Saturday, 15 March 2025 21:14

ጾምና ድግስ “ይቃረናሉ”። ግን እኩል ይከበራሉ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

የጾም ቀናትን ከድግስ በዓላት ጋር በጥሬው ስናነጻጽራቸው ርቀታቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው፡ እንዲያውም ይቃረናሉ ብንል ይሻላል። እንደ ረሀብና ጥጋብ፣ ወይም እንደ ሐዘንና ደስታ።
ነገር ግን እንደ ፈተናና እንደ ሽልማት ልንቆጥራቸውም እንችላለን። በዚህ መነጽር ካየናቸው፣ ጸበኛ አይደሉም። አዎ እንደ ጥረትና ውጤት፣ ጾምና ድግስም ይለያያሉ፡ ግን እርስ በርስ አይቃረኑም። አድካሚ ጉዞና ደማቅ አቀባበል… አንዱ አስቸጋሪ ሌላኛው ተናፋቂ ቢሆኑም፣ የማይታረቁ ጸበኞች አይደሉም። እንዲያውም ዝምድና አላቸው።
ከዕለት ጉርስ በመቀነስ ፍራፍሬ ተክሎ መንከባከብ የብዙ ወራት ድካም ነው። በባዶ ሆድ ቀን በቀን ብንለፋላቸውም ለጊዜው ከአፍ ጠብ የሚል ውጤት አይኖራቸውም። ትዕግሥትን ይፈታተናሉ። አብበው ለፍሬ ሲበቁ ደግሞ፣ ጣፋጭ ድግስ ይሆናሉ።
በዐጭሩ፡
ጾምን “የጥረት ግረት ምልክት”…
ድግስን ደግሞ “የመልካም ምኞትና የስኬት ምልክት” አድረገን ካየናቸው…
ተቃራኒ ቢመስሉም እንኳ ዝምድናቸውን አጉልተው ይመሰክራሉ። ልዩነት ቢኖራቸውም እንኳ ቅርርባቸውንም ገልጠው ያሳያሉ።
በሃይማኖት ታሪኮች ውስጥም፣ ጾምና ድግስ አብረው ጎን ለጎን እንደ ጥንዶች ተቆራኝተው ነው የሚታዩት።
የማይታረቁ ጸበኞች ቢመስሉም እኩል ይከበራሉ።
እኩል ባይከበሩም፣ በየፊናቸው እየተፈራረቁ ይነግሣሉ። የድግስ በዓል የጾም ቀናትን ተከትሎ ይመጣል፤ እንደገና በተራው ወደ ጾም ያሻግራል።
እንዲያም ሆኖ፣ ልዩነታቸው ጎልቶ ይታየናል። ቅራኔ እንጂ ዝምድና የላቸውም ያስብለናል።
አንዱ ቀድሞ መምጣቱ፤ ሌላኛው ተከትሎ በቦታው መተካቱ፣ መልሶም ማሻገሩ… እውነት ነው። ቢሆንም ግን፣ “ድግስ ጾምን ይሽራል፤ የተሻረው ተመልሶ ያሸንፈዋል፤ ከነገሠበት በኋላ እንደገና ሌላኛው መጥቶ ያስወግደዋል” ማለትም እንችላለን። ሊታረቁ የማይችሉ ጸበኞች ስለሚመስሉ።
ግን ደግሞ ዝምድና ቢኖራቸው ነው በሃይማኖቶች ታሪክ ውስጥ ጎን ለጎን ተጎዳኝተው፣ ለእልፍ አእላፍ አመታት በክብር እስከ ዛሬ የዘለቁት። የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖታዊ ትምርቶችን በመጥቀስ ማየት እንችላለን።
(ከዚያ በኋላ ጆርዳን ፔተርሰን በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ “የመሥዋዕት” ትርጉም ላይ ያሰፈሩትን ማብራሪያ በመጥቀስ ጉዳያችንን ብንደመድም ሳይሻል አይቀርም። በቅድሚያ ግን ሃይማኖታዊ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን በጥቂት በጥቂቱ እንመልከት)።
የኦሪት፣ የወንጌልና የቁርዓን ትምህርቶች - በጾምና በድግስ ላይ።
የኢየሱስ ስብከት የሚጀምረው በጾምና በፈተና ማግስት ነው። የኢየሱስ መነሻ ትረካ በኦሪት መጻሕፍት ከተገለጸው የሙሴ ትረካ ጋር ይመሳሰላል።
