የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከሌሎች ሃይሎች ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ያወጡትን መግለጫ አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃወሙት ሲሆን፤ ፓርቲዎቹ መግለጫውን “እሳት ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ የሚቆጠርና ቀን አይቶ የመጣል አዝማሚያ ያለው ነው” ሲሉ ነቅፈውታል።
ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ሐሙስ የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ "ኦፌኮ እና ኦነግ ያወጡት መግለጫ፣ በአመዛኙ እሳት ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ የሚቆጠርና ቀን አይቶ የመጣል አዝማሚያ ያለው ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች የተስማሙባቸውንና በመግለጫቸው ያወጧቸውን ጉዳዮች ያወሱት አራቱ ፓርቲዎች፤ “እኛ የትብብር ፓርቲዎች በኦሮሚያ ክልል ብቻ አይደለም፤ በመላ አገራችን ሰላም እንዲሰፍን ለዚህም መንግሥት ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት ያለመታከት ስንወተውት ቆይተናል” ብለዋል። አክለውም፣ አሁን ለአገሪቱ ሰላም በጋራ መታገል የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑን አስምረውበታል፡፡
“በተናጠል ያውም በክልል ደረጃ ወርደን የሚመጣ ሰላም አይኖርም፣ የአገራችንን አንድነትም ማስጠበቅ አይቻልም” ያሉት አራቱ ፓርቲዎች፤ “በአንድ ክልል ሊቋቋም የታሰበው የሽግግር መንግሥት አገራችንን አሁን ከምትገኝበት ሁኔታ የበለጠ ያመሰቃቅላታል፣ ችግሮችንም ያባብሳል እንጂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል” ሲሉ አስረድተዋል።
በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላም ካልሰፈነ “ማንም ወገን ብቻውን ነጻ እንደማይወጣ” ጠቅሰውም፤ የተናጠል ሰላም እንደማይሰፍን አብራርተዋል።
በመሆኑም፣ በኦፌኮ እና ኦነግ መግለጫ አማካይነት ይፋ የተደረገው የሽግግር መንግሥት የማቋቋም እንቅስቃሴን አጥብቀው እንደሚቃወሙ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል። እንቅስቃሴው ኦሮሚያ ክልልን “ጥቂት ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሞኖፖል የያዙት ደሴት በማድረግና ራስን ብቸኛ ወኪል አድርጎ በማስቀመጥ አሁንም የተጠቂ ፖለቲካና የመጡብህ ዓይነት ቅስቀሳ የማራመድ” አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ይህን አካሄድ በአገር ፍርስራሽ ላይ የራስን ጎጆ ለመቀለስ ያለመ ቅርብ አዳሪ፣ ፍትሕ አልባ፣ ኢ-ሕገ መንግስታዊና ኢ-ሞራላዊ ሆኖ አግኝተነዋል” ሲሉ የተቹት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ በኦፌኮ እና ኦነግ መካከል “ተደርጓል” ያሉት ስምምነት አገሪቱን በበርካታ አስርት ዓመታት “ወደ ኋላ የሚመልስ” ነው ብለውታል፡፡
በቅርቡ ኦፌኮ እና ኦነግ ባወጡት መግለጫ፣ በጋራ ይፋ ያደረጉት አቋማቸው፣ ለሕብረተሰቡ እንቅፋት የሆነውን በኦሮሚያ ክልል ያለውን የሰላም ችግር በትብብር ለመፍታት ያለመ ብቻ መሆኑን ጠቁመው፣ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸው ነበር፡፡
Saturday, 08 March 2025 21:09
ኦፌኮ እና ኦነግ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ያወጡትን መግለጫ 4 ፓርቲዎች ተቃወሙት
Written by Administrator
Published in
ዜና