉዳዩ ሽማግሌዎች ፊት ይቀርባል፣ ፍርዳቸውን ያስታውቃሉ፡፡ የዘር ጥራትና የሀብት ብዛት ተመዝኖ በደለኛው ውሽማ ለተበደለው ህጋዊ ባል የተወሰኑ በሬዎች፣ በጐች ወይም ፍየሎች፣ እና ምናልባት አንድ አህያ ይከፍላል፡፡
ከዚያ በኋላ ፍቅረኝየው ወደ አብሮ አደግ ፍቅረኛው ቤት እንደ ልቡ ይመላለሳል፡፡ ሲገባ ጦሩን በሩ ጋ ይተክላል፡፡ ባልየው ቢመጣ (ከእንግዲህ “አሳቻ ሰአት” የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም) ወደ ቤት ልግባ አይልም፣ መንገዱን ይቀጥላል እንጂ፡፡
ቅር አይለውም፡፡ ምክንያቱም እሱ ራሱ እቺን ሚስቱን ለፍቅረኛዋ እንደሚለቅለት፣ በተራው እሱ አብሮ አደግ ፍቅረኛው ትዳር የያዘችበት መንደር ሄዶ፣ በስርቆሽ “የሰው ሚስት ሲያማግጥ” ተይዞ፣ ተገቢውን ካሳ ከከፈለ በኋላ፣ ወደ ቤቷ እንደልብ ይገባል (ጦሩን በሩ ጋ እየተከለ)
እዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ሴትና ወንድ በአዋጅ ሳይሆን በተጨባጭ ኑሮ እኩል መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሳይሆን የማህበረሰብ አኗኗር ስልጣኔ ይህን ይመስል ነበር፡፡ ያነበብነውን በልባችን ያሳድርልን አሜን፡፡
ምርቃት አንድ
ህንድ አገር ውስጥ ነን፣ በግምት ከአራት ሺ አመት በፊት፡፡ ያን ጊዜ ተረትና ታሪክ ገና መራራቅ አልጀመሩም ነበር፡፡)
ንጉሱ ለአልጋ ወራሹ ሰርግ ደገሰ፡፡ ለዜጋዎቹ ሁሉ ግብር ጣለ፡፡ ህዝብ ወደ ቤተ መንግስት ጐረፈ፡፡ ጥሪውን አክብረው ከመጡት መሀል አንዱ ሽማግሌ ለማኝ ነው፡፡ በቁመት ስንዝር የምታክል ከረጢት ይዟል፡፡ ንጉሱ አይቶት አስጠራውና “ምን ልስጥህ?” አለው “አይዞህ አትራፍ፡፡ የምትፈልገውን ተናገር
“ንጉስ ሆይ” አለ ለማኙ “መልካም ፈቃድህ ከሆነስ በዚች ከረጢት ሙሉ ሳንቲሞች ለግሰኝ”
“ሳንቲም አይደለም የምሰጥህ” ብሎ፣ የገንዘብ ሹሙን “ወርቅ አምጣና ሙላለት” ሲል አዘዘ፡፡ ሹሙ በሁለት እጁ የወርቅ እንክብሎችን በማፈስ አምጥቶ ጨመረው፡፡ ከረጢትዋ አልሞላችም፡፡ ድጋሚ አምጥቶ ጨመረባት፡፡
ከረጢትዋ ዋጠችው እንጂ እንኳን ልትሞላ ቀርቶ፣ ጨርሳ ቅም አላላትም፡፡ ሶስተኛም፣ አራተኛም፣ አምስተኛም፣ አስረኛም ጊዜ እያፈሰ እያመጣ አጐረሳት፡
ንጉስ እልህ ያዘው፡፡ ከረጢቷ እቤተ-መንግስት ተከማችቶ የነበረውን ወርቅ በሙሉ ዋጠችው፡፡ አሁንም ያው ባዶዋን ናት፡፡
ንጉሳችን መገረሙ አልፎለት ትእግስቱ አለቀ፡፡ ለማኙን በአንገቱ ብድግ አርጎ ወደ ላይ እያንጠለጠለው “እቺ ጉደኛ ከረጢትህ ከምንድ’ነው የተሰራችው?” ብሎ አፋጠጠው፡፡ ለማኙም “ከሰው ቆዳ ነው፣ ንጉስ ሆይ” ብሎ መለሰለት፡፡
ምርቃት ሁለት
ኢየሩሳሌም ውስጥ ነን፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ እያለ፣ አንድ በማእረግ ዝቅተኛ የሆነ መኳንንት እየሮጠ ገብቶ ንጉሱ እግር ስር በግምባሩ ተደፍቶ “የሙጥኝ!” ሲል ተማፀነ፡፡ የፕሮቶኮል ሹም (ማለት የጊቢ ሚኒስትር) እያዳፋ ሊያስወጣው ሲቃጣ፣ ንጉሱ በእጁ ምልክት ገታው፡፡ እና “ምን ሆነህ ነው?” አለው ያጎነበሰውን
“ይቅርታህ ንጉስ ሆይ፣ መልአከ ሞት በክፉ አይን አየኝ፣ ፈርቼ መሄጃ በማጣቴ ወዳንተ ሸሸሁ”
“እና ምን ላድርግልህ?”