የሙሴ የ40 ቀናት ጾም በሲና ተራራ
ሙሴ የኑሮ መርሖችንና ትዕዛዛትን ከእግዚሄር ለመቀበልና ለማስተማር በቅድሚያ በሲና ተራራ አርባ ቀናትን በጾም እንዳሳለፈ ተጽፏል (ዘጸአት 34፡28)።
ሙሴ በዕድሜ መጨረሻው ላይ የሲና ተራራ ታሪኩን በማስታወስ ለሕዝብ እንዲህ ሲል ይናገራል። “እግዚሄር ከእናንተ ጋር ቃል የተዋዋለባቸውን የኪዳን ጽላቶች ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ እህል ሳልበላ፣ ውኃም ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቆየሁ” በማለት ይተርካል (ዘዳግም 9፡9)።
ኢየሱስም በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የማስተማር ጉዞና ስብከት ከመጀመሩ በፊት የአርባ ቀን ጾምና ፈተና ገጥሞታል - እንደ ሙሴ።
ለነገሩ የሙሴ ትረካም፣ የቀድሞ ትረካዎችን በተለይም የኖኅ ዘመንን የሚዘክር ነው።
የኖኅ የ40 ቀን ፈተናና የመሥዋዕት ድግስ
ጥንት በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ምድርን ለማጥለቅለቅ ለአርባ ቀንና ለአርባ ሌሊት እንደጎረፈ የኦሪት ዘፍጥረት ትረካ ይገልጻል (ዘፍጥረት ምዕ 7፡10)። እግዚኦ የሚያሰኝ ከባድ የፈተና ጊዜ ነው። ኖኅ በሠራው መርከብ ውስጥ የነበሩ ስምንት ሰዎች ብቻ ከእልቂት እንደተረፉ ይነግረናል - ትረካው።
በዚያ ፈተና ማግስት ነው፣ የመጀመሪያ የሕግ አንቀጽ የተሰበከው - የሰው ነፍስ ማጥፋትን የሚከለክል።
በዚያ ፈተና ማግስትም ነው ኖኅ ለእግዚሄር መስዋዕት ያቀረበው። እንስሳትን አርዶ፣ እሳት አቀጣጥሎ ባቀረበው መሥዋዕት እግዚሄር ደስ ተሰኘ ይላል - (ዘፍጥረት ምዕ 8-9)።
ከትምህርትና ከስብከት ጋር፣ ጾምና ፈተና፣ ድግስና መሥዋዕት ተያይዘው የተተረኩት በአጋጣሚ አይደለም። ዝምድና ቢኖራቸው ነው። ዝምድናቸውን ለማየት እንዲያግዘን፣ የትረካዎቹን ሰንሰለት ባጭር ባጭሩ ብንመለከት አይከፋም።
ለማንኛውም፣ ከብዙ ምዕተ ዓመታት በኋላ የኖኅን ትረካ የሚዘክር የሙሴ ትምህርት ይመጣል። እንደገና ብዙ ምዕተ ዓመታትን ተሻግሮ፣ የሙሴ ትምህርቶች ላይ የተመረኮዘ የኢየሱስ ትረካ እናገኛለን።
የኢየሱስ የ40 ቀን ጾምና ፈተና
ትረካው እንዲህ ይላል (ማቴዎስ ምዕ 4፡1-17)።
ኢየሱስ በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ።
ፈታኙም ቀርቦ፣ “የእግዚሄር ልጅ ከሆንክ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው።
ኢየሱስም፣ “ሰው ከእግዚሄር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት።
የሙሴ የኦሪት ትምህርትን ነው ኢየሱስ የጠቀሰው - ኦሪት ዘዳግም 8፡3። “ፈታኙ” ወዲያውኑ አልተሸነፈም። እሱም በፊናው የኦሪት መጻሕፍትን እያጣቀሰ ኢየሱስን እንደገና ሁለቴ ይፈታተነዋል። ኢየሱስ የኦሪት ዘዳግም ተጨማሪ መልሶችን በማቅረብ ፈተናውን ይሻገራል። ወደ ተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ማስተማርና መስበክ የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነው።
