Saturday, 22 March 2025 12:08

መሥዋዕትነት ማለት ማገዶነት ከሆነ፣ ለሰው ክብር አይመጥንም!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  ከምንጩ በፊት ጅረቱን ያያሉ - ሰዎች። ፀሓይ ስትወጣና ስትጠልቅ ሳይመለከቱ፣ ብርሃንን ከጨለማ ይለያሉ።
መቼ እንደተገነባና ምን ያህል እንደተደከመበት ሳያውቁ፣ የተዋበ ግቢና ምቹ መኖሪያ ቤት ውስጥ ይወለዳሉ። ወይም እንደ ዓቅሚቲ የተቀለሰች ጎጆ ውስጥ። ከየት የመጣ ቤት ነው ብለው አይጨነቁም።
ማን እንዳመረተው ሳይጠይቁ የተጋገረውን እየበሉ ያድጋሉ። እንዴት እንደተሸመነ ሳይገባቸው፣ ሸማ ይለብሳሉ። በስንት ሂሳብ እንደተገዛ ወጪውን ሳያሰላስሉ ሱሪና ቀሚስ ያደርጋሉ።
እና ምን ችግር አለው? ለጊዜው ችግር አይኖረውም። ኀጢአት ወይም ወንጀል አይደለም።  እንደ ድክመት ወይም እንደ ጉድለትም አይቆጠርም። እንዲያውም፣ ለመነሻ ያህል የግድ አስፈላጊ ነው። መኖሪያ ቤቱን አደላድሎ፣ ሕይወቱን ለመምራት ተዘጋጅቶ የሚወለድ ሕፃን የለም።  ግን ደግሞ ዕድሜ ልኩን ሕፃን ሆኖ የሚኖር ሰው የለም። ያኔ ነው ችግር የሚሆነው። ቤት ስለ መሥራት ሳያስቡ፣ “እመ-ቤት” ወይም “ባለ-ቤት” እንሆናለን ማለት የጀመሩ ጊዜ ነው ችግሩ።
ለጊዜውማ ቀድሞ በተዘጋጀላቸው ግቢ፣ እንዲሁም ተሠርቶ በጠበቃቸው ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት። “ሲያርሱና ሲዘሩ” ሳይሆን፣ የተሰበሰበው አዝመራ ተጋግሮ “ሲቆርሱና ሲጎርሱ” ነው የሚያድጉት። የፍራፍሬ ዛፍ ሲተከል ሳይሆን፣ ብስል ፍራፍሬ ተቀንጥሶ ሲገመጥ ነው የሚታያቸው።
ተፈጥሯዊ ነው።
ከጥረት ግረት በፊት ውጤትና ድግስ ቀድሞ ቢታያቸው፣ ከእርሻ በፊት ጉርሻ ቢታሰባቸው አይገርምም። ከምንጩ በፊት ጅረቱ እንዲሉ ነው።
ከፀሓይ በፊት ብርሃን ተፈጠረ?