“መልካም ፈቃድህ ይሁንልኝና፣ ነፋስን አሁኑኑ ወደ ህንድ አገር እንዲወስደኝ እዘዝልኝ”
“እሺ በል ተነስ” አለው፣ ሰውየው አመስግኖ እጅ ነስቶ ወጣ . . .
. . . በነጋታው ንጉስ ሰሎሞን በአታክልቱ ውስጥ እየተዘዋወረ ከሀሳቡ ጋር ሲጫወት፣ መልአከ ሞትን አየው፡፡ በምልክት ጠራው፣ መጣ፡፡
“ለምንድ’ነው ትላንት በዚህ ሰአት የኔን መኳንንት ያስፈራራኸው?”
“ኧረ እኔ በክፉ አይን አላየሁትም”
“እንግድያውስ?”
“ከሰማይ ወደ ስራዬ ስሰማራ፣ ያንን ሰው ወደ ማታ ላይ ከህንድ አገር እንድወስደው ታዝዤ ስለነበረ፣ ከዚህ እስከዚያ ርቀቱን እያሰብኩ በነዚህ ጥቂት ሰአታት ውስጥ በምን አይነት ዘዴ ህንድ አገር ደርሶ ልንገናኝ ይሆን?” እያልኩ ግራ ተጋብቼ ነበር ያየሁት”
ምርቃት ሶስት
ዛሬስ የምር አርእስተ ጉዳዮች በዙብን፡፡ እስቲ ለማሳረግያ ከጥንት ተረቶቻችን አንዱን ላቀብላችሁ፡፡
ባልና ውሽማ “በአሳቻ ሰአት” ማታ ተገናኙና ወድያው ትግል ተያያዙ፡፡ ሚስት ቆማ ታያለች፡፡ ሁለቱም ጉልበተኛ ስለነበሩ ለረዥም ጊዜ ታገሉ፡፡ በመጨረሻም ሁለቱም ደክመው እያለከለኩ፣ ባል “እቃዎቹን ወደዚያ በያቸው” አላት
“ልትወድቁ ነው’ንዴ፣ አንቱዬ?” ብትለው
“እንግድያው ላንቺ ብዬ ቆሜ ላድር ኖሯል?” አላትና . . .
ምርቃት አራት
አሁንም ከጥንት ተረቶች አንዱ ጐበዝና ፈሪ አብረው ሲጓዙ፣ ሰው ቤት ሳይደርሱ ጨለመባቸው፡፡ አንዱን አለት ተጠግተው ጐን ለጐን ተኙ፡፡ ሌሊት ጐበዙ ነቃ፡፡ የሆነ የመቆረጣጠም የመሰለ ድምፅ ይሰማዋል፡፡
“ምንድነው ይሄ ድምፅ፣ አንተ?” አለው
“እሽሽ!” አለ ፈሪው በሹክሹክታ “አትጩህ፡፡ ድብ አንድ እግሬን ጐርሶ ነው”
“ባይሆን አትጮህም ነበር?”