የኢየሱስ የመጨረሻ ትምህርት ደግሞ “ከበዓል ድግስ” ማግስት ነው - (ማቴዎስ ምዕ 26፡17-20)። በአርብ ስቅለት ዋዜማ የተሰናዳው እራት የክብረ በዓል ድግስ ነው። መሥዋዕት ተብሎም ይጠቀሳል።
ጾምና ፈተና፣ የበዓል ድግስና መሥዋዕት… ከፊትና ከኋላ ትምህርትንና ስብከትን ያጅባሉ።
ቁርዓን፣ የጾም፣ የድግስ ወይም የመሥዋዕት ትምህርቶችን ሲያቀርብ የቀድሞ ትረካዎችን ይዘክራል።
እናንተ ያመናችሁ ሆይ፣ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ፤ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና። (ሱረቱ አል-በቀራህ 2፡183)።
የጾም ፋይዳ እንድትጠነቀቁ ነው፤ ወይም ክፉ መንፈስን እንድትከላከሉ ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል።
በፈተና ጊዜም ቢሆን፣ ለችግር አለመንበርከክን፣ መልካም መንፈስ የመቀጠል ጽናትን ማክበር እንዳለብን የሚያስተምር ነው። ሳንበላ ስለዋልን፣ ወይም ሌላ እንቅፋትና ችግር ስለገጠመን፣ ፈተናውን ለመቋቋም ሰንፈን ወይም ለጊዜያዊ ስሜት አሸብርከን መንገድ የምንስት ከሆነማ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሕይወታችን መበላሸቱ አይቀሬ ነው።
በፈተና የማይሸነፍና መንገድ የማይስት የመልካም መንፈስ ጽናትን እንድናከብር ይጠቅማል ማለት ነው - የጾም ሥርዓት።
ነገር ግን፣ የጾም ሥርዓት የተጻፈው በሰዎች ላይ ሸክም ለማብዛተ፣ የኑሮ ፈተና ለማክበድ፣ መከራ ለመደረብ እንዳልሆነም ተጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የጾም ሥርዓቱን ማሟላት ያልቻለ ሰው፣ የዓቅሙን ያህል ችግረኛ ሰዎችን በማብላት ማካካስ እንደሚኖርበት ይገልጻል (ቁርዓን 2፡184)። ለቤተሰብ፣ ለቤተ ዘመድና ለተቸገሩ ሰዎች የሚከናወኑ የእርድና የመስተንግዶ ሥርዓቶች፣ እንዲሁም ከሐጅ ጉዞ ጋር የተያያዙ ሥጦታዎች ላይም ተመሳሳይ ትምርቶችን እናገኛለን።
በእርድ ብዛትና በሥጋ መስተንግዶው ስፋት መጠን ብቻ የሚለካ አይደለም ቁምነገሩ። ይልቅስ የመስዋዕት፣ የድግስ፣ የስጦታ መነሻ የሆነው መልካም አስተሳሰብና በጎ መንፈስ ትልቅ ክብር እንዳላቸው ተጠቁሟል።
በአላህ ስም መስዋዕት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ፣ ሰዎች እንደየዓቅማቸው የእርድ ሥርዓት እንዲያከናውኑና እንዲበሉ ይመክራል። የተቸገሩ ሰዎችንም እንዲያበሉ ያስተምራል።
ታዲያ የመሥዋዕት ሥርዓቱን ማከናወን ማለት ከመንፈሳዊ ትርጉሙ ጋር እንዳይፋታ ያሳስባል። መሥዋዕት… ከበጎ ምግባርና ከመልካም መንፈስ ጋር ከተፋታ፣ መነሻ ቁም ነገሩን ያጣል። በጎ ምግባርን የሚመሠክር መሆን አለበት የመሥዋዕት ሥርዓት። (Quran 22:37) “It is not their meat nor their blood that reaches God. It is your piety that reaches Him...”)