ሃይማኖታዊው ትረካ ገና “ሀ” ብሎ ሲነሣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ፣ ከሁሉም በፊት ብርሃን ተፈጠረ ይለናል። ፀሓይና ጨረቃ ተፈጠሩ ብሎ አይጀምርም። ከጨለማ ማሕፀን ውስጥ ብርሃን ተወለደ። ብርሃንና ጨለማ ተለይተው፣ ቀን እና ሌሊት የሚል ስም ወጣላቸው። “አሀድ ዮም” ተባለ ይለናል - የዕብራይስጡ ትረካ። “አሀድ ዕለት” ወይም እሁድ… ልንለው እንችላለን በግዕዝ።
ከዚያም ሰማይ እንደተፈጠረ ትረካው ይነግረናል - ሰኞ ዕለት። በሦስተኛው ዕለት (ሠሉስ) ላይ፣ ውኃና የብስ ተለይተው፣ ባሕርና ምድር ተብለው ተጠሩ። የሣር ዐይነቶች፣ የእህል ሰብሎች፣ የፍራፍሬ ተክሎች… የዕፅዋት ዘር ሁሉ በቀለ ይለናል - ትረካው።
ረቡዕ ዕለት ላይ ደግሞ፣ ቀንና ሌሊትን የሚለዩ የብርሃን አካላት እንደተፈጠሩ ይገልጽልናል።
ብርሃን ነው ቀድሞ የመጣው። በዚህም ቀንና ሌሊት ተለይቷል - ገና በመጀመሪያው ዕለት።
በአራተኛው ዕለት ደግሞ እንደገና፣ ቀንና ሌሊትን የሚለዩ ፀሓይና ጨረቃ እንደተፈጠሩ ይነግረናል።
ትረካው በጥሬው የነገሮችን ክስተት ለማስተማር ሳይሆን የሰዎችን የእይታ ቅደም ተከተል በምሳሌያዊ ዘይቤ ለማሳየት የታሰበ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም፣ ከፀሓይ በፊት ብርሃን፣ ከምንጭ በፊት ጅረት ነው የሚታየን።
ይህም ብቻ አይደለም። ከግል ኀላፊነት በፊት የግል ነጻነት እንደሚያምረን ትረካው ይጠቁማል። ወደ ሥራ ከመሰማራታችን በፊት፣ የሥራ “ፍሬ” ይማርከናል። ራሳችንን ለመቻልና ኑሮ ለመመሥረት የግል ኀላፊነት ሳንወስድ፣ ተዘጋጅቶ የቀረበልን ግቢ ውስጥ የተፈቀደልንን እየበላን ከማደግ ባሻገር፣ ያሰኘንን አንሥተን ለመውሰድ፣ ከማሳው ውስጥ በነጻነት እየሸመጠጥንና እየተገባበዝን ድግስ ለመብላት እንፈልጋለን። ሔዋንና አዳም እንዳደረጉት።
ከጥረት ግረት በፊት፣ ውጤትና ምቾት ነው የሚታየን። ከጾም በፊት ድግስ። ቢሆንም ግን “መብላት አልነበረባቸውም” ለማለት አይደለም።
ሕይወትን ማጣጣም ወይም መደገስ ክፋት የለውም፤ በጎ ነው።
ውጤትና ምቾት፣ የፍራፍሬ ጣዕምና ድግስ… መጥፎ አይደሉም። እንዲያውም ጥሩ ናቸው። ጥሩ ባይሆኑ ኖሮማ፣ ጥረትና ግረትም ትርጉም አይኖራቸውም ነበር።
መሥራት ጥሩ የሚሆነው የሥራ ፍሬ ለማግኘትና ለማጣጣም ነው።
ጣፋጭ ፍሬ መብላት  መልካም እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን፣ ሥራ ይቀድማል። ከውጤት በፊት ጥረት መኖር አለበት።
አዎ እስከ ተወሰነ ዕድሜ ድረስ፣ ውጤት ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው። መብላት እንጂ መሥራት አንችልም። ከእርሻ ሥራ በፊት የፍራፍሬ ጉርሻ ነው የሚታየን። ለጊዜው ችግር የለውም። ዐራሽ ወይም መሀንዲስ ሆኖ የሚወለድ ሰው የለም። ጥበበኛ ሆኖ አይወለድም። ሁሉንም ነገር በአንዴ ማወቅ ወይም በአንድ ጀምበር የብቃት ማማ ላይ መውጣት አንችልም።
የመድረስ ምኞት ብቻ ሳይሆን፣ ዐቀበቱን የመጓዝ መከራም!
