Saturday, 08 March 2025 21:13

ዓዴፓ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት ራሱን አገለለ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዓዴፓ) ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት ራሱን አግልሏል። ፓርቲው ምክር ቤቱን “የሃይማኖት እኩልነት የሌለበት ነው” ሲል ተችቷል።
ፓርቲው ከትላንት በስቲያ የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ዓዴፓ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት በክልሉ ሕዝብ ላይ “አጋጥሟል” ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል አቅም እንደሚያዳብር ተስፋ አድርጎ ለመቀላቀል ወስኖ እንደነበር አስታውሷል። አክሎም፤ “ምክር ቤቱ ብዙ ድክመቶች ቢኖሩበትም፣ እኛ ተቀላቅለን ድክመቶቹን እያረምን ለመዝለቅ ተስፋ አድርገን ነበር። ወደ ምክር ቤቱ ከገባን በኋላ፣ የተለያዩ የፖለቲካና ሌሎች ድርጅቶችን በማቀፍ አሳታፊ አሰራር እንዲኖር ታግለናል” ሲል አትቷል።
በተጨማሪም፣ ምክር ቤቱ በወሳኝ አጀንዳዎች ላይ ክርክር የሚካሄድበትና የዴሞክራሲ ስርዓት የሚያድግበት ተቋም እንዲሆን ፓርቲው መታገሉን በመግለጽ፣ ይህ ግን ዕውን ሊሆን አለመቻሉን በመግለጫው አብራርቷል። “ከወረዳ ተወክለው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው። በተለይም የኢሮብ እና ኩናማ ብሔሮች እኩል ውክልና እየተሰጣቸው አይደለም። የሴቶች እኩል ተሳትፎ አልተረጋገጠም” በማለት አመልክቷል።
ከጊዜያዊ ምክር ቤቱ ዕውቅና ውጪ፣ የተመረጡ ሰዎች ብቻ የሚሳተፉበት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እንዳለ በመግለጫው የጠቀሰው ፓርቲው፤ ምክር ቤቱን “የሃይማኖት ዕኩልነት የሌለበት ነው” በማለት ነቅፎታል። ይሁንና ምክር ቤቱ ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ የትግራይ ክልል ሙስሊም ሕብረተሰብ ተሳታፊ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ ፍትሐዊ አሰራርና መርሕን እንደማይከተል በመጠቆም፣ በተለይም ቁልፍ የቋሚ ኮሚቴ ሹመቶችን “አሳታፊ እና ፍትሐዊ” ባልሆነ መንገድ በሃሳብ ተመሳሳይ ለሆኑ ድርጅቶች ተላልፎ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሷል። ይህን ተከትሎ “ምክር ቤቱ በጥቅማጥቅም ትስስር አማካይነት የተዋቀረ ነው” ሲል ዓዴፓ በመግለጫው ወቅሷል።
“የተዋቀረው ጊዜያዊ ምክር ቤት የታሰበውን ለውጥ ለማምጣት አይችልም። የትግራይን ሕዝብ የሕልውና አደጋ ለመቅረፍ የሚያስችል ቁመና የለውም” ያለው ፓርቲው፤ በምክር ቤቱ ያለውን ውክልና በማንሳት ራሱን እንዳገለለ አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም ጊዜያዊ ምክር ቤቱ ሲቋቋም፣ በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል የሚመራው ህወሓት ተሳታፊ አለመሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በበኩሉ፣ ምክር ቤቱን እንደማይቀላቀል ገልጾ ነበር። ነገር ግን ከሳምንታት በፊት ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ወደ ምክር ቤቱ እንደገባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት የቀድሞ ስያሜው “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤት” የሚል ነበር። ቀደም ሲል ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ይህ ስያሜ እንዲቀየር ጥያቄ አቅርቦ፣ የመጀመሪያ አስቸኳይ ጉባዔውን በመቐለ ከተማ ያካሄደው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤት፣ የተቋቋመበትን ደንብ ቁጥር 10/2016 አሻሽሎ አጽድቋል፡፡ በዚህም ስያሜ ተቀይሯል።
ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ባቀረባቸው ትችቶች ዙሪያ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ ምክር ቤቱ እስካሁን የሰጡት ይፋዊ ምላሽ የለም።

Read 752 times