የኦሪት ትረካዎች ላይም ተመሳሳይ መልእክት ያዘሉ ትምህርቶችን እናገኛለን። ከመልካም ሐሳብና ተግባር፣ ከመልካም መንፈስና ከቅን ልቦና ጋር የተፋታ መሥዋዕት፣ ከንቱ ነው። አንድም አላዋቂነት ነው። አልያም ግብዝነት።
What need have I for all your sacrifices? says the Lord. (ኢሳያስ 1፡11)። Your burnt-offerings are not desirable to Me, nor are your sacrifices pleasing to Me.(ኤርሚያስ 6:20)።
ጾምና ድግስ - የመሥዋዕት ሁለት መልኮች
ጆርዳን ፔተርሰን እንደሚሉት ከሆነ፣ ጾምንና ድግስን ሁለቱንም አንድ ላይ “መሥዋዕት” በሚል ስያሜ ልንጠራቸው እንችላለን። በአንድ ስያሜ ስር የሚጠቀቃለሉ ከሆነ፣ ከቅርርብ ባሻገር የጋራ ባሕርይ አላቸው ማለት ነው። እንዴት?
ጾምን ከመሥዋዕት ጋር ማዛመድ ብዙም ላያስቸግር ይችላል።
ከእለት ጉርሱ ቀንሶ “ምርጥ ምርጡን የእህል ፍሬ” ለማሳው ይገብራል። ለምድር መሥዋዕት ያቀርባል። በቀን አንዴ እየበላም ቢሆን፣ ጥሪቱን ለእርሻ ሥራው ያውላል - ወይም ለኢንቨስትመንት። ዋናው “የመሥዋዕት” ትርጉም ይሄው እንደሆነ ይገልጻሉ - ፔተርሰን።
ለነገ ውጤት በማሰብ፣ ዛሬ “መሥዋዕት” መክፈል፣ ዋናው የሕይወት ቃል ኪዳን ነው ሲሉም ያስረዳሉ።
ዛሬ ቀበቷችንን ጠበቅ አድርገን፣ ጾም ወይም ፈተና ሳይበግረን፣ ዕለታዊ ችግሮችን ተቋቁመን፣ የቀን ዝለትና ሕመም ሳያሸንፈን፣ ጊዜያዊ ስሜት ሳያዘናጋን፣ በሙሉ ልብ ሙሉ ዓቅማችን ሰጥተን፣ ሳንሰስትና ሳንለግም በሙሉ ነዳጅ መሥራት ነው መሥዋዕትነት።
እሺ፣ ይህን እንቀበልላቸው። ጾም የመሥዋዕነት ምልክት ሊሆን ይችላል እንበል። ለነገ ውጤት በማሰብ፣ “የዛሬ መሥዋዕትነትን እንድናከብር፣ ፈተናን አሸንፈን የማለፍ ጥረታችንንና ጽናታችንን እንድናደንቅ” የሚገፋፋ ምልክት ነው - ጾም።
በዚህ መልኩ ስናየው በእርግጥም፣ ጾም “የመሥዋዕት” ምልክት ተደርጎ ቢቆጠር አይገርምም።
ድግስስ እንዴት የመሥዋዕት ምልክት ይሆናል?
ድግስ የጾም ግልባጭ ነው። አይደለም እንዴ? ደግሞስ ጾምን እንደ ምልክት ተጠቅመን ጥረትንና ጽናትን ካከበርን አይበቃንም?