ውለን ስናድር፣ ከብርሃን ጋር ፀሓይንም ማየት ይኖርብናል። ከጅረቱ ጋር ምንጩንም። ከዛፉ ላይ ፍሬ ቀንጥሰን ለመብላት መንጠራራት ብቻ ሳይሆን፣ ዛፍ ተክለን ለማሳደግና ፍራፍሬ ለማምረትም ጎንበስ ቀና ማለት እንዳለብን ጥንታዊው የሃይማኖት ትረካ ይገልጽልናል። ከሰው ተፈጥሮ ጋር የሚስማማና ለሰው ክብር የሚመጥን አኗኗር እንደዚያ ነው።
የተፈጥሮው ቅኝት፣ “ለፍሬያማ የሥራ ጥረት” ነው። ወይም “የሥራ ፍሬውን ለማጣጣም”። አንዱ ያለ ሌላው… ከንቱ ነው። ወይም የማገዶነት አምልኮ ይሆናል።
መሥዋዕትነት ማለት ማገዶነትን ማምለክ ከሆነ፣ ውጉዝ ይሁን
ውጤት የማያመጣ ጥረት፣ ፍሬ የሌለው ሥራ፣ መድረሻው የማይታወቅ የዐቀበትና የቁልቁለት ጉዞ… ከንቱ ልፋት ነው። ተቸግረውም ቢሆን፣ በቀን አንዴ ብቻ በልተውና ፈተናዎችን ተጋፍጠውም ቢሆን (ጾመውና ሰግደውም ቢሆን) በብርቱ የመትጋት ጽናት ያስፈልጋል ከተባለ፣ ለነገ ለከነገ ወዲያ የተሻለ ሕይወት ለመፍጠር መሆን አለበት። አለበለዚያ ከንቱ ልፋት ይሆናል።
ውጤት የማያመጣ ጥረት፣ ድግስ አልባ ጾም፣ መድረሻ ቢስ ውጣ ውረድ፣ ፋይዳ የሌለው የዕድሜ ልክ ፍዳ… አንድም አላዋቂነት ነው። አልያም ባርነት ነው። ወይም ሌሎች ተቀምጠው የሚሞቁት ማገዶ ነው። እነዚህ ሁሉ ለሰው ክብር አይመጥኑም። በፈቃደኝነት የተማገዱና ራሳቸውን ለእርድ ያቀረቡ የሰው ልጆች የሰውን ክብር አዋርደዋል።
በግዴታ የማገዱም የሰውን ክብር አዋደዋል - ሰውን እንደ መሥዋዕት በግ የሚቆጥሩ ናቸውና።
ሌሎች ሰዎችን እየማገዱ እሳት መሞቅ፣ በሌሎች ስቃይ እየተዝናኑ እንደመሳቅ ነው። ሳይሠሩ የመበልጸግ እንደመመኘትም ነው። ሁሌም ፋሲካ ሊሆን አይችልም - ከሌሎች ሰዎች ካልዘረፉ በቀር።  
ሳይጓዙ ለመድረስ፣ ከዐቀበት ጋር ሳይታገሉ ወደ ከፍታ ለመውጣት፣ ሳይጥሩ ውጤት ለማምጣት፣ ሳይዘሩ ለማጨድ፣ ሳይተክሉ ፍሬ ለማግኘት፣ ሳይሠሩ ለመደገስ መመኘት ከንቱ ነው። አንድም ዕድሜ ልክ ከሕፃንነት ላለመውጣት በዓቅመ ቢስነት ተቀንጭሮ መቅረትን ወይም ተመጽዋችነትን መርጧል። አልያም ከሌሎች ሰዎች ጉዳትና ኪሳራ ላይ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ያሰፈስፋል። ሊማግዳቸውና መሥዋዕት ሊያደርጋቸው ያደባል።
ሌሎች ሰዎችን በባርነት ለመግዛት ይመኛል። በዝርፊያ ይተማመናል።
ሌላ ሰው ይሠራል፤ ይለፋል።
እሱ ሣይሰራ ፍሬ ያፍሳል፤ ወይም ይዘርፋል።