“ተቆጥቶ ከዚህ የባሰ እንዳይበላኝ ፈርቼ ነው”
ምርቃት አምስት
በአፄ ዮሀንስ (በዝብዝ ካሳ) ዘመነ መንግስት “አባ ሆር” የሚባሉ አንድ ሰው ነበሩ፡፡ እውነተኛ ስማቸው ተረስቷል፡፡ አባ ሆር ወደ ጥርጊያ ጐዳና ይወጣሉ፡፡ እዚያ ቆመው ይጠብቃሉ፡፡ ተጓዥ ሰዎች ሲመጡላቸው፣ ከተለመደው ሰላምታ በኋላ ሰውየው “ወዴት ናችሁ?” ይጠይቃሉ
“ወደ ጐንደር ነን” ካሉዋቸው
“እኔም ወደዚያው ነኝ” ብለው አብረዋቸው ይሄዳሉ (እንዲህ አይነቱ ረዥም ጉዞ ላይ ሰዎች ብዙ መረጃ ወይም information) ይለዋወጣሉ፡፡
ጐንደር ሲደርሱ አባ ሆር ተጓዦቹን ተሰናብተው፣ የመሸበት እንግዳ የሚያሳድር ቤት ፍለጋ ይዘዋወራሉ፡፡ ወደ ጐንደር መጡ እንጂ፣ ተጓዦቹ ወደ ደብረ ብርሀን የሚሄዱ ቢሆኑ ኖሮ፣ አባ ሆር “እኔም ወደዚያው ነኝ” ብለው አብረዋቸው ይሄዱ ነበር፡፡
ይሄ ካጋጠሙዋቸው ተጓዦች ጋር መሄድ፣ አልፎ አልፎ ወደ መኖሪያ መንደራቸው ያመጣቸዋል፡ቤታቸው ይገባሉ፡፡ የመጓዝ አባዜያቸው ተነስ ሂድ እስኪላቸው ድረስ አርፈው ቤታቸው ይቀመጣሉ፡በነዚህ አጋጣሚ በያባ ሆር የእረፍት ቀናት፣ ሚስታቸዉ ስራ ስለማይፈቱ ሶስት ልጆች ወለዱላቸው
. . . በአባ ሆርነታቸው ዝነኛ ሰው ሆኑ እንጂ፣ ሰውየው ራሳቸው ማን እንደነበሩ በውል የሚያውቅ ስለሌለ፣ በስማቸው ዙሪያ ልዩ ልዩ የመላ ምት ወይም የነሲብ ወሬዎች ይናፈሱ ጀመር፡፡ ሁለቱን ብቻ እንዳስታወስኩዋቸው እነሆ፡-
ወሬ አንድ
አባ ሆር በአፄ ዮሐንስና በምኒልክ ንጉሰ ሸዋ መሀል የምስጢር መልእክት ያመላልሱ ነበር፡፡ (አባ ሆርነታቸው ለዚህ ስራቸዉ ሽፋን ነበር ማለት ነው)
ወሬ ሁለት
በየአመቱ የስቅለት እለት እየመጡ አፄ ዮሀንስ ጋር የሚሰግዱ የበቁ መነኩሴ ነበሩ ይባላል፡፡ እኛ ደርቡሽ የምንለው የማህዲ ሰራዊት ከሱዳን ድረስ መጥቶ መተማ አጠገብ መድረሱ ሲታወቅ ግን፣ መነኩሴው እስከ አርብ ስቅለት ሳይጠብቁ አፄ ዘንድ ብቅ አሉ፡፡ “ሁለት ምርጫ አለህ” አሉዋቸው “ወደ መተማ ከዘመትክ በውጊያ ላይ ተገድለህ ትፀድቃለህ፡፡ ካልዘመትክ አርባ አመት በሰላም ትገዛለህ፣ ግን አትፀድቅም”
አፄ ዮሀንስ ዘመቱ፣ ሞቱ፡፡ ወሬ ሁለት እንደሚነግረን ከሆነ ግን፣ መነኩሴው ውስጡን የንጉስ ምኒልክ ሰላይና ሁነኛ አማካሪ ነበር፣ እና አፄ ዮሀንስ ከሞቱ በኋላ ምኒልክ ሸዋ የነበሩት ሰውዬ አጤ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ሆኑ፡፡ እና ወሬው እንደሚለው፡ የበቁት መነኩሴ አባ ሆር ራሳቸው ነበሩ፡፡
ይህን ጉዳይ ለጊዜው እንጥልጥል እንተወውና . . .