በእርግጥ አብዛኛው ጥረት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፍሬ አይበቃም። የወራት ድካምን ሊጠይቅ ይችላል። ለዓመታት የሚያለፉ፣ ትዕግሥትን የሚፈታተኑና ጽናትን የሚገዳደሩ የረዥም ጊዜ የሕይወት ዓላማዎችም አሉ።
የዕለት ለዕለት ሥራው መከራ ነው። ማብቂያ ያለው አይመስልም።
ፍሬው ግን እንኳን ልንጨብጠው ይቅርና ከአድማስ ጥግ በጨረፍታ አልታይ ይለናል።
አንዳንዴም “ሕልም ብቻ” ሆኖ የሚቀር እየመሰለን እንጠራጠራለን። ተስፋችን ይደበዝዛል። መንፈሳችን ይቀዘቅዛል። ነገር ግን፣ የመልካም ሕይወት ምኞታችንና ዓላማችን፣ ምንም ያህል ቢርቅብን፣ የቱንም ያህል ቢያስቸግረን እንኳ፣ ከአእምሯችንና ከመንፈሳችን ተለይቶ እንዲደበዝዝ መፍቀድ የለብንም።
ለተሻለ ኑሮ፣ ከፍ ላለ ዓላም፣ ለላቀ የሕይወት ጣዕም ያለን መልካም ምኞትና ክብር በጭራሽ ተዳፍኖ መቅረት የለበትም። ለዚያም ነው ማስታወሻ ምልክት የሚያስፈልገን።
“ለወደፊቱ መልካም ሕይወትና ምኞት” ያለንን ክብር ለመግለጽ፣ ያንን መልካም ምኞት ዛሬ ለአፍታ ያህል ለአንድ ቀን ለማጣጣም የሚያገለግል ምልክት ነው - የበዓል ድግስ።
በእርግጥ የበዓል ድግስ በቀላሉ የሚሳካ ነገር አይደለም። ኪሳችንን የዕለት ተዕለት ዓቅማችንን ይፈታተናል። በተቻለ መጠን “ምርጥ ምርጡን ለክብረ በዓል ይሁን!” ብለን መሥዋዕት እንድንከፍል ያስገድደናል።
ግን ለከንቱ አይደለም። ለመጪው መልካም ሕይወት ያለንን ክብር በተጨባጭ የምናይበት ምልክት ነው - የድግስ መሥዋዕት። ለአንድ ቀን ያህል የወደፊቱን መልካም ዓለም፣ መጪውን መልካም ሕይወት ወደ ዛሬ አቅርበን እናይበታለን።
ለነገሩ ቆም ብለን ካሰብነው፣ ከመነሻውም ድግስ እንደ መሥዋዕት መቆጠሩ አይገርምም።
ቃሉ ራሱ… “እርድ” ማለት ነው - በጥሬው ከተተረጎመ። የሥጋ ምግቦች የተትረፈረፉበት ድግስ፣ ግብዣ፣ ስጦታ፣ ግብር እንደ ማለት ነው - መደበኛ ትርጉሙ። ሰፋ ተደርጎ ሲታይ ደግሞ፣ ምርጥ ምርጡን ለድግስ መሥዋዕት ማድረግ ብቻ አይደለም ትርጉሙ።
“ምርጥ ምርጡን ለእርሻ ማሳ መገበር! ምርጥ የእህል ፍሬዎችን ለዕለት ጉርስ ከመቆርጠም ይልቅ፣ መጪው አዝመራ እንዲበረክት ማሳችን ላይ የመዝራት መሥዋዕትነትንም” ይጨምራል። ለጊዜው በቀን አንዴ ብቻ እየበላንም ቢሆን፣ ለመጪው አዝመራ ዛሬ መሥዋዕት እናቀርባለን።
ዞረን ዞረን ወደ ጾም ተመለስን።
ጾም በፈተና የማይበገር የዛሬ ጥረትን የምናከብርበት ምልክት ነው። ድግስ ደግሞ የወደፊት መልካም ሕይወትን የምናከብርበት፣ በጊዜ ርቀት የማይደበዝዝ መልካም ዓላማን የምናደንቅበት ምልክት ነው። የአንድ ሕይወት ሁለት ገጽታዎች ናቸው - እንደ ጥረትና ውጤት።

 

Read 978 times