ካልሆነለትም በምቀኝነት የሰዎችን ሕይወትና ንብረት በማጥፋት ለመርካት የሚሞክር መሠሪ ይሆናል። ከሌሎች ጉዳት ጥቅም ለማግኘት ስለሚጠብቅ፣ ጉዳት ሲደርስባቸውና ሲሰቃዩ፣ ትልቅ ቁምነገር የሠራ ይመስለዋል። ያለ ጥረት ውጤትን መመኘት እንደዚህ ነው። ሳይጾሙና ፈተና ሳያልፉ ድግስና ሽልማትም እንደዚያው።
በዚህም ተባለ በዚያ፣ ውጤት የማያመጣ ጥረትን፣ አልያም ያለ ጥረት የሚገኝ ውጤትን መመኘት… ማገዶነትን እንደማምለክ ነው። ይማግዳሉ ወይም ይማገዳሉ። የመበላላት እሽቅድምድም ነው  ልንለው እንችላለን።
ማገዶነትም ሆነ መበላላት ከሰው ተፈጥሮ ጋር አይስማሙም። ለሰው ክብር አይመጥኑም። ብዙዎች ግን “መሥዋዕትነት እንደዚህ ነው” በማለት ማገዶነትንና መበላላትን እያደነቁ ይናገራሉ። እንደ መልካም ተግባር እየቆጠሩ ብቻ ሳይሆን እንደ ትክክለኛና እንደ ዋና የሥነ ምግባር መርሕ እያስመሰሉ ይሰብካሉ።
አንዱ ሌላኛውን እያነደደ እንደ አውሬ እንዲበላ ሊያነሣሡት ፈልገው ነው? ወይስ ሌሎች ሰዎች እያነደዱ እንዲበሉት በፈቃደኝነት ራሱን ለእርድ እንዲያቀርብ ሊያግባቡትና ሊያበረታቱት ፈልገው ነው? እሺ ካላለም ሊገፋፉትና ሊያስገድዱት?
የሰው ተፈጥሮ ለመንደድም ሆነ ለማንደድ፣ እርስ በርስ ለመተራረድም ሆነ ለመበላላት፣ በከንቱ እንዲለፋም ሆነ ሳይሠራ እንዲበላ የተቃኘ አይደለም።
የድግስ አድናቂ ቢሆን ክፋት
የለውም። በጎ ነው።
ጣፋጭ ፍሬ ይብላ፤ ይመቸው። የተሻለ ሕይወትን በእጅጉ ቢመኝ መልካም ነው። ደግ አደረገ። የተንዠረገገውን ጣፋጭ ፍሬ ለማድነቅ፣ የሥራ ውጤትን ለማሞገስ፣ ለመጪው ጊዜም መልካም ሕይወትን ለመመኘትና የወደፊት ዓላማውን ለማክበር… በየጊዜው ቢደግስ ጥሩ ነው። ነገር ግን ሳይሠራ ለመብላት መሆን የለበትም።
በጥበብ ተግቶ ከሠራ የዚያኑ ያህል ፍሬ እንደሚበዛለት በመተማመን መሆን አለበት ድግስ የሚያሰናዳው። የመሥራት ኀላፊነትን በመውሰድ መሆን አለበት ለክብረ በዓል የሚታደመው።
የሥራ አድናቂ ልሁን ካለም በጎ ነው። ክፋት የለውም።
ሳልበላ ብውልም ሳልሠራ አልውልም ይበል። ይቅናው። ብርታቱ ዕጥፍ ይጨምርለት። በእርግጥም ገና ከመነሻው፣ ሰው የተፈጠረው ለሥራ እንደሆነ የአዳምና የሔዋን ትረካ ይገልጻል። ምድርን ለማረስና ለማለምለም፣ በውስጧ የያዘችውንም ሁሉ ለፍሬ ለማብቃት ነው የሰው አፈጣጠሩ።
ምድር የሚያርሳት ሰው ስላልነበረ ዕፅዋት አላበቀለችም ነበር ይለናል ሃይማኖታዊው ትረካ። መሥራትና ማልማት የሰው ድርሻ መሆኑን ነው ገና ከመነሻው የሚነግረን።