. . . ከደርቡሽ በፊት መተማ ውስጥ የሚኖሩ፣ሲበዛ የሚፋቀሩ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ባልየው በመላው ክርስትያን ኢትዮጵያ እየዘተዋወሩ የሚያስተምሩ ሊቀ ሊቃውንት ነበሩ፡፡ ማለት በአመት ለሶስት፣ አራት አምስት ወራት ያህል ከሚስታቸው ጋ መነፋፈቅ እንጂ መላላክ እንኳ የለም፡፡ ይህ እየተራራቁ መገናኘት ፍቅራቸውን በልማድ ብዛት እንዳይሰለች፣ በናፍቆት ብዛት ሁልጊዜ አዲስ እንዲሆን አስቻለው፡፡
አንድ ቀን መምህር ከአመታዊ ጉዞዋቸው ሲመለሱ መተማ በከፊል ተቃጥላለች፡፡ ቤታቸው ሲደርሱ ባዶውን ነው፡፡ ቢያጠያይቁ ሚስታቸውን ደርቡሾች ማርከው ወስደዋታል፡፡
እንኳን ደርቡሽ ቱርክ ቢማርካት ፈልጌ አገኛታለሁ! እግዚአብሔር አንድ ያደረጋቸውን ባልና ሚስት ሰው አይለያቸውም፡፡
እንኳን ደርቡሽ ዲያብሎስ ራሱ ቢማርካት ሄጄ እወስዳታለሁ (ሳይሉ አይቀርም ለገዛ ራሳቸው) ያኤል ማህዲ የሚሉት ንጉሳቸው’ኮ ጦር ሜዳ ላይ ካልሆነ እንደኔው አንድ ሰው ነው፡፡ ሚስቴን ከአንድ ሰው መልሼ መንጠቅ ካልቻልኩማ ምኑን ባል ሆንኩት?
አባይን እየተከተሉ ወደ ካርቱም ለመጓዝ ተነስተው ባውራ ጐዳናው ጥቂት እንደተራመዱ ከአባ ሆር ጋር ተገናኙ፡፡
ከመከረኛው ሰላምታ በኋላ “ወዴት እየሄዱ ነው፣ መምህር?” ጠየቁ አባ ሆር
“ወደ ካርቱም”
“እኔም ወደዚያው ነኝ”
[እስከ ካርቱም የነበረው ጉዞ ከአደጋው ብዛትና ከተከሰተው የሰው ልጆች ስግብግብነት፣ ክፋትና አላስፈላጊ ጭካኔ መደጋገም የተነሳ፣ የማዝናናት ተግባሬን አስታውሼ ትረካውን እዘለዋለሁ]
ከሶሰት ወር ጉዞ በኋላ ካርቱም ሲደርሱ ሊቀ ሊቃውንቱ መምህርና አባ ሆር ወድያው ወደ ማህዲ ተወሰዱ፡፡
የመጡበትን ጉዳይ ሲጠየቁ “በሌለሁበት የሰረቅኸኝን ሚስቴን ልወስዳት ነው የመጣሁት”
“ሚስትህ ንብረቴ ናት፡፡ ብፈልግ ገበያ ወስጄ እሸጣታለሁ፡፡ ቢያሰኘኝ ወጥ ቤቴ ትሆናለች፣ ካማረችኝ ደግሞ እቁባቴ ትሆናለች፡፡ አንተ ሙስሊም ብትሆን ኖሮ ግን አሁኑኑ ሚስትህን አስረክብህ ነበር፤ ከተገቢው ካሳ ጋር”
“ማህዲ ሆይ፣ እኔ’ኮ የጠራሁ ሙስሊም ነኝ”
“ከመቼ ወዲህ?”
“ካሁን ወድያ”
ኤል ማህዲ እጅጉን ተገረመ፡፡ “ይሄ ሁሉ ለአንዲት ሴት?”
“እቺ አንዲት ሴት ዛሬ ካሉህ ሚስቶች፣ እቁባቶች እና የሀሪም ሴቶች ትበልጣለች”
“እድለኛ ሰው ነህ” ብሎ ሚስታቸውን አስረከባቸውና “መተማ የሚያደርሱህ ወታደሮች አዝልሀለሁ” ቢላቸው
“ሙስሊም ነኝ’ኮ ክርስትያን አገር ምን ላደርግ እመለሳለሁ?” . . .
. . . አባ ሆር ካርቱም መኖሩን ለመዱት፡፡ እየሰለቻቸው ሄደ፡፡ አንድ ቀን ወደ አውራ ጐዳና ወጡ፡፡ ተጓዦች እስኪመጡላቸው ድረስ “እኔ ጉዞዬን የምወደውን ያህል መምህር-ሼክ ሚስታቸውን ያፈቅሩ ይሆን” ከሚለው ሀሳብ ጋር እየተጫወቱ ቆዩ . . .
ቸር ይግጠመን አሜን፡፡
በሚቀጥለው እንገናኛለን፤ ኢንሻላህ!

 

Read 3252 times Last modified on Saturday, 29 October 2011 16:02