በእርግጥ የሰው ልጆች እስከ ተወሰነ ዕድሜ ድረስ መሥራት አይችሉም። አዳምና ሔዋንም እንደዚያ ነበሩ። ሰዎች በጨቅላ ዕድሜያቸው፣ ቀድሞ በተዘጋጀ ግቢ፣ በተመቻቸ መኖሪያ ቦታ፣ ለፍሬ የበቃ የአትክልት ስፍራ ውስጥ ነው የሚቆዩት። በዔደን ገነት ወይም በወላጆችና በአሳዳጊዎች እንክብካቤ ውስጥ።
ነገር ግን፣ ውለው ሲያድሩ ብርሃንን ብቻ ሳይሆን ፀሓይንም ማየት አለባቸው። ከአትክልት ስራው ውስጥ ጣፋጭ ፍራፍሬዎችን መብላት ብቻ ሳይሆን፣ መሥራትንም ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። መሥራትና ምድርን ማልማት የሰው ድርሻ ነውና።
ሁሉም ሰው በየፊናው እንደየ ዓቅሙ የየራሱን ኑሮ መምራትና የየራሱን “የአትክልት ስፍራ” ማበጀት ይችላል፤ ይገባዋልም።
አዳምና ሔዋን፣ ያልተፈቀደላቸውን ፍሬ በራሳቸው ውሳኔ ከበሉ በኋላ፣ ከዔደን ገነት የወጡት፣ የተፈጠሩባትን ምድር እንዲያርሱ ነው።
ቀድሞ ያልነበረ አዲስ ዓላማ አልተሰጣቸውም። ፍዳ አልተጫነባቸውም። የሰው ተፈጥሮ ከመነሻውም ለሥራ የተቃኘ ነውና። ምድር የምትለማው ሰው ሲሠራባት እንደሆነ አስቀድሞ በሃይማኖታዊው ትረካ ተጠቅሷልና።
አሁን እንደገና ተደግሞ በግልጽ ተነገራቸው። ወደ ሌላ ዓለም አልተሰደዱም። የተፈጠሩባትን ምድር እንዲያርሱና እንዲያለሙ ነው ከዔደን ግቢ የወጡት። ደግሞም ድካማቸው ለከንቱ አይደለም። ሕይወታቸውን ለማለምለም ነው ምድርን ማልማትና መሥራት የሚጠበቅባቸው።
ሥራው ከባድ ነው። ከእህልና ከፍራፍሬ ተክሎች ጎን ለጎን፣ አረምና እሾህ ይበቅላል። ለጊዜው ይቸግራል። ሁሉም ነገር ተሟልቶ አይገኝም። ከዕለት ተዕለት ምግባቸው ቆጥበው፣ ከእህል ፍሬዎችም ምርጥ ምርጡን ለይተው ለእርሻቸው ማዋል አለባቸው። ከወትሮው የባሱ ፈተናዎች ሲገጥሟቸውም… (እየጾሙም ቢሆን) ከመሥራት ወደ ኋላ ማለት አይኖርባቸውም።
“መሥዋዕትነት” ነው። ነገር ግን ለከንቱ አይደለም።
ስቃይን እንደ በጎ በመቁጠር ወይም ማገዶ ለመሆን አይደለም። ለእርድ ለመቅረብ፣ ለመንደድና ለመበላትም አይደለም።
ሠርተው ለማፍራት ነው። የሥራ ፍሬያቸውን ለማጣጣም ነው።
ጥረታቸው ለውጤት ነው። ጥረህ ግረህ ትበላለህ የሚል ነው የተግባራቸው መመሪያ። ፍሬያማ ሥራ ወይም የሥራ ፍሬ የሚል ነው ዋናው ፍሬ ሐሳብ። ይህም ለትክክለኛ የሥነ ምግባር መርሕ ጥሩ መነሻ ይሆናል - ከማገዶነት አምልኮ የጸዳ።


Read 1